Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መድን ድርጅት የገጠር ዋስትና ፖሊሲ ዝግጅት መጀመሩን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማትንና የኅብረት ሥራ ማኅበራትን በማሳተፍ የመድን ዋስትናን ገጠር ድረስ በመዝለቅ ለአርሶ አደሩና ለአርብቶ አደሩ ማቅረብ በሚቻልበት ፖሊሲ ዝግጅት ላይ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ጥናት አዘጋጅቶ ለውይይት አቀረበ፡፡ ድርጅቱ 80 ከመቶ በሚደርሰው አርሶ አደርና አርብቶ አደር አኗኗር ላይ መደበኛ የኢንሹራንስ አገልግሎት ማዳረስ በሚቻልበትና ከተለያዩ ተቋማት ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያግዘውን ጥናት ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ በቅርቡም የገጠር ኢንሹራንስ ፖሊሲን ለመተግበር ማቀዱን የድርጅቱ ዋና የሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንደሰን ኢተፋ አስታውቋል፡፡ ጥር 5 ቀን 2007 በሒልተን በጠራው የውይይት መድረክ ላይ ከተለያዩ የፋይናንስ ተቋማትና ከገጠሩ ክፍለ ኢኮኖሚ ጋር ተያያዥነት ካላቸው መንግሥታዊና የግል ተቋማት ጋር ሰፊ ውይይት አካሂዷል፡፡ በድርጅቱ የማርኬቲንግና ስትራቴጂክ ማኔጅመንት ዳይሬክተር አቶ ፍቅሩ ፀጋዬ በቀረበው ጥናት መሠረት፣ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የመድን ዋስትናን ማስፋፋት የአደጋ ሥጋት ያለው ሥራ ቢሆንም፣ መተግበር የሚቻልና ጊዜው የሚጠይቀው አንገብጋቢ ሥራ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ በሁሉም አርሶ አደር ቀዬ የመድን ዋስትናን ማዳረስ ለኢትዮጵያ መድን ድርጅት አስቸጋሪና ፈታኝ ቢሆንም፣ በገጠሩ ማኅበረሰብ ከሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሥራት የመድኅን ሽፋንን ማዳረስ እንደሚችል አቶ ፍቅሩ ጥናቱን ለውይይት ባቀረቡበት ወቅት አመልክተዋል፡፡ የመድን ሽፋንን በገጠሩ ክፍል ለማዳረስ ማነቆ ይሆናሉ ተብለው ከተነሱት ነጥቦች አንዱ፣ አብዛኛው አርሶ አደር የመድን ሽፋን መግዛትን እንደ አላግባብ ወጪ ሊቆጥረው ይችላል የሚለው ሥጋት ሲሆን፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ማካሄድ ሥጋቱን ሊቀርፈው እንደሚችል አቶ ፍቅሩ አስረድተዋል፡፡ በውይይቱ ላይ የተገኙ የግል ፋይናንስ ተቋማትና የተለያዩ መንግሥታዊ ድርጅቶች ተወካዮች፣ የገጠር መድን ዋስትናን ለማስፋፋት የቀረበውን ሐሳብ በአብዛኛው ቢቀበሉትም፣ በፖሊሲው ትግበራ ላይ በርከት ያሉ ጥያቄዎችንና ሐሳቦችን አቅርበዋል፡፡ ደደቢት ማይክሮ ፋይናንስን በመወከል የተገኙት አቶ ዮሐንስ ገብረመስቀል፣ የመድን ሽፋኑን በገጠሩ ማኅበረሰብ ዘንድ ለማስፋፋት ሥጋት መፍጠሩ አይቀርም ይላሉ፡፡ ሥጋት ከሌለ ግን ለውጥ እንደማይኖር በማይክሮ ፋይናንስ ዘርፍ ያላቸውን ልምድ በመግለጽ መድን ድርጅት በዕቅዱ እንዲገፋበት ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹ሁሌም ቢሆን ሥጋት የግድ ይኖራል፡፡ ያንን መጋፈጥ ሲቻል ነው ለውጥ የሚመጣው፡፡ ከሃያ ዓመት በፊት የማይክሮ ፋናንስን ለማስተዋወቅ ሲሞከር፣ ድሃው ገበሬ እንዴት ሊበደር ይችላል? የሚል ትልቅ ሥጋት ነበር፡፡ አሁን ማይክሮ ፋይናንሶች የት እንደደረሱ ማየት ይቻላል፤›› በማለት ሐሳባቸውን አጠናክረዋል፡፡ የገጠር መድን ዋስትና የቱንም ያህል ሥጋት ቢኖረው የኢንሹራንስ ሽፋን የግድ ያስፈልገዋል፤›› በማለት አቶ ዮሐንስ አክለዋል፡፡ የአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ እንደወሰደ በተነገረለት ጥናት መሠረት፣ በገጠር ኢንሹራንስ ለማስፋፋት ከ25 ዓመታት በፊት ተሞክሮ የነበረ ቢሆንም፣ አብዛኛው ከሙከራ (ፓይለት) ፕሮጀክትነት ማለፍ አለመቻሉ ተመልክቷል፡፡ በተሳታፊዎች በኩል ሙከራዎቹ ወደ ተግባር ሊለወጡ አለመቻላቸው ለምን እንደሆነ የሚጠይቁ ሐሳቦች ተነስተዋል፡፡ አቶ ኃይሉ ለታ የአጋር ማይክሮ ፋይናንስን ወክለው መገኘታቸውን በመግለጽ አስተያየት የሰጡ ሲሆን፣ አብዛኛው አርሶ አደር የመድን ዋስትና መግዛትን እንደ ወጪ ሊቆጥረው ይችላል የሚለውን ሥጋት እንደሚጋሩት ገልጸዋል፡፡ በኅብረት ሥራ ማኅበራትና በተለያዩ ተመሳሳይ ማኅበረሰባዊ ተቋማት በኩል እስከ ቤተሰብ ድረስ በመዝለቅ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራትን በማካሄድ ማሳካት ይቻላል የሚል ዕምነት እንዳላቸው አመልክተዋል፡፡ ከግብርና ትራንስፎርሜሸን ኤጀንሲ የተገኙት አቶ ብርሃነ ኪዳኑ በበኩላቸው፣ በሙከራ ፕሮጀክቶች ላይ የሚታዩት የመድን ዋስትና እንቅስቃሴዎች የራሳቸው ስኬትና ውድቀት ቢኖራቸው ለኢንሹራንሱ የታሰበውን ያህል አለመስፋፋት የፋይናንስ ተቋማት በበቂ ሁኔታ ካለመስፋፋት ጋር የሚያያይዘው ነገር አለው በማለት አስረድተዋል፡፡ በአገሪቱ የገጠር የፋይናንስ ስትራቴጂ አለመኖሩም ሌላው የዘርፉ ችግር እንደሆነና ‹‹በገጠር ያሉትን የኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ ማይክሮ ፋይናንስና የተለያዩ የኤክስቴንሽን ተቋማትን በሚገባ መጠቀም ከቻልን በትክክል ለአርሶ አደሩ የሚገባውን የዋስትና ሽፋን ማዳረስ እንችላለን፤›› ሲሉ አቶ ብርሃነ አስታያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ የተሰነዘሩትን አስተያየቶች ሙሉ ለሙሉ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት እንደሚቀበላቸው የገለጹት አቶ ፍቅሩ፣ የድርጅታቸው ዋና ዓላማ የኅብረት ሥራ ማኅበራትንና የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትን ‹‹አዳብረን መሔድ እንጂ መተካት አይደለም፤›› በማለት የመድን ሽፋኑን በእነዚህ ተቋማት አማካይነት ሊተገብር እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ ‹‹በእነሱ ያለውን የፋይናንስ ዝርጋታ ማጠናከር እንጂ ማፍረስ አይደለም ዋና ዓላማው፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡ ባለፉት ሁለት አሠርት ውስጥ የተጀመሩት የሙከራ ሥራዎች በአብዛኛው የታሰበውን ያህል ዕድገት ያላሳዩበት ዋንኛ ምክንያት በተቀናጀ አካሄድ ባለመተግበራቸው እንደሆነም አቶ ፍቅሩ ተናግረዋል፡፡ በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ ተጨማሪ ማብራርያ የሰጡት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንደወሰን፣ ጥናቱ ሰፊና የሌሎች አገሮችን ልምድ የዳሰሰ በመሆኑ ለግብርናው ዘርፍ ጥሩ ዋስትና ከመስጠቱም በላይ የአገሪቱን አርሶ አደሮች ለተለያዩ የአደጋ ሥጋቶች ከመጋለጥ ይታደጋል ብለዋል፡፡ ‹‹እያንዳንዱ ገበሬ በሚደርስበት አደጋ ተማርሮ እንዳይሰደድ ይረዳል፡፡ በድርቅና በአደጋ ቀዬውን ለቆ ወደ ከተማ እንዳይፈልስም ይረዳዋል፤›› የሚል ዕምነት እንዳላቸው አቶ ወንደወሰን ተናግረዋል፡፡ የኢንሹራንስ ተቋማት እንቅስቃሴ በከተማ ብቻ ተወስኖ መቆየቱንና በከተማ እየተተገበረ ያለው የኢንሹራንስ ሥርዓት ራሱ ከ50 እና 70 ዓመት በፊት በተቀረፀው ዒላማዎች ላይ ያነጣጠረ መሆኑን፣ በዚህም ለገበሬው ሊደርሱ አለመቻላቸውን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ጠቁመዋል፡፡ በመንግሥት በኩልም ቢሆን አርሶ አደሩ የአገሪቱን ኢኮኖሚና ልማት ቁልፍ አካል በመሆኑ ከፍተኛ ቦታ ስለሚሰጠው፣ የገጠር ዋስትና ፖሊሲው መምጣት ያስፈለገው ለዚህ ዓላማ መሳካት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ውይይቱን ሲመሩ የቆዩትና የመዝጊያ ሐሳብ ያቀረቡት የመንግሥት የፋይናንስ ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ዋና ኤጀንሲ ዶ/ር ስንታየሁ ወልደሚካኤል፣ ኢንሹራንሱ በድርቅ ወቅት በገበሬው ላይ ያጋጥም ከነበረው የኢኮኖሚ መመሰቃቀል ይታደገዋል ብለዋል፡፡ ‹‹በተፈጥሮ አደጋና በዋጋ መዋዠቅ የሚፈጠረውን ሥጋት ለአርሶ አደሩ መቀነስ ከቻልን፣ አርሶ አደሩም የተረጋጋ ኑሮ በመምራት ወደ ኢንቨስተርነት እንዲሸጋገር ይረዳዋል፤›› በማለት ዶ/ር ስንታየሁ ተናግረዋል፡፡ የመድን ሥራ በኢትዮጵያ ሲካሄድ 100 ዓመት በላይ ያስቆጠረ ቢሆንም፣ እስካሁን የሚገኝበት ደረጃ ግን ብዙ የሚቀረውና የኢንሹራንስ ሽፋን ያላቸው ሰዎች ቁጥርም ከግማሽ ሚሊዮን እንደማይበልጥ ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡ ‹‹በዚህ ሁኔታ ካለው አጠቃላይ የሕዝብ ብዛት አንፃር የመድን ሽፋኑን ለሁሉም ለማድረስ ከ250 ዓመት በላይ ይፈጃል፤›› በማለት አዲስ የሕግ ማዕቀፍ ያስፈለገበትን ምክንያት አብራርተዋል፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚው የገጠር ኢንሹራንስ መስፋፋትን ለጋሽ አገሮችም የሚደግፉትና የመድን ድርጅት እንዲተገበርም የራሳቸውን እገዛ ሲያደርጉበት የቆየ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ኒያላ ኢንሹራንስና ኦሮሚያ ኢንሹራንስን ጨምሮ የተለያዩ የመድን ድርጅቶች የገጠር የመድን ዋስትና አገልግሎትን በሙከራ ደረጃ መስጠት የጀመሩ ሲሆን፣ 25,000 የሚደርሱ አርሶ አደሮች የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች እንደሆኑ ታውቋል፡፡ አዲሱ የገጠር መድን ዋስትና ፖሊሲ ሲፀድቅ የገጠሩ ኅብረተሰብ በድርቅ፣ በበረዶ፣ በበሽታና በተለያዩ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ አደጋዎች አማካይነት በሚደርሱ ውድመቶች ላይ ዋስትና ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የዋስትና ሽፋኑም በአነስተኛ እርሻ ለተሰማሩ አርሶ አደሮች፣ ከአንድ ሔክታር መሬት በታች የሚያርሱትንና በእንስሳት እርባታ የተሰማሩትንመድን ድርጅት ሊጨምር እንደሚችል ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች