ዞሲማስ ሚካኤል የባህል ባለሙያ ነው፡፡ ባለከተራና ጥምቀቱ ጥር ወር በመጣ ቁጥር የሚሰማው ስሜት ከደስታ በላይ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ለጥምቀት በዓል ልዩ ትውስታ አለው፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ የሚሠርፅ፡፡ ከዋዜማው ከከተራ በዓል ጀምሮ ታቦታት ወደ ጃንሜዳ በሚያደርጉት ጉዞ ነፍስ ከማወቁ በፊት ጀምሮ ከወላጆቹና ከአቻዎቹ ጋር ሲያጅብ ኖሯል፡፡ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይወሰን በተለያዩ አጋጣሚዎች በጎንደርና በማይጨው፣ በላሊበላም ከሦስት ቀናት በዘለለ በዓለ ጥምቀቱን ሲያከብር ኖሯል፡፡ ዕለቱን ጥር 11 እንዲሁም በማግስቱ ጥር 12 ቀን የቃና ዘገሊላና ሚካኤል በዓላትንም ከማክበር አልተለየም፡፡ ሥዕላዊ ከሆነው ከሃይማኖታዊና መንፈሳዊ አከባበሩ በተጓዳኝ ባህላዊ ገጽታው ቀልቡን ሲገዛው እንደኖረም ያስታውሳል፡፡ ሐርሞኒካው ከቢጤዎቹ ጋር የነበረው ዳንስ የሌሎች እስክስታና ዳንኪራም አሁንም ይታወሱታል፡፡ በየዓመቱ በመላ ኢትዮጵያ የሚከበረው የጥምቀት በዓል፣ ታቦታት ከመንበራቸው ወጥተው፣ በየጥምቀተ ባሕሩ የሚከበሩ በመኾናቸው፣ ሀገሬውን ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ መስህብነትን በመጎናጸፉ፣ ቱሪስቶችን መሳቡ አልቀረም። ከአዲስ አበባ እስከ ላሊበላ፣ ከአክሱም እስከ ጎንደር በሁሉም ሥፍራዎች በዚሁ ዓይነት ደምቆ ይከበራል። የምእመናኑም ሆነ የካህናትና ዲያቆናት አለባበስ ፍፁም በሚማርክ ባህላዊ አልባሳት የተዋበ በመሆኑ ከውጭም ሆነ ከአገር ውስጥ ለሚመጡ ጎብኚዎች ሁል ጊዜ አዲስ ነው። በኦርቶዶክሳዊቷ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሚከበረው የጥምቀት በዓል፣ እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ በ30 ዓመቱ በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ባሕር የተጠመቀበትን ዕለት የሚያስታውስ ነው፡፡ ኤጲፋንያ በመባልም ይታወቃል፡፡ ጥር 10 ቀን፣ በከተራ፣ በገጠርም ሆነ በከተማ ታቦታት ከየአብያተ ክርስቲያናቱ ወደየጥምቀተ ባሕር የሚያደርጉት ጉዞና መንፈሳዊ አዳር በማግስቱ የጥምቀት ዕለት ‹‹ተጠምቀ ሰማያዊ በእደ መሬታዊ፤ ሰማያዊው በመሬታዊው እጅ ተጠመቀ››ን ይዞ የሚኖረው ያሬዳዊ ዝማሬ የበዓሉ ገጽታ ነው፡፡ ከሃይማኖታዊው ሥነ ሥርዓት በኋላ ካህኑ በሃሌታ፣ ወንዱ በሆታ፣ ሴቱ በእልልታ ታቦተ ሕጉን አጅበው፣ እንደያመጣጣቸው ወደየአጥቢያቸው ይመለሳሉ። ‹‹እዩት ወሮ ሲመለስ መድኃኔ ዓለም በፈረስ ወሮ ሲመለስ የሚካኤል አንበሳ ሎሌው ሲያገሳ። ማር ይፈሳል ጠጅ በእመቤቴ ደጅ።» እያሉ ምእመናኑ ታቦታቱን በዝማሬቸው ያጅቡታል። ታቦተ ሕጉም ቅጽር ግቢው ሲደርስ ሁሉም ምኞታቸውን በፍሡሕ ገጽ እንዲህ እያሉ ይገልጻሉ። «በሕይወት ግባ በዕልልታ የዚህ ሁሉ አለኝታ በሕይወት ግቢ እምዬ እንድበላ ፈትዬ›› ሊቃውንቱ እንደሚናገሩት፣ ዘመነ አስተርእዮ የሚባለው፣ ከጥር 11 ቀን ጀምሮ እስከ ጾመ ነነዌ ያለው ጊዜ ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ አምላክ ሰው ሆኖ በሥጋ መገለጡ፣ በዮርዳኖስ በተጠመቀ ጊዜ የአንድነትና የሦስትነት ምሥጢር መታወቁ፣ በቃና ዘገሊላ በተደረገው ሠርግ ላይ የመጀመሪያው ተዐምር በመፈጸሙ፣ አምላካዊ ኃይሉ መገለጡ፣ እየታሰበ ምስጋና ይቀርባል። ይህ ኩነት ኢትዮጵያ ብሂልን ከባህል ጋር አዛምዳ ከሌላው የክርስቲያን ዓለም በተለየ አከባበር በዓሉን ማክበሯ፣ አያሌ ቱሪስቶችን ለመሳብ አስችሏታል። ዞሲማስ የባህል ተማሪ ከመሆኑ አንፃር በዓሉን ከማክበር ውጪ በትኩረት ተመልክቶታል፡፡ ያኔ የሎሚ ውርወራው፣ የከተራው ሽልምልም ዱላ አሁን አሁን በከፊል ሎሚው ወደ ፕሪም፣ ሽልምልሙ ዱላ ወደ ረዥም ቄጠማ (ጨፌ ላይ የሚበቅል) ተለውጦ መታየቱ፣ ከባህላዊ ጭፈራው በተጓዳኝ ወጣቱ በአመዛኙ ከመንፈሳዊ ማኅበራት (ሰንበት ትምህርት ቤቶች) መዘምራን ጋር ወደ ዝማሬ ማዘንበሉንም አይቶታል፡፡ ዱሮ ከሚያውቀው በተለየ መልኩ ከሺዓመቱ (ሚሌኒየሙ) በዓል ወዲህ ወጣቶች በልዩ ልዩ መንገድ ለበዓሉ ውበትና ድምቀት ለመስጠት ያደረጉት የለውጥ ሒደት ፀጥታንና ሥርዓትን እስከማስከበር ድረስ የሔዱበት መንገድ እንዳስደተው ሁሉ፤ ይህን ክርስቲያናዊ በዓል ብሂልን ከባህል ጋር አዛምዶ ከሌላው ዓለም በተለየ መንገድ የማክበር ሒደትን የውጭ ቱሪስቶች ቀልብ በየዓመቱ እየገዛ ያለውን ከተራና ጥምቀት በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የሚደረግ ጥረት በሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጥረት ሲደረግ አለማየቱን ከተማረው የባህል ትምህርት አኳያ እያነሣ መተቸቱን ከመግለጽ አልተቆጠበም፡፡ ‹‹ከ80 በላይ ብሔረሰቦች ያቀፈችው ኢትዮጵያ በመንፈሳዊ ቅርሶች (Intangible heritages) የታደለች ሁና ከዘጠኝ ቁሳዊ ቅርሶች (tangible heritages) ውጭ ያስመዘገበችው ብቸኛው ቅርስ የመስቀል በዓል ነው፡፡ ሌሎችንስ የማታስመዘግበው ለምንድን ነው?›› በማለት ይጠይቃል፡፡ በዓለም አቀፍ የፌስቲቫሎች መድበል የአፍሪካ ኤጲፋኒያ /ጥምቀት (The African Epiphany) እየተባለ የጎንደሩ፣ የላሊበላው፣ የአዲስ አበባው… የጥምቀት አከባበር በዓለም የክብረ በዓላት (Festivals) ድርሳን ላይ በየጊዜው የሚተዋወቀው፣ ቱሪስቶችም እየመጡ የሚያደንቁት አንዳንዶችም ‹‹ጥምቀትን ለምን በቅርስነት አላስመዘገባችሁም?›› እያሉ እየጠየቁ ባሉበት የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ለከተራ ጥምቀት አከባበር ምዝገባ ትኩረት አለመስጠቱ ምነው ያሰኛል ይላል፡፡ አምና (2006 ዓ.ም.) የጥምቀት በዓል በአዲስ አበባም ሆነ በጎንደር ሲከበር የቤተክህነትም ሆነ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከፍተኛ ሹማምንት ክብረ በዓሉን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ እየሠራን ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ በተግባር ግን የሚታይ እንቅስቃሴ እንደሌለ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ሪፖርተር መሰንበቻውን ባወጣው አንድ መጣጥፉ የጥምቀት በዓልን በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ለማሰጠት እየተደረገ ያለ ጥረት እንዳለ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የቅርስና ጥናትና ምርምር ዳይሬክተሩን አቶ ደሳለኝ አበባውን አነጋግሮ ነበር፡፡ እንደ አቶ ደሳለኝ ገለጻ፣ በቅርብ ጊዜ ውስጥ በዩኔስኮ በመንፈሳዊ የዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ በጥናት ከተያዙት መካከል (የሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫና የኦሮሞገዳ ሥርዓት ከኢሬቻ ጋር ይገኙበታል) የጥምቀት በዓል ግን አልተካተተም፡፡ ለዚህ ዋነኛ ምክንያት ብለው የጠቀሱት ጥናት የሚያደርግ ባለሙያና የገንዘብ እጥረትን ነው፡፡ የይመዘገብልን ጥያቄም በይፋ ያቀረበም አለመኖሩንም ያወሳሉ፡፡ ‹‹በእርግጥ አንድ ቅርስ እንዲመዘገብ ከመጠየቁ በፊት ስለመንፈዊ ቅርስነቱ መረጋገጥ አለበት፡፡ የጥምቀት በዓልን ለማስመዝገብ እስካሁን ከአንዳንድ ግለሰቦች ውጪ ግልጽ የሆነ የተቋም ጥያቄ ያቀረበ የለም፡፡ የድርጅቱ አቅም ሲጠናከር ግን መመዝገብ ካለባቸው ቅርሶች መካከል መካተት ያለበት ነው፤›› ብለዋል፡፡ የጥምቀት በዓል እንደ መስቀል በዓል ሁሉ በዓለም ቅርስነት ለመመዝገብ የዩኔስኮን መስፈርት ለማለፍ የሚቸገር እንዳይደለ አንዳንድ ጠቋሚ ነገሮች አሉ፡፡ የሚመለከታቸው አካላት አሁንም ከዲስኩር ባለፈ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው አስተያየት እየተሰነዘረ ይገኛል፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍና ፎክሎር ክፍለ ትምህርት በቅድመ ምረቃም ሆነ በድኅረ ምረቃ ስለአዲስ አበባው፣ ስለላሊበላና ስለጎንደር የጥምቀት አከባበር የተሠሩ የመመረቂያ ድርሳኖች (ቴሲሶች) ያሉ በመኾናቸው የሚመለከታቸው አካላት በተለይም የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ለመነሻ ጥናት አጋዥ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይታመናል፡፡