የሮማው ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ ከጥር 7 እስከ 11 በፊሊፒንስ የሚያደርጉትን ጉብኝት በማስመልከት ትራፊክ ፖሊሶች ዳይፐር እንዲያደርጉ ትዕዛዝ እንደተሰጣቸው አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ ትራፊክ ፖሊሶች ዳይፐር እንዲያደርጉ ትዕዛዝ የተሰጠው በጳጳሱ ጉብኝት ወቅት ለረዥም ሰዓታት በሥራ ገበታቸው ላይ በተጠንቀቅ እንዲገኙ ታስቦ ነው፡፡ ዳይፐሩን ትራፊኮች ብቻ ሳይሆኑ የፀጥታ አስከባሪዎችም ጭምር የሚያደርጉ ሲሆን ይህም በጳጳሱ ጉብኝት ወቅት ፀጥታ አስከባሪዎቹም ሆኑ ትራፊኮች ለተፈጥሮ ጥሪ ወደ መፀዳጃ ቤት እንሂድ ሳይሉ በተጠንቀቅ ቦታቸው ላይ እንዲገኙ ዳይፐር ማድረጋቸው አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ እንደሆነ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት ኃላፊ ኤመርሰን ካርሎስ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል፡፡ ይህ ዕቅድ ከጳጳሱ ጉብኝት በፊት ቀደም ብሎ እንደሚሞከርም አስታውቀው ነበር፡፡ ጳጳሱ በአገሪቱ ከፍተኛ አድናቆት ስለሚሰጣቸው በጉብኝታቸው ወቅት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ እንደሚጠበቅ የገለጹት ኤመርሰን ‹‹የሕዝቡ ብዛት ከልክ በላይ ሊሆን ስለሚችል ዳይፐር እንሰጣቸዋለን›› ብለዋል፡፡ ይህ የመንግሥት ትራፊኮችንና የፀጥታ ኃይሎችን ዳይፐር የማስደረግ ፕላን በብዙዎች እንደ ቀልድ ታይቷል፡፡ ለትራፊክና ለፀጥታ አስከባሪዎች ጭምር ጉዳዩ እንደፌዝ ሆኗል፡፡
***************
እብድ የሰው ፍልስፍናው አኗኗሩ ቢለይ ሐሳቡ ቢመጥቅ ቢተኮስ ወደ ላይ ሰው ያለ ባይመስለው ቆሞ መሃላቸው ንግግሩ ቢከብድ ቢያደናግራቸው እብድ ነው ይሉታል በሙሉ አፋቸው ሀሰትን በጠላ ሐቅን ባፈቀረ የውስጠቱን ሐሳብ በቃላት ባኖረ አትምጡብኝ ባለ ለብቻው በኖረ ሐሜትን በጠላ ሥራን ባከበረ እብድነቱ ብቻ ፈጥኖ ተነገረ እንበልጽግ ባለ እንደግ እንለወጥ በባህል በይሉኝታ ታስረን እንቀመጥ በነፃነት እንኑር እንደየምርጫችን እኛ እንወስን ባለ ለግል ሕይወታችን ማን አይቶት ማንሰምቶት … ወገኑማ ትቶት እብድ ብሎ ሸሽቶት፡፡ ማለዳ፣ 1993 ዓ.ም.፣ አየናቸው አሰፋ ሆረስ – አሉባልታ ክፉኛ በሚናፈስበት ጊዜ የመንፈስ እርጋታ እንዳይለይህ በተድላ ጊዜ ደግሞ ከመጠን ያለፈ ደስታ እንዳይለውጥህ ተጠንቀቅ፡፡ – በሠራው ሥራ ተጸጽቶ ይቅርታ የሚጠይቅ ሰው ሌሎችንም ይቅርታ ለማለት ዝግጁ እንደሆነ ጥርጥር የለውም፡፡ – ከእኔ የተሻለ ግልጽ ሐሳብ ካለህ ንገረኝ፣ ከሌለህ ደግሞ ሐሳቦቼን ከማከናውናቸው ተግባራት ዓይተህ ተጠቀምባቸው፡፡ ሞልየር – ጓደኞቻችንን የበለጠ እየወደድናቸው በሄድን መጠን ማንቆለጳጰሳችን እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ – ንጹህ ፍቅር የሚኖረውም ምንም ዓይነት ስህተት ሲሠሩ በማረም እንጂ በይቅርታ ስናልፋቸው አይደለም፡፡ ቤንጃሚን ፍራንክሊን የመንግሥት ባለሥልጣን፣ ጋዜጠኛና ሳይንቲስትም የነበረው ቤንጃሚን ፍራንክሊን (1906 – 1790) ለአባቱና ለእናቱ 5ኛ ልጅ ነበር፡፡ አባቱ ድሃ ስለነበረም በ17 ዓመቱ ፊላደልፊያ በሚገኝ አንድ ማተሚያ ቤት ተቀጠረ፡፡ ወዲያውኑም የራሱን የሆነ ማተሚያ ቤት ለማቋቋም ስለፈለገ ያኔ አሜሪካን ትገዛ የነበረችውን የእንግሊዝ መንግሥትን የገንዘብ ዕርዳታ ጠየቀ፡፡ ነገር ግን የሚፈልገውን ያህል ገንዘብ ሊያገኝ እንደማይችል ተረጋገጠለት፡፡ ዓላማውን እግቡ ለማድረስም ለ18 ወራት ያህል በማተሚያ ቤት ተቀጥሮ መሥራት እንደሚኖርበት ተረዳ፡፡ ከጊዜ በኋላም የሚፈልገውን የማተሚያ መሣሪያ ገዛና ወደ አሜሪካ በመመለስ ፔንሲልቫኒያ ጋዜት የሚል ጋዜጣ ማሳተም ጀመረ፡፡ የጋዜጣው ዋና አዘጋጅም እራሱ ስለነበረ ተቀባይነትና የሥራው ተነባቢነት ከፍተኛ ሆነ፡፡ ቀጥሎም ዛሬ ዩኒቨርሲቲ የሆነውን የፔንሲልቫኒያ ኮሌጅ አቋቋመ፡፡ በ40 ዓመቱ ላይም ስለኤሌክትሪክ ማጥናት ጀመረ፡፡ በ48 ዓመቱም የእንግሊዝ ሮያል ሶሳይቲ አባል የመሆን ዕድል አጋጠመው፡፡ ቤንጃሚን ፍራንክሊን በሳይንስ መስኩ የሚያደርገው ምርምር እየተሳካ እንደነበረ ቢታወቅም በፖለቲካዊ እንቅስቃሴም ግንባር ቀደም ሚና ይጫወት ስለነበረ ብዙ ነገሮች በጅምር ቀርተውበታል፡፡ በአሜሪካ ነፃነት ላይ ሁነኛ ተሳትፎ በማድረጉም የአሜሪካ አብዮታውያንን በመወከል ወደ ፈረንሳይ ሄዷል፡፡ ተልዕኮውም ተሳክቶለት ከፍተኛ ድጋፍ አስገኝቷል፡፡ አሜሪካ ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ከተላቀቀች በኋላም በሁለቱም አገሮች መካከል ሰላም ለመፍጠር ጥረት አድርጓል፡፡ ተሾመ ብርሃኑ ከማል ታላላቅ ጸሐፊዎችና ጥቅሶቻቸው (2007 ዓ.ም.)
***************
የፌስ ቡክ ጓደኛን ፍለጋ ቤልጄማዊው ቪክተር ቫን ሮዚም እንደ ወትሮው ፌስቡክ ሲከፍት፣ ኒል ዲ ፌቴክ ከተባለ አሜሪካዊ፣ ወዳጆች እንዲሆኑ የሚጠቁም መልዕክት ያገኛል፡፡ የ25 ዓመቱ ቪክተርና የ49 ዓመቱ ኒል ተመሳሳይ ፍላጎት የላቸውም፡፡ ሆኖም በፌስቡክ ጓደኞች እንዲሆኑ ኒል ለምን እንደጠየቀው ለማወቅ ስለ ኒል ማጥናት ጀመረ፡፡ ፈጽሞ የተለያዩ ሰዎች ቢሆኑም ቪክተር ስለ ኒል ባነበበው ነገር ተማረከ፡፡ በአካል መተዋወቅ እንዳለበትም ወሰነ፡፡ ከፊልም ትምህርት ቤት ከተመረቀ ጓደኛው ጋር ሆኖ ከ5,000 ማይል በላይ ተጉዘው ኦስተን፣ ቴክሳስ ገቡ፡፡ ጉዞአቸውን በሙሉ በቪዲዮ ካሜራ እየረቀፁ ነበር፡፡ ቴክሳስ ውስጥ ኒልን የሚያውቅ ሰው አጠያየቁ፡፡ ‹‹ኒልን የምታውቁ አገናኙን›› የሚል ፖስተር ለጠፉ፡፡ የአፋልጉን ቲ ሸርት ለብሰው ከተማውን ዞሩ፡፡ ኒል ፌስቡክ ላይ የጻፋቸውና የሚወዳቸውን አካባቢዎች አሰሱ፡፡፡ ከአንድ ሳምንት በኋላ በአንድ መጽሐፍ መደብር ውስጥ ያገኙት ሰው ኒልን አገናኛቸው፡፡ በቪክተርና ጓደኛው ጥረት የተገረመው ኒል ለአንድ ወር አብረውት እንዲቆዩ ጋበዛቸው፡፡ ቆይታቸውን በሙሉ በካሜራቸው የመዘገበው ቪክተር፣ ‹‹ፍለጋዬ ትንሽ መጠኑን ያለፈ ሊሆን ይችላል፤ ያልተለመደም ነው ቢሆንም እኔና ኒል ጥሩ ጓደኞች ሆነናል፤›› ሲል ለኦሬንጅ ኒውስ ገልጿል፡፡
***********
ራሱን ያጋለጠው ዕፅ ሻጭ ፖሊሶች አደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ከፍተኛ ክትትል ያደርጉባቸዋል፡፡ አዘዋዋሪዎቹም ፖሊስ እጅ እንዳይገቡ ሲጣጣሩ ይስተዋላል፡፡ ከፍሎሪዳ የተሰማው ዜና ግን ከተለመደው አካሄድ ወጣ ያለ ነው፡፡ የ50 ዓመት አደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪ ‹‹አደንዛዥ ዕፅ የሚፈልግ አለ? የእውነቴን ነው አደገኛ ዕፅ ይዣለሁ፤›› የሚል ቲሸርት ለብሶ ከመደብር ወደ መደብር ይዘዋወር ነበር፡፡ ቲሸርቱን ያየ ፖሊስ ለጥያቄ ሲጠጋው ማሪዋና ሊሸጥ እየተደራደረ ነበር፡፡ ፖሊሱም ራሱን ያጋለጠውን ወንጀለኛ ሕግ ፊት አቅርቦታል፡፡