ባለፈው ቅዳሜ ጠዋት ከቶጐ ዋና ከተማ ሎሜ ተነስቶ ወደ ጋና አክራ ያቀናው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዕቃ ጫኝ አውሮፕላን ማረፊያ መስመሩን ስቶ ጉዳት ደረሰበት፡፡ የአየር መንገዱ ንብረት የሆነው ቦይንግ 737 – 400 አውሮፕላን በኮኮታ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሊያርፍ ሲሞክር መንገዱን በመሳቱ የአውሮፕላኑ ቀኝ ክንፍ፣ የታችኛውና የፊተኛው ክፍሉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል፡፡ በበረራ ቁጥር “ETAQV-KP-4030” ከሎሜ የተነሳው አውሮፕላን ውስጥ የነበሩት ሦስት የበረራ ሠራተኞች ላይ አነስተኛ ጉዳት ሲደርስባቸው፣ በአክራ ወታደራዊ ሆስፒታል ሕክምና እንደተደረገላቸው ታውቋል፡፡ የአየር መንገዱ ቃል አቀባይ ግን ሦስቱ ሠራተኞች በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆናቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የዕቃ ጫኝ አውሮፕላኑ በሚያርፍበት ወቅት ጐማዎቹ በመተንፈሳቸው ምክንያት ከመስመሩ ወጥቶ ጉዳቱ እንደደረሰበት ተገልጿል፡፡ የጋና የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣናት የአደጋው ምክንያት በወቅቱ የነበረው አስቸጋሪ የአየር ፀባይ ሊሆን ይችላል ቢሉም፣ የአደጋው መንስዔ እየተጣራ መሆኑ ታውቋል፡፡ ሪፖርተር ለሕትመት እስከገባበት ማክሰኞ እኩለ ሌሊት ድረስ የአደጋው መንስዔ አልታወቀም፡፡ አየር መንገዱ በአፍሪካ ከሚገኙ አየር መንገዶች ቀዳሚ የደኅንነት ታሪክ ያለው ሲሆን፣ ይህ አደጋ ግን የኮኮታ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ጥያቄ አስነስቷል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2012 በተመሳሳይ የናይጄሪያ የዕቃ ጫኝ አውሮፕላን በዚሁ አውሮፕላን ማረፊያ መንገዱን ስቶ ከመንገደኞች ማመላለሻ መኪና ጋር ተጋጭቶ አሥር ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል፡፡