Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልከክለብ ያላለፉ

ከክለብ ያላለፉ

ቀን:

ሠፈሩ ልብስ፣ ጫማ፣ ሸቀጣሸቀጥና ጫት የሚሸጥባቸው መደብሮችን እንዲሁም ካፌና መዋለ ሕፃናትን እስከ አመሻሽ ያስተናግዳል፡፡ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት አንስቶ ደግሞ ቀን ተዘግተው ለሚያንቀላፉት የምሽት ክለቦች ቦታቸውን ይለቃሉ፡፡ ወደ ሁለት ሰዓት አካባቢ በየምሸት ክለቡ ያሉ ሠራተኞች ክለቡንና ራሳቸውንም ማስዋብ ይጀምራሉ፡፡ አንዳንድ ቤት ደጃፍ ላይ ሳር ይጎዘጎዛል፤ እጣን ይጨሳል፣ ልዩ ልዩ ቀለማት ያላቸው ቀጫጭንና ረዣዥም መብራቶች ይበራሉ፡፡ ዳትሰን ክለቦች እንደሚበራከቱባቸው ሌሎች አካባቢዎች ባህላዊና ዘመናዊ ሙዚቃ የሚያስደምጡ መዝናኛዎች ይገኙበታል፡፡ በመሲንቆና በከበሮ ባህላዊ ሙዚቃ የሚያቀርቡ አዝማሪዎችና በኦርጋን ዘመናዊ ሙዚቃ የሚያስደምጡ ድምፃውያን ያሉ ሲሆን፣ የተመረጡ የሲዲ ዘፈኖችን በሞንታርቦዎች የሚያስኮመኩሙ ክለቦችም ይጠቀሳሉ፡፡ ክለቦች አጠገብ ላጠገብ ስለሚገኙ በመንገድ ለሚያልፍ ሰው አንዱን ሙዚቃ ከሌላው ለመለየት ሊያስቸግር ይችላል፡፡ ወደ ክለቦቹ ከዘለቁ በኋላ ግን የሙዚቃ ድምፅ ስለሚጎላ ጎረቤት ያለው አይሰማም፡፡ ሰሜን ሆቴል አካባቢ ከገዳም ሠፈር ጀርባ የሚገኘው ዳትሰን ሠፈር ስያሜውን ያገኘው ወ/ሮ ፋንታዬ ተስፋዬ፣ ወ/ሮ ዓለሚቱ ይማምና ወ/ሮ በላይነሽ አሸራ ይባሉ የነበሩና በመደዳ ሦስት የምሽት ክለብ ያላቸው ግለሰቦች ዳትሰን መኪና ማሽከርከራቸውን ተከትሎ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ስለ ዳትሰን ሠፈር ሙዚቃና አዝማሪዎች በ1992 ዓ.ም. ጥናት የሠራው የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ተማሪ ፍፁም ሲራክ፣ ከሠፈሩ ጀርባ ብዙዎች የሚያዘወትሩትና ዝናን ያተረፈው ገዳም ሠፈር ለዳትሰን መታወቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ይገልጻል፡፡ በጽሑፉ እንደተመለከተው፣ አብዛኛው በአካባቢው ያሉ ባህላዊ ሙዚቀኞች በልምድ የሚጫወቱ ናቸው፡፡ ብዙ አስተያየት ሰጪዎች ክለብ የሚሠሩ ሙዚቀኞች በልምድ ከመሥራታቸው ባለፈ ከምሽት ሥራ ሲያልፉ አይታዩም ይላሉ፡፡ ድምፃውያኑ በአንድና ሁለት የሙዚቃ መሣሪያ ታጅበው የሚያቀርቧቸው ሙዚቃዎች ደረጃቸውን የጠበቁ እንዳልሆኑ ይገለጻል፡፡ ሙዚቃዎቹ አመሻሽ ላይ ወደ ክለብ የሚመጡ ተዝናኞችን ከማስደሰትና ገንዘብ ከማግኘት አያልፉም የሚል አስተያየትም ይደመጣል፡፡ በሌላ በኩል ክለቦቹ ዘፋኞች ድምፃቸውን የሚገሩበትና የሙዚቃ ችሎታና ፍላጎት ላላቸው ዕድሉን የሚሰጡ እንደሆኑ ይታመናል፡፡ ክለብ የሚሠሩ ሙዚቀኞች ሥራውን ለሙዚቃ ሕይወታቸው እንደ መነሻ ቢያዩትም፣ ፈታኝ እንደሆነና ነጥረው የሚወጡ ጥቂት እንደሆኑ ይገልጻሉ፡፡ የክለብ ሙዚቃዎች ከተፋ የበዛባቸው እንደሆኑ የሚናገሩ አሉ፡፡ በተቃራኒው በሠርግ፣ በምርቃት ወይም መሰል ቦታዎች የሚደመጡ ሙዚቃዎች ያለ ልምምድ የሚሠሩበት ጊዜ ስለሚበዛ ከተፋ ቢባሉም የክለብ ሥራ ባጠቃላይ ከተፋ አይደለም የሚል አስተያየት የሰጡን ሙዚቀኞች አሉ፡፡ ዳትሰን ከሚገኙ ክለቦቹ አንዱ የሺሐረግ ባር ሲሆን፣ ክለቡ ዘመናዊ ሙዚቃ ያቀርባል፡፡ በቦታው በተገኝንበት ዕለት ድምፃዊው በኦርጋን ታጅቦ ታዋቂ ዘፈኖች ሲያስደምጥ ተጠቃሚዎቹ ጠባቧ ቤት መካከል ላይ ባለው ክፍት ቦታ በየሙዚቃው ይወዛወዙ ነበር፡፡ ድምፃዊውም የበለጠ እንዲዝናኑ የሚያሳስብ ማሟሟቂያ ቃላት ጣል ጣል እያደረገ አራት ዘፈን ከተጫወተ በኋላ መድረኩን ለሌላ ድምፃዊ አስረክቦ ከመድረኩ ወረደ፡፡ ድምፃዊው ቴዎድሮስ ገዛኸኝ የ30 ዓመት ጎልማሳ ሲሆን፣ የዕድሜውን ግማሽ ያህል ክለብ ውስጥ እንደሠራ ይነገራል፡፡ ክለብ ውስጥ መዝፈን ከመጀመሩ በፊት በተለያዩ የበጎ አድራጎት ክበቦች ይሠራ ነበር፡፡ በየሺሐረግ ባር በሳምንት ስድስት ቀን ይሠራል፡፡ በቤቱ በርካታ ድምፃውያን ስላሉና ስለሚተካኩ በሙዚቃዎች መካከል እረፍት እንደሚያገኙ ይገልጻል፡፡ ድምፃዊው በዋነኛነት የሚዘፍነው የቴዎድሮስ ታደሰንና አበበ ተካ ሥራዎችን ነው፡፡ ክለብ ውስጥ የማንኛውም ድምፃዊ ዘፈን በተዝናኞች ሊጠየቅ ስለሚችል የተለያዩ ድምፃውያንን ሥራ ልሠራ እችላለሁ የሚለው ቴዎድሮስ፣ በአንድ ምሸት እስከ አሥር ዘፈን ያቀርባል፡፡ ቴዎድሮስ በየዕለቱ የሚያቀርበውን ከተቀሩት ድምፃውያንና ኦርጋን ተጫዋቹ ጋር ይለማመዳል፡፡ ተመልካቾች ድንገት የሚመርጡትን ዘፈን ለተለማመደ ድምፃዊ ዕድል ቢሰጠውም ብዙ ጊዜ ለዕለቱ ይሆናል ብለው የመረጡትን ዘፈን አዘጋጅተው ይገባሉ፡፡ ዐውደ ዓመት ሲሆን ባህላዊ ሙዚቃዎች እንደሚመረጡና በአብዛኛው ግን የብሶት ሙዚቃ እንደሚወደድ ቴዎድሮስ ይናገራል፡፡ እሱ እንደሚለው፣ ከፍቅር ጋር የተገናኘና ብሶት አዘል ሙዚቃ በክለብ ተመራጭ ሲሆን ይስተዋላል፡፡ ምናልባትም መጠጥ ስለሚጠጣና ወደ ምሽት ክለቦች ከሚመጡ ተዝናኞች በብዙዎቹ ስለሚመረጥ ይሆናል ሲል ያክላል፡፡ በምሽት ክለቦች የሚደመጡ ሙዚቃዎች ጥራት የጎደላቸው እንደሆኑ ስለመተቸቱ በሙሉ ባንድ የሚሠሩ ሙዚቃዎችን የሚያስደምጡ ክለቦች የገንዘብ አቅም ያላቸው በመሆናቸው የሚቀርበውን ሙዚቃ ለማወዳደር እንደሚያስቸግር ተዎድሮስ ይገልጻል፡፡ እሱ ሲጫወት እንደነበረው በኦርጋን ብቻ የሚታጀቡ ሙዚቀኞችን ችሎታ ጥያቄ ውስጥ ማስገባት ከባድ ነው ይላል፡፡ በየአካባቢው የሚቀርበው ሙዚቃ ጥራት ደረጃ ልዩነት ቢኖረውም የምሸት ክለብ ሙዚቃዎች ባጠቃላይ ከተፋ በሚል መጠራት እንደሌለባቸው ይናገራል፡፡ ክለብ ውስጥ ድምፃውያን በብዛት ስለሚገኙና እርስ በእርስ ስለሚተካኩ አንዱ መድረክ ላይ ወጥቶ ልዩ ልዩ ዘዬ ያላቸው ጥቂት ሙዚቃዎችን ተጫውቶ ሌላ ድምፃዊ የሚተካበት አሠራር ከተፋ መባል የለበትም ይላል፡፡ በግዴለሽነት የሚቀርብ ሙዚቃን አድማጩም ቢሆን እንደማይቀበለው ይናገራል፡፡ ክለብ ውስጥ ያለው ሰው ምንም እንኳን መጠጥ እየጠጣ ቢዝናናም፣ ለጆሮው የሚጎረብጥ ዘፈን ሲዘፈን ይተቻል ይላል፡፡ እንደ ድምፃዊው ተዝናኚዎች በሙዚቃው ካልተደሰቱ ለዘፋኞች ስሜታቸውን ይገልጻሉ፣ ሽልማት አይሰጡም አንዳንዴ ክለቡን ጥለው እስከመውጣት ይደርሳሉ፡፡ የክለብ ሙዚቃ በተደጋጋሚ መተቸቱን አይስማማበትም፡፡ በየክለብ ባለው መሣሪያ በልምምድ የተደገፈ ዜማ እንደሚደመጥ ያምናል፡፡ በርካታ ድምፃውያን መነሻቸውን ክለብ ውስጥ እንደሚያደርጉና ድምፅ በመግራት ረገድ የጎላ ሚና እንዳለው ይናገራል፡፡ ቴዎድሮስ እንደ ብዙዎች ሁሉ የክለብ ሥራ ፈታኝ እንደሆነ ይስማማበታል፡፡ ጫናው በሴት ድምፃውያን ላይ ቢያመዝንም ለወንዶችም አስቸጋሪ ነው፡፡ ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባት ሲሆን፣ እንደ ቤተሰብ ኃላፊ ምሽትን በክለብ ቀን ደግሞ በእረፍት ማሳለፍ እስቸጋሪ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ሌላው ከክለብ ባለፈ ድምፃውያን የራሳቸውን ሙዚቃ አለማቅረባቸው ነው፡፡ ሁሌ ባይሆንም የግል ሙዚቃ ለመሥራት ክለብ መሥራት አጋዥ ነው ይላል፡፡ የራሱን ሙዚቃ እያዘጋጀ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት መጨረሻ እንደሚወጣ ይጠብቃል፡፡ ‹‹ሙዚቃ አንዳንዴ ዕድል ነው፤›› የሚለው ቴዎድሮስ፣ ከክለብ ሥራ ወጥቶ የራስ አልበም መሥራት የሚችሉ ጥቂት መሆናቸውን ያስረዳል፡፡ ገንዘብ ኖሯቸው ያለችሎታ አልበም የሚያወጡ ሰዎች መኖራቸው፣ እሱም ጥረቱ ቀጥሎ አልበም ማውጣቱ እንደማይቀር ያስረዳል፡፡ የክለብ ሥራ ልምድ በማካበትና አድናቂ በማፍራት ረገድ ጠቃሚ ቢሆንም የሚገኘው ገንዘብ ከሥራው ጋር አይመጣጠንም፡፡ ከዚህ ቀደም ቀን ቀን ፀጉር ቤት በመሥራት ተጨማሪ ገንዘብ ቢያስገባም ከምሽት ሥራ ጋር ድካሙን መቋቋም ስላልቻለ ትቶታል፡፡ የክለብ ሥራ የሙዚቃ ፍቅሩን የሚወጣበት መሆኑ ዋንኛ ግቡ ቢሆንም ገቢ ማግኘትና ቤተሰብ ማስተዳደሪያውም እንደሆነ ይገልጻል፡፡ የ25 ዓመቷ የምሥራች ዘውዱ ካሳንችስ አካባቢ በሚገኘው አበጋዝ ክለብ ውስጥ ትሠራለች፡፡ የምሽት ክለብ ሥራዎች በብዛት የከተፋ ሥራ የሚባሉት ከአንድ ዘፈን ጋር ተመሳሳይ ምት ያለው ሌላ ዘፈን አስከትለው ያለማቋረጥ ስለሚሠሩ ነው ትላለች፡፡ እሷ አልፎ አልፎ የምትሠራቸው ሙዚቃዎች ከከተፋ የሚካተቱ እንደሆነ ትገልጻለች፡፡ የክለብ ሥራ የተዋጣላት ሙዚቀኛ ለመሆን ሁነኛ መሠረት የሚጣልበት ሊሆን እንደሚችል ታምናለች፡፡ በሆቴልና በተለያዩ ክለቦች የሠራችው የምሥራች የክለብ ሥራ ለሴት ሙዚቀኞች ፈታኝ ነው ትላለች፡፡ ሙዚቃ የጀመረችው ልጅ ሳለች ነበር፡፡ ቤተሰቦቿ ድምፃዊ እንድትሆን ስለማይፈልጉ በውሳኔዋ ከቤተሰቧ ተቀያይመው ነበር፡፡ ከጅምሩ የሚደግፋት ባለመኖሩ ድምፃዊነት ያስቸገራት የምሥራች፣ ፆታዊ ትንኮሳ እስካሁንም ችግር እንደሆነባት ታስረዳለች፡፡ ከዚህ ቀደም የምራች ከምትሠራበት ክለብ የለቀቀችው በተመሳሳይ ችግር ነበር፡፡ አንድ ምሽት ከመድረክ ወርዳ ሌላ ጊዜ እንደምታደርገው የክለቡ በረንዳ ላይ አረፍ ትላለች፡፡ በረንዳ ላይ የነበረ የክለቡ ደንበኛ ‹‹ካልጋበዝኩሽ›› በሚል እሰጣ ገባ ይፈጥራል፡፡ የክለቡ ባለቤቶች ‹‹ደንበኛ ማስቀየም የለብሽም፤ ገበያ ትዘጊያለሽ›› በሚል ለደንበኛው ፍላጎት ቅድሚያ ሰጥተው ሲጫኗት ክለቡን ለቃ ወጥታለች፡፡ ከዚያ በኋላም በተመሳሳይ ምክንያት ክለቦችን ለቃለች፡፡ የወንድ ጓደኛዋ ይህን የሥራዋን ሁኔታ እንደሚያውቅና እንደሚረዳት ትገልጻለች፡፡ ስትዘፍን እንደሚታደምና እንደሚደግፋትም ትናገራለች፡፡ በብዛት የአስቴር ከበደና ሐመልማል አባተን ዘፈን የምትጫወተው የምሥራች፣ አልበም መሥሪያ ገንዘብ ለማግኘትና ራሷን ለመደገፍ ቀን ቀን ደግሞ በሴቶች ፀጉር ቤት ትሠራለች፡፡ በዚህ ዓመት መጨረሻ ይወጣል ብላ የምትጠብቀው ነጠላ ዘፈን አላት፡፡ እንደምትለው፣ አንዳንድ የምሽት ክለቦች ጥቂት ድምፃዊ ሲኖራቸው መዚቃው በአግባቡ አይሠራም፡፡ ሙዚቃው ጥራት እንዲኖረውና ዘፈን ሳይቆራረጥ ሙሉ ሥራዎች እንዲቀርቡ በርካታ ድምፃዊያን መኖራቸው በተወሰነ መልኩ ይረዳል፡፡ እሷ ሁለት ወይም ሦስት ዘፈን ዘፍና ሌላ ሰው ስለሚቀየር ጥራት ያለው ሥራ መቅረብ እንደሚችል ታምናለች፡፡ የምሥራች በአንድ ወቅት አቢሲኒያ የሥነ ጥበብና ሞዴሊንግ ትምህርት ቤት ሙዚቃ ተምራለች፡፡ ክለብ መሥራት በመደበኛ ትምህርት ከሚገኝ ዕውቀት በተጨማሪ ልምድ እንደሚያዳብር ታምናለች፡፡ ክለብ ውስጥ ከሚመጡ ሰዎች ለሙያው አጋዥ የሆኑ እንደሚታወቁበትም ታክላለች፡፡ ትኩረታቸውን በከተፋ ላይ አድርገው በአጠቃላይ በምሽት ክለቦች ስለሚሠሩ ሙዚቃዎች ጥናት ካደረጉ መካከል የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ምሩቃን አቶ በኃይሉ ካሳሁንና አቶ ሲሳይ ፈቃዱ ይጠቀሳሉ፡፡ ጥናታቸው ምሽት ክለብ የሚሠሩ ሙዚቃዎች በብዛት ትኩረት የተሰጣቸው ናቸው ለማለት እንደማያስደፍር ያመለክታሉ፡፡ አቶ ሲሳይ ጥናት መነሻ ጅምራቸውን የምሽት ክበብ አድርገው ሩቅ መጓዝ የቻሉ አንጋፋ ሙዚቀኞች ተሞከሮ ነው፡፡ ክለቦች ሙዚቀኞች ብዙ ልምምድ ሳያደርጉ የሚያቀርቡ ቢሆንም፣ አንዳንንድ ጥሩ ሙዚቀኞች ያሉበት በመሆኑ ከተፋ በሚል መጠቃለል እንደሌለበት አጥኚው ያመለክታል፡፡ የምሽት ክለቦች ኃላፊነት በማይሰማቸው የሚተዳደሩ መሆናቸው ጥራት ያለው ሙዚቃ እንዳይሠራ ተፅዕኖ ሆኗል፡፡ አቶ ሲሳይ እንደሚለው፣ የምሽት ክለብ ሥራዎች ተገቢውን ደረጃ እንዲይዙና ዘርፉ እንዲከበር ባለሙያዎች በኃላፊነት መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ አቶ በኃይሉ እንደሚለው፣ የምሽት ክለብ ተዝናኞች ምርጫቸው የሆነውን ዘፈን ሲጠይቁ እነሱን ለማርካት ሙዚቀኛው ያልተለማመደውን እንዲያቀርብ ይገደዳል፡፡ በዚህም ቅንብሩ ያልተስተካከለ ሥራ ሲቀርብ ይስተዋላል፡፡ እንደ አጥኚው፣ በሙዚቃ እጅግ አስፈላጊ የሆኑት ኅብረ ቀለማት (ሐርመኒ)፣ መግቢያ ሙዚቃ (ኢንትሮ)፣ ከዜማ ወደ ሌላ መሸጋገሪያ (ብሪጅ) አለመኖሩ ሙዚቃውን ባዶ ማድረጉ ነው፡፡ አቶ በኃይሉ ዘፋኞቹም፣ የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋቹም ኃላፊነት ሊሰማቸው እንደሚገባ ያመላክታል፡፡ ቴዎድሮስና የምሥራች በበኩላቸው ፈታኙ የምሽት ክለብ ሥራ አልበም ለማውጣትና ወደ ግላቸው ሥራ ለመሸጋገር መነሻ ነው ይላሉ፡፡ ሥራው ግን በአግባቡና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ መሠራት እንዳለበት ይስማማሉ፡፡ ክለብ ለሙዚቃ ያላቸውን ፍቅር የሚወጡበትና ገቢ ማግኛቸው ቢሆንም፣ ሁሉም ሙዚቀኛ በጥራት ይሠራል ማለት እንዳልሆነ ግን ይረዳሉ፡፡ በተጨማሪ ክለብ ውስጥ ሥራቸውን ባግባቡ የሚሠሩ ሙዚቀኞች ስላሉ ዘርፉ በአንድ መጨፍለቅ እንደሌለበት ይገልጻሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...