Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ሳማ ጎመን መስሎ ስንቱን ለበለበ?

ሰላም! ሰላም! ሰማችሁ? እትዬ ፈረንሳይ እመት አሜሪካንን ‘ለቅሶ አልደረሽኝም’ ብላ አፍንጫዋን ነፋችባት አሉ። አይገርምም! ዓለም የመንደር ፖለቲካችንን በካርቦኗ ‘ኮፒ’’ እያደረገች አስቸገረችን እኮ? እኛማ ምርጫ ይለፍ ብለን ነው እንጂ የኮፒ ራይት መብት ይከበር ብለን ሰላማዊ ሠልፍ ለመውጣት አስበን ነበር። እውነቴን እኮ ነው! ታዲያ አሜሪካም በበኩሏ “ሞት ምንጊዜም ሞት ነው ገዳዩን ይወዳል፣ ለእኛ ለእኛ ጊዜ ‘ሴኩሪቲ’ ይቀድማል” ብላ ፈረንሳይን ‘ፕሮቶኮል’ የሚባል ነገር እወቂ ማለቷን ሰማን። መቼም መልስ አያልቅባት እሷ? ስጠረጥር ፈረንሳይ ፈንታዋን፣ “የዘንድሮ ወዳጅ አወይ ማስተከዙ፣ ደግ ቀን አብሮ ነው ክፉ ቀን ከራሱ፤” ሳትል አልቀረችም። “ሀብታም በተኳረፈ እኛን ምን አገባን? ለራሳችን ልማት ላይ ነን ተዋቸው እነሱን! ይልቅ ከቀን ቀን እየከፋ የሄደውን የሽብር ጥቃት አውግዝ!” ሲለኝ የሰነበተው የባሻዬ ልጅ ነው። እናም እላችኋለሁ ዕልቂት ብዙ እያስተዛዘበን ነው። “እኔስ አንዳንዴ ብዙ ተባዙ ነው ያለን ወይስ ተናከሱ?” የሚሉኝ ደግሞ ባሻዬ ናቸው። ‘የሰው ልጅ ሐሳብ ከልጅነቱ አንስቶ ክፉ ነው’ የሚለውን ምዕራፍ እየጠቀሱ። ከሁሉ በላይ በሃይማኖት ጉያ እየተጠለለ ዓለምን ሰላም ያሳጣት የእኩዮች ተግባር ያናድዳል። አያናድድም? ባሻዬንም የሚያንገበግባቸው ከሁሉ በላይ ይኼ ነው። “ከሀብት ጥቂቶች ብቻ እያግበሰበሱት ሀብት የለንም እንጂ፣ የምድር በረከት ለሁላችን ይበቃን ነበር። ደግሞ ብለው ብለው መፅናኛችንና መጠጊያችን የሆኑትን ሃይማኖቶች በስውር ደባቸው እያነቋቆሩ ሰላም ያሳጡን?” ይሉኛል። ለስንት ነገር መፍትሔ ማፈላለጊያ ካልሆነም ሰላም ማስጠበቂ መሆን እንዳይችል የእምነትን ሰናይ ገጽታ የሚያጠፉና በስውር የሚዘውሩ የዓለም ፖለቲከኞች ባሻዬን አይመቹዋቸውም። ግን እናንተ እስከ መቼ እንዲህ የሚቆረቁረን አልጋ ላይ ይሆን የምንኖረው? አንድ ታታሪ፣ አንድ ብልህ እንባ አባሽ፣ ሁሉን አስማሚ ጥበበኛ አጥተን እንቅር? ኧረ! ኧረ! እንዲህና እንዲያ እየተወዛገብን ይኼው ሰንብቱ ብሎን መቼም አለነው። መሰንበት ደጉ በባቡር ሊያሳፍረን ቀን ግፉ ይለናል። ከምንገፋው ቀን ይልቅ የሚገፋን ቀን በዛ እንጂ። አንድ መለኛን ሰው “ማን ነው ጀግና?” ቢሏቸው ምን እንዳሉ አልሰማችሁም? አዎ! “የጊዜ እንጂ የሰው ጀግና የለውም፤” አሉ። እውነታቸውን ነው። እናም በዚህ ሥልት የምንገፋ እየገፋን፣ የምንገፋ እየተገፋን ‘አጃኢብ’ ስንል እንውላለን። አጃኢብ! በበኩሌ የትጥቅ ትግል የጀመርኩ እስኪመስለኝ ድረስ ፀሐዩ እያነደደኝ ለሥራ እዚያና እዚህ ስሯሯጥ የሕዝብ ትራንስፖርት እንደምጠቀም ታውቃላችሁ? ነው ወይስ በሕዝብ ንብረት ስለሚጫወቱ ሰዎች ‘ፕሮፋይል’ ስታገላብጡ እኔን ረስታችሁኛል? አይታወቅም ብዬ እኮ ነው። በመሆኑም ለአንድ ሥራ ስባክን (የሆነ ቀን ነው) እንደማንም ቆሜ ታክሲ እጠብቃለሁ። አቤት በመጠበቅ የፈጀነው ማገዶ! ቆሜ ስጠብቅ፣ ደማቅ ሰማያዊ አውቶብሶች እየመጡ ይሄዳሉ። ሰው ተዝናንቶ ይሳፈራል። ወዲያው ጠጋ አልኩና አንዱን “ደስ ይላል! ቢያንስ ሠራተኛው መሥሪያ ቤቱ በመደበለት መጓጓዣ ሳይንገላታ መጓጓዙ ጥሩ ነው። ጫናው ይቀንሳል፤” አልኩት። እኔን የመሰለኝ አውቶብሶቹ ለሠራተኛው የተመደቡ ማመላለሻ ሰርቪሶች ነበር። ታዲያ እሱ ግራ ገብቶት “ማለት?” አለኝ። አብራራሁለት። ለካስ ወዳጄ ‘በግዕዝ ፊደል የተጻፈ እንግሊዝኛ አንብቦ የመረዳት ችሎታው ይኼን ያህል ደካማ ከሆነ፣ ዋናውን እንግሊዝኛማ እንኳን እሱ ዘር ማንዘሩም አያነብ’ ብሎ ተሳልቆብኝ ኖሯል። “ኧረ አዲስ የመጡ የሕዝብ ማጓጓዣዎች ናቸው! ምን ይላል ይኼ!” ብሎኝ ፊቱን አዞረ። ከመሸማቀቅ ይልቅ በገዛ አገሬና ቋንቋዬ ባይተዋር መሆኔ አጦፈኝ። በእንግሊዝኛ ክፍለ ጊዜ የፎረፍኩባቸው የትምህርት ቤት ዘመናት ቆጩኝ። ጥቃቅን የሚመስሉን ስህተቶች ፋፍተው የባህልና የማንነት ዝቅጠት ውስጥ እንደሚከቱን ለምን ቶሎ አይገባንም እያልኩ ብቻዬን እንደ እብድ መለፍለፍ ስጀምር፣ ወዲያው ሌላ አውቶብስ መጥቶ ፊቴ ገጭ አለ። እያቅማማሁ ተሳፈርኩ። ደንበኞቼ እየደወሉ የት ደርሰሃል እያሉ ያሳብዱኛል። መድረሱን ተውትና መነሻዬን መሳቴን ምን ብዬ ላብራራው? በጣም አካበድኩት እንዴ? ፍረዱኝ እስኪ? የምጓዘው የኮንዶሚኒየም ቤት ላሻሽጥ ነው። የኮንዶሚኒየም ቤቶች ሽያጭ ሥራ ደስ ከሚለኝ ነገሩ አንዱ ቤቶቹ ተሽጠው አያልቁም። ማን ነበር “ትውልዱ በቤት እጦት ማቆ ማቆ እስኪያልቅ ድረስ ገና የእነሱ ቢዝነስ አያልቅም፤” ሲለኝ የነበረው? ማን ነበር እባካችሁ? ስላቁና ሰቀቀኑ በዛና የተባባልነውንም ማስታወስ አቃተን እኮ? ይሁን እስኪ! እናም ባለሁለት መኝታ ኮንዶሚኒየም ቤት ለአዲስ ጎጆ ወጪዎች አሻሽጨ ‘ኮሚሽኔን’ እንደተቀበልኩ ወዳጆቼ ደውለው “ጥሬ ሥጋ ካልበላን” ይሉኛል። ሥጋ ለመብላትና ለመዘልዘል የማበራችንን ያህል ለሐሳብ ልዕልና ሀብትና ሥልጣኔ ያለመቆማችን ክፍተት እያናደደኝ፣ አንዴ ሆዴን አስጩኸውታልና ሄድኩ። መቁረጥ እንደጀመርን ይኼን መላ ቅጡን ያጣ ጉራማይሌ ቋንቋ አጠቃቀም ልማድ ለጨዋታ ባነሳው ያም ያም እንደ ደመኛ ጠላት ተረባረብኝ። “አንተ ደግሞ ዓለም ስንት ደረጃ ላይ ደርሷል አንተ ቋንቋ የባህል ዕድገት ገለመሌ ትላለህ! ይልቅ እንካ ይኼ ጮማ አለው፤” ይለኛል አንዱ። አላወቀ የእኔ ጮማ የቱ እንደሆነ እያልኩ እሱን ስታዘብ ሌላው፣ “አንበርብር በአሁኑ ጊዜ የግል ጭንቀትና ንጭንጭ የሚያዳምጥ የለም። አገሮች የየራሳቸውን ምጥ የሚያምጡበት ዘመን አክትሟል። ዓለም በአንድ አንጎል ወደምታስብበት መንገድ ለመቀላቀል ሞክር፤” ብሎኝ “የዛሬው ሥጋ የተለየ ነው” እያለ ሐሳብ አጣጥሎ የያዘውን ሙዳ ያዳንቃል። አልበላህ አለኝ ብል ታምናለችሁ? ያውስ እሱን ካልበላን ምግብ የበላን የማይመስለን ሥጋ ነዋ! ጉድ እኮ ነው ዘንድሮ! “አወይ ቢጤ ማጣት!” የሚሉት እኮ ባሻዬ ወደው አይደለም። “አብረን እየበላን አብረን ማዘን የነሳን እንዲያው ግን ምን አጥፍተን ይሆን?” ብለው የባሻዬን ልጅ፣ “ዲሞክራሲ የሚሉት የገባን የመሰለን ግን ያልገባን ፍልስፍና ነዋ!” ብሎኝ አረፈው። እኔ ምለው የወል ሀብትን እየናደ ለግል ስለመጨነቅ ሆነ እንዴ ዲሞክራሲ የሚሰበከው? የመሠረተ ትምህርት ያለህ እንበል በስተርጅና እንደፈረደብን! ከወጪ ቀሪ ታዲያ ሰሞኑን ደህና ዝግ ዘግቻለሁ። የባሻዬ ጓደኛ ሴት ልጅ ከአውሮፓ ጠቅልላ መጥታለች። እኔ ደልዬ እሷ ከገዛችው ዘመናዊ ፎቅ ቤትና ኮሮላ መኪና የበጠሰችልኝ በኃይለኛው ነው። በነገራችን ላይ ይህቺ ዳያስፖራ ወጣት በአገራችን ዕድገትና ልማት ተማርካ፣ “ከእንግዲህ ባህር ልሻገር እግሬን አላነሳም!” ስትል ያልተላከባት አማላጅ ያልገዘታት ቄስ የለም። በሽምግልናው እንድሳተፍ አባቷ ሲያግባቡኝ፣ “እናንተ ደላሎች እኮ እንኳን ይኼን ይኼን ሰማይ ቤት ሳይቀር ሰው አሾልካችሁ ታስገባላችሁ፤” ብለውኛል። እኔ ግን እንዲህ ሲሉኝ ደስ አላለኝም። የምር! ምክንያቱም ይህ አባባላቸው ደላላ የተባለ ሁሉ ለሰው የሚነግድ ሳይሆን በሰው የሚነግድ ከሚል የተሳሳተ አመለካከት የመነጨ እንደሆነ ስለማውቅ ነው። ባሻዬ፣ “መቼስ አንድ በሉልኝ ከተባልን ምን እናደርጋለን? ልጅቷ አገሩን ወዳዋለች። ብዙ ለውጥ አይቻለሁ ከእንግዲህ ሰው አገር አንገት አልደፋም ብላ ፀንታለች። አባት ደግሞ ‘ሳማ እስኪለበልብ ጎመን ይመስላል’ መሄድ አለብሽ ይላሉ። ከሰማች ሰማችን ካልሰማችም እንዳሻት ትሁን፤” እያሉ በሽምግልናው እንድሳተፍ በብዙ ሊያግባቡኝ ሞከሩ። “ግን ባሻዬ አባት ናቸው ወይስ ልጅት ናት ተው መባል ያለባቸው?” ብላቸው፣ “ይኼን ጥያቄ አያትየውን ጠይቅ እኔን አይደለም፤” ብለው አመለጡኝ። እየቀፈፈኝ ልጅትን በቀጠሮ ቁጭ አድርገን፣ “አባትሽን ስሚ!” ብንላት “እዚያ እያለሁ የግለሰቦችን መብት በማፈን መንግሥትን አምቻለሁ። ለካ ከመንግሥት በላይ ግለሰቦች ናቸው የግለሰብን መብት እየጣሱ ያሉት? ለመሆኑ የምትሠሩትን ታውቃላችሁ?” ብላ በማይመጣ ብትመጣብን አስበርግጋ በተነችን። እኔ መጀመሪያም ደስ አላለኝም ብያችሁ አልነበር? ይኼውላችሁ! ደግሞ ነገ የ ‘አምነስቲዎች’ ክስ ወደ እኛ ቢዞር እንዴት ባለው መላችን ነው ‘ዓይኔን ግንባር ያድርገው’ ብለን የምንሸመጥጠው? አስባችሁታል? ሆሆ! በሉ እስኪ እንሰነባበት። ውዷ ማንጠግቦሽ ዘወትር በጥምቀት አዲስ ቀሚስ ማጥለቅ ትወዳለች። ማንጠግቦሽ አለኝታዬ ስለሆነች ብቻ አይደለም የምወዳት። ልማታዊ ስለሆነችም ነው! የሴቶች መብትና መዋቢያ ዕቃዎች ዘመን እንደመሆኑ በነጋ በጠባ እጅ እጄን አታይም። ተመስገን አይደል የሚባለው? እንዲህ ካልተዛዘንን መንግሥት እጅ እጃችን አይቶ፣ ተረጂ ተመፅዋቹ እጅ እጅቻንን እያየ እንዴት ይኮናል? የኑሮ ሸክም የነዳጅ ዋጋ ቢቀንስም አልቀንስ ብሏል እኮ። በበኩሌ ሲቀንስ የምታዘበው ለመኖር የሚመደብልን ዕድሜ ብቻ ነው። በዚህም ‘ተመስገን እንዳልል የደላው ይከፋብኛል። አያድርስ እንዳልል የመረረው ያጠቁረኛል’ ብዬ ዝም እንዳልኩ ከተራ ደርሷል። እናም ለማንጠግቦሽ የምትሆን ውብ ቀሚስ ልሸምት ቡቲክ ለቡቲክ ስዞር ያጠፋሁት ሰዓት ሳይሆን ዕድሜ ነው ብል ማጋነን አይሆንብኝም። ዓይኔ ያረፈባት ባለአበባ ቀሚስ ሸምቼ ወደ ቤቴ ስሮጥ ለእህቶቻችን ፅናቱን እንዲሰጣቸው ተማፀንኩ። ለሾፒንግ ሴቶቻችን የሚዞሩትን ዙረት ያላየ ብቻ ይመስለኛል የማጂላን አድናቂ። ታዲያ ሠፈር ስደርስ ለወትሮው በጥምቀት ምድር ሠፈር ውስጥ የማይታየው ምሁሩ የባሻዬ ልጅ አገኘኝ። “ምነው ጃንሜዳ ሳትሄድ?” ብዬ ስጠይቀው፣ “የለም ዘንድሮስ ጥምቀቱ በአንድ ሠፈር ብቻ መወሰን የለበትም ባይ ነኝ በዝቷል!” አለኝ። “ምኑ ነው የበዛው?” ስለው “ግፉ፣ በደሉ፣ ኃጥያቱ ነዋ! ያልገባበት ሥፍራ ያልሰፈረበት ክልል አለ እንዴ? በማኅበራዊ፣ በፖለቲካዊና በኢኮኖሚያዊ ሕይወታችን በግል ትላለህ በጋራ ህሊና ያላጣንበት፣ ከዕውነት ያልጎደልንበት፣ ከፍትሕ ያልሸሸንበት ምን ማንነት አለን? አጥማቂው ጥቂት ተጠማቂው ብዙ፣ ታማሚው እልፍ አካሚው ትንሽ ሆኖ ነው አንድም እያደር የሚብስብን፤” ብሎ ጥሎኝ ሄደ። ማንጠግቦሽ በደስታ ሰክራ በሐሴት ስታጠምቀኝ ታድራለች ያልኩት ሰውዬ በባሻዬ ልጅ ንግግር ‘ሙዴ’ ተረባብሾ ገብቼ ጥቅልል ብዬ ተኛሁ። እውነትም ታማሚው በዝቷል ጃል! እንዴት ነው ነገሩ? ሳማ ጎመን መስሎ እየለበለበን ነው እንዴ? እስኪ ረጋ እንበል፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት