የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ፣ በሥር ፍርድ ቤት የዋስትና መብት የተነፈጋቸው ያለበቂ ምክንያትና የተለወጠላቸው የሕግ ድንጋጌ ግምት ውስጥ ሳይገባ መሆኑን በመጥቀስ፣ የዋስትና መብታቸው እንዲከበር የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ወሰነ፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ሰኞ ጥቅምት 20 ቀን 2010 ዓ.ም. አቶ በቀለ ገርባ በ30 ሺሕ ብር ዋስትና ከእስር ተለቀው ጉዳያቸውን በውጪ ሆነው እንዲከታተሉ በሰጠው ውሳኔ፣ ዓቃቤ ሕግ የፀረ ሽብር አዋጁን ጠቅሶ ክስ ያቀረበበባቸው ሚያዝያ 13 ቀን 2008 ዓ.ም. እንደነበር አስታውሷል፡፡ አቶ በቀለ ክሱ ከቀረበባቸው ጊዜ ጀምሮ እንደታሰሩ ግምት የሚወሰድ በመሆኑ አንድ ዓመት ከስድስት ወራት የታሰሩ መሆናቸው ሲታይ፣ ተከላከሉ ከተባሉበት የወንጀል ሕግ አንቀጽ 257(ሀ) አኳያ ጉዳዩ መታየት እንዳለበት ገልጿል፡፡
በተቀየረው የሕግ ድንጋጌ ተከላከሉ ቢባሉ እንኳን፣ ድንጋጌው ያስቀመጠው የቅጣት መጠን በቀላል እስራት ወይም ከአሥር ዓመታት በማይበልጥ ፅኑ እስራት መሆኑን ችሎቱ በውሳኔው ገልጿል፡፡ ነገር ግን አቶ በቀለ በክርክሩ ከፈጸሙት የእስራት ጊዜ አኳያ፣ በእስር ከቆዩበት ጊዜ በታች ቅጣት ቢወሰንባቸው ሊካስ የማይችል ጉዳት ሊደርስባቸው የሚችል መሆኑን መገመት የሚቻል በመሆኑ፣ የዋስትና መብት ክልከላ መደረጉ ተገቢ አለመሆኑን አክሏል፡፡
የዋስትና መብት የክርክር ሒደቱ ተጠናቆ የመጨረሻ ውሳኔ እስከሚሰጥ ጊዜ ብቻ ጊዜያዊ አገልግሎት ከመሆን አልፎ የቅጣት ውሳኔ የመሆን አጋጣሚ እንደሚኖረው በመጠቆም፣ ይኼ ከመሠረታዊ ሕገ መንግሥታዊ መርህ መውጣት እንደሚሆንም ችሎቱ በውሳኔው አስፍሯል፡፡ በልዩ ሁኔታ የዋስትና መብት እንዲከለከል ሕጉ ታሳቢ ካደረገው ዓላማና ግብ ውጪ እንደሚሆንም ጠቁሟል፡፡
በአጠቃላይ የሥር ፍርድ ቤት የአቶ በቀለን የዋስትና መብት የከለከላቸው በበቂ መነሻና በሕጉም ያልተደገፈ፣ እንዲሁም የተለወጠው የሕግ ድንጋጌ ሊያስቀጣ የሚችለውን የቅጣት መጠን ግምት ውስጥ ያላስገባ በመሆኑ፣ ውሳኔው ተሽሮ በ30 ሺሕ ብር ዋስትና ተለቀው በውጪ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡