Saturday, June 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ጃፓኖች በፈጣኑ ባቡር የሚቋደሱት የጅማው የተፈጥሮ ቡና

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የጃፓኑ ዩሲሲ ሆልዲንግስ ኩባንያ ከሚንቀሳቀስባቸው የቢዝነስ መስኮች አንዱ የቡና ንግድ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ የይርጋጨፌ ቡናን ሲገዛ ይታወቃል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ወደ ተፈጥሮ ቡና ፊቱን ለማዞር ፍላጎት አሳይቷል፡፡ በዚህም በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ውስጥ ከሚገኙት ጥብቅ ደኖች ውስጥ በሻቤ ወረዳ የሚገኙትንና በለጠና ጌራ በተባሉ አካባቢዎች ውስጥ ያሉትን ጫካዎች ምርጫው አድርጓል፡፡ የበለጠ ጥብቅ ደን በአካባቢው በአንድ ወቅት ታዋቂ ከነበረው ሽፍታ ስያሜውን እንዳገኘ የአካባቢው ሰዎች ይተርካሉ፡፡ ከአራት ዓመት በፊት ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ግንኙነት የመሠረተው ዩሲሲ ኩባንያ፣ የአካባቢው ጥብቅ ደን ሳይመነጠርና ተፈጥሯዊ ይዘቱን ሳይለቅ የቡና ምንጭ ሆኖ እንዲቀጥል በማሰብ፣ ማዳበርያ ያልነካው፣ ከሰው ንክኪ የፀዳ የጫካ ቡና እየገዛ ወደ ጃፓን መውሰድ ጀምሯል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከጃፓን የመጡት ናዖሚ ናኪሐራ የዩሲሲ ኩባንያ የቡና አማካሪ ከመሆናቸውም ባሻገር የተመሰከረላቸው ቡና ቀማሽ ሲሆኑ፣ የመጡበት ዓላማም ወደ ጃፓን የሚላከው የጫካ ቡና ጥራት ላይ ለመምከርና የጥራት ደረጃውንም ለመመልከት ነበር፡፡ የበለጠ ጌራ የጫካ ቡና ብቸኛው የጫካ ቡና ከመሆኑም በላይ፣ የአሜሪካው ግሪን አሊያንስ የተባለ ኩባንያ ለጫካ የተፈጥሮ ቡና ማረጋገጫ መስጠት የጀመረው ከ1995 ዓ.ም. ጀምሮ በጃፓን ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) ሲሆን፣ ለአምስት ዓመት የቆየ የቡና ጥራት ማረጋገጫና የኦዲት ሥራ ሲሠራም አብሮ ቀጥሎ ነበር፡፡ በ2000 ዓ.ም. ጀምሮ የጫካ ቡና ጥራት ማረጋገጫ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ በጃይካ ድጋፍ የሚደረግለትና አሳታፊ የጫካ ቡና ጥበቃና ማስፋፊያ ፕሮጀክት በኦሮሚያ ክልል የደንና የዱር እንስሳት ልማት ኢንተርፕራይዝ ባለቤትነት ሲተገበር ቆይቷል፡፡ ከአምና ጀምሮም ለመጪው አምስት ዓመት ተኩል ፕሮጀክቱ ተራዝሞ እየተተገበረ ይገኛል፡፡ የጃፓን ኩባንያዎች በጥራት ረገድ ዕውቅና ከሚሰጧቸው የጥራት ተቋማት አንዱ የሆነውና በደን ጥበቃና ክብካቤ ላይ ትኩረት የሚያደርገው ግሪን ፎረስት አሊያንስ ተቋም የሚሰጠውን ማረጋገጫ ጃፓኖቹ ይቀበሉታል፡፡ ሁለተኛው የጃይካ ድጋፍ በዋናነት በጫካ ቡና ግብይት ላይ ያተኩራል ተብሏል፡፡ በመሆኑም ዩሲሲ ኩባንያ ከጌራ ወረዳና ከበለጠ ጫካ በርካታ መጠን ያለው ቡና ለመግዛት ፍላጎት ከማሳየት ባሻገር በጥራት አመራረት ላይ ሥልጠና ይሰጣል፡፡ ናኪሐራ እንደሚገልጹት ኩባንያቸው ከሚገዛው ቡና ባሻገር ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ሲል የጫካ ቡና የመግዛት ፍላጎት አለው፡፡ ከ1998 ዓ.ም. ጀምሮ ከበለጠ ጌራ የጫካ ቡና ሲገዛ መቆየቱ የተገለጸው ዩሲሲ ኩባንያ፣ በሚቀርብለት ቡና ጥራት ደስተኛ አለመሆኑን ናኪሐራ ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም ከአራት ዓመት በፊት ናኪሐራን ወደ ኢትዮጵያ እየተመላለሱ የቡናውን የጥራት ደረጃ በመመዘንና የሚሻሻለውን አሠራር እንዲስተካከል በማድረግ ተግባር ላይ ተጠምደው ይገኛሉ፡፡ ካለፈው ዓርብ ጀምሮ በጅማ ለሁለት ቀናት በተካሄደ ሥነ ሥርዓትም ከ30 በላይ የቡና ዓይነቶችን ከአገር ውስጥ ቡና ቀማሽ ባለሙያዎች ጋር በመሆን ደረጃ ሰጥተዋል፡፡ የቡናው የጥራት ደረጃ ብቻም ሳይሆን የሚመረተው ወይም ከጫካ የሚለቀመው መጠንም እንዲሻሻል ኩባንያቸው ፍላጎቱ መሆኑን ናኪሐራ ገልጸዋል፡፡ ይሁንና ኩባንያው በዓመት አንድ ወይም ሁለት ኮንቴይነር ወይም ከ15 እስከ 30 ቶን የሚገመት የጫካ ቡና በመግዛት ላይ ይገኛል፡፡ ይህንን መጠን መግዛቱ በቂ ባይሆንም ቡናውን ለሚያመርቱት ገበሬዎች ደን ሳይቆርጡና መሬት ሳይመነጥሩ በመኖራቸው፣ የኬሚካልና የሰው ንክኪ ሳይኖረው የሚቀርብለት ቡና በመሆኑ ከመደበኛው ቡና ይልቅ ጥሩ ዋጋ እንደሚከፍል ይገልጻል፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት ሲገዛ የቆየው ቡና ላይ የሚታየው የጥራት ችግር እየተሻሻለ በመምጣቱ የሚገዛው ቡናም በየዓመቱ እስከ 15 ከመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ከገበያ ዋጋ በኪሎ እስከ ሦስት ብር ጭማሪ ያለው ገንዘብ በመክፈል ቡናውን እንደሚገዛ ናኪሐራ ይናገራሉ፡፡ አንዳንድ የበለጠ ጌራ አካባቢ ገበሬዎች ግን ቅሬታ አላቸው፡፡ የሚከፈላቸው ገንዘብ ያን ያህል ከገበያ ዋጋ ለውጥ እንደሌለው በመግለጽ ቅር መሰኘታቸውን ሪፖርተር ለመረዳት ችሏል፡፡ የኦሮሚያ ደንና ዱር እንስሳት ልማት ኤጀንሲ ምክትል ኃላፊ አቶ መሐመድ ሰዒድ ለጋዜጠኞች እንዳብራሩት፣ በአካባቢው ያሉ ገበሬዎች ደን ሳይነኩ ከጫካ ለቅመው ለሚያቀርቡት ቡና ሁለት ጊዜ ክፍያ ይፈጸምላቸዋል፡፡ የመጀመሪያው ክፍያ ቡናውን ለኤጀንሲው ሲያቀርቡ የሚፈጸምላቸው ነው፡፡ ይህም ቢሆን ከገበያ ዋጋ በላይ መሆኑን አቶ መሐመድ ተናግረዋል፡፡ ቀጥሎም ቡናው ለጃፓን ገበያ ቀርቦ ከሚገኘው ገቢ እስከ 70 ከመቶው መልሶ ለገበሬው እንደሚከፋፈል አስታውቀዋል፡፡ በዚህም እስካሁን ከ300 ሺሕ ኪሎ ግራም በላይ ተሽጦ ከተገኘው ውስጥ 2.8 ሚሊዮን ብር ለገበሬው ተከፋፍሏል ብለዋል፡፡ ገበሬዎች ግን ቡናው ለውጭ ገበያ ቀርቦና ተሸጦ የሚደርሳቸው መጠን በሳንቲም ቤት የሚቆጠር እንደሆነና እሱም ቢሆን ዘግይቶ እንደሚደርሳቸው ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡ ይህንን የማይቀበሉት ደግሞ አባቢያ አባገሮ ናቸው፡፡ 601 አባላት ላሉት ናኖ ሰባቃ የገበሬዎች የኅብረት ሥራ ማኅበር ሊቀመንበር ናቸው፡፡ አባቢያ እንደሚሉት ከሆነ በመጀመሪያው ዙር ክፍያ ብቻ በአማካይ እያንዳንዱ ገበሬ ላቀረበው ቡና ከገበያ ዋጋ በላይ ሁለት ብር ያገኛል፡፡ ወደ ጃፓን ከሚላከው ቡና እንደየድርሻው ከ450 እስከ 12,500 ብር በነፍስ ወከፍ እንደሚደርሰው ይገልጻሉ፡፡ ዝቅተኛ ይዞታ ያላቸው ገበሬዎችና ቤተሰቦቻቸው ደግሞ ማኅበሩ በሚያከናውናቸው ልዩ ልዩ ሥራዎች ላይ ቅድሚያ በማግኘት እየተቀጠሩ ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡ ሌላኛው አንገብጋቢ የገበሬዎች ጥያቄ ደግሞ የቤተሰብ መስፋፋትና የመሬት ይዞታ ነው፡፡ በደን ውስጥ በሚገኝ ይዞታ ላይ ምንም ዓይነት ተጨማሪ እርሻም ሆነ ምንጣሮ ወይም የደን ቆረጣ ማድረግ አይፈቀድም፡፡ አቶ መሐመድ እንደሚገልጹት፣ ማንኛውም ሰው በጥብቅ ደን ውስጥ እንዲኖር አይፈቀድለትም፡፡ ይህ በአዋጅ የተደነገገ ቢሆንም በተጨባጭ ግን የአካባቢው ሕዝብ በደን ውስጥ ኑሮውን መሥርቶ ሲኖር አያሌ ዘመናትን አስቆጥሯል፡፡ በመሆኑም ደኑን ባለበት የማቆያው ዘዴ፣ ደኑን ሳይነኩ አማራጭ የኢኮኖሚ መፍትሔዎችን መፈለግ ነበር፡፡ በዚህም አሳታፊ የደን አስተዳደር በሚለው ፕሮጀክት አማካይነት ገበሬዎች ደን ነክ ባልሆኑ የእርሻ ተግባራት ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ ተጀመረ፡፡ ከመፍትሔዎቹ አንዱም የልዩ ጣዕም የተፈጥሮ ቡና ነው፡፡ ቅመማቅመሞችና በጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ ከማልማት ባሻገር፣ ገበሬዎች ራሳቸው የዛፍ ችግኞችን እንዲተክሉ በማድረግ፣ ተንከባክበው በማሳደግ፣ ያረጁ ዛፎችንም በአዲሶች በመተካት እንዲጠቀሙ ማስቻል የሚሉ አማራጮች ቀርበዋል፡፡ ገበሬዎች ግን ራሳቸውን ለማኖር እንደሚፈልጉት ባይበቃቸውም የደረሱ፣ ተተኪ ልጆቻቸውን የሚያሰፍሩበት ተጨማሪ ቦታ ይፈልጋሉ፡፡ መንግሥት ከደን ይዞታችን ያስወጣናል ብለው በሰቀቀን ከመኖር ግን ነፃ ወጥተዋል፡፡ አባቢያና መሰሎቻቸው ከወደ ጃፓን አዲስ ተስፋ መምጣቱን በሩቁ እየተመለከቱ ይጠባበቃሉ፡፡ ይኸውም የበለጠ ጌራ የጫካ ቡና በሰዓት ከ320 ኪሎ ሜትር በላይ በሚወነጨፈው የጃፓን ባቡር ውስጥ ለሚሳፈሩ ተጓዦች ቡናቸው እየተዋወቀ እንደሚገኝ ሰምተዋል፡፡ ዩሲሲ ኩባንያ ከጃፓን ሬልዌይ ኩባንያ ጋር በመተባበር በዓመት አንድ ጊዜ ለአንድ ወር የሚቆይ የቡና ሽያጭ በባቡር ውስጥ እያካሄደ ይገኛል፡፡ ዘንድሮው በመጪው ወር የጅማውን የበለጠ ጌራ የጫካ ቡና ለመሸጥ ቀን ቆጥሯል፡፡ ይህ ቀስ በቀስ እየተስፋፋ ሲመጣ እንደ ይርጋጨፌ፣ ሐረርና ሲዳማ ቡናዎች ሁሉ፣ የበለጠ ጌራ ቡናም ዓለም አቀፍ ብራንድ አግኝቶ እንዲሸጥ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ ናኪሐራ አስታውቀዋል፡፡ ይህ እስኪሆን ግን በጅማ የበለጠ ጌራ ጫካ ቡና አምራቾች፣ ደኑን እየጠበቁ ቡናቸውን በብዛትና በጥራት እንዲያመርቱ ምክርና ሥልጠና እያገኙ ይቀጥላሉ፡፡ የአባቢያና ሌሎች 67 የኅብረት ሥራ ማኅበራት በማር ምርቶቻቸው ዓለም አቀፍ የዕውቅና ማረጋገጫ ሠርቲፊኬት ለማግኘት ዝግጅት መጀመራቸውንም አባቢያ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ጃፓኖቹ ቀጥለዋል፡፡ ከጅማ ከተማ በ50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኙት የበለጠ ጫካና ጌራ ወረዳ ባሻገር ከአዲስ አበባ ከ430 ኪሎ ሜትር በላይ በምትርቀው፣ በከፋ ዞኗ መናገሻ ቦንጋም የሚንቀሳቀሱባቸው የትብብር መስኮችን እየተገበሩ ነው፡፡ በከፋዎች ምድር ከግብርና ባሻገር የተሳተፉባቸው መስኮች አሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች