Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበመንግሥትና በሲቪል ማኅበራት ግንኙነት ውጥረት እንዲረግብ ተጠየቀ

በመንግሥትና በሲቪል ማኅበራት ግንኙነት ውጥረት እንዲረግብ ተጠየቀ

ቀን:

በመንግሥትና በሲቪል ማኅበራት ግንኙነት የሚስተዋለው ውጥረት እንዲረግብ ጥር 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ፎርም ፎር ሶሻል ስተዲስ (FSS) ‹‹በድህነት ቅነሳ ጥረቶች የሲቪል ማኅበራት ድርሻ›› በሚል ርዕስ አዘጋጅቶት በነበረው የውይይት መድረክ ላይ ተገለጸ፡፡ በአገሪቱ የድህነት ቅነሳ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የሲቪል ማኅበራትንና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ሚና በሚመለከት ጥናት ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ገብሬ ይንቲሶ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመንግሥትና በሲቪል ማኅበራት ግንኙነት እየተስተዋለ ያለውን ውጥረት ወይም ጥርጣሬ ለመቅረፍ አስፈላጊ ጥረቶች ሁሉ ሊደረጉ እንደሚገባ በጥናታቸው ማሳረጊያ አመልክተዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሲቪል ማኅበራት በፖሊሲዎች ላይ በሚደረጉ ውይይቶች እየተሳተፉ አለመሆን ችግር እንደሆነ ተገልጿል፡፡ አጥኚዎች፣ የጥናቱ ገምጋሚዎችና ተሳታፊዎች ተቋማቱ አገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በሚዘጋጁ መድረኮች ላይ እንዲሁም በትምህርት፣ በጤናና በሌሎችም ዘርፎች ከፓርላማ ቋሚ ኮሚቴዎችና ከመሰል የመንግሥት አካላት ጋር እየተወያዩ አለመሆኑን አንስተዋል፡፡ በሌላ በኩል የእንቅስቃሴ አቅጣጫቸውን ለይቶ ያለማወቅ፣ ሊሰማሩ የሚፈለጉባቸው ጉዳዮች መሬት ላይ ካለው እውነታና ፍላጐት ጋር የማይሄድ መሆን፣ የሲቪል ማኅበራቱና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድክመት ተብለው ከተጠቀሱ መካከል ነበሩ፡፡ በመድረኩ ተሳታፊ የነበሩት የአዲስ አበባ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኤክስፐርት አቶ ነብዩ ዳዊት፣ ሲቪል ማኅበራት አብዛኛውን ጊዜ የሚያቀርቡት ፕሮጀክት ከአገሪቱ ፍላጐትና እውነታ የራቀ ስለሚሆን አራት አምስት ጊዜ ተከልሶ ካለው ፍላጐት ጋር እንዲጣጣም እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡ ለአገሪቱ የልማት እንቅስቃሴ በተለያየ መንገድ አስተዋጽኦ ያደረጉ ቢኖሩም፣ በጤናው ዘርፍ ውጤት ለማስመዝገብ ተጠቃሽ እንደሆነው የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ያሉ ተሞክሮዎች መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት የተወሰዱ ቢሆንም፣ የሲቪል ማኅበራት ወይም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንቅስቃሴ በመንግሥት ፍላጐት፣ በለጋሾች ፍላጐትና በራሳቸው በተቋማቱ እምነትና አቋም ድምር ጫና የተቃኘ መሆኑ መሠረታዊ ችግር ሆኖ ተነስቷል፡፡ ከዘጠኝና ከስምንት ዓመታት በፊት ፎረሙ ያዘጋጃቸው የውይይት መድረኮች የሲቪል ማኅበራትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተሳትፎ የታየባቸው እንደነበሩ በማስታወስ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የተቋማቱ ተሳትፎ መቀዛቀዙንና በፖሊሲ ውይይቶች ላይም እንደሌሉ የፎረሙ ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ዶ/ር ምሕረት አየነውም ገልጸዋል፡፡ የተቋማቱ የውጭ ፈንድ ላይ ጥገኛ መሆን፣ በመርህ ደረጃ የተሰማሩባቸውን ችግሮች ቀርፈውና አጥፍተው የእነሱም ህልውና እዚያ ላይ ማብቃት ሲኖርበት፣ ‹‹ከችግር ጋር አብሮ የማደግ ነገር›› በስፋት መታየት የተጠቀሰ ሌላ ችግር ነበር፡፡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የሲቪል ማኅበራት የገንዘብ ምንጭ የውጭ አገር ፈንድ መሆን ዓለም አቀፍ እንጂ፣ የኢትዮጵያ የተለየ ሁኔታ አይደለም በማለት የተከራከሩት ዶ/ር ምሕረት፣ ‹‹በኢትዮጵያ ተቋማቱ ከውጭ ገንዘብ ማግኘታቸው ለምን እንደ ትልቅ ኃጢያት ይታያል?›› የሚል ጥያቄ አንስተው ነበር፡፡ በተፈጥሮው መንግሥት ሊሠራ የማይችላቸው ቁም ነገሮች በመኖራቸው የሲቪል ማኅበራትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሚና ሁልጊዜም ወሳኝ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ተቋማቱ በፖሊሲ ሐሳብ ላይ መወያየት ብቻም ሳይሆን ቀደም ሲል ታይቶ እንደነበረው የፖሊሲ ሐሳብ እስከማምጣትም መሄድ አለባቸው ቢባልም፣ ባለው የተቋማቱና የመንግሥት ግንኙነት የዚህ ዓይነቱ የተቋማቱ እንቅስቃሴ የሚደገፍ አካሄድ እንደማይሆን ሥጋታቸውን የገለጹም ነበሩ፡፡ የመንግሥት፣ የሲቪል ማኅበራትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ግንኙነት ጥርጣሬና ውጥረት የተሞላበት ነው የሚለው ግልጽ አለመሆኑን የተናገሩት አቶ ነብዩ፣ በመንግሥት በኩል የተቀመጠው አቅጣጫ መቀራረብና መተባበር መሆኑንና ምናልባት ውጥረትና ጥርጣሬ አለ የሚለው ነገር በተቋማቱ በኩል ካለው አመለካከት የተነሳ እንደሚሆን አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ ተቋማቱ እየታዩ ያሉት እንደ ልማት አጋር ወይስ እንደ ክፍተት ሞይ? መንግሥትና ተቋማቱ የሚያደርጉት የልማት እንቅስቃሴ የተናበበ ነው ወይ? ጥረታቸው የሚገናኝበት ነጥብስ አለ? የመንግሥት ሚና በራሱ ወጥቶ ያለ ታክስ ከፋዩ አንዳች ሐሳብ በራሱ የሚጨርሰው መሆን ይገባዋል? የሚሉ ጥያቄዎችም ተነስተው ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ