Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናፓርላማው የሰብዓዊ መብትና የእንባ ጠባቂ ኮሚሽነሮችን የሥራ ዘመን በውሳኔ ሐሳብ አራዘመ

ፓርላማው የሰብዓዊ መብትና የእንባ ጠባቂ ኮሚሽነሮችን የሥራ ዘመን በውሳኔ ሐሳብ አራዘመ

ቀን:

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ዘመናቸው ጥር 5 ቀን 2007 ዓ.ም. የሚያበቃውን የሰብዓዊ መብትና የእንባ ጠባቂ ኮሚሽነሮችን የሥራ ዘመን እስከ ሰኔ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ አራዘመ፡፡ የሁለቱም ተቋማት የሥራ ዘመን የሚጠናቀቀው ጥር 5 ቀን 2007 ዓ.ም. ቢሆንም፣ በዚሁ ዕለት የተሰበሰበው ፓርላማው የኮሚሽነሮቹን የሥራ ዘመን አራዝሟል፡፡ ‹‹ኮሚሽኖቹ ከዋና ኮሚሽነሩ በተጨማሪ ሌሎች ኮሚሽነሮችም በተመሳሳይ መልኩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚሾሙና የሥራ ዘመናቸውም ለአምስት ዓመት እንዲቆይ በሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ አንቀጽ 10 እና አንቀጽ 14(1)፣ እንዲሁም በእንባ ጠባቂ ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ አንቀጽ 10 እና አንቀጽ 14(1) በመደንገጉ፣ ሁሉም የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች የሥራ ዘመናቸው የሚጀመርበትና የሚጠናቀቅበት ጊዜ አንድ ዓይነት መሆኑ ለኮሚሽኑ ውጤታማ የሥራ አፈጻጸም አስፈላጊነት እንደሚኖረው በመታመኑ ነው፤›› በማለት በአፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ያስረዳል፡፡ በተጨማሪም የሁለቱም ተቋማት ዋና ኮሚሽነሮች የጀመሯቸውን ሥራዎች በማጠናቀቅና የተሟላ ዝግጅት በማድረግ ለቀጣዩ ለማስረከብ እንዲችሉ በቂ ጊዜ የሚያስፈልግ በመሆኑ፣ የሥራ ዘመናቸው እስከ ሰኔ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. እንዲራዘም በፓርላማው የአሠራርና የአባላት የሥነ ምግባር ደንብ ቁጥር 3/1998 አንቀጽ 49(4) መሠረት የውሳኔ ሐሳቦቹ እንዲፀድቁ አፈ ጉባዔው ጠይቀዋል፡፡ ይሁን እንጂ አንድ የምክር ቤቱ አባል በአዋጅ የተገደበን የሥራ ዘመን በውሳኔ ሐሳብ እንዴት ማሻሻል እንደሚቻል ግልጽ እንዳልሆነላቸው በማንሳት ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡ የፓርላማው የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ ቁጥር 3/1998 አንቀጽ 49 መሠረት ፓርላማው አዲስ ሕግ የማውጣት፣ ነባር ሕግ የማሻሻልና የመሻር፣ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን የማፅደቅና የውሳኔ ሐሳብ የማሳለፍ ኃላፊነቶችን እንደሚሰጥ ያብራሩት ጠያቂው፣ ‹‹የውሳኔ ሐሳብ ማሳለፍ ከሥራ ዘመን ማራዘም ጋር እንዴት እንደተገናኙ ግልጽ አይደለም፤›› ሲሉ ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡ የምክር ቤቱ የሕግ፣ የፍትሕና የአስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢና በሚኒስቴር ዴኤታ ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፍትሕና የአስተዳደር ጉዳዮች አማካሪ አቶ አስመላሽ ወልደሥላሴ፣ በአፈ ጉባዔው የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ እንደሚደግፉ ከገለጹ በኋላ ለተነሱት ጥያቄዎችም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ የሥራ ዘመናቸው በጥር እና በሰኔ የሚያልቀውን የሁለቱ ተቋማት ዋና ኮሚሽነሮችና ሌሎች ምክትል ኮሚሽነሮችና ኮሚሽነሮች የሥራ ዘመን የተጣጣመና በተመሳሳይ ወቅት እንዲሆን ለማድረግ ከዚህ ቀደም የተሞከረው ጥረት አለመሳካቱን ገልጸው፣ ወጥነት ለማምጣት ስለተፈለገ በተጠቀሰው የውሳኔ ሐሳብ መሠረት ማስተካከሉ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹ያለው አማራጭ ሰኔ አካባቢ ጊዜያቸው የሚጠናቀቅ ተሿሚዎችን አሁን ጥር ላይ ከሚያልቀው ዋና ኮሚሽነሮች ጋር ማድረግ፣ አልያም የዋና ኮሚሽነሮቹ የሥራ ዘመን ሰኔ አካባቢ ከሚያበቃው ተሿሚዎች ጋር እንዲጠናቀቅ ማድረግ ነው፤›› ብለዋል፡፡ የውሳኔ ሐሳብን በተመለከተ ባቀረቡት ማብራሪያ ደግሞ ሕግና የውሳኔ ሐሳብ አቻ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡ ‹‹በእኛ ሁኔታ የውሳኔ ሐሳብ ማለት የሕግ አካል ነው፣ ስንሠራበት የነበረ ነው›› በማለት ለአብነት በ1998 ዓ.ም. የአዲስ አበባ አስተዳደር ምክር ቤትን በምርጫ ያሸነፉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምክር ቤት አንገባም በማለታቸው የተፈጠረውን የሥልጣን ክፍተት፣ በባላደራ አስተዳደር መሙላት የተቻለው ፓርላማው ባሳለፈው የውሳኔ ሐሳብ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹በተግባርም የሠራንበት ስለሆነ የሕግ አካል ነው ብለን አስቀምጠናል፡፡ ዋናው ጉዳይ ዓላማው ነው መሆን ያለበት፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ለዚህ ከሰጡት ተጨማሪ ምክንያት አንዱ በተለይ የእንባ ጠባቂ ዋና ኮሚሽነሯ በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ እንባ ጠባቂ ተቋም ፕሬዚዳንት መሆናቸውንና ለዚህ ክፍተት መፍጠር የማይገባ መሆኑን ነው፡፡ የውሳኔ ሐሳቡን ያቀረቡት አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ የውሳኔ ሐሳብ ከሕግ አግባብ ውጪ አለመሆኑንና አገሪቱ አሁን እየገባችበት ካለው አገር አቀፍ ምርጫ አንፃር፣ ተቋማቱ በተረጋጋ ሁኔታ ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በዚሁ ማብራሪያም የውሳኔ ሐሳቡ በሙሉ ድምፅ ፀድቆ የዋና ኮሚሽነሮቹ የሥራ ዘመን ተራዝሟል፡፡ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ያነጋገርናቸው የሕግ ባለሙያ በውሳኔ ሐሳብ የኮሚሽነሮቹን የሥራ ዘመን ለማራዘም የቀረበው ዋነኛ ምክንያት ማለትም ዋና ኮሚሽነሮቹና ሌሎቹ ኮሚሽነሮች የሥራ ዘመንን ማጣጣም የሚለውን ‹‹ተገቢ ያልሆነ ምክንያት ነው፤›› ብለውታል፡፡ የሰጡት ማብራሪያም ‹‹ተቋማዊ የተደራጀ አሠራርን ለመፍጠርና የአዲስ ተሿሚዎችን መደናገር ለማስቀረት ወይም ‹‹ኢንስቲትዩሽናል ሜሞሪን›› ለመፍጠር ዋና ኮሚሽነሮቹና ሌሎቹ ኮሚሽነሮች የተለያየ የሥራ ዘመን ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ወይም የሥራ ዘመኑ መዛባት ተገቢ ነበር፤›› ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል የሁለቱ ተቋማት መሪዎች አሿሿም ከሌሎች የዲሞክራሲ ተቋማት በተለየ ሁኔታ ገለልተኛ እንዲሆን ተብሎ ሁሉም የኅብረተሰብ ከፍሎች በሚወከሉበት ኮሚቴ ታጭተው እንዲሾሙ የተፈጠረውን አሠራር፣ ፓርላማው በራሱ ድክመት ምክንያቶችን እየደረደረ እንዳያጠፋው ሥጋት የሚያሳድር ውሳኔ ነው ሲሉ ተችተውታል፡፡ ‹‹ይህም ማለት በፓርላማው አፈ ጉባዔ ሰብሳቢነት በሚመራው ኮሚቴ ውስጥ አባል የሚሆኑ የእምነት ተቋማት ተወካዮች፣ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች፣ የፓርላማ አባል ተወካዮችና የመሳሰሉት የሚሳተፉበት ኮሚቴ ዕጩዎችን እንዲመርጡና እንዲያሾሙ በተለየ ሁኔታ በሕግ የተደረገው፣ የተጠቀሱትን ሁለት ተቋማት ገለልተኝነትና ነፃነት ለመጠበቅ ነው፡፡ ነገር ግን ኮሚቴውና ፓርላማው ሥራቸውን በአግባቡ መሥራት ባለመቻላቸው በውሳኔ ሐሳብ ዕድሜ ማራዘም ተገቢ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ በፀደቀው የውሳኔ ሐሳብ መሠረት የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ዋና ዕንባ ጠባቂ ወ/ሮ ፎዚያ አሚንና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር አምባሳደር ጥሩነህ ዜና የሥራ ዘመን እስከ ሰኔ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ሆኗል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...