Monday, March 4, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤትን የሚመሩ አዲስ ፕሬዚዳንት ተመረጡ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከአንድ ዓመት በላይ የዘገየውን ጠቅላላ ጉባዔ ያካሔደው የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ ዓርብ ጥቅምት 17 ቀን 2010 ዓ.ም. አዳዲስ አመራሮች ተቀላቅለውታል፡፡ የ39 ዓመቱ አቶ መላኩ እዘዘው (ኢንጂነር) የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት በመሆን ተመርጠዋል፡፡  

በተለያዩ ችግሮችና አለመግባባቶች እንዲሁም ከሕግ ውጪ በተከናወኑ ምርጫዎች ጠቅላላ ጉባዔውን ሲያራዝም የቆየው ንግድ ምክር ቤቱ፣ ችግሮቹን በመፍታት ጠቅላላ ጉባዔውን በሰላም ለማካሄድ በቅቷል፡፡

የጠቅላላ ጉባዔው አጀንዳዎች ከሆኑት ውስጥ የምክር ቤቱን የሦስት ዓመታት ሪፖርቶች ማዳመጥ አንዱ ሲሆን፣ ትኩረት የተሰጠው ግን የንግድ ምክር ቤቱን ተተኪ አመራሮች መምረጥ ነበር፡፡ ወደ አመራር ቦታው ለመምጣት በሚደረግ ፉክቻ ስሙ የሚጠቀሰው ምክር ቤቱ፣ ዘንድሮስ ምን ያስተናግድ ይሆን? የሚል ጥያቄ ሲስነሳ ቢቆይም፣ በንግድ ምክር ቤቱ ታሪክ ‹‹ወጣት›› የሆኑትን አቶ መላኩን በፕሬዚዳንትነት ለመምረጥ የቻለበት ክስተት ተፈጥሯል፡፡

አቶ መላኩ በዕለቱ ቅርብ ተፎካካሪያቸው ከነበሩትና ከኦሮሚያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የታጩትን አቶ ፈይሳ አራርሳን በ87 ለ75 በሆነ ድምፅ አሸንፈው የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ለመሆን ችለዋል፡፡ በምርጫው ሌላው ተፎካካሪ ሆነው የቀረቡት የጨርቃ ጨቅርና አልባሳት ኢንዱትሪዎች ማኅበርን በመምራት የቀረቡት አቶ ፋሲል ታደሰ ሦስተኛ ሆነው በስምንት ድምፅ ተሰናብተዋል፡፡

ለምክትል ፕሬዚዳንትነት በተደረገው ምርጫ ደግሞ ቀደም ብለው በዕጩነት ከቀረቡ ሦስት ተወዳዳሪዎች መካከል ሁለቱ ራሳቸውን በማግለላቸው፣ ለቦታው ብቸኛ ተወዳዳሪ ሆነው የቀረቡት የትግራይ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አሰፋ ገብረ ሥላሴ ናቸው፡፡ አቶ አሰፋ የኢትዮጵያ ንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነዋል፡፡     

ንግድ ምክር ቤቱን በቦርድ አባልነት እንዲያገለግሉ ስምንት ዕጩዎች ድምፅ በማግኘት ሊመረጡ ችለዋል፡፡ የዘንድሮው ምርጫ ከዚህ ቀደም ከነበረው አሠራር ወጣ ብሎ 18ቱም አባል ምክር ቤቶች ሁለት ሁለት ዕጩዎችን እንዲያቀርቡ በማድረግ የተከናወነ ነበር፡፡

በዚህም መሠረት እስከ ረቡዕ ጥቅምት 15 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ የንግድ ምክር ቤቱን የፕሬዚዳንትነት ቦታ ለመያዝ አምስት አባል ምክር ቤቶች ዕጩዎች ማቅረብ ችለው እንደነበር ይታወሳል፡፡ ለፕሬዚዳንትነት እንዲወዳደሩ ከታጩት ውስጥ ከኦሮሚያ አቶ ፈይሳ አራርሳ፣ ከአማራ አቶ መላኩ እዘዘው (ኢንጂነር)፣ ከአዲስ አበባ አቶ ውብሸት ኃይሉ (ኢንጂነር)፣ ከደቡብ አቶ ሰሎሞን አፈወርቅ፣ ከጨርቃ ጨርቅ አልባሳት አምራቾች ማኅበር አቶ ፋሲል ታደሰ ነበሩ፡፡ ሆኖም ምርጫው አንድ ቀን ሲቀረው ከዕጩዎች መካከል ሁለቱ ከዕጩነት በመውጣታቸው ውድድሩ በሦስቱ መካከል ሆኗል፡፡ በተለይ ንግድ ምክር ቤቱን በፕሬዚዳንትነት ሲመሩ የቆዩት አቶ ሰሎሞን አፈወርቅ የሚወከሉበት የደቡብ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በድጋሚ ለፕሬዚዳንትነት እንዲወዳደሩ ቢያጫቸውም፣ ባለፈው ሐሙስ በድጋሚ ለመወዳደር እንደማይችሉ በማሳወቅ ራሳቸውን ከምርጫው አግልለዋል፡፡

አቶ ሰሎሞን ላለፉት ሦስት ዓመታት በዚህ ኃላፊነት በቆዩበት ወቅት ለዳግም ምርጫ እንደማይቀርቡ አስታውቀው የነበረ በመሆኑ፣ ድጋሚ መታጨታቸው አነጋጋሪ ሆኖ ነበር፡፡

ነገር ግን የቀድሞ ሐሳባቸውን በማጠንከር ደጋግሞ ወደ አመራር ለመምጣት ሲደረግ የነበረውን ፍትጊያ ላለመድገም በፈቃዳቸው ከውድድሩ መውጣታቸውን በደብዳቤ አሳውቀዋል፡፡ ይህም ውሳኔያቸው በተደጋጋሚ ወደ አመራር ቦታ ለመምጣት ይታይ የነበረውን አካሄድ ይገታል ተብሏል፡፡  

አዲሱ ፕሬዚዳንት አቶ መላኩ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ዋናው ሥራቸው የንግድ ምክር ቤቶች የእርስ በርስ ግንኙነት እንዲጠነክርና አብሮ የመሥራት ባህልን በማዳበር በተገቢው መንገድ የንግዱን ኅብረተሰብ ማገልገል ነው፡፡

አቶ መላኩ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ፋኩሊቲ በኤሌክትሮ ሜካኒካል የመጀመርያ ዲግሪ፣ ሁለተኛ ዲግሪቸውን ደግሞ ከህንድ በተልዕኮ ትምህርት በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን አግኝተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በጎንደር በሪል ስቴት፣ በአሽከርካሪ ማሠልጠንና በትራንስፖርት ቢዝነስ ዘርፍ ላይ ተሰማርተው  እየሠሩ ይገኛሉ፡፡

አቶ መላኩ የጎንደር ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ከሁለት ዓመት በፊት ሲሆን፣ የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራትን በፕሬዚዳንትነት ለመምራት ከተመረጡ አምስት ወራት አስቆጥረዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች