Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርየጽሕፈት ቤት ኃላፊው ስለ ኃላፊነታቸው ይታረሙ

የጽሕፈት ቤት ኃላፊው ስለ ኃላፊነታቸው ይታረሙ

ቀን:

ታኅሳስ 26 ቀን 2007 ዓ.ም. የሪፖርተር ስፖርት ዓምድ ላይ በታተመው የዳኞችና ታዛቢዎች (ኮሚሽነሮችን) የቀን አበልና የሙያ ጥያቄን በተመለከተ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሰጡት ምላሽ፣ የኢትዮጵያ ዳኞችና ታዛቢዎች (ኮሚሽነሮች) እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ የእግር ኳስ ክለቦች የፌዴሬሽኑ አካላት ሆነው ሳለ፣ በመካከላቸው የሚነሱ ማንኛውም ጉዳዮች በፌዴሬሽኑ በኩል እንደሚያልፉ እየታወቀ የአንድ አካል ጥያቄ ብቻ እንደሆነ ተቆጥሮ አስተያየቱ መሰንዘሩ ትክክል እንዳልሆነና በተሰጠው ምላሽ ላይም ማኅበራችን ቅሬታ እንደተሰማው ለመግለጽ እንወዳለን፡፡ በመሆኑም የአበል ጭማሪ ጥያቄ መነሻ ምክንያቱ የወቅቱ የኑሮ ውድነት የፈጠረው አጋጣሚ እንጂ ሌላውን አካል አስገድዶ ጥቅም ለማግኘት እንዳልሆነ ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል፡፡ ማኅበራችን የተመሠረተበት ዋና ዓላማ ሙያተኞች በሙያቸው እንዲከበሩና ለሙያው ከፍተኛ ከበሬታ እንድንሠራ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን ከሚመለከተው አካላት ጋር በመነጋገርና በመተባበር እንዲሰጡ ለማድረግ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴና የኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ትብብር ሲያደርጉልን ቆይተዋል፡፡ አሁንም ከጎናችን በመሆን እየረዱን ይገኛሉ፡፡ በዚህ መሠረት ማኅበራችን ይህንን የአበል ማሻሻያ ጥያቄ ሲያቀርብ ከመነሻው የእያንዳንዱ ከተማ የመኝታና የምግብ ወጪን በመመልከት በጥናት ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡ ይህንንም ጥያቄ ለፌዴሬሽኑ በማቅረብ ማኅበራችን ሰኔ 17 ቀን 2006 ዓ.ም. በቁጥር ኢ/ዳ/ማ/51/06 የጠየቀ ሲሆን የ2006 ዓ.ም. የውድድር መርሐ ግብር ሲያልቅ በፕሪሚየሪ ሊግ ክለቦችና በብሔራዊ ሊግ ዓመታዊ ግምገማ ላይ ጥያቄው ቀርቦ ክለቦች የቀረበው ጥናት ላይ የሚሻሻለውን ተሻሽሎ እንዲላክላቸው ጠይቀዋል፡፡ በ2006 ዓ.ም. የነበረው የዳኝነት ሒደት በማመስገን፣ መሟላት ያለበት እንዲሟላ አነሳሽነት በራሳቸው ጥያቄ በመጠየቃቸው ጥናቱ እንዲሻሻል በማድረግ ነሐሴ 17 ቀን 2006 ዓ.ም. በቁጥር ኢ/እ/ኳ/ዳ/ታ/ሙ/ማ/58/06 በተጻፈ ደብዳቤ ለፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት አቅርበናል፡፡ ማኅበራችን ያቀረበው ጥያቄ ክለቦቹ በሰጡት አቅጣጫ መሠረት በጀት የሚይዙበት ጊዜ ስለሆነ፣ የተሰጠው አቅጣጫ በጽሕፈት ቤት በኩል እንዲገለጽላቸው የሚል ስለሆነ ማኅበራችን የበጀት ወቅቱን ጠብቆ ነበር ጥያቄውን ያቀረበው፡፡ ነገር ግን ለሦስት ወር ያህል ይህ ደብዳቤ ወደ ክለቦቹ ሳይላክ በመቆየቱ፣ መስከረም 26 ቀን 2007 ዓ.ም. ለሦስተኛ ጊዜ በቁጥር ኢ/ዳ/ታ/ሙ/ማ/59/07 ለፌዴሬሽኑ የማስታወሻ ደብዳቤ ጽፈናል፡፡ ጽሕፈት ቤቱ የሰጠው አቅጣጫ ባለመፈጸሙ ሲጉላላ ቆይቶ በዚህ ዓመት መጀመርያ ማለትም ኅዳር 28 ቀን በ2007 ዓ.ም. በሐርመኒ ሆቴል በተደረገው የጠቅላላ ጉባዔ ላይ ዳኞችና ታዛቢዎችን በተመለከተ ከቀረበው ሪፖርት በመሳነት ማኅበራችንን ወክለው የተሳተፉ አባላት ጥያቄውን አቅርበዋል፡፡ የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚና ክለቦቹ በተጠየቁትና በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ከጉባዔው ማብቂያ በኋላ እንዲሰበሰቡ ተደርጎ የብሔራዊ ሊግ ክለቦች በሙሉ በተገኙበት የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት፣ ምክትል ፕሬዚዳንትና የሥራ አስፈጻሚ አባላትና የማኅበሩ አመራር አባላት እንዲሁም የጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ የውድድሮች የሥራ ሒደት ኃላፊ ጭምር በተገኙበትና በተለያዩ ክለቦች ሐሳብ ተሰጥቶበት በተደረሰ ስምምነት መሠረት ውሳኔ ያገኘ ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ፌዴሽኑ እንደማይመለከተው ተደርጎ በሪፖርተር መግለጫ መሰጠቱ አግባብ አይደለም፡፡ እንዲያውም የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊም በስብሰባ ላይ ተገኝተው ውሳኔ እንዲያስፈጽሙ የተሰጣቸው ዓብይ ሥራ መሆኑን እያወቁ የሰጡት አስተያየት ፌዴሬሽኑን ከማኅበሩ ጋር የሚያጋጭ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ የስፖርት ቤተሰቡም ወደ እውነታዊ አመለካከት እንዲመለስ እየጠየቅን፣ ማኅበራችን ሙያ ከማስከበር ባሻገር የአበል ማሻሻያ ጥየቄ አቅርቦ ውሳኔ እንዲያገኝ የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትና ክለቦች ላደረጉልን ድጋፍ ከልብ ለማመስገን እንወዳለን፡፡ ማኅበራችን ከፌዴሬሽኑ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ የሚሠራና ልንሠራም የሚገባን መሆኑን በድጋሚ እንገልጻለን፡፡ (ሚካኤል ዓርአያ ሽፈራው፣ የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ዳኞችና ታዛቢዎች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት) ****** የአዲስ አበባ መንገዶችን ልብ በሉ ሰሞኑን በወጣው ሪፖርተር ላይ የአዲስ አበባ መንገዶች ግንባታ መጓተትን አስመልክቶ የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ የሰጡትን መግለጫ ተመልክቼዋለሁ፡፡ የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ለቀረበላቸው ዋና ዋና ጥያቄ የሰጡት ምላሽ የሚያስገነዝበው በበላይነት የሚመሩትን መሥሪያ ቤት አስመልክቶ ማወቅ ሲገባቸው የማያውቋቸው ብዙ ዓቢይ ጉዳዮች መኖራቸውን ነው፡፡ ለምሳሌ አገሪቱ ያላትን አገር በቀል ኮንትራክተሮች አቅም፣ ተለዋጭ ኮንትራክት የመኖሩንና ያለመኖሩን ጉዳይ፣ የኮብል ድንጋይ መንገድ ዲዛይንን የቀለበት መንገዱን የጥራት ችግር በተመለከተ የሰጡት ምላሽ እንደሥራው ባለቤት ሳይሆን፣ እንደውጭ ተመልካች በመሆኑ፣ ሥራው ባለቤትና መሪ ያለው መሆኑን ለማመን ያጠራጥራል፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጁ የጠቀሷቸው የአቅም ውስንነቶች ባሉበት ሁኔታ በከተማው ውስጥ ያሉት መንገዶች በሙሉ በአንድ ጊዜ መቆፋፈራቸው ከፍተኛ የፕላኒንግ ችግር እንዳለ የሚያመላክት ነው፡፡ የአቅም ውስንነት እስካለ ድረስ የአገሪቱ ሀብት ተሰብስቦ በአንድ አካባቢ የተጀመረ ፕሮጀክት እንዲጠናቀቅ ለማድረግ ማዋል፣ ወደሚቀጥለው መሄድ ሲገባው የከተማውን መንገዶች ሁሉ ቆፋፍሮ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ ከአንድ ትልቅ መሥሪያ ቤት የሚጠበቅ አይደለም፡፡ አንድ ሰው ከቤቱ ሲወጣ ያልተዘጋ መንገድ አግኝቶ መሔድ የሚፈልግበት ቦታ እንዴት መድረስ እንደሚችል አያውቅም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ረዥም መንገድ ከተጓዘ በኋላ መውጫው ላይ ሲደርስ መንገድ (በትራፊክ ምልክት ሳይሆን በድንጋይ ወይም በአፈር ክምር) ተዘግቶ ስለሚያገኘው የመጣበትን ያህል ርቀት ለመመለስ ይገደዳል፡፡ ምናልባት የተዘጋ መሆኑን የሚያሳይ ምልክት መግቢያው ላይ ቢያስቀምጡ፣ ከዚህም በተጨማሪ ዛሬ የተጓዘበትን መንገድ ነገ ተቆፍሮ ስለሚጠብቀው፣ ዕለት ከዕለት በተመሳሳይ ችግር ውስጥ ለማለፍ ይገደዳል፡፡ በአጠቃላይ ባለሥልጣኑ የመገንባት የሚሠራው ሥራ ሁሉ በዕቅድ ሳይሆን በግብታዊነት የሚመራ ይመስላል፡፡ ይኼ እንግዲህ መሥሪያ ቤቱ ከሚያፈራርሰው ባሻገር በጥራት ጉድለት፣ በዝናብና በፀሐይ ምክንያት የሚፈራርሰውን ሳይጨምር ነው፡፡ የከተማው ዋና ዋና መንገዶች ላይ ያሉት ጉድጓዶች ጠንከር ያለ አደጋ የሚያደርሱበት ጊዜም ቀላል አይደለም፡፡ አንድ ወዳጄ አንድ ጊዜ ከውጭ መጥቶ በመንገድ መካከል ያለ ጉድጓድ የመኪናውን እግር ሰብሮት በእርግጥ የሚመለከታቸው ባለሥልጣኖች የሚኖሩት አዲስ አበባ ውስጥ ነው ወይ? ብሎ የጠየቀኝ ይታወሰኛል፡፡ መንገዶች በርካታ ሚሊዮን ገንዘቦች ለግንባታ ከፈሰሰባቸው በኋላ፣ ብዙም ሳይቆዩ ለማፍረስ ሌላ ብዙ ገንዘብ ይወጣባቸዋል፡፡ ለማስተካከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ የሚፈጠረው የመንገድ ችግርና መጨናነቅ ደግሞ በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ ለአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት የሚዘረጋው መንገድም እንዲሁ በጥድፊያ የተጀመረና በሚገባ ያልታደቀ መሆኑን ከሚከተሉት ምክንያቶች የተነሳ እጠራጠራለሁ፡፡ ፕሮጀክቱ የራሱ መንገድ ስላልተቀየሰለትና ከዋና ዋና የመኪና መንዶች ጋር እየተጋፋ ስለሚገነባ ለብዙዎቹ የተሽከርካሪ መንገዶች መፈራረስና መጨናነቅ ምክንያት ሆኗል፡፡ በአማራጭነት ሊታዩ የሚችሉ ብዙ ቅያሶች እያሉ የባቡርና የመኪና መንገዶች ጎን ለጎን ማድረግና የመኪናውን መንገድ ማፍረስ ለምን እንዳስፈለገ አይታወቅም፡፡ የባቡሩ ፕሮጀክት በአሁኑ አያያዝ ‹‹ላም አለኝ በሰማይ›› እንደመሆኑ መጠን አማራጭ እስኪገኝለት ድረስ ዘግይቶ የሚከናወን መንገድ በአግባቡ ብንጠቀምበት ይሻለን ነበር፡፡ በጉዳዩ ላይ እግዚአብሔር ጣልቃ ገብቶ ቢጠናቀቅ እንኳን ባቡሮቹ እንኳን እንዲንቀሳቀሱ የታቀደው በኤሌክትሪክ ኃይል በመሆኑ አሁን ካለው የኃይል አቅርቦት አንፃር ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል ወይ? የሚለው ጉዳይ በበኩሌ ያሳስበኛል፡፡ ቤታችን ውስጥ ያሉትን አምፖሎች ለማብራት እንኳን ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ልብ ልንል ይገባል፡፡ የባቡሩ መንገድ በአብዛኛው የተገነባው በድልድይ መልክ መሆኑ አስፈላጊነት እኔ አልገባኝም፡፡ ምናልባትም ከላይ እንደጠቀስኩት ከመኪና መንገድ ጋር አንድ ላይ እንዲገነባ ስለተፈለገ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ድልድይ ለመገንባት የተጠቀምንባቸው ማቴሪያል አንድ የኮንዶሚኒየም ከተማ መገንባት የሚያስችሉ ከመሆናቸውም በላይ ድልድዮቹ የከተማውን ውበት አበላሽተውታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መገናኛ ያለው ድልድይ ላይ የተፈጠረውን ዓይነት ወይም ሌላ ማንኛውም ችግር ቢፈጠር ለመጠገን ያለው አስቸጋሪነት የታሰበበት አይመስልም፡፡ ምናልባት መኪኖቹ ከላይ ባቡሩ ከሥር ቢሆን ይሻል ነበር? በማንኛውም ጊዜ የባቡር መንገድን የሚያክል ትልቅ ፕሮጀክት ቀርቶ ትንሽ የዘይት ፋብሪካ ለመክፈት ሲታሰብም ቅድመ ጥናት እንደሚደረግ የሚታወቅ ሆኖ ሳለ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ፕሮጀክቱ ሲጠናቀው ሊያስከትል የሚችለውን ችግር በአሁን ወቅት ማጥናቱን፣ ፕሮጀክቱ ችግር እንዳለው ቢያሳይ የሚቀጥለው ዕርምጃ ምን ሊሆን ነው? ለምን ፕሮጀክቱ በፓይለት ደረጃ የተወሰነ ቦታ ላይ ብቻ እንዲጠናቀቅ ተደርጎ ሊያስከትል የሚችለው ችግር አልታየም? የባቡር ሐዲዶቹ ገና ከአሁኑ የሕዝብ መፀዳጃ ሥፍራ የመሆናቸው ጉዳይና ከሕዝቡ ንቃተ ሕሊና አንፃር ሐዲዶችን ያላግባብ ማቋረጥ ሊያስከትል የሚችለው ችግርም ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ የመንገድ ነገር ከተነሳ ከነዳጅ ዋጋ ጋር በተያያዘ ሰሞኑን በከተማው ውስጥ ያለው ትርምስ ሁኔታውን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎታል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ንግድ ሚኒስቴር የሸቀጥ ዋጋ ለማረጋጋት የዋጋ ተመን ካወጣ በኋላ ብዙ የንግድ ሱቆች ታሽገውና የተለያዩ ዕርምጃዎች ተወስደው ሲያበቃ፣ በጀመረው አካሄድ ከመቀጠል ይልቅ ተሸንፎና ውሳኔውን ቀልብሶ ወደኋላ መመለሱ የሚታወስ ነው፡፡ ዋጋ እንዲቀንስ ታስቦ የተወሰደው ዕርምጃ ዋጋ ሊያስቀንስ ቀርቶ ይበልጡኑ ቀድሞ ከነበረበት መጠን በላይ ንሮ፣ ነጋዴዎች መንግሥት ምንም ሊያመጣ አይችልም ብለው ተደላድለው እንዲቀመጡ አደረጋቸው፡፡ አሁንም ያለው ሁኔታ ተመሳሳይ እንዳይሆን ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት ጣልቃ ሲገባ ጣልቃ ገብነቱ ባይሳካ ምንድነው የሚደረገው የሚለውን ጭምር ራቅ አድርጎ ማሰብ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ ነጋዴዎች መንግሥት በተመነው ዋጋ አንሸጥም ቢሉ መንግሥት ራሱ ሸቀጡን በማቅረብ አማራጭ አቅርቦት ሊገኝ የሚችልበትን መንገድ ማሰብ አለበት፡፡ (ዳዊት ወልደኢየሱስ ከአዲስ አበባ) ****** ዜሮ አመራር በላም በረት አውቶብስ መናኸሪያ የአንድ ድርጅት ዋና ዓላማው ቢያንስ የደበኞቹን ፍላጎት በተገቢው ሁኔታ ማሟላት እንደሆነ አጠያያቂ አይደለም፡፡ መንግሥትም ቢሆን ለዚህ ብቁ የሆነ አመራርና አስተዳደር ሊኖረው ግድ ይላል፡፡ እነዚህ ነገሮች በላምበረቱ የአውቶብስ መናኸሪያ አሉ ለማለት ያስቸግራል፡፡ መናኸሪያው በሁከት እየተናጠ ይገኛል፡፡ ለማን ይሆን ሁከት ይታገድልኝ የሚባለውን በእርግጥ ከሁከት አልፎ ሽብር መስሏል፡፡ የላምበረቱ መናኸሪያ በ1996 ዓ.ም. ገዳማ ተጠናቆ በ2006 ዓ.ም. አካባቢ ነው አገልግሎት መስጠት የጀመረው፡፡ አለመታደል ሆኖበት በ1997 ዓ.ም. በተነሳው አገራዊ የምርጫ ውዝግብ የተደናበረው ኢሕአዴግ፣ የመከላከያ ሠራዊቱን አስፍሮበት ስለነበር መናኸሪያው ሳይመረቅ ለዕድሳት ተዳርጓል፡፡ አሁን ደግሞ ገና ከመመረቁ በአመራሩ የብቃት ማነስ መፈራረስ ጀምሯል፡፡ አካባቢውም በሁከት ተበክሏል፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ወደዚህ መናኸሪየ የመጣ ሰው ‹‹የድረሱልን ጥሪ›› የሚያሰሙ በሚመስሉት ትኬት ሻጮች ከመደንገጥ አልፎ መበርገጉ አይቀሬ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ለመሳፈር ወደ መናኸሪያው የመጣ የውጭ አገር ዜጋ ይኼን ጉድ አይቶ ግራ በመጋባቱ፣ ‹‹Are they looking for help›› (የድረሱልኝ ጥሩ እያሰሙ ነው) ብሎ መጠየቁ አሳፍሮኛል፡፡ ቀኑን ሙሉ ሲሰሙትና ሲያዩት ለሚውውት መናኸሪያው አመራሮች ግን ሙዚቃ የሆነላቸው ሳይሆን አይቀርም፡፡ የመናኸሪያው የትኬት መቁረጫ ጉርኖ አሥር ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፣ የፊት ለፊቱ መስኰት በሃያ ሳንቲም ርቀት በቆሙ ቀጫጭን ብረቶች እንደ ስድስት ኪሎው አንበሳ ግቢ ታጥሯል፡፡ ከ30 የማያንሱ ትኬት ቆራጮች ታጉረው ትኬት ለመሸጥ በአንድ ላይ የሲኦል ድምፅ ያሰማሉ፡፡ ምን እንደሚናገሩ እንኳ ማዳመጥ አይቻልም፡፡ ጆሮ ይበጥሳል፡፡ ጩኸታቸው በራሱ ሞገድ ፈጥሮ ይገፈትራል፡፡ እኔም እንደ ዘወትር ተጠቃሚነቴ ጩኸቱን መቋቋም ስላልቻልኩ በሌላ ሰው አማካይነት ትኬት ለማስቆረጥ ተገድጃለሁ፡፡ ሌላ ተጨማሪ ወጪ ማለት ነው፡፡ ጅሩ ለመሄድ ጆሮዬን ማጣት ያለብኝ አይመስለኝም፡፡ በዚህ ላይም የተለመደው ማጭበርበር አለ፡፡ ሕዝብ በሚከፍለው ግብር የመንግሥት ቅጥረኞች ሊያሾፉብን አይገባም፡፡ እነዚህ ጉደኛ ትኬት ቆራጮች እንደ ስድስት ኪሎው አንበሶች ብርቱዎች ናቸው፡፡ እጃቸውን ብቻ በቀጫጭኖቹ ብረቶች መሀል አሾልከው ነው ትኬት የሚሸጡት፡፡ ኋላ ግን ብረቶቹን ገንጥለው ጭንቅላታቸውን ብቅ አደረጉ፡፡ ቀጠሉናም ብረቶቹን ሁሉ ገንጥለው ወገባቸውን አውጥተው እየተውረገረጉ ቤቱንም ይወዘውዙት ጀምረዋል፡፡ በቅርብ ጊዜ ውስጥም አሥር ሜትሩን የብረት መስኮትና ግድግዳ ገንጥለው ጉዳት ሊያደርሱ እንደሚችሉ መናገር ጠንቋይ መሆንን አይጠይቅም፡፡ ከዚያስ ወዴት? ለዚህም ነው በላምበረት አመራር የለውም ከሚል ድምዳሜ ላይ የደረሰኩት፡፡ የሥራ ሒደት ለውጥ፣ ውጤት ተኮር፣ ስኰር ካርድና አንድ ለአምስት፣ መልካም አስተዳደር እያለ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን የሚያደርቀን የት ገባ? በጣም የሚገርመውና እንዲያውም የሚያስደንቀው የመንገድ ላይ የታክሲ ተራ አስከባሪዎች አንዲት ድምፅ ኮሽ ሳይል ማስተናገድ መጀመራቸው ነው፡፡ ለአድናቆታችን ቆባችንን ከፍ አድርገናል፡፡ ሁሉ ነገር በተራ ወይም በወረፋ በሆነበት አገር ሰላም አጣንሳ? ወይስ የላምበረቱን መናኽሪያ የሚመሩት እነዚያ አምባሪቂ (ጯሂ) ትኬት ቆራጮች ይሆኑ እንዴ? (ቀለሙ በዛብህ፣ ከአዲስ አበባ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...