አቶ ዜናዊ መስፍን፣ የኢንተር ኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴል ዋና ሥራ አስኪያጅ
አቶ ዜናዊ መስፍን ተወልደው ያደጉትና እስከ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተማሩት በሽሬ እንደስላሴ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቴክኒካል ቲቸር ኤዱኬሽን የሁለት ዓመት ኮርስ ተከታትለዋል፡፡ ወደ ሐንጋሪ አቅንተው በቡዳፔስት ዩኒቨርሲቲ በሆቴልና ቱሪዝም ማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በኢንተርናሽናል ሪሌሽን ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ እንዲሁም ወደ አሜሪካ ተሻግረው ከሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አድሚንስትሬሽን የማስተርስ ዲግሪ ተቀብለዋል፡፡ በቡዳፔስትና በአሜሪካ በሚገኙ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሆቴሎች ውስጥ ምግብና መጠጥ ዲፓርትመንት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሠርተዋል፡፡ ወደ አገር ቤት ከተመለሱ በኋላ፣ በኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴል ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ ሆቴሉ የወርልድ ሌግዠሪ ሆቴል አዋርድ የ2014 ተሸላሚ ሆኗል፡፡ በዚህ ዙሪያ ከአቶ ዜናዊ ጋር ታደሰ ገብረማርያም ቆይታ አድርጓል፡፡
ሪፖርተር፡- ኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴል የ2014 የዓለም አቀፍ የሆቴሎች ውድድር ተሸላሚ መሆኑን አብስራችኋል፡፡ ሽልማቱን የሰጠው የትኛው አካል ወይም ተቋም ነው፡፡ ሆቴሉስ በምን መሥፈርት ታይቶ ነው ለሽልማት የበቃው?
አቶ ዜናዊ፡- ኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴልን የሸለመው ‹‹ወርልድ ሌግዠሪ ሆቴል አዋርድ›› የተባለው ዓለም አቀፍ ተቋም ነው፡፡ የተቋሙ ዋና መሥሪያ ቤት የሚገኘው እንግሊዝ ውስጥ ሲሆን፣ በተለያዩ አኅጉራትም ቅርንጫፎች አሉት፡፡ ኒውዮርክ በሚገኘው ኢንተርናሽናል ሆቴል አሶሴሽን የሚደገፈው ይኸው ተቋም በዓለም የታወቁ የሆቴልና የቱሪዝም ኤክስፐርቶች አሉት፡፡ እነዚህ ኤክስፐርቶችም በየአገሩ እየተዘዋወሩ ለሽልማት ይመጥናሉ የሚሏቸውን ሆቴሎች ይመርጣሉ፡፡ ለዚህም ተስማሚ የሚሆኑ 51 ዓይነት መሥፈርቶችን አስቀምጠዋል፡፡ በመሥፈርቱ መሠረት 20 በመቶ ያህሉን ነጥብ የሚሰጡት ለሆቴሉ ፋሲሊቲ ሲሆን፣ የቀረው 80 በመቶ ያህሉ ደግሞ ለእንግዳ አቀባበል፣ ለአገልግሎት ብቃት፣ ለውስጣዊ አደረጃጀት ወዘተ የሚያዝ ነው፡፡ ኤክስፐርቶችም በመመዘኛው መሠረት አንድን ሆቴል የሚገመግሙት ወይም የሚያወዳድሩት በዚህ ቀን እንመጣለንና ጠብቁን ብለው ሳያውጁ ድንገት ቱሪስት መስለው ወይም ለሌላ ሥራ የመጡ አስመስለው ነው፡፡ ማንና ምን መሆናቸውም አይታወቅም፡፡ በሪሴፕሽን፣ በምግብና መጠጥ ላይ፣ እንዲሁም ወደ መኝታ ክፍል ሲገቡና ሲወጡ ላጋጠማቸው የሥራ እንቅስቃሴ ሁሉ ነጥብ ይሰጣሉ፡፡ ኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴል በዚህ መልኩ ተገምግሞና ታይቶ ነው ለሽልማት የበቃው፡፡ መምጣታቸውን የማያሳውቁት ወይም ራሳቸውን ግልጽ አድርገው የማይቀርቡት ሆቴሉ ይህንን አውቆና ተዘጋጅቶ እንዳይጠብቃቸው ለማድረግ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የኤክስፐርቶች አገማገም ምን እንደሚመስል ሊያስረዱን ይችላሉ?
አቶ ዜናዊ፡- ኤክስፐርቶቹ እንደመጡ የሆቴሉ ሪሴፕሽኒስቶች ከመቀመጫቸው ብድግ ብለው ‹ወደ ሆቴላችን እንኳን በደህና መጣችሁ› በማለት ፈገግታ በተሞላበት ሁኔታ አቀባበል እንዳደረጉላቸው፣ ከዛም ሻይ ቢና እንዳሏቸውና በዚህም እንደተደሰቱ ነግረውናል፡፡ በሁለት ደቂቃ ውስጥም አስፈላጊውን መሥፈርት አሟልተው የአልጋ ክፍል እንዳስያዙዋቸው፣ ጥቂትም እንዲቀዩ ‹ጤና ይስጥልኝ ጌታዬ ክፍሉን እንዴት አገኙት? ካልተስማማዎት እንቀይርልዎት ወይ? ብለው እንደ ጠየቋቸው ለመረዳት ችለናል፡፡ ቁርስ ላይ ደግሞ ‹ደክሞዎታል ስለዚህ ቁጭ በሉ እኛ እናመጣልዎታለን› ብለዋቸዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ደግሞ ሠራተኞች እንግዳን እንዴት አድርገው እንደሚንከባከቡ ያሳያል፡፡ ማንኛውም እንግዳ በሆቴሉ አልጋ ለመያዝ ሲፈልግ በቅድሚያ ይመዘገባል፡፡ ኤክስፐርቶቹም እንደመጡ ይህንን ፈጽመዋል፡፡ በዚህ ዓይነቱ ምዝገባ ላይ የእንግዳው ስም፣ የተወለደበት ዘመን ወዘተ የሚሞላበት ፎርም አለ፡፡ ከኤክስፐርቶቹ መካከል አንዷ እንስት በፎርሙ ላይ የትውልድ ዘመን በተባለው ቦታ ላይ በሞላችው ዘመን መሠረት ሲታይ ከሦስት ቀናት በኋላ የልደት ቀኗ ይሆናል፡፡ ይህንን የተገነዘቡት ሠራተኞች ክፍል ድረስ በመሄድ ‹መልካም ልደት› (ሐፒ በርዝ ዴይ) በማለት አስደንቀዋታል ወይም ሰርፕራይዝ አድርገዋታል፡፡ ከላይ እስከ ታች ድረስ የተዘረዘሩት የተግባር አፈጻጸም ሁሉ የየራሳቸው ነጥብ አላቸው፡፡ ስለሆነም ኤክስፐርቶቹ የቆዩትን ያህል ባዩት የሥራ እንቅስቃሴ መጠን የሰጧቸውን ነጥቦች በመቀመር ሆቴሉ የወርልድ ሌግዠሪ ሆቴል አዋርድ የ2014 ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል፡፡
ሪፖርተር፡- የሆቴሉ ውስጣዊና ውጫዊ ገጽታ በምን መልኩ ነው የታየው?
አቶ ዜናዊ፡- ሆቴሉ ካለው ውስጣዊና ውጫዊ ገጽታው ለሚያርፉት እንግዶች ልዩ የሆነ እርካታ፣ ስሜትና ደስታ የሚፈጥር ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በዚህም የተነሳ ብዙዎቹ ከዓለም ከታወቀው ሆቴል ጋር ያመሳስሉታል፣ ያደንቁታል፡፡ በዘመናዊ መልክ በመሠራቱ ለአገር ከፍተኛ ገጽታ ፈጥሯል፡፡ የሆቴሉ ግንባታ ሲታይ በመጀመሪያ የሎቢ አሠራሩ ክፍት መሆን፤ ጣራው ደግሞ በተለየ መስተዋት መሠራቱ መልካም ገጽታ ፈጥሯል፡፡ ከታች ወደ ላይ ያለውም ጥሩ እይታ በብዙ እንግዶች ከፍተኛ አድናቆትን አትርፏል፡፡ ከዚህም ሌላ ጣራው ላይ መዋኛ መኖሩ ሆቴሉን ልዩ አድርጐታል፡፡ አሁን የሚገነባው ቅጥያ ሆቴል ደግሞ ከመሰብሰቢያ አዳራሽ እስከ ዘመናዊ ሬስቶራንት አካትቷል፡፡ በአጠቃላይ ቅጥያው ሆቴል ምርጥ ከሚባሉት ሆቴሎች አንዱና በከፍተኛ ወጪ እየተገነባ ስለሆነ ለአገር ገጽታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጥርጥር የለውም፡፡ በተለይ ተሽከርካሪው ሬስቶራንት ጣሪያው ላይ መሆኑ የተለየ ስሜትና እርካታ ይፈጥራል የሚል እምነት አሳድሯል፡፡
ሪፖርተር፡- ሰርቪስን በተመለከተ ከሌላው ሆቴል ሁሉ ልዩ የሚያደርገው ምንድነው?
አቶ ዜናዊ፡- ከሌሎች ሆቴሎች ሁሉ ልዩ የሚያደርገው ለእንግዶቻችን የምንሰጠው አቀባበል ባህላችንን መሠረት ያደረገና በዘመናዊ መልክ የተቀናጀ መሆኑ ነው፡፡ ይህም ዓይነቱ የእንግዳ አቀባበላችን አካሄድ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በእያንዳንዱ ዲፓርትመንት ለሚገኙ ሠራተኞቻችን የአቅም ግንባታ ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ እርስ በርስ መማማር የሚል አሠራር ዘርግተን ዕውቀት፣ የአሠራር ዘዴና ተሞክሮ በመቅሰም ላይ እንገኛለን፡፡ በዚህም አካሄድ ከፍተኛ የሆነ የአመራር ብቃትና መተማመንን ፈጥረናል፡፡
ሪፖርተር፡- ሽልማቱ የተሰጠው የት አገር ነው?
አቶ ዜናዊ፡- ሽልማት የተሰጠው ኬፕታውን ደቡብ አፍሪካ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ኬፕታውን ለዚህ የተመረጠችው ለምንድነው?
አቶ ዜናዊ፡- የዓለም ቱሪስቶች መዳረሻ እና የወርልድ ሌግዠሪ ሆቴል አዋርድ የአፍሪካ ቅርንጫፍ የሚገኝባት በመሆኗ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ሽልማቱን ኬፕታውን ሄዶ የተቀበለው ማን ነው?
አቶ ዜናዊ፡- ሽልማቱን ከሥፍራው ተገኝቼ እንድቀበል የተጋበዝኩት እኔ ነበርኩ፡፡ ነገር ግን የሆቴሉ የማርኬት ማናጀሯ ሄደው እንዲቀበሉ ወክዬአቸው ነበር፡፡ ይህም ሆኖ ግን አልተሳካም፡፡ ምክንያቱም ኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴል የወርልድ ሌግዠሪ አዋርድ ሆቴል የ2014 አሸናፊ መሆኑንና ሽልማቱንም ኬፕታውን በሚገኘው በወርልድ ሌግዠሪ አዋርድ ሆቴል ተቋም ቅርንጫፍ በሚከናወነው ሥርዓት ላይ ተገኝተን እንድንቀበል የተላከልን የጥሪ ወረቀት የተጻፈው ሥነ ሥርዓቱ ከመድረሱ ከ15 ቀናት በፊት ነው፡፡ የጥሪው ወረቀት ግን እጃችን የገባው የሽልማት አሰጣጡ ሥነ ሥርዓት ሊካሄድ ሦስት ቀናት ሲቀረው ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ባለችው ቀናት ውስጥ አስፈላጊውን ሁሉ አጠናቅቆ ለመሄድ ጊዜ ስላጠረን ከጉዞ ቀርተናል፡፡ ተቋሙም የሽልማቱን ሰርቲፊኬት በዲኤችኤል ልኮልን ተቀብለናል፡፡ ዋንጫውን ለመቀበል ወይም ለመውሰድ በቅርቡ ወደ ኬፕታውን እንሄዳለን፡፡
ሪፖርተር፡- ሽልማቱ ለሆቴሉ የሚያስገኘው ጥቅም ምንድነው?
አቶ ዜናዊ፡- አሥራ ስድስት ዓይነት ጥቅሞችን ያስገኛል፡፡ ከጥቅሞቹም መካከል በዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ የመሳተፍ፣ ሆቴሉ ከአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂነትን ማትረፉ፣ ከዓለም የጉዞ ወኪሎች፣ ቱር ኦፕሬተሮች፣ ሲኤንቢሲና ፍራንስ 24 ከተባሉት ዓለም አቀፍ የቴሌቪዥን ድርጅቶች፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ ከሆኑ ጋዜጦችና መጽሔቶች ጋር ትስስር (ኔትወርክ) መፍጠር የመሳሰሉትና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡ አንድ ቱሪስት ወደዚህ ለመምጣት ሲያስብ በመጀመሪያ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን መረጋጋት ያያል፡፡ ቀጥሎ ኢንተርናሽናል ሆቴል ፍለጋ ድረ ገጽ ውስጥ ሲገባ በመጀመሪያ የሚያገኘው ኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴልን ነው፡፡ ምክንያቱም ግሎባል ስታንዳርድ ስላሸነፈ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ይህን መሰል ሽልማት በማግኘታችሁ ምን ተሰማችሁ?
አቶ ዜናዊ፡- በሆቴሉ ባለቤት፣ በማኔጅመንቱና በጠቅላላው በሠራተኞቻችን የፈጠረው ስሜት ከፍተኛ ነው፡፡ ይህም ለበለጠ ሥራ እንድንነሳሳ አድርጐናል፡፡ ኢትዮጵያን አስጠርተናል፡፡ በአጠቃላይ የወርልድ ሌግዠሪ ሆቴል አዋርድ የ2014 ተሸላሚ በመሆናችን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ደረጃውን የጠበቀ ሆቴል የለም ይባል የነበረውን አመለካከት ለመስበር በቅተናል፡፡
ሪፖርተር፡- ለሆቴሎች ደረጃ ገና አልወጣላቸውም፡፡ ከዚህ አኳያ ኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴል በምን ደረጃ ላይ ነው ትላለችሁ?
አቶ ዜናዊ፡- መንግሥት የሆቴሎችን ደረጃ የሚያወጣ አንድ የቴክኒክ ቡድን አቋቁሞ እየሠራ ነው፡፡ በየዓለም ባንክ ድጋፍ የሚንቀሳቀሰው ይህ ቡድን ሥራውን አጠናቅቆ ውጤቱን እስከሚያመጣ ድረስ እየጠበቅን ነው፡፡ አንድ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ምንድነው ማሟላት ያለበት የሚለው በሚታይበት ጊዜ እንግዳው ከገባበት ጀምሮ እስከ ወጣበት ድረስ ያለው ሁኔታ በመሥፈርት የሚዳሰስ ይሆናል፡፡ ይህንንም መሥፈርት እናሟላለን ወይ? ብለን ራሳችን ስንጠየቅ በአገሪቱ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር መቶ በመቶ እናሟላለን የሚል መልስ እናገኛለን፡፡ ባለአምስት ኮከብ ደረጃ የሚያሟላቸውን ነገሮች ሁሉ አሟልተናል፡፡ ለምሳሌ ያህል ሁለት ሬስቶራንቶች፣ አራት ባሮች አሉን፡፡ ከዚህም ሌላ ደረጃው የሚጠይቀው የመኝታ ክፍሎች ስፋት 28 ሜርት ካሬ ሲሆን፣ የእኛ ክፍሎች ግን ስፋታቸው 32 ሜትር ካሬ ነው፡፡ የጣሪያውም ከፍታ ከሚያስፈልገው መሥፈርት በላይ ነው፡፡ የመታጠቢያ ክፍሉ ስፋት አራት ስኩዌር ሜትር መሆን አለበት ተብሎ ተቀምጧል፡፡ የእኛ ግን ከአራት ስኩዌር ሜትር በላይ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን ሆቴላችን ባለአምስት ኮከብ ነው ብዬ በእርግጠኝነት ለመናገር ይከብደኛል፡፡ ምክንያቱም ቡድኑ የራሱ የሆነ መለኪያዎች አሉት፡፡
ሪፖርተር፡- በአገራችን በኢንተርናሽናል ደረጃ ያሉ ትላልቅ ሆቴሎች በነጮች መመራት አለባቸው የሚል የተሳሳተ አመለካከት አለ፡፡ በዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድነው?
አቶ ዜናዊ፡- ይህ ዓይነቱ አመለካከት መቀረፍ አለበት እላለሁ፡፡ ምክንያቱም ከፍተኛ ነጥብ የሚገኘው በነጮች ከተመራ ነው የሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ በውስጣችን አለ፡፡ ብዙ የተረሱና ውጤት ማምጣት የሚችሉ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችን እንዳሉ መዘንጋት የለበትም፡፡ እነዚህም ወንድሞቻችን በኢንተርናሽናል ደረጃ ያሉትን ሆቴሎች በበቂ ሁኔታ መምራትና ትርፋማ እንዲሆን የማድረግ ብቃትና ችሎታ አላቸው፡፡ ነገር ግን ባለው የተሳሳተ አመለካከት የተነሳ፣ ዕድሉን ሳያገኙ ቀርተዋል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙት ኢንተርናሽናል ወይም ታላላቅ ሆቴሎች መካከል አብዛኞቹ በነጮች መመራታቸው የሚያሳዝንና የሚያሳፍርም ነው፡፡ በወርልድ ሌግዠሪ ሆቴል አዋርድ ላይ ግን አሸናፊ ሆኖ የወጣው በነጮች የተመራው ሳይሆን በኢትዮጵያውያን ማኔጀር የተመራው ኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴል ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንተርናሽናል ሆቴሎች በነጮች መመራት አለባቸው የሚለውን የተሳሳተ አመለካከት ሰብረናል፡፡ ማንኛውም ተቋም በነጮች ይመራ የሚለው አመለካከት በቶሎ ተወግዶ በምትኩ በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች መተካት እንደሚኖርበት ሽልማቱ አንድ ማሳያ ነው፡፡