Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊዘመን ተሻጋሪ ግጥሞች

ዘመን ተሻጋሪ ግጥሞች

ቀን:

ወር በገባ የመጀመሪያው ረቡዕ የሚካሄደውን ግጥምን በጃዝ ለመታደም የተቻኮሉ ሰዎች ራስ ሆቴልን ሞልተዋል፡፡ ላለፉት ሦስት ዓመታት የተከናወነው መርኃ ግብር 42ኛ ሳምንቱን ለማስተናገድ መሰናዶው ተጠናቋል፡፡ እንደ ወትሮው በአዳራሹ ወንበር ያላገኙ በኮሪደርና ጥግ ጥግ ላይ ይታያሉ፡፡ በዕለቱ ዶ/ር ፈቃደ አዘዘና በረከት በላይነህ ግጥሞቻቸውን አቅርበዋል፡፡ የመንግሥቱ ለማን ግጥሞች ተፈሪ ዓለሙ ሲያነብ ‹‹ፋቡላ›› ባህላዊ ውዝዋዜ አሳይተዋል፡፡ የግሩም ዘነበና ዲ/ን የዳንኤል ክብረት ወግም ተስተናዷል፡፡ ከዳንኤል ወጎች አንዱ በቅርብ በእሳት ቃጠሎ የደረሰበት ጣይቱ ሆቴልን መነሻ በማድረግ የተሰናዳ ሲሆን፣ የእሳት አደጋ መከላከያ ድርጅት ራሱ የእሳት አደጋ ቢገጥመውና ለአደጋው ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ቢዘገይ የተከሰተውን ውድመት በምናብ አስቃኝቷል፡፡ ግሩም ማኅበራዊ ጉዳዮችን እንደ አዕምሮ ሕመምተኛ ገፀ ባህሪ (እያዩ ፈንገስ) ሲተች ታዳሚው ድጋፉን ያሰማ ነበር፡፡ ወቅታዊና ሁሉን ያማከሉ የሚባሉ ጉዳዮች የታዳሚውን ስሜት በበለጠ ፈንቅለው ሲያስጨበጭቡ ነበር፡፡ ልዩ ልዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላነሱት ጥበባዊ ሥራዎች ታዳሚው ሞቅ ያለ ምላሽ ሰጥቷቸዋል፡፡ ግጥምን በጃዝና መሰል ዝግጅቶች የሚታደሙ እንደሚናገሩት፣ ትችት አዘል ሥራዎች ትኩረት ሳቢ ናቸው፡፡ ስሜት የሚኮረኩሩና ያለውን ነባራዊ ሁኔታ የሚያንፀባርቁ ሥራዎች እንደሚፈለጉ የሚገልጹ አሉ፡፡ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውንም የሚስባቸው በርካቶች መሆናቸውን ለመርሐ ግብሮችና መጻሕፍት ከሚሰጠው ትኩረት መገንዘብ እንደሚቻል የሚያምኑም አሉ፡፡ ገጣሚያን ደስ የማይለውን አጋጣሚ ሲጽፉ ትርጉም እንደሚሰጠው የገለጸልን ወጣት፣ እንዲነገር ስለምፈልገው ብቻ ሳይሆን አንዳንዴ ሊሰማኝ የሚገባ ነገር ግን ቸል ያልኩት ስለሚነገርም አደምጣለሁ፤›› ይላል፡፡ የማኅበረሰቡን የዕለት ከዕለት ሕይወት በማሳየትና አንድን ሥርዓት ተችቶ ለለውጥ በማነሳሳት ሚና ያላቸው ግጥሞች ዘመን ሲሻገሩ ይታያል፡፡ በሥነ ጽሑፍና ዘርፍ ያሉና ሌሎችም ለግጥሞች ጭብጥ የሚሰጠውን ምላሽ ያስረዳሉ፡፡ ጉዳዩን በሚመለከት ጽሑፎች ያዘጋጁት ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልሳን ትምህርት ክፍል መምህርና ገጣሚ ናቸው፡፡ አያሌ መጻሕፍት ቢታተሙም ስንቶቹ ጥሩ ግጥሞች የያዙ ናቸው የሚለው አጠያያቂ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በማንኛውም ዘመን የተጻፉ ግጥሞች ጊዜያቸውን እንደሚገልጹና ግጥም ለሰው ልጅ ስሜት ካለው ቅርበት አንፃር ፈጣን ምላሽ እንደሚያገኙ ይናገራሉ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታየው የሁነቶችና የግጥም ቁርኝት በኢትዮጵያም ይስተዋላል ይላሉ፡፡ የግጥም ስሜት ኮርኳሪነት በቀላሉ ሕዝብ ጆሮ እንዲሰጥ ያስገድዳል የሚሉት ዶ/ር በድሉ፣ ለአነሳሽ ግጥሞች መብዛት ዋና ምክንያት ከሚሏቸው አንዱ የግጥም አቅም ማጣት ነው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ጀማሪ ገጣሚዎች ለመደመጥ የኅብረተሰቡን ስሜት የሚኮረኩር ግጥም የሚያቀርቡበት አጋጣሚ ይበዛል አንዳንዴ የግጥም ውበት ተዘንግቶ ገጣሚው ማንም ያልደፈረውን መናገሩ አንባቢዎችን ያስደንቃቸዋል ይላሉ፡፡ አንገብጋቢ ጉዳይ እያነሱ ጥሩ ግጥም የሚያቀርቡ ቢኖሩም አናሳ ናቸው፡፡ ግጥሞች በራሳቸው ጉልበት አልባ ሲሆኑ፣ የማኅበረሰቡን እሮሮ ማሰማት ወይም ለብዙኃኑ ትርጉም ሊሰጥ የሚችል መልዕክት ላይ ማተኮር ይስተዋላል ይላሉ፡፡ አካሄዱ ግጥሙን እንደፈጠራ ሥራ ያላሞገሰ አንባቢ ጉዳዩን ከራሱ ጋር ማዛመድ ስለሚችል አድናቆት እንዲቸረው እንደሚያረግ ያክላሉ፡፡ እንደሳቸው፣ ግጥሞች ውበት ኖሯቸው የማኅበረሰቡን ችግር ማሳየት አለባቸው፡፡ ጠጣር ጉዳይ ላይ የሚያተኩሩ ግጥሞች የገጣሚው ችሎታ የሚፈተሽባቸው ናቸው፡፡ ቢነገርላቸው ማራኪ እንደሚሆኑ የማይገመቱ ጉዳዮች አንዳንዴ በአጻጻፋቸው መወደዳቸውን ያስረዳሉ፡፡ አብዛኛው ሰው ስሜቱን የሚገልጽበት ክፍተት ማጣቱና ግጥሞቹ ይህን ማንፀባረቃቸው እንዳስመረጣቸው ይናገራሉ፡፡ ‹‹በግጥም ብቻ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ባይባልም ለጊዜው ሰው ውስጡ የታወቀውን ስለሚተነፍሱ ለአንባቢ እፎይታ ይሰጣሉ፤›› በማለት ግጥሞቹን ከእፎይታ ባለፈ የሚኖራቸው ፋይዳ ላይ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ ሐሳቦቹ ፍሬአማ የሚሆኑት መነጋገርያ መድረክ ሲኖር እንጂ በአንድ ወገን ብቻ ሲሆን መልዕክቱ አንባቢው ጋር ይቀራል ይላሉ፡፡ ነገር ግን በታደሙት ጊዜአት ለለውጥ የጎላ ሚና ያለው ግጥም በኢትዮጵያ ታሪክ መፍትሔ ሲያመላክት መታየቱን በማስታወስ የችግሮች መፍትሔ ለሚመለከታቸው ተቋማትም ግጥሙ ተደራሽ መሆን አለበት ይላሉ፡፡ መልዕክት እንዳለ ሆኖ ከጥራት አንፃር ሚዛን የማይደፉ ግጥሞች ስለመወደዳቸው ዶ/ር በድሉ ሒስ አለመኖሩን አጽንኦት ይሰጣሉ፡፡ ጥሩውን ለመለየት የሠላ ሒስ እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ፡፡ ሒስ ሲኖር አንባቢ ጥሩ ግጥሞችን የመለየት እድሉ ይሰፋል ይላሉ፡፡ ሒስ በይዘታቸው ብቻ ከሰሞነኛ ምላሽ ባሻገር ለዘመናት ተነባቢ ግጥሞች የሚበዙበት መንገድ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ ብዙዎች ቀድሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በተጋበዙበት ይቀርቡ የነበሩ የ‹‹ኮሌጅ ቀን›› ግጥሞችን ይዘት ያነሳሉ፡፡ የ‹‹ኮሌጅ ቀን›› ገጣምያን ማኅበር ፖለቲካዊ አመለካከትና ሒስ በሚል ጥናት ያቀረቡት አቶ ገዛኸኝ ፀጋዬ ከ1950 እስከ 1960 ዓ.ም. የአገሪቱን አንኳር ክንውኖችን ከኮሌጅ ቀን ግጥሞች አስተሳስሮ ያቀርባል፡፡ እንደ ጸሐፊው፣ ከግጥሞቹ ማኅበራዊ ሒሶች መካከል በሰው ልጅ ባህሪና በማኅበራዊ መስተጋብር በሚያሳየው ፀባይ ያተኮሩ ይጠቀሳሉ፡፡ ገጣሚዎቹ የዘመናቸውን ትውልድ ከተለያየ አቅጣጫ ይመዝናሉ፡፡ በፖሊቲካ ረገድ ሐሳብን በነጻነት ስለ መግለጽ፣ ኢ-ፍትሐዊ የኑሮ ልዩነትና መልካም አስተዳዳር እጦትን እንደሚተቹ የሚያመላክተው ጥናት፣ መደምደሚያ በ1951 ዓ.ም. የሰውን ልጅ ውስጠት የሚመረምሩ ጭብጦችን ማቀንቀን ጀምረው በ1960 ዓ.ም ለአገሪቱ ፖለቲካ መፍትሔው የትጥቅ ትግል እንደሆነ እስከ መግለጽ መድረሳቸውን ያስረዳል፡፡ ዶ/ር በድሉ በቅርብ ያሠሩት ጥናት በ2005 ዓ.ም. ከወጡ የግጥም መድብሎች 98 በመቶ ጥሩ እንዳልሆኑ ያሳያል፡፡ ከዚህ በመነሳት ዘመን ተሻግረው የማኅበረሰቡን አኗኗር ለመጪው ትውልድ የሚያሳዩ ጥቂት መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ እንደ ቀደመው ጊዜ ሕሊና ላይ የሚቀርና ነገም የሚነበብ ግጥም መቅረብ እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡ ከግጥም መድብሎች የበረከት በላይነህን ‹‹የመንፈስ ከፍታ›› ጠቅሰዋል፡፡ አስተያየታቸውን ከሰጡን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጽሑፍና ፎክሎር መምህርና ገጣሚ ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ ይገኙበታል፡፡ የዕለት ከዕለት ማህበራዊ ጉዳዮች የሚከነክኗቸው ገጣሚዎች ሥራ በአመዛኙ የኅብረተሰቡን በጎ ምላሽ እያገኘ ነው ይላሉ፡፡ ከድምዳሜ ለመድረስ ጥናት ግድ ቢሆንም ከሌላው የጥበብ ዘርፍ ለግጥም እንደሚዳላ ይገልጻሉ፡፡ ግጥም ከጥበብ ዘርፎች በበለጠ ገንዘብ ሲወጣበትና ድጋፍ ሲሰጠው መታየቱ ማስረጃ እንደሚሆን ያክላሉ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ግጥሞች በይዘታቸው የሚወደዱት ዘወትር ከሚሰማው ዘዬ በተለየ ስለሚቀርቡ ወይም ገጣሚዎች በቅርብ የሚያውቁትንና ብዙዎች ያለፉበትን ሕይወት በጥሩ ቋንቋ ስለሚያቀርቡ ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ ግጥሞቹ ከምናባዊነት አልፈው መሬት የወረዱና ከተሞክሮ የመነጩ እንደሆኑ ይገልጻሉ፡፡ ዶ/ር ፈቃደ በአዲስ አበባና በአንዳንድ ክልል ከተሞች የግጥም ንባብ ምሽቶች መዘውተራቸው ለግጥሞች የሚሰጠውን ምላሽ ያስረዳል የሚል ዕምነት አላቸው፡፡ ግጥሞች መተንፈሻ እየሆኑና አንዳች ስሜት እያጫሩ መሆኑ እንደማያጠራጥር ገልጸው፣ ሁሉም ግን የሚወደሱ አለመሆናቸውን ያሰምሩበታል፡፡ ከጥበብ ግጥም ማኅበረሰቡን ከነካበት ምክንያት አንዱ ብዙ ገጣሚዎች ቅሬታቸውን በዘለፋ ሳይሆን በምክር አዘል ትችት በማቅረባቸው ነው ይላሉ፡፡ የሚነሳው ጉዳይ ሁሉን አቀፍ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ለኅብረተሰቡ ደርሷል ማለት እንደማይቻልና በምስልና ድምፅ ማሰራጨት ቢቻል ተጠቃሚው እንደሚሰፋ ያመለክታሉ፡፡ ከተሞክሯቸው በመነሳት የሕይወት ውጣ ውረድን የሚያሳይ ግጥም ቀና ምላሽ እንደሚያገኝና የኢኮኖሚ ቀውስ ወይም ሌላ ችግር የሞላው ኑሮ የሚገፋ ግለሰብ መሰል ይዘት ላለቸው ግጥሞች ማድላቱ አይቀሬ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹ግጥም የጎደለውን መሙላት አለበት፤ ገጣሚ በምናቡ የሚመኘውን መግለጽ ይገባዋል፤›› የሚል አመለካከት ያላቸው ዶ/ር ፈቃደ፣ ግጥሞች ከሆነው አልፈው ገጣሚ እንዲሆን የሚመኘውን ቢያቀርቡ ጥሩ ነው ይላሉ፡፡ ክፍተትን ከማሳየት በተጨማሪ ገጣሚው የሚመርጠው ጉዳይ መገደብ እንደሌለበትም ይናገራሉ፡፡ ከቃል ግጥም ጀምሮ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ‹‹የኮሌጅ ቀን›› ግጥሞችን እየታደሙ የሸለሙበትን ጊዜ ያወሳሉ፡፡ የያኔው ሥርዓት ተቺና ለለውጥ የሚያነሳሱ ግጥሞች ሚና እየጎላ የመጣበት ወቅት እንደነበር ዶ/ር ፈቃደ ያብራራሉ፡፡ ከቀደሙት የኃይሉ ገብረዮሐንስ (ገሞራው) ‹‹በረከተ መርገም›› ጠቅሰዋል፡፡ አስተያየት የሰጡን አቶ ደረጄ በላይነህ በበኩላቸው፣ አንገብጋቢ ጥያቄ ከሚሰነዝሩ ግጥሞች ቀላል ሚባሉ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ግጥሞች ይበዛሉ ይላሉ፡፡ ማህበራዊ ሁነቶች ሲገኑ ፍልስፍና ያዘሉ አነስተኛ እንደሆኑና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከታተሙ ሥራዎች የግጥም ይዘት ብቻ ሳይሆን ቴክኒክ መለኪያ ሲሆን ከደረጃ የወረዱ ያደርጋቸዋል ይላሉ፡፡ በማኅበረሰቡ ተቀባይነት የሚያገኙ ሥራዎች አስገራሚ አጨራረስ ያላቸውና ፌዝ የበዛባቸው መሆናቸውን የሚገልጹት አቶ ደረጄ፣ የየአንባቢ ስሜት ልዩነት ቢኖረውም ለግጥም የሚሰጠው ምላሽ አጠቃላይ ትውልዱ ያለበትን የአስተሳሰብ ደረጃ የሚያመላክት ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡ እንደ አቶ ደረጄ፣ ማኅበረ ታሪካዊ ዐውድ፣ የትውልዱ አመለካከትና አስተሳሰብ ተጨምቀው ለግጥም የሚሰጠውን ምላሽ አቅጣጫ የሚያሲዙ ናቸው፡፡ ግጥሞች ከቀደመው ጋር ሲነፃፀሩ በሁለቱም ወገን ጥሩና ረብየለሽ ግጥሞች እንዳሉ ይናገራሉ፡፡ የአሁኑ ካለፈው አንሶ ከታየ ምናልባትም ይዘቱ ላልቷል ሊባል ይችላል፡፡ በሌላ በኩል በአሁን ወቅት ትልቅ ጉዳይ አንስተው ጥሩ ግጥም የሚያቀርቡ ገጣምያን ያን ያህል በቂ ጆሮ ተሰጥቷቸዋል ለማለት አያስደፍርም ይላሉ፡፡ ለዓመታት በርካታ ታዳሚዎች ይዞ የዘለቀው ግጥምን በጃዝ አሰናጅ መንቶ ኪነ ጥበባት ፕሮጀክት አስተባባሪ እንዲሁም ገጣሚ አበባው መላኩ፣ ብዙኃኑን የሚነኩ የወል ጉዳዮች ለየግለሰቡ ትርጉም ከሚሰጡ በበለጠ እንደሚገኑ ያምናል፡፡ በየወቅቱ የተጋጋለ ጉዳይ የሚያንፀባርቁ ግጥሞች እያንዳንዱ ሰው ለጉዳዩ ምልከታ ስለሚኖረውና ቅርቡ ስለሆነ ይመረጣሉ፡፡ በሌላ በኩል ነገሮችን ብዙኃኑ ከሚያዩበት በተለየ የሚያቀርብ ግጥም ቀልብ የሚስብ ይሆናል፡፡ አበባው እንደማንኛውም ማኅበረሰብ ሳንካ ሲገጥመን ችግሩን ደፍሮ የሚገልጸውን አካል እናዳምጣለን ይላል፡፡ በተለይ ዛሬ ዛሬ ማኅበረሰቡ የሚያስተናግደው ፈጣን ለውጥ ቀድሞ ከተለመደው አኗኗር ጋር ሲጣረስ ይታያል፡፡ ገጣሚያኑ በከተሜነት መስፋፋት (ሉላዊነት) ሳቢያ ማኅበራዊ እሴቶች ቸል መባላቸውን ሲተቹ ወቅቱ በመሆኑ አንባቢ ወደነሱ እንዲያዘነብል ግድ እንደሚል ይገልጻል፡፡ በተለያየ መድረክ ከሚቀርቡ ግጥሞች ምን ያህሉ ለኅትመት ይበቃሉ የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ እንደ አበባው፣ አንድ ወቅት ላይ የሚጋጋሉና ከጊዜ በኋላ ከጉዳይ የማይቆጠሩ ነገሮች በኅትመት አይካተቱም፡፡ ከኅትመት ጋር በተያየዘ ያልተቀረፉ ችግሮች እንዳሉ ሆነው ሁሉን ያማከለ ይዘት የሚያነሱ ግጥሞች እየታተሙ ነው ይላል፡፡ ትችት አዘል ግጥም ሲጽፉ የበለጠ እንደሚደመጡና ተቀባይነት እንደሚያገኙ በማሰብ ይዘቱን የሚመርጡ ገጣሚዎች ቢኖሩም፣ በእሱ ዕምነት ‹‹ብዕር የሚያጋድለው እውነት ወዳለበት ነው፤››፡፡ ትችት አመዝኗል የሚል አስተያየት ሲነሳ፣ ጸሐፊ ስሜቱን ያነሳሳውን የመጻፍ መብቱ መጠበቅ አለበት ይላል፡፡ ለኅብረተሰቡና ለገጣሚው የቀረቡ ሁነቶች ትኩረት ቢሰጣቸውም ከትችት ውጪ ውበትንና ተፈጥሮን የሚገልጹ እንዳሉም ያስረዳል፡፡ ትችት የሚሰነዘሩ ግጥሞች መፍትሔ አመላካችነታቸው ምን ድረስ ነው የሚል ጥያቄ አንስተንለት ነበር፡፡ እያንዳንዱ ሰው ድርሻውን ቆም ብሎ እንዲመለከት ያሳስባል የሚል ዕምነት አለው፡፡ ከኅብረተሰቡ ውጪ የሚመለከታቸው ተቋሞች ጋር ደርሷል ብሎ ለመደምደም የሚያስችሉ ምልክቶች እንደሌሉ ይገልጻል፡፡ ሐሳቦችን የማንሳት ዓላማውን እያስካ እንደሆነና የየድርሻውን መወጣት ያለበት ተቋም ለውጥ አሁን ባይታይም ለወደፊት እንደሚኖር ተስፋ አለው፡፡ በመርሐ ግብሩ ለባህልና ቱሪዝም ምንስቴሮች ጥሪ ቀርቦ አለመገኘታቸውን ገልጾ፣ የቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ፣ ህላዊ ዮሴፍ ከመንግሥት ተቋሞች እንደሚጠቀሱና ሌሎችም መርሐ ግብሩን እንዲታደሙ ፍላጎታቸው መሆኑን አክሏል፡፡ የሥነ ልቦና ባለሙያዋ ራሔል ተስፋዬ እንደምትለው፣ ማኅበረሰቡን የሚቀሰቅሱና ሁሉንም የሚያስማሙ ጉዳዮች ወይም ለጋራ ችግሮች መፍትሄ አመላካች ግጥሞች ሲቀርቡ በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነተቻው ይጨምራል፡፡ ነባራዊ ሁኔታ የተመረኮዙ ጉዳዮች ተነስተው ግጥሞቹ የሚጠቁሟቸውን መፍትሄዎች ግን ሁሉም ላይቀበላቸው ይችላል ትላለች፡፡ ችግሮች በተለያየ መንገድ ቢነሱም በጥበብ ሲሆን፣ ኅብረተሰቡ በቀላሉ ይቀበላቸዋል፡፡ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ የተቃራኒ ጾታ ጉዳይ ወይም ሌላ እንደየመልዕክቱ ይዘት በየዕድሜ ክልሉ የሚሰጠው ምላሽ ይለያያል ትላለች፡፡ እንደ ራሔል፣ ኅብረተሰቡ አንድ ገጣሚ ችግሩን ከመፍትሔ ጋር ሲያቀርብለት እፎይታ ይሰጣል፡፡ ስሜቱ ከሰው ሰው የሚለያይ ቢሆንም ታዋቂ ሰዎች የመደመጥ ዕድላቸው እንደሚሰፋና የጥቆማቸው ተቀባይነት እንደሚጎላ ታሰረዳለች፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...