Monday, December 4, 2023

መኢአድና አንድነት ከምርጫ ቦርድ ጋር የገቡበት ውዝግብ ወዴት እያመራ ነው?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

አምስተኛው ጠቅላላ ምርጫ የፊታችን ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡ በዚህ ፕሮግራም መሠረትም የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ እንቅስቃሴ ገብተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በቦርዱ በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ካለፈው ጥር 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ የመራጮች ምዝገባ በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ቦርዱ ይፋ ካደረገውና እየተገበረው ካለው የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ በተጨማሪ፣ ሁለት ፓርቲዎችን የውስጥ ችግራችሁን ባለመፍታታችሁ በእናንተ ጉዳይ ውሳኔ መስጠት ቸግሮኛል በማለት ሲከስ፣ ክሱ የሚቀርብባቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ ምርጫ ቦርድ ይህን የማለት የሕግም የሞራልም መሠረት የለውም በማለት ይከራከራሉ፡፡ በእነዚህ ክርክሮች መሀል ቦርዱ ታኅሳስ 10 ቀን 2007 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ የውስጥ ጉዳያቸውን በአስቸኳይ እንዲፈቱና ለቦርዱ ሪፖርት እንዲያቀርቡ የአንድ ሳምንት ጊዜ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም፣ ፓርቲዎቹም ውሳኔውን ክፉኛ በመተቸት ቦርዱ አለ የሚለው ልዩነት ፓርቲዎቹ በጠሩት ጠቅላላ ጉባዔ አማካይነት የተፈታ ነው ሲሉ ምላሽ መስጠታቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ከዚህ በመቀጠልም በሚኒስትር ማዕረግ የቦርዱ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና ታኅሳስ 28 ቀን 2007 ዓ.ም. ሰጥተውት በነበረ መግለጫ ለፓርቲዎቹ እነዚህ ጉዳዮች እስከ ጥር 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ ተፈትተው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥተው ነበር፡፡ በዚህ ጊዜም የቦርዱ ውሳኔ የመጨረሻ ይመስል ነበር፡፡ ይህን ትዕዛዝ ተከትሎም ሁለቱ የውስጥ አመራራችሁን አስተካክሉና ጉዳያችሁን በተገቢው መንገድ አክናውኑ የተባሉት ፓርቲዎች አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) እና የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ባለፈው እሑድ ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. በየጽሕፈት ቤቶቻቸው ጠቅላላ ጉባዔ ለማድረግ በመወሰናቸው ጠቅላላ ጉባዔያቸውን አክናውነዋል፡፡ ሁለቱም ፓርቲዎች ባካሄዱት ጠቅላላ ጉባዔ ፓርቲውን በመምራት ላይ ያሉትን ፕሬዚዳንቶች በድጋሚ መርጠዋል፡፡ በዚህም መሠረት አንድነት አቶ በላይ ፈቃዱን በፕሬዚዳንትነት በድጋሚ ሲመርጥ፣ መኢአድም አቶ ማሙሸት አማረን እንዲሁ በፕሬዚዳንትነት መርጧል፡፡ ምንም እንኳን ሁለቱም ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባዔ በማካሄድ የፕሬዚዳንት ምርጫቸውን ቢያከናውኑም፣ በአንድነት ፓርቲ ውስጥ ልዩነት አለን የሚሉ ግለሰቦችም በዚሁ ዕለት ሌላ ጠቅላላ ጉባዔ በመጥራት እንዲሁ ሌላ ፕሬዚዳንት መርጠዋል፡፡ ይህ ደግሞ ምርጫ ቦርድ ጥር 5 ቀን 2007 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ ፓርቲዎቹ እንዲያርሙ የተሰጣቸው ትዕዛዝ ተፈጻሚ አይደለም በማለት፣ አሁንም ፓርቲዎቹ በውስጣቸው የተፈጠረውን ልዩነት እንዲፈቱና ወደ ምርጫው እንዲገቡ የሁለት ሳምንት ጊዜ መስጠቱን የቦርዱ ሰብሳቢ አስታውቀዋል፡፡ የቦርዱና የፓርቲዎቹ ልዩነት አንድነት የፓርቲው አመራሮችን ምርጫ በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ 572/2000 አንቀጽ 8(2) ረ እና ከፓርቲው ደንብ አንቀጽ 13(1) መሠረት ፕሬዚዳንቱ በጠቅላላ ጉባዔው ማከናወን ሲገባው፣ ከሕግ አግባብ ውጪ በብሔራዊ ምክር ቤት እንዲመረጥ አድርጓል የሚለው የመጀመሪያው መታረም ያለበት ነጥብ እንደሆነ ምርጫ ቦርድ ያሳስባል፡፡ የአንድነት አመራሮች ግን በተደጋጋሚ ይህን ጉዳይ በሕጉ መሠረት መከናወኑን፣ ጠቅላላ ጉባዔው በብሔራዊ ምክር ቤት አማካይነት እንዲካሄድ የተደረገው አዲስ ፕሬዚዳንት ለመምረጥ በመሆኑ ሕጋዊ ነው በማለት ሒደቱን ማፅደቁን ይገልጻሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አሁን ‹‹መርህ ተጥሷል›› በማለት የሚከራከሩት ወገኖች የፓርቲውን ህልውና አደጋ ላይ ለመጣል የሚንቀሳቀሱና ሌላ ተልዕኮ ያነገቡ ናቸው በማለት ይወቅሳሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ምርጫ ቦርድ በፓርቲው የተካሄደውን አዲስ ፕሬዚዳንት ምርጫ እንዲያፀድቅ የሚጠይቁ ሲሆን፣ ይህ ዓይነት ውንጀላም ለግንቦቱ ምርጫ በሰፊው ለመሥራትና ለመንቀሳቀስ በማቀዳቸውና አቅም በመፍጠራቸው የተሰነዘረ በትር ነው በማለት አመራሮቹ ይተቻሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የውስጥ ችግሮቻቸሁን ፍቱ የሚለው ፖለቲካዊ ውሳኔ ነው በማለት ምርጫ ቦርድን የሚተቹ ሲሆን፣ የፓርቲው ተጠባባቂ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አስራት አብርሃ ታኅሳስ 28 ቀን 2007 የተላለፈው ውሳኔ፣ ‹‹ፖለቲካዊ ውሳኔ ነው ብለን የምናምነው ሥርዓቱ በምርጫ ቦርድ በኩል እየታገለን ነው፤›› በማለት ለሪፖርተር ምላሽ መስጠታቸው የሚታወስ ነው፡፡ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ በበኩላቸው ጥር 5 ቀን 2007 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ ‹‹ቦርዱ ፓርቲዎች ራሰቸው ላወጡት ሕግ ተገዢ መሆናቸውን ማረጋገጥና መከታተል ሥራው በመሆኑ፣ በፓርቲ አመራሮች መካከል ልዩነት ተፈጥሮ የፓርቲው ደንቦች ሲጣሱ ዝም ብሎ አይመለከትም፤›› በማለት የቦርዱ ውሳኔ ሕግና ሕግን ብቻ መሠረት ያደረገ እንደሆነ ይከራከራሉ፡፡ መኢአድን በተመለከተ ቦርዱ ተጥሰዋል ካላቸው ነጥቦች መካከል ደግሞ፣ ‹‹የፓርቲው ፕሬዚዳንትና ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት በ2003 ዓ.ም. ከፓርቲው አባልነት የተሰረዙ፣ የአባልነት መዋጮ ሲያዋጡ ያልነበሩና ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንቱ የማዕከላዊ ምክር ቤት አባል ያልነበሩ በመሆናቸው ከፓርቲው ደንብ አንቀጽ 7.4፣ 4.2.2 ውጪ በመሆኑ ሕገወጥ ሆኗል፤›› የሚለው ይጠቀሳል፡፡ ለዚህ ጥያቄ ለሪፖርተር ምላሽ የሰጡት የፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ ማሙሸት አማረ በበኩላቸው፣ ባለፈው እሑድ ጠቅላላ ጉባዔ መካሄዱን አስታውሰው ጠቅላላ ጉባዔው ከተወያየባቸው ነጥቦች መካከልም ይኼው የቦርዱ ትዕዛዝ እንደነበረ አብራርተዋል፡፡ ማብራሪያቸውን የቀጠሉት አቶ ማሙሸት ምርጫ ቦርድ እሑድ ዕለት ባካሄዱት ጠቅላላ ጉባዔ ባለመገኘቱ ቅሬታቸውን ገልጸው፣ ‹‹ቦርዱን በጠቅላላ ጉባዔው እንዲገኝ በደብዳቤ ያሳወቅን ሲሆን፣ ቦርዱም እንደሚገኝ ገልጻልን ነበር፤›› ካሉ በኋላ ቦርዱ በዕለቱ አለመገኘቱን ተችተዋል፡፡ በዚህም መሠረት ‹‹ቦርዱ በራሱ ጊዜ አልተገኘም፡፡ ካልተገኘ ደግሞ የጠቅላላ ጉባዔውን ውሳኔ ተቀብሏል ማለት ነው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡ ማክሰኞ ዕለት መግለጫ የሰጡት የቦርዱ ሰብሳቢ ግን ልዩነት ፈጥረዋል የተባሉት ግለሰቦች በየግል ለቦርዱ ደብዳቤ ማስገባታቸው ሌላ ችግር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የአባልነት መዋጮን በተመለከተአቶ ማሙሸት፣ ‹‹ቦርዱ እኛን ከሚከስበት እንደ ምክንያት ብሎ ከሚያቀርባቸው የመኢአድ አሁን የተመረጡት አመራር አባላት የአባልነት መዋጮ ያልከፈሉ ናቸው የሚል ነው፡፡ እንግዲህ በመኢአድ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት የአባልነት መዋጮ የሚከፈልባቸው መሥፈርቶች አሉ፡፡ አንድ ሰው አባል የሚሆነው የአባልነት መዋጮ ሲከፍል ነው ይላል፡፡ የአባልነት መዋጮውን ከሦስት ወራት በላይ ያለ በቂ ምክንያት ያልከፈለ አባል ይሰረዛል ይላል፡፡ እኛ ግን የአባልነት ክፍያ ያልከፈልነው በበቂ ምክንያት ነው፡፡ ምክንያቱም እዚህ ቤት የነበሩ ሰዎች እኛን በፍርድ ቤት ከሰውን ዕግድ ተጥሎብን ስለነበር ነው፡፡ ወደ መኢአድ ጽሕፈት ቤትም እንዳንንቀሳቀስ በፓርቲው እንቅስቃሴ ላይ ሁሉ እንዳንሳተፍ ውሳኔ ተሰጥቶብን ስለነበር ጉዳዩ በፍርድ ቤት ተይዞ በእንቅስቃሴ ላይ ነው የነበረው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ስለዚህ የአባልነት ክፍያ ለመክፈል ብንሞክርም ተቀባዩም ወንጀለኛ ስለሚሆንና ሁለተኛ ደግሞ እኛም እንኳንስ ለመክፈል ለመንቀሳቀስም ታግደን የነበረ በመሆኑ፣ የአባልነት ክፍያ ልንከፍል አልቻልንም፤›› በማለት ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡ ‹‹አቶ አበባው መሀሪ የመኢአድ ፕሬዚዳንት የሚል የተፈረመበትና የመኢአድ ማኅተም ያረፈበት ደብዳቤ ሸኝነት ጥቅምት 29 ቀን 2007 ዓ.ም. መኢአድ ያካሄደው ልዩ ጠቅላላ ጉባዔ ሪፖርት በሚል 17 ገጽ ሪፖርት አቅርበዋል፤›› የሚል ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪም ‹‹አቶ ማሙሸት አማረ የመኢአድ ሪፖርት በሚል ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. የመኢአድ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ እንደተካሄደ በመግለጽ በቦርዱ ዕውቅና የሌለው አዲስ ማኅተም የቀረበ ቢሆንም፣ ሰነዱንም ሆነ ማኅተሙን ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ ላቀረቡት ግለሰቦች ተመልሶላቸዋል፤›› በማለት ቦርዱ ተወካይ ለመላክ ያልቻለበትን ምክንያት ገልጸዋል፡፡ ሁለቱም ወገኖች ትክክለኛው መንገድ የእኔ ነው፣ የተጣሰ የሕግ አሠራር የለም፣ ምርጫ የተከናወነው በፓርቲው ሕገ ደንብ መሠረት ነው የሚሉ በመሆናቸው፣ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ መጀመሪያ የውስጥ ችግራችሁን ፍቱ በማለት ተጣሱ የሚላቸውን የፓርቲዎቹን ሕገ ደንቦች እየጠቀሰ ወደ ትክክለኛው መንገድ ተመለሱ እያለ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ምርጫ ቦርድ ጥቅምት 5 ቀን 2007 ዓ.ም. ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ በሁለቱም ፓርቲዎች ላይ የመጨረሻ ያለውን ውሳኔ ለመወሰን የሁለት ሳምንት ጊዜ ገደብ ሰጥቷል፡፡ ይህ የተሰጠው የጊዜ ገደብ ታኅሳስ 10 እና 28 ቀን 2007 ዓ.ም. ከሰጠው ትዕዛዝ የመጨረሻው ማስጠንቀቂያ እንደሆነ የቦርዱ ሰብሳቢ በሒልተን ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ገልጸዋል፡፡ ‹‹አንድነትና መኢአድን በተመለከተ ቦርዱ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ችግሩ የፓርቲው አመራሮች የፈጠሩት መሆኑን በመረዳት፣ የፓርቲዎቹ ህልውና ግን በተቻለ መጠን መቀጠል ስላለበት ከፓርቲዎቹ በስተጀርባ ያለውን ሕዝብ በመመልከት፣ አሁንም ጉዳዩን በሆደ ሰፊነት ለመመልከት በመጨረሻ ጊዜ የሁለት ሳምንት ጊዜ ሰጥቷል፤›› በማለት የቦርዱ ሰብሳቢ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ‹‹በዚህ ሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ አመራሮቹ ፓርቲዎቹ የገቡበትን ችግር በማጤን የውስጥ ጉዳዮቻቸውን አንድ ላይ በመሆን በጠቅላላ ጉባዔያቸው በማስወሰን፣ የጠቅላላ ጉባዔውን ሪፖርት ለቦርዱ በማቅረብ ወደ ምርጫው እንቅስቃሴ እንዲገቡ አዟል፤›› በማለት ፕሮፌሰር መርጋ መግለጫቸውን አጠቃለዋል፡፡ ቦርዱ ባወጣው የጠቅላላ ምርጫ ጊዜ ሰሌዳ መሠረት የፖለቲካ ፓርቲ ዕጩዎች ምዝገባ በየምርጫ ክልሉ ጽሕፈት ቤት ጥር 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ከመጠናቀቁ ጋር በተያያዘ፣ የተወሰነው ጊዜ ፓርቲዎቹን አይጎዳም ወይ የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው የነበሩት የቦርዱ ሰብሳቢ፣ ‹‹ችግሮቻቸውን ፈተውና አስተካክለው እንዲመጡ ነው ቦርዱ እያለ ያለው፡፡ ጊዜውም እስከ ጥር 27 ይቀጥላል፡፡ ተስተካክለው ሲመጡ ያኔ የቦርዱ ውሳኔ ነው የሚሆነው፤›› በማለት ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡ መጪው ጊዜ ቦርዱ ማክሰኞ ዕለት የሰጠው የጊዜ ገደብ የመጨረሻ ከመሆኑ አንፃር የመጨረሻው ዕርምጃ ምን ሊሆን ይችላል የሚል ጥያቄ ከሪፖርተር ቀርቦ የነበረ ሲሆን የቦርዱ ሰብሳቢ፣ ‹‹ቀጣዩ ምን ይሆናል የሚለው የቦርዱ ውሳኔ ነው የሚሆነው፡፡ ይህ ደግሞ ወደፊት የሚታይ ነው፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ አቶ ማሙሸት በበኩላቸው፣ ‹‹ቀጣዩ ምን ሊሆን እንደሚችል እኛ የምናውቀው ነገር የለም፡፡ እኛ መጀመሪያም የውስጥ ችግራችሁን ፍቱ የሚል ደብዳቤ ሲጻፍልን መኢአድ ቦርዱ ባለበት የውስጥ ችግሩን ፈቷል፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -