ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ከ2.8 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሴቶችና ሕፃናትን ተጠቃሚ የሚያደርግ የ862 ሚሊዮን ብር የልማት ፕሮግራም ስምምነት ከክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋር ባለፈው ሰኞ ተፈራረመ፡፡ ለአምስት ዓመታት ያህል በክልሉ በሚገኙ ልዩ ልዩ ወረዳዎች ተግባራዊ የሚሆነው ይኼው ፕሮግራም ካቀፋቸው የልማት ተግባራት መካከል ሥርዓተ ምግብ፣ ኤችአይቪ ኤድስ፣ ትምህርት፣ የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ የሳኒቴሽን አገልግሎትና የመሳሰሉት ይገኙባቸዋል፡፡ ከፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች መካከል 1,953,286 ያህሉ ሕፃናት መሆናቸውን ድርጅቱ አመልክቷል፡፡ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎችና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ 100 ወረዳዎች ውስጥ የሚንቀሳቀሰው ይኼው ድርጅት ኢትዮጵያ ውስጥ ቢሮ ከፍቶ መሥራት የጀመረው በ1963 ዓ.ም. ነው፡፡