Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ባለታርጋ ሕገወጦች

 

በግብይት ሥርዓታችን ውስጥ በርካታ ግራ የሚያጋቡ ጉዳዮች ይስተዋላሉ፡፡ በርካታ የተምታቱ አሠራሮችም አብረውን ይኖራሉ፡፡ ሕጋዊና ሕገወጥ ድርጊቶች ሲደበላለቁ እንታዘባለን፡፡ በሕጋዊ መንገድ የሚሠራው የልፋቱን ያህል ማግኘት ሲሳነው፣ አየር በአየር የሚነግደው ማማ ላይ ተቀምጦ እንዳሻው ሲሆን መመልከት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ በንግድና በአገልግሎት ዘርፍ ውስጥ በተደጋጋሚ ለምንመለከታቸው ችግሮች አንዱ ምክንያት ይኸው ሕጋዊ የሥራ ፈቃድ ባለውና  ፈቃድ በሌለው ነገር ግን በተመሳሳይ ሥራዎች ውስጥ አብረው በመሰማራት ሰበብ የሚፈጠረው መደበላለቅ ነው፡፡

      በሕገወጥ መንገድ፣ አየር በአየር የሚነግደው፣ ያለ ሕጋዊ ንግድ ፈቃድ የሚሸቅጠው፣ በሚሊዮኖች የሚገመቱ ንብረቶችን የሚያሻሽጠው ደላላ፣ ከሕጋዊው ይልቅ በብዛት የተንሰራፋ ይመስላል፡፡ ሕጋዊ የንግድ ፈቃድና የሥራ መደብ ምዝገባ የሌለው ነጋዴ በየዕለቱ ከንግድ ሰንሰለቱ እያጋበሰ ወደየቤቱ የሚያስገባው ገንዘብ የትየለሌ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ ገንዘብ ግብር የማይከፈልበት ሆኖ መገኘቱ ትልቅ ችግር ከመሆኑም በላይ ሕገኞቹን እየደቆሱ የንግድ መስመሮችንና የአገልግሎት አሰጣጡን እየበረዙ ነው ማለት ይቻላል፡፡

      ፈቃድ ሳይኖራቸው በሕግ የተፈቀደ ሥራ የሚሠሩ በርካቶች ናቸው፡፡ ይህ እውነት ቢሆንም እንዲህ ባለው ድርጊት የተሰማሩትን ወደ ሕጋዊነት ለማምጣት የሚያግዝ ዕርምጃ ሲወሰድ አይታይም፡፡ ‹‹እንዲህ ማድረግ ሕገወጥ ድርጊት ነው፤›› የሚባልለትን ድርጊት ለመቆጣጠር ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላትም ቢሆኑ፣ ከልብ የቆረጠ ዕርምጃ ሲወስዱ አይታዩም፡፡ አንድ ሰሞን በዘመቻ ቁጥጥር ይጀመርና ውሎ ሳያድር ይከስማል፡፡ ችግሩ ግን ከማንሰራራት አልፎ ብሶበት ይቀጥላል፡፡ ሕገወጥ ድርጊቶችን በቀላሉ ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ዕድሎች ቢኖሩም፣ ኃላፊነት ተሰምቶት የሚያስፈጽም አካል ወይም ቆራጥ የሥራ መሪ ስማይታይ ሕገወጥ ሥራዎች እየባሱ፣ እየተባባሱ እንዲሄዱ ሰበብ እየሆኑ ነው፡፡ ሕገወጦችም የልብ ልብ ተሰምቷቸው  ተከታዮቻቸውን ጭምር የሕገወጥ አሠራር ተጠቃሚነትን የሚያመቻቹ ኔትወርኮችን እንዲያበራክቱ መንገዱ ተመቻችቶላቸዋል፡፡

      የዚህ ዓይነቱ ውጥንቅጥ መገለጫው በርካታ ነው፡፡ አንዱ ማሳያም የትራንስፖርት ዘርፉ ነው፡፡ በችግር የተተበተበው ይህ ዘርፍ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ሕገወጦች እየተበራከቱበት፣ በኃላፊነት የማይሠራበት፣ ተጓዦች የሚጉላሉበት ዘርፍ ነው፡፡

      በዚህ ዘርፍ ከፍተኛ ችግር እየሆነ የመጣው ደግሞ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡ ፈቃድ ከተሰጣቸው ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች ውጭ አገልግሎት የሚሰጡ የተሽከርካሪ ባለንብረቶች ዘርፉን እየተቆጣጠሩት መምጣታቸው ሲታይ ነው፡፡

      በሕግ ከሚታወቁ ታክሲዎችና የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ባሻገር፣ ኮድ ሁለት የመኪና ታርጋ ያላቸው ተሽከርካሪዎች እንዳሻቸው በከተማው ‹‹የታክሲ›› አገልግሎት ሲሰጡ ጉዳዬ የሚላቸው አለመገኘቱ ነው፡፡ ተጓዣቸውን በኮንትራት እያሳፈሩ በግልጽ ይሠራሉ፡፡ በርካታ ደንበኞችን የሚያሳፍሩም ጥቂት አይደሉም፡፡ እንደ መደበኛ ታክሲ ተራ እየጠበቁ መንገዶችን ሲያመላልሱም ሃይ ባይ አላገኙም፡፡

ደላሎች ለኮድ ሁለት ተሽከርካሪዎች ገበያ በማመቻቸት ድርሻቸው እንዲሰፋ፣ ተገልጋዮችን እያላመዱላቸው ብቻ ሳይሆን፣ ጥሩ እንዲሸቅሉ እያገዟቸው ነው፡፡ ሌሎችም በዚህ መስክ እንዲገቡ ሲገፋፉ መታየታቸው ሕጋዊ አገልግሎት ሰጪዎችን  የሚደቁስ ነው፡፡

      እንዲህ ያለው አሠራር የግል ታርጋ በለጠፉ ተሽከርካሪዎች ብቻ የሚፈጸም አይደለም፡፡ ለመስክ ሥራ የሚሰማሩ የመንግሥትና የግል ድርጅት አሽከርካሪዎችም   ከደላሎች ጋር በመመሳጠር የቸገረውን መንገደኛ ከሥፍራ ሥፍራ ያውም ጠቀም ባለ ክፍያ ያጓጉዛሉ፡፡

      በደላሎች እየታገዘ የሚካሄደው ይህ ተግባር፣ ተሽከርካሪዎቹ አየር በአየር ሲጭኑ፣ አገር አቋራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት ሲሰጡ፣ እንደ ሕጋዊ አገልግሎት ሰጪ ቦታ ይዘው ሲጭኑ እንኳ ከልካይ የለባቸውም፡፡ የትራንስፖርት አገልግሎት የመስጠት ፈቃድ የሌላቸው፣ ነገር ግን እንደ ሕጋዊ አካል ሥራውን የሚሠሩ ግለሰቦች የወንጀል ምንጭ እየሆኑ መምጣታቸው ግን ሊያሳስብ ይገባል፡፡  

      ንብረት እያሻሻጠ ገንዘብ የሚያገኘው ደላላ የደከመበት ነውና ማግኘቱ ባይጠላም፣ ብዙውን ጊዜ ግን ሕጋዊነት ስለማይታይበት ገበያውን ያበላሸዋል፡፡    በኮሚሽን የሚገኘው ገቢ ጥቂት የሚባል አይደለም፡፡ የሚያሽከረክሩት ገንዘብ መጠን ከታወቀም ገንዘቡን ሕጋዊ መሠረት እንዲይዝ ማድረግ ካልተቻለ ግን ችግሩ ነገም ከነገወዲያም ይቀጥላል፡፡ ሕጋዊ አሠራሮች ለሕገወጥ አሠራሮች በር ይከፍታሉ፡፡  

      መንግሥት በዚህ ረገድ ችላ ብሏል የሚባልበት ምክንያት ሽያጩ ሲካሄድ፣ በሕጋዊ መስመር ሲያልፍ የውል ስምምነቱ የተካሄደው በደላላ ነው? ወይስ ያለ ደላላ ብሎ በመጠየቅ ከዚያ ሽያጭ ተጠቃሚ የሆነውን በቀላሉ በመለየት ሕጋዊ ሥርዓት እንዲሰፍን ማድረግ የሚቻልበት አንዱ መንገድ ነው፡፡

ሌላም መጨመር እንችላለን፡፡ የእንግዳ ማረፊያ ወይም ‹‹ገስት ሀውስ›› ተብለው ውስጥ ውስጡን የጦፈ ቢዝነስ የሚሠራባቸው ቤቶች ከማንም የተሠወሩ አይደሉም፡፡ ቪላዎች ያለምንም ከልካይና ፈቃድ የአገሬውንም የውጩንም እንግዳ በዶላር ሲያስተናግዱ እንዴት ነው የምትሠሩት? በምን አግባብ ነው? የሚላቸው ያለ አይመስልም፡፡

አንዳንድ ሆቴሎች በእነዚህ ቪላዎች የገበያ ድርሻ እየተወሰደባቸው ተቸገርን  ሲሉና ሲያማርሩ ምንድነው ችግራችሁ አልተባሉም፡፡ በኮንትሮባንድ ዕቃዎች የተሞሉ መደብሮች በከተማው የትኛው ክፍል እንደሚገኙ አይታወቅም ማለት ሞኝነት ነው፡፡ በግል ታርጋ ተሳፋሪዎችን የሚያመላልሱትና ያለፈቃድ እንግዶችን የሚያስተናግዱት ቪላዎች ትስስር አላቸው፣ ሥራ የሚያገኙላቸውም ደላሎች መሆናቸው እየተነገረ ነው፡፡

በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች እየተበራከቱ የመጡት የሞተር ብስክሌቶች የሚሰጡት የትራንስፖርት አገልግሎት እንደ ሕጋዊ እየታየ ነው፡፡ ይህ ግልጽ ቢሆንም የተወሰደ ዕርምጃ ግን የለም፡፡ ሥራቸው ቢዝነስ ነው፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ተግባራት ግብይቱንና የአገልግሎት አሰጣጡን እየበረዙት ለተለያዩ አደጋዎችም ምንጭ እየሆኑ የመዝለቃቸው ነገር ሲታይ መንግሥት ምን እየሠራ ነው? የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ይጋብዛል፡፡

በሕጋዊ መንገድ የሚሠሩትንም ወደ ሕገወጥነት እንዲገፋፉ ያደርጋል፡፡ ሕገወጡ ምንም ዕርምጃ ካልተወሰደበት ሕጋዊው መቀላቀሉ አይቀርም፡፡ ሕጋዊ ያልሆነ ሰው የሚያደርስው ጉዳትና አደጋ መቆጣጠርም አይቻልም፡፡ ተጠቃሚዎችም ቢሆኑ ስለሕጋዊነትና ትክክለኛነት ማሰብ አለባቸው፡፡ እንዲህ በማድረጋቸው ጉዳትና አደጋ ለመነቀስ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡

እርግጥ ነው ለሕገወጥ ትራንስፖርት መበራከት አንዱ መንስዔ አገልግሎት የሚሰጡት ተገቢውን ግልጋሎት ባለማቅረባቸው፣ ሕዝብ አገልግሎት በማጣት የሚማርበት፣ ለፀሐይና ዝናብ እየተጋለጠ ተሰልፎ የሚልበት የቀን ተቀን አጋጣሚና ክስተት እየተበራከተ መምጣቱና የሕዝቡ ምርጫ ማጣት ለሕገወጦች ዕድሉን መፍጠሩም አይካድም፡፡ ይህም በመንግሥት የተፈጠረ ችግር ማለት ይቻላል፡፡

በትራንስፖርት አገልግሎት ሕጋዊውን ከሕገወጥ የመለየቱ ሥራ እንደተጠበቀ ሆኖ ተጎድተናል የሚሉ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችም መብታቸውን ለማስከበር እየጣሩ ቢሆኑም፣ የአገልግሎት አሰጣጣቸውን ማሳመር፣ ያልተገባ ዋጋ እየጠየቁ ተገልጋዩን የማማረር ድርጊታቸውን ሊገቱት ይገባቸዋል፡፡

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት