Sunday, March 3, 2024

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገሪቱን ሰንገው ስለያዟት ግጭቶች ማብራሪያ የሰጡበት የፓርላማ ውሎ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

መስከረም 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ሦስተኛ ዓመት የሥራ ዘመኑን በአገሪቱ ፕሬዚዳንት የመክፈቻ ንግግር የጀመረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) ሦስተኛ መደበኛ ስብሰባውን ለማካሄድ፣ ሐሙስ ጥቅምት 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ተሰይሟል፡፡ የዕለቱ አጀንዳ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) መስከረም 29 ቀን የተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የሥራ ዘመናቸውን ለመጀመር ባደረጉት የጋራ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፣ መንግሥት በበጀት ዓመቱ ትኩረት ሊያደርግባቸው ይገባል ባሏቸው የሥራ ዝርዝሮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፍ ነው፡፡ ውሳኔውን ለማሳለፍ ይረዳ ዘንድ የምክር ቤቱ አባላት በሥራ ዝርዝር ውስጥ ሊካተቱ ይገባቸዋል የሚሏቸውን እንዲካተቱ ወይም ለምን እንዳልተካተቱ ግልጽ ግንዛቤ ይኖራቸው ዘንድ፣ የሥራ አስፈጻሚውን የሚመሩት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በምክር ቤቱ ተገኝተው ማብራሪያ መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡

ይህ አሠራር በምክር ቤቱ የአባላት ሥነ ምግባርና የሥነ ሥርዓት ደንብ የተደነገገ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በምክር ቤቱ ተገኝተዋል፡፡ የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ የድርጅታቸው ኦሕዴድና የክልሉ ሕዝብ ክብር ተነክቷል በሚል የፖለቲካ ቅሬታ ከሥልጣናቸው ለመልቀቅ የጠየቁ መሆኑ ይታወሳል፡፡ ነገር ግን ጥያቄያቸው ገና ተቀባይነት ያላገኘ በመሆኑ በዕለቱ የምክር ቤቱ ስብሰባም ሆነ በአፈ ጉባዔ መንበራቸው ላይም አልተገኙም፡፡ በመሆኑም የዕለቱንም ስብሰባ ለመምራት የተሰየሙት የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ሽታዬ ምናለ ናቸው፡፡

ከምክር ቤቱ 547 አባላት መካከል 370 የሚሆኑት በዕለቱ የተገኙ ቢሆንም፣ ባልተለመደ ሁኔታ ከአፈ ጉባዔዎቹ መንበር በስተቀኝ የሚገኘው ረድፍ ኦሕዴድን የሚወክሉ በርካታ መቀመጫዎች ባዶ ሆነው ታይተዋል፡፡ በዚህ ረድፍ የሚቀመጡት በርካቶቹ የኦሕዴድ አባላት ቢሆኑም፣ ጥቂት የብአዴን አባላትና ከኋላ ረድፍ እንዲሁም በፊት ለፊት መቀመጫዎች ላይ ለአጋር ክልል ተወካዮች የተደለደለ ነው፡፡ በተቃራኒው የሕወሓት (የትግራይ ክልል)፣ የደኢሕዴን (የደቡብ ክልል) እና የብአዴን (የአማራ ክልል) ተወካዮች የሚገኙበት ተቃራኒው ረድፍ መቀመጫዎች በአንፃራዊነት በተወካዮች ተይዘዋል፡፡

ይሁን እንጂ በዚህ ረድፍ የመጀመሪያዎቹ የፊት ለፊት መቀመጫዎች የምክር ቤቱ አባላት ለሆኑ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት የተደለደሉ ናቸው፡፡ ከተለመደው በተለየ በዚህ ሥፍራ በርካታ መቀመጫዎች ክፍት ሆነው ታይተዋል፡፡ ከሚታወሱ ፊቶች መካከል የሕወሓት ጎምቱ ፖለቲከኛ አቶ ዓባይ ፀሐዬ፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ በዕለቱ የምክር ቤቱ ውሎ አልተገኙም፡፡

ምክር ቤቱ መስከረም 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ፕሬዚዳንት ሙላቱ በመክፈቻ ንግግራቸው የዘረዘሯቸውን ትኩረት የሚሹ የበጀት ዓመቱ ዓበይት አጀንዳዎች ሙሉ በመሉ የሚቀበል የድጋፍ ሞሽን በመንግሥት ረዳት ተጠሪው ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አማኑኤል አብርሃ በኩል ቀርቦ ለተጨማሪ ውይይት አልፏል፡፡ በዕለቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በምክር ቤቱ የተገኙት ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ማብራሪያ በመስጠት፣ የቀረበውን የድጋፍ ሞሽን ምክር ቤቱ እንዲያፀድቀው ነው፡፡

በዚህ መሠረት የምክር ቤቱ አባላት በፕሬዚዳንቱ ንግግር ላይ ለሚያነሷቸው የማብራሪያ ጥያቄዎችና ቢካተቱ ያሏቸውን ሐሳቦች እንዲያነሱ ጥያቄ ላቀረቡ የምክር ቤቱ አባላት ጥያቄዎቻቸውን እንዲያቀርቡ መድረኩን ፈቅደዋል፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል አብዛኞቹ የአገሪቱን ወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች የተመለከቱ ናቸው፡፡ የብር ዶላርን የመግዛት አቅም እንዲዳከም የተደረገበት አመክንዮና ተያያዥ የዋጋ ግሽበት ሥጋቶችን የተመለከቱ ጥያቄዎችም ቀርበውላቸዋል፡፡

ብሔር ተኮር ግጭቶችና ወቅታዊ የአገሪቱ ፖለቲካ

ፕሬዚዳንት ሙላቱ ለሁለቱ ምክር ቤቶች የሥራ ዘመን መክፈቻ የጋራ ስብሰባ ላይ ያደረጉት ንግግር፣ በበጀት ዓመቱ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ዓበይት ተግባራትን ያዘለና በአመዛኙ የአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ማስቀጠልና ማኅበራዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ላይ ያጠነጠነ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ በአገሪቱ የሚስተዋሉትን ግጭቶች ማቆም እንደሚገባም በአጽንኦት ተናግረው ነበር፡፡

‹‹ለግጭቶች ምክንያት የሆኑ ያልተፈቱ የወሰን ማካለል ጉዳዮች ከሞላ ጎደል ለመፍታት የተቻሉ ቢሆንም፣ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አካባቢ ያልተስተካከሉ አፍራሽ አመለካከቶች የወለዷቸው ግጭቶች ተከስተው የሰው ሕይወት በአሰቃቂ ሁኔታ ያለፈበትና ንብረቶች የወደሙበት አሳዛኝ ክስተት አጋጥሟል፤›› በማለት ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው ገልጸው ነበር፡፡

ይህ ክስተት በፍፁም መወገዝ ያለበትና መንግሥት ፀጥታውን ከማስከበር በተጨማሪ፣ አጥፊዎችን ወደ ሕግ ማቅረብ እንደሚገባውና በዚህ ረገድም እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ‹‹በሕዝቦች መካከል ለዘመናት የቆየውን አንድነት የሚያፈርስ አካሄድ በጭራሽ ሊደገም የማይገባው ነው፤›› ብለው ነበር፡፡ በሁለቱ ክልሎች መካከል የተከሰተው ግጭት ቢረግብም እስካሁን ሙሉ በሙሉ አልተቀረፈም፡፡ የሕዝቡን ለዘመናት የቆየ አንድነት የሚያፈርስ አካሄድ በጭራሽ ሊደገም እንደማይገባ ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው ቢያሳስቡም፣ በተቃራኒው ብሔር ተኮር ግጭቶች በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች እየተስፋፉ ነው፡፡

የግጭቶቹ በድንገት በተለያዩ አካባቢዎች መስፋፋትና ሊገታ አለመቻሉ፣ ለብዙዎች እንቆቅልሽ እንደሆነው ሁሉ ለፖለቲካ ተንታኞችም አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ የግጭቶቹ መንስዔ የድንበር አለመካለልና የአመራሮች ጠባብ የአመለካከት ችግር መሆኑ በተለያየ መንገድ በመንግሥት ኃላፊዎች ቢጠቀስም፣ ከዚህ በተለየ መንገድ የሚተነትኑ አመራሮች አሉ፡፡

ከእነዚህም መካከል የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ መስከረም 15 ቀን 2010 ዓ.ም. ከኦሮሚያ ክልል ከተውጣጡ አባ ገዳዎችና የአገር ሽማግሌዎች ጋር በመከሩበት ወቅት፣ የክልሉ መንግሥት ኪራይ ሰብሳቢነትን መታገል በመጀመሩ የተከፉ ኃይሎች ላይ ጣታቸውን ቀስረው ነበር፡፡

‹‹የጥቅል ተሃድሶ ንቅናቄያችንን መሠረት በማድረግ በኪራይ ሰብሳቢዎች ላይ ትንንሽ ዕርምጃዎችን መውሰድ ጀምረናል፡፡ ከመሬት፣ ከማዕድን፣ ከኮንትሮባንድና ከመሳሰሉት ጉዳዮች ጋር የተገናኙ ኪራይ ሰብሳቢዎች ላይ ዕርምጃ በትንሹ መውሰድ በመጀመራችን የክልሉን አመራር እንደ ጠባብ ብሔረተኛ፣ የአገራችንን ብሔር ብሔረሰቦች እንደ ጠባብ የሚያይ፣ በአጎራባች ክልል የሚኖሩ ወንድሞቻችንን ለማጥፋት የተነሳን ጠብ አጫሪ አስመስለው እኛን ለማቅረብ ላይ ታች እያሉ ይገኛሉ፤›› ብለው ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ሐሙስ ጥቅምት 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በፓርላማው በተገኙበት ወቅት ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል አብዛኞቹ ግጭትና መንስዔውን፣ እንዲሁም የፌዴራል መንግሥት እየሰጠ ስላለው መፍትሔ የሚሉት ይገኙበታል፡፡

የኦሕዴድ ተወካዮች በተደለደሉበት የምክር ቤቱ የቀኝ ረድፍ የሚገኙ መቀመጫዎች ክፍት ሆነው ቢታዩም፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቀረቡ 15 ጥያቄዎች አብዛኞቹን መሠረታዊ የፖለቲካ ጥያቄዎች ያነሱት የኦሕዴድ አባላት ናቸው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽም በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች መካከል የተፈጠረው ግጭት የድንበር ግጭት ነው ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ይኼ ግጭት የወሰን ግጭት፣ አይደለም፡፡ የግጭቱ ዋናው መንስዔ ያልተፈቱ የኪራይ ሰብሳቢነት ጉዳዮች በዚያ አካባቢ በመኖራቸው ነው፤›› ብለዋል፡፡ ይህ ንግግራቸውም ፕሬዚዳንት ለማ መገርሳ መስከረም 15 ቀን 2010 ዓ.ም. ከአባ ገዳዎችና አገር ሽማግሌዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ከተናገሩት የግጭቱ መንስዔ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡

‹‹በዚያ አካባቢ ያለውን የጫት ንግድ ለመቆጣጠር የሚደረግ ሩጫ ይህንን ግጭት ብሔራዊ መልክ እንዲይዝ አድርጎታል፡፡ ሁለተኛ በዚህ መስመር ላይ የሚዘዋወር ዶላር ነው፡፡ በአንድ ወር ውስጥ በተደረገ ተከታታይ ዘመቻ ብቻ ሁለት ሚሊዮን ዶላር ይዘናል፡፡ ስለዚህ በዚህ አካባቢ ያለው ሕገወጥ የዶላር ዝውውርና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ የብሔር መልክ እንዲይዝ ተደርጓል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ እንደዚህ ካልተደረገ በስተቀር፣ እነዚህ ጥገኛ ኃይሎች ይህንን ሕገወጥ ንግድ ማስቀጠል ስለማይችሉ ወይም አለመረጋጋት በተፈጠረ ቁጥር ይህንን ሕገወጥ ንግድ ማስቀጠል የሚቻል መስሏቸው በየጊዜው በሚያደርጉት ፍጥጫ የብሔር መልክ እንዲይዝ ያደርጋሉ፤›› ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

በመሆኑም በሁለቱ ክልል ሕዝቦች መካከል ምንም ዓይነት ግጭት እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ ለዚህ ግጭት መሠረታዊ መፍትሔውም ፖለቲካዊ እንደሆነ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ ትግሉ እነዚህን ጥገኛ ኪራይ ሰብሳቢዎች በሚደፍቅ መልኩ ካልተካሄደ በስተቀር መቼም ቢሆን ግጭት ለማቆም አይቻልም ብለዋል፡፡ ‹‹መንግሥትም፣ ኢሕአዴግም፣ ብሔራዊ ድርጅቶችም በዚህ ላይ ጠንካራ ትግል ማድረግ የሚጠብቀን ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ ንግግራቸው ‘ኪራይ ሰብሳቢና ጥገኛ’ የተባለው ኃይል ማን እንደሆነ በግልጽ ማወቅ አለመቻሉን፣ እንዲሁም ትግሉ ገና የሚካሄድ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል ለግጭቶቹ በመንስዔነት ያነሱት ሌላ ጉዳይ የአመራሮች የተሳሳተ አመለካከትን ነው፡፡

እንደ እርሳቸው አባባል ይህ ችግር የሚስተዋለው በድንበር ማካለል ወቅት አመራሮች ‹‹የእኔ ሕዝብ›› እና ‹‹የዚያኛው ሕዝብ›› በማለት በሚያራምዱት የተሳሳተ አመለካከት የድንበር መካለሎች የሚንከባለሉ በመሆኑ ነው፡፡

በአንድ የምክር ቤት አባል የመከላከያ ሠራዊቱ በዚህ ግጭት ውስጥ ፈጥኖ አለመድረሱ ምክንያቱ ምንድነው ተብሎ ለተነሳው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ይህ አስተያየት በመሠረቱ ተገቢ አይደለም፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹በገለጽኳቸው ጥገኞች በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች የመከላከያ ሠራዊታችን ፈጥኖ ባይደርስ ኖሮ ዕልቂቱ የባሰ ይሆን እንደነበር ከተፈናቃዮቹ አንደበት ሰምተናል፤›› ብለዋል፡፡

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ መፈናቀላቸውን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህ ሁሉ ሕዝብ መከላከያ ሠራዊቱ ባይደርስ ኖሮ አደጋ ላይ ይወድቅ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ‹‹የመከላከያ ሠራዊታችንን ሕዝባዊ ባህርይ ለማፍረስ ከውስጥም ከውጭም የሚንቀሳቀሱ አሉ፤›› ብለው፣ ከእንደዚህ ዓይነት አፍራሽ አስተሳሰብ መጠንቀቅ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በቅርቡ ከመንግሥት ከፍተኛ አመራርነት ለመልቀቅ ጥያቄ ያቀረቡትን አፈ ጉባዔ አባዱላና የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በረከት ስምኦንን አስመልክቶ ምክንያቱን እንዲያብራሩ የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እንደዚህ ዓይነት ዴሞክራሲያዊ ተግባር ሊለመድ እንደሚገባ በመግለጽ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ አቶ በረከት ስምኦን በተደጋጋሚ ለመልቀቅ ጥያቄ አቅርበው በኢሕአዴግ ስላልተፈቀደላቸው እስካሁን ሲያገለግሉ ሊቆዩ መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡

አሁን ግን ባቀረቡት ጥያቄ በድርጅቱ ኢሕአዴግ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምሥጋና ተቸሯቸው እንደተፈቀደላቸው ጠቁመዋል፡፡ አፈ ጉባዔ አባዱላ ግን ያቀረቡት ጥያቄ ለመጀመርያ ጊዜ መሆኑንና ጉዳዩንም በተመለከተ በድርጅት ውይይት እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ውይይቱ ገና ያልተጠናቀቀ መሆኑን ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አቶ አባዱላ መልካም ፈቃዳቸው ሆኖ ቢቀጥሉ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -