Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

ወርኃ ጥር በባተ በሦስተኛው ቀን (እሑድ) የማይቀርበት የዘመድ የሠርግ ሥነ ሥርዓት ላይ መታደም ግዴታዬ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት እኔና ባለቤቴ ከሌሎች ዘመዶቻችን ጋር ሆነን ከማለዳ እስከ ምሽቱ የሠርግ ሥነ ሥርዓት መጠናቀቂያ ድረስ መገኘት ስለነበረብን ወደዚያው አመራን፡፡ የዚያን ቀን ገጠመኞቼ ሦስት ስለሆኑ እንዲህ ተራ በተራ ልተርክላችሁ፡፡ የመጀመሪያው እንዲህ ነበር፡፡ ሠርጉ ከመድረሱ ከጥቂት ቀናት በፊት በምሳ ፕሮግራም ላይ ለሠርጉ ታዳሚዎች ጥሬ ሥጋ ከሚቆርጥ ባለሙያ ጋር ተነጋግሬ ቀጠሮ ይዘናል፡፡ ሙሽራው ከረፋዱ አምስት ሰዓት ሲሆን በሆታና በእልልታ ሸኝተነው ወደ ሙሽሪት ቤት ያመራል፡፡ እኛም አብረን አጅበን ሄደን ሙሽሪትን በወግ ማዕረጉ መሠረት ከእናት አባቷ ቤት አስወጥተን ለፍቶግራፍ ሥነ ሥርዓት ወደ ግዮን ሆቴል በአጀብ እንዲሄዱ እናደርጋለን፡፡ እኛ ደግሞ የምሳ ድግሱን ለማቀላጠፍ ወደ አዳራሽ እናመራለን፡፡ አዳራሹ ደርሰን ከመስተንግዶ ኮሚቴ አባላት ጋር በመሆን የዲኮሩን፣ የመቀመጫዎችንና ጠረጴዛዎችን፣ የምግብና የመጠጥ ዝግጅቶችን በቅጡ ዓይተን የጎደለውን ካስተካከልን በኋላ የእንግዶች አቀባበል ይጀመራል፡፡ በዚህ መሀል የጥሬ ሥጋ መስተንግዶውን የሚያከናውነው ባለሙያ ይመጣል፡፡ ለሰውየው የተዘጋጀውን የበሬ ሥጋ፣ ቢላዎች፣ የሚጥሚጣ፣ የአዋዜና የሰናፍጭ ግብዓቶችን ካስረከብን በኋላ እንደተለመደው ለሥራ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጦልን እንለያያለን፡፡ ከአዳራሹ ውጭ ሆኜ እንግዶችን ከሌሎች የኮሚቴ አባላት ጋር መቀበል እጀምራለሁ፡፡ አዳራሹ በእንግዶች ተሞልቶ የሙሽሮች መምጫ ሲቃረብ አንዲት ሴት በድንጋጤ ተውጣ መጥታ በጆሮዬ የሆነ ነገር ሹክ ትለኛለች፡፡ የሰማሁትን ባለማመን የምትናገረውን እንድትደግምልኝ ስጠይቃት፣ ‹‹ሥጋ ቆራጩ ሰክሮ ተኝቶ እያንኮራፋ ነው…›› ስትለኝ በቆምኩበት ፈዝዤ ቀረሁ፡፡ ሙሽራ እየተቃረበ ሥጋ ቆራጩ ሰክሮ ተኝቷል ሲባል ያስደነግጣል፡፡ እንደምንም ብዬ ወደ ሥጋው ቦታ ስደርስ ሴትየዋ እንዳለችው ሰውየው አብቅቶለታል፡፡ ውስጤ በንዴት እየነፈረ፣ ‹‹ምንድነው የጠጣው? ሳገኘው ደህና አልነበረም ወይ?›› ስል አንድ ወጣት በሌባ ጣቱ ወደ ጥግ አቅጣጫ ጠቆመኝ፡፡ ጠጅ ተሞልቶባቸው የነበሩ አራት ጠርሙሶች ባዶአቸውን ተበታትነዋል፡፡ ደነገጥኩ፡፡ አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንዴት አራት ጠርሙስ ጠጅ እንዳጋባ ገረመኝ፡፡ ለማንኛውም ሰውየውን በወሳንሳ አንስተን ሌላ ሥጋ ቆራጭ ፍለጋ አሰሳ ጀመርን፡፡ ሳንወድ በግድ ከመደበኛው ዋጋ ሁለት እጥፍ ከፍለን አምጥተን ከጉድ ወጣን፡፡ አያድርስ ነው የሚባለው፡፡ ሁለተኛው የዕለቱ ገጠመኜ ደግሞ ይህንን ይመስላል፡፡ ምግብ ተበልቶ መጠጥ እየተጠጣ ጭፈራው ደራ፡፡ ወጣቶች፣ ጎልማሶችና አዛውንቶች ሳይቀሩ በተለያዩ የሠርግ ሙዚቃዎች በእስክስታ ሠርጉን ሲያደምቁት ሳለ ዕድሜ ለዘመናችን ቴክኖሎጂ፣ ብዙዎቹ የሠርጉ ታዳሚዎች በአነስተኛ ካሜራዎች፣ በአይፓዶችና በዘመናዊ የሞባይል ቀፎዎች ትዕይንቱን በምሥልና በቪዲዮ ይቀርፁ ነበር፡፡ ይኼ ሁሉ ሕዝብ እነዚህን የቴክኖሎጂ መሣሪያዎች በመጠቀም ያደርግ የነበረውን ርብርብ ሳይ ወደድንም ጠላንም አገሪቱ ውስጥ ካለፉት ዘመናት የተሻለ ለውጥ መኖሩን ማሳያ እንደሆነ አሰላሰልኩ፡፡ እኔ ከሁለት አሥርት ዓመታት በፊት ሳገባ ቪዲዮ ምን ያህል ብርቅ እንደነበር አልዘነጋውም፡፡ ሌላው ቀርቶ ዲጂታል ካሜራዎች እንኳን አልነበሩም፡፡ ብቻ ይህ ዘመን ከቴክኖሎጂ አንፃር አስደሳች ሲሆን፣ የቴክኖሎጂው ተቋዳሽ መሆን ደግሞ የበለጠ ያስደስታል፡፡ ነገ ተነገ ወዲያ በጣም የሚያስደምሙን ነገሮች እንደሚፈጠሩም አያጠራጥርም፡፡ ይህ ትዕይንት ተሟሙቆ በቀጠለበት አንዲት ወጣት በጣም ተክዛ ተቀምጣ አየኋት፡፡ በዚህ የሠርግ ፈንጠዝያ ላይ ምን ያስተክዛታል ብዬ ሄጄ ሳነጋግራት፣ አዲስ ሳምሰንግ ሞባይሏን መሰረቋን ነገረችኝ፡፡ ጊዜ ሳላጠፋ የስልክ ቁጥሯን ጠይቄያት ስደውል ጥሪ ተሰማኝ፡፡ ነገር ግን ቶሎ ይጠፋል፡፡ ደግሜ ስደውል እንዲሁ፡፡ አዳራሹን ዙሪያውን እያካለልኩ ስደውል አንድ ቦታ ላይ እንዴ ድምፅ ተሰምቶኝ ሲጠፋ ተሰማኝ፡፡ እዚያው አካባቢ ሆኜ እንደገና ስደውል ድምፁ ተሰምቶ ሲጠፋ ቦታውን አወቅኩ፡፡ በቀጥታ ተንደርድሬ ሄጄ አሁንም ስደውል ድምፁ ተሰምቶ ሲጠፋ ሰውየውን አፈፍ አድርጌ ያዝኩት፡፡ ዕድሜው ከሃምሳዎቹ የሚበልጥ ግለሰብ ጥግ ላይ ጠጁን እየጠጣ በግራ እጁ ጥሪ ሲመጣ ጥፍት ያደርጋል፡፡ ሳምሰንግ ሞባይሉን ከእጁ ነጥቄ፣ ‹‹ከየት አመጣኸው?›› ስለው ወንበሩን ገለባብጦ በሩጫ ወደ አንደኛው በር በረረ፡፡ እሱን ተከትሎ ሁከት መፍጠር ሥነ ሥርዓቱን መረበሽ ስለመሰለኝ ተውኩት፡፡ ለወጣቷ ሞባይሏን አስረክቤ ሐዘኗን ወደ ደስታ ቀየርኩላት፡፡ ሰውየው የሳምሰንግ ሞባይሉን አጠቃቀም ባለመቻሉ ነው እንጂ ቀልጣ ቀርታ ነበር፡፡ ሦስተኛውና ማሳረጊያው ደግሞ ይህ ነው፡፡ ሙሽሮቹን ከመሸ በኋላ መኖሪያቸው አድርሰን ራት ተበልቶ የዳቦ ስም የማውጣት ሥነ ሥርዓት ይጀመራል፡፡ ለሙሽሪት የዳቦ ስም ጥቆማ በአስተናባሪው አማካይነት ተካሂዶ እናት፣ አሳዳጊ ጎረቤት፣ ጓደኞችና የመሳሰሉት ተዳርሶ ይጠናቀቃል፡፡ በተጠቆሙት ስሞች ላይ ድምፅ ለመስጠት ስንዘጋጅ፣ አንድ ጎልማሳ ሥነ ሥርዓት በማለት እጁን ያወጣል፡፡ አስተናባሪው ይፈቅድለታል፡፡ እሱ እንደሚለው በሥርዓቱ መሠረት ‹‹ወርቅ›› የሚል ቅጥያ የሌላቸው ስሞች ተቀባይነት የላቸውም፡፡ ከእናትና ከአባት ወይም ከአሳዳጊ ጎረቤቶች በስተቀር የቀረቡት ስያሜዎች ውድቅ መደረግ አለባቸው፡፡ የሙሽራዋ ዘመዶችማ ጭራሽኑ ጥቆማ ማቅረብ የለባቸውም ካለ በኋላ፣ ከቀረቡት አሥር ስሞች ስምንቱ እንዲሰረዙ ይደረጋል፡፡ አንድ ሌላ ሰው በበኩሉ ሥነ ሥርዓት ብሎ፣ ከአሥር ስሞች ውስጥ ስምንቱ ውድቅ ተደረጉ ማለት ዲሞክራሲያዊ አይደለም ቢልም ተቀባይነት ያጣል፡፡ በዚህ ጊዜ ሒደቱን በአንክሮ ይከታተሉ የነበሩ በርካታ ወጣቶች ‹‹ምርጫው ተጭበረበረ›› እያሉ በኅብረት ሲያዜሙ እዚያ የነበርን በሙሉ በሳቅ አውካካን፡፡ ያውም ምርጫ ዋዜማ ላይ ሆነን፡፡ (በሪሁን መንገሻ፣ ከኮተቤ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...