– ሦስት ተጨማሪ ዓለም አቀፍ ሆቴሎች እንደሚመጡ ይጠበቃል
ከወራት በፊት በአዲስ አበባ ተስተናግዶ ዓለም አቀፍ ትኩረትን ስቦ የነበረው የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረም፣ በድጋሚ አዲስ አበባ ላይ እንደሚካሄድ ታወቀ፡፡ የፎረሙ አዘጋጆች ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ለአራተኛ ጊዜ ተካሂዶ በነበረው ፎረም ሪከርድ የሰበረ ተሳትፎና ያልተጠበቀ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ሽፋን ማግኘቱ አዲስ አበባ ላይ በድጋሚ እንዲካሄድ ለመወሰን ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በሆቴልና በሌሎች የኢንቨስትመንት መስኮች የተሰማሩ ትልልቅ ኩባንያዎች ያሳዩት ፍላጎትና ተሳትፎም ውድድሩ በድጋሚ አዲስ አበባ ላይ እንዲካሄድ ማስገደዱን፣ ፎረሙን የሚያዘጋጀውና መገኛው እንግሊዝ የሆነው ቤንች ኤቨንተስ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ማቲው ዌይስ አስታውቀዋል፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት ጀምሮ የአፍሪካ ሆቴሎች ኢንቨስትመንት ፎረም አዲስ አበባ ላይ እንዲካሄድ ለማድረግ ሲንቀሳቀስ የቆየው አገር በቀሉ ካሊብራ ሆስፒታሊቲ ኮንሰልታንሲ ኤንድ ቢዝነስ ኩባንያ መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡ ስለፎረሙ በድጋሚ መምጣት ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው የካሊብራ አማካሪ ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ነዋይ ብርሃኑ፣ በመጪው ዓመት መስከረም ወር አጋማሽ ላይ እንዲካሄድ ቀነ ቀጠሮ የተያዘው በፎረሙ ከዚህ ቀደም የታየው ስኬታማ ዝግጅት ምክንያት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ፎረሙ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ ድልድዩን የመሠረተው ካሊብራ አማካሪ ሆኖ የተሳተፈባቸው ስድስት ዓለም አቀፍ ሆቴሎች በአዲስ አበባ እንዲከፈቱ ስምምነት መደረጉ ይታወሳል፡፡ ሆቴሎቹ ከዚህ ዓመት መጨረሻ ጀምሮ ባሉት ሁለት ዓመት ውስጥ ተጠናቀው አገልግሎት እንደሚሰጡ ይጠበቃል፡፡ ከእነዚህ ሆቴሎች ባሻገር በካሊብራ አማካሪ ኩባንያ በኩል ድርድር እያደረጉ ከሚገኙ መካከል ሦስት ተጨማሪ ሆቴሎች፣ ቀጣዩ ፎረም ከመካሄዱ በፊት ስምምነት ይፈጽማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ነዋይ አስታውቀዋል፡፡ ለሁተለኛ ጊዜ በሸራተን አዲስ ይካሄዳል ተብሎ ለሚጠበቀው ፎረም፣ በቅርቡ ሥራ የጀመረው የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅትና የኢትዮጵያ ቱሪዝም ምክር ቤት እንቅስቃሴ መጀመራቸው ተሰምቷል፡፡ ቤንች ኤቨትንስ ኩባንያም ለእነዚህ መንግሥታዊ ተቋማት ፎረሙ በድጋሚ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ የኩባንያው ቦርድ መወሰኑን በደብዳቤ እንዳሳወቃቸው ታውቋል፡፡ በዚህ ቀደም የተካሄዱትን የአፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረሞችን ሞሮኮ አንድ ጊዜ፣ ኬንያ ሁለት ጊዜ ያስተናገዱ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ መጪውን ጨምሮ ለሁለተኛ ጊዜ በማስተናገድ ኬንያን ትስተካከላለች፡፡ ከስድስት መቶ በላይ ተሳታፊዎች፣ በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ ዓለም አቀፍ ሆቴሎችና አማካሪዎች እንዲሁም የሆቴል አስተዳዳሪዎች በስፖንሰርነት የተሳተፉበት ከፍተኛው ፎረም በአዲስ አበባ መካሄዱን ቤንች ኤቨንትስ አስታውቋል፡፡ በመጪው ፎረም በስፖንሰርነት ለመሳተፍ ከወዲሁ ከተመዘገቡት መካከል ሰንሻይን ኮንስትራክሽን ግንባር ቀደም ሆኗል፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ብራንድ ያላቸው ሆቴሎች ቁጥር ሦስት ብቻ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ውስጥ አገሪቱ ይኖራታል ተብሎ የሚጠበቀው ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን የሚያሟሉ ብራንድ ሆቴሎች በከፍተኛ መጠን እንደሚጨምር ትንበያዎች ይጠቁማሉ፡፡ በአገሪቱ ያሉ ጠቅላላ ባለኮከብ ሆቴሎች ቁጥር 120 ሲሆን፣ ያሏቸው የመኝታ ክፍሎች ብዛትም ከአንድ ሺሕ በታች ሆኖ ይገኛል፡፡ ከዚህ ባሻገር የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አገሪቱን ባለኮከብ ሆቴሎች የደረጃ ምደባ ለማውጣት ከዓለም የቱሪዝም ድርጅት ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት ከወራት በኋላ ሆቴሎች አዲስ የኮከብ ደረጃ ይወጣላቸዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ መዘገባችን ይታወሳል፡፡