ዶ/ር አዲሱ ገብረ እግዚአብሔር፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ
ዶ/ር አዲሱ ገብረ እግዚአብሔር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ናቸው፡፡ በዓለም አቀፍ ሕግ የዶክትሬት ዲግሪ ያላቸው ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪም በሲቪል ሕግና በኢኮኖሚክ ማኔጅመንት የማስተርስ ዲግሪ አላቸው፡፡ ዘንድሮ ከሚካሄደው አምስተኛ ዙር ጠቅላላ ምርጫ ጋር በተገናኙ በፖለቲካ ፓርቲዎች ቅሬታዎችና ስሞታዎች፣ እንዲሁም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከቦርዱ ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ በገቡት አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና ሰማያዊ ፓርቲ ጉዳይ ላይ ነአምን አሸናፊ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ቦርዱ አምስተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማካሄድ እያከናወናቸው ያሉ ሥራዎች ምን ይመስላሉ? እስካሁን ድረስ በነበሩት ሥራዎች የገጠሙት ችግሮች ምንድናቸው? እንዴትስ ተፈቱ?
ዶ/ር አዲሱ፡- ምርጫ እንደሚታወቀው አንድ አገራዊ ክስተት ነው፡፡ አገራዊ ክስተት ነው የሚባልበት ምክንያት ምንድነው ቢባል የማይሳተፉበት ባለድርሻ አካላት የሉም፡፡ በዋናነት ሕዝቡና ፖለቲካ ፓርቲዎች ይሳተፉበታል፡፡ የግል ዕጩዎችም እንዲሁ አልፎ አልፎ፣ የፍትሕ አካላት፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች፣ የሕዝብ ታዛቢዎችና ጋዜጠኞች የሚሳተፉበት ነው፡፡ ዘንድሮ በግንቦት የሚካሄደውን ምርጫ የተሳካ ለማድረግ ዝግጅት ይፈልጋል፡፡ ዝግጅቱ ቀላል አይደለም፡፡ እነዚህ ሁሉ ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ቀደም ብለን ነው ዝግጅታችንን የጀመርነው፡፡ የዝግጅቱ ምዕራፍ በተለይ አንዱ ከሥልጠና ይጀምራል፡፡ ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት ትምህርትና ሥልጠና በመስጠት፣ የሥነ ዜጋና የመራጮች ሥልጠና በመስጠት፣ ሰፋፊ ሥራዎችን በ2006 ዓ.ም. ስናከናውን ቆይተናል፡፡ 2006 ዓ.ም. የዝግጅት ዓመት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ትምህርት በመስጠትም የምርጫ ቁሳቁስ በማዘጋጀትም፡፡ በተለይ ሥልጠናችን ላይ ዘንድሮ በምናካሂደው ምርጫ ያኔ ስንነጋገር አንደኛ እነማን ናቸው በተለይ የተለየ ትኩረት ከቦርዱ የሚፈልጉ ብለን ስናይ፣ አንዱ መላው ሕዝባችን ነው፡፡ በሥነ ዜጋና በመራጮች ትምህርት ላይ መላው ሕዝባችንን ከጫፍ እስከ ጫፍ ተንቀሳቅሰን ማስተማር እንዳለብን በሰፊው የሄድንበት ነው፡፡ በተለይ ደግሞ የሥነ ዜጋና የመራጮች ትምህርት በአገር ደረጃ የምንሠራው እንዳለ ሆኖ፣ እኛም ራሳችን ታች ወርደን መሥራት እንዳለብን ነው፡፡ በተለይ ተደራሽነቱ ላይ፡፡
የ2002 ምርጫ እንደተጠናቀቀ ምርጫውን ገምግመናል፡፡ የግምገማውን ሪፖርትም አሠራጭተናል፡፡ ምን ነበር ያሳካነው? ምን ነበር ያላሳካነው? ምን ነበር አጠናክረን መቀጠል ያለብን? የሚለውን በዝርዝር ሄደንበታል፡፡ አንዱ አጠናክረን መሄድ የነበረብን ብለን ያሰብነው የሥነ ዜጋና የመራጮች ትምህርት ተደራሽነት ነበር፡፡ በአገር ደረጃ ላይ የምንሰጠው እንዳለ ሆኖ በቴሌቪዥንም፣ በሬዲዮም፣ በጋዜጣም የምንሰጠው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ታች በመድረስ ረገድ ግን መሥራት እንዳለብን ያኔ አጤንን፡፡ ስለዚህ በተለያዩ ቋንቋዎች ራሳችን ወደ ታች በመሄድ የሥነ ዜጋና የመራጮች ትምህርት መስጠት እንዳለብን ያኔ በትክክል ሄድንበት፡፡ በ2006 ዓ.ም. የተሳካ አደረግነው፡፡ ደቡብ ክልል ላይ 32 ቋንቋዎች ተጠቅመናል፡፡ የማኅበረሰብ ሬዲዮ የምንላቸውን በሚገባ ተጠቅመናል፡፡ አፋር ክልል በመሄድ እዚያ ባሉ የተለያዩ ቋንቋዎች፣ ቤንሻንጉል ጠረፍ ላይ ያሉት ዓረብኛ ቋንቋ ነው የሚሰሙት ዓረብኛ ቋንቋ ተጠቀምን፡፡ በአጠቃላይ በአገራችን ያሉ ቋንቋዎችን በተቻለ መጠን በሁሉም መጠቀም ባንችልም፣ አብዛኛዎቹ በሚግባቡበት ቋንቋ ላይ በሰፊው ሄደን ለማሠልጠን የቻልንበት ሁኔታ አለ፡፡ በ2006 ዓ.ም. ያደረግነው ዝግጅት አሁን ፍሬውን እያየነው ነው፡፡ በተለይ የመራጮች ምዝገባ እስከ ሐሙስ ከሰዓት ድረስ [ጥር 7 ቀን 2007 ዓ.ም.] ከ12 ሚሊዮን በላይ ሄዷል፡፡ ይህ ውጤት የሥነ ዜጋና የመራጮች ትምህርት ሥልጠና የመስጠታችን ውጤት ነው፡፡
ሌላው በማኅበር የተደራጁ በተለይ ወጣቶች፣ ሴቶችና መምህራን በሁሉም ክልሎች አዲስ አበባና ድሬዳዋን ጨምሮ በተደራጀ መልኩ ሰጥተናል፡፡ እነዚህ በራሳቸው ሌሎችን ይደርሳሉ ከሚል እምነት ነው፡፡ ወጣቶችን ያየን እንደሆነ በማኅበር በዞንም በወረዳም በቀበሌም የተደራጁ ወጣቶች ስላሉ እነሱን በመድረስ ረገድ፣ ራሳቸውም የአሠልጣኞች ሥልጠና ቢያገኙ መልሰው እነሱም ያሠለጥናሉ የሚል እምነት ወስደን፣ እነሱን በመጠቀም ይህን የሥነ ዜጋና የመራጮች ትምህርት ሥልጠና ሰጥተናል፡፡ የጋዜጠኞች ሚና በዲሞክራሲያዊ ምርጫ አዘጋገብ ላይ በተለይ ትክክለኛ የሆነ እውነታ ያለው ለሕዝብ መድረስ ያለበት መረጃ በማድረስ፣ ጋዜጠኞች ትልቅ ድርሻ አላቸው፡፡ በዚህ እምነታችንን ደግሞ በትክክል ለጋዜጠኞች በዚያ መልኩ የሰጠነው ሥልጠና አለ፡፡
በ2006 ዓ.ም. በሰፊው የሄድንበት ሌላው ነጥብ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉዳይ ነው፡፡ በአመራር ሰጪነት፣ በምርጫ ሕጉ፣ በግጭት አፈታት፣ በተለይ የቅሬታ አፈታት ደረጃ ምን ሊመስል እንደሚችል ሥልጠና ሰጥተናል፡፡ በአጠቃላይ ስናየው በአገር ደረጃ በተለይ ትልቅ ድርሻ ያላቸውን በምርጫው ድርሻ አላቸው የምንላቸውን ባለድርሻ አካላትን በማሠልጠን የአሠልጣኞች ሥልጠና በመስጠት ዘመናዊ የምርጫ መርሆዎችን በተመለከተ፣ የፖለቲካ ፓርቲ አደረጃጀትን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በውስጥ ያላቸውን ግንኙነት ዲሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ ለአገር የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ እንዳለ ስለምናምን፣ ያንን ደግሞ ለማስተባበርና እነዚህንና እነዚህን የመሳሰሉትን ነገሮችን ለመስጠት ችለናል፡፡ የተጓደሉ የምርጫ አስፈጻሚዎችን የመመልመል ሥራ ነበር፡፡ እርሱም አንዱ የዝግጅት ሥራ ተደርጐ የሚወሰድ ምዕራፍ ነበር፡፡ እንደሚታወቀው ምርጫ አስፈጻሚዎች በተለያየ ምክንያት ይጓደላሉ፡፡ ገለልተኛ የሆነና ምርጫን ማስፈጸም የሚችል ብቃት ያለው መልምሎ ማሠልጠን አለ፡፡ ምክንያቱም እንደመለመልን ወደ ምርጫ ሥራ አናስገባቸውም፡፡ እነሱን ደግሞ የማሠልጠንና የማብቃት ሥራ ነው የሠራነው፡፡ በአገር ደረጃ በኅዳር ወር እንኳን በሁሉም ክልሎች ለምርጫ አስፈጻሚዎች ሥልጠና መሰጠቱ የሚታወስ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ የዝግጅት ምዕራፎች ናቸው፡፡ በማሠልጠኑ፣ ምርጫ አስፈጻሚዎችን በመመልመሉና እነርሱን ደግሞ መልሶ ወደ ሥራ በማስገባቱ ረገድ ሰፋፊ ሥራዎች ሠርተናል፡፡
ሌላው የቁሳቁስ አቅርቦት ሥራ ነው፡፡ ይህ በጣም አድካሚ ሥራ ነው፡፡ ሥራው ለሁሉም መራጭ ከ45,000 በላይ የሚሆኑ የምርጫ ጣቢያዎችን ሊደርስ የሚችል ዝግጅትና የመራጮች ካርድ አለ፡፡ የዕጩዎች ሰነዶች አሉ፡፡ የሕዝብ ታዛቢዎች የሚፈርሙበት ሰነድ አለ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰነዶች አሉ፡፡ በአጠቃላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰነዶች በሚገባ አዘጋጅቶ ማተም፣ ማሸግ፣ አሽጐ ደግሞ መላክ እስከ ቀበሌ ጣቢያ ድረስ አንዳንዱ መንገድ ትራንስፖርት አለው፣ አንዳንዱ ደግሞ የለውም፡፡ ስለዚህ ፈረስም በቅሎም የምንጠቀምበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ ወደ አርብቶ አደር አካባቢዎች ግመልም እንጠቀማለን፡፡ እነዚህ ሁሉ ተጠቅመን 45,000 ምርጫ ጣቢያዎች የማድረስ ሥራ ቀላል ስላልሆነ፣ የቁሳቁስ ሥርጭት ሥራው ራሱ በጣም ቀላል ስላልሆነ ይህንን አዘጋጅቶ በመጠበቅና ጊዜው ሲደርስ በጊዜ ሰሌዳው መሠረት የመላክ ሥራም አንዱ የዝግጅት ምዕራፍ ነው፡፡ ይህን ሁሉ ተደምሮ ለ2007 ጠቅላላ ምርጫ የምናደርገው ጉዞ ትልቅ መደላደል የሚፈጥርልን ዝግጅት አድርገናል ማለት ይቻላል፡፡ ከዚያ አኳያ እስካሁን በጥሩ ሁኔታ ላይ እንገኛለን፡፡ ቀጣይ ሥራዎችም ይኖራሉ፡፡ በተለይ ምርጫ አስፈጻሚዎቻችን የመጀመሪያውን ዙር ሥልጠና የወሰዱት በመራጮች ምዝገባ፣ በዕጩዎች ምዝገባ ላይና በሰነዶች አያያዝና አጠቃቀም፣ በምርጫ አስፈጻሚዎች ሥነ ምግባርና በበጀት አጠቃቀም ላይ ያተኮረ ሥልጠና ነው የተሰጠው፡፡ ሁለተኛ ዙር ደግሞ ጊዜው ሲደርስ የሚመጣ ነው፡፡ እርሱ ደግሞ በድምፅ አሰጣጥ፣ በድምፅ ቆጠራና ውጤት አገላለጽ ላይ የሚሉትን ደግሞ ወደ በኋላ የምንመጣበት ነው፡፡ እስካሁን ባለን አካሄድ በጣም ጥሩ ነው ብለን መውሰድ እንችላለን፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ደግሞ በማስመዝገብ በጊዜ ሰሌዳው መሠረት ምልክቶቻቸውን ወስደዋል፡፡ 60 የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ እነዚህ 60 የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ ዕጩዎቻቸውን እያስመዘገቡ ይገኛሉ፡፡ መራጮችም እየተመዘገቡ ይገኛሉ፡፡
ሪፖርተር፡- በተለይ የቁሳቁስ ሥርጭትን የተመለከቱ ሥራዎችንና አጠቃላይ ሒደቱን የተቃና ለማድረግ ከፍተኛ የሆነ ወጪ ያስፈልጋልና የዘንድሮ ምርጫ ወጪ ምን ያህል ነው? ካለፈው ጋር እንዴት ይነፃፀራል?
ዶ/ር አዲሱ፡- ቦርዱ የጠየቀው በጀት አለ፡፡ እስካሁን ምን ያህል በጀት ተጠቅመናል? ምን ያህል ቀርቶናል? ምን ያህልስ ነው? የሚለው ነገር የተለየ የፋይናንስ ሪፖርት ስለሚጠይቅ በአሁኑ ጊዜ ይህን የበጀት አጠቃቀምና አሁን ያለን አካሄድ በይበልጥ የሚያውቁት ፋይናንሶች ናቸው፡፡ ማለት የምችለው ግን የመራጮች ቁጥርና የፖለቲካ ፓርቲዎችም ተሳትፎ በአጠቃላይ ያለው ሁኔታ ስለሚታወቅ፣ ካለፈው ጠቅላላ ምርጫ አሁን ከፍ ያለ በጀት እንደሚሆን ግን ታሳቢ ይሁን፡፡
ሪፖርተር፡- ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የቦርዱን ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባሉ፡፡ ቦርዱ ደግሞ በማስረጃ አስደግፈው የቦርዱን ገለልተኛ አለመሆን አስረዱ ይላል፡፡ ነገር ግን እርስዎ እንደ ቦርዱ ምክትል ሰብሳቢነትዎ የምርጫ ቦርድን ገለልተኝነት እንዴት ማረጋገጥ ይችላሉ?
ዶ/ር አዲሱ፡- ገለልተኝነት እንደ ቦርድ እንደ ሕገ መንግሥታዊ ተቋም በተለያየ ጊዜ ለፖለቲካ ፓርቲዎችና ለሚመለከታቸው አካላት ለማስረዳት ሞክረናል፡፡ አሁንም ይህ ጥያቄ ቢነሳ ይህን ጥያቄ መመለስ ይቻላል፡፡ ገለልተኛ መለኪያው ሥራ ነው፡፡ ከሥራ በላይ ሊናገሩ የሚችሉ ቃላት የሉም፡፡ ገለልተኝነትን የሚያስረዳ ቃላት ሊኖሩ ሊደረደሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን እኛ ከቃላት በዘለለ ተግባሮቻችን ቢለኩ እነርሱ መልስ ይሆናሉ ነው በተደጋጋሚ ስንል የነበረው፡፡ እንግዲህ ወደኋላ መለስ ብለን እንመልከት፡፡ አዋጅ 532 ቦርዱ ገለልተኛ መሆን አለበት፣ ገለልተኛ የሆነ ተቋም ነው ይላል፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያለው የቦርዱ አባላት ሁሉም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 102 መሠረት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚሾሙ ዘጠኝ አባላት ይኖሩታል ይላል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መሥፈርቱን የሚያሟሉ ሰዎች ለቦርድ አባልነት ለምክር ቤት ከማቅረቡ በፊት፣ በምክር ቤቱ መቀመጫ ያላቸው ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ዕጩ ሊሆኑ የሚችሉ ግለሰቦች ነፃና ገለልተኛ መሆናቸውን በማረጋገጥ ጉዳይ ላይ፣ ተሳትፎ እንዲኖራቸው የሚያስችል የምክክር መድረክ እንዲኖር ይደረጋል ይላል፡፡ አሁን ያለነው የቦርድ አባላት ስንመረጥ የኮሚቴው ሰብሳቢ የነበሩት የተቃዋሚ ፓርቲ ፕሬዚዳንት የነበሩ ናቸው፡፡ እርሳቸውም አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ናቸው፡፡ እሳቸው የሰበሰቡት ኮሚቴ ዕጩ አድርገው ምክክር ተደርጎና መቀመጫ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ያኔ በፓርላማ ምክክር አድርገው፣ ዘጠኛችን ገለልተኛ መሆናችንን ዓይተውና መርምረው ያቀረቡት ዋናው የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ቡልቻ ናቸው፡፡
ገለልተኛ ናቸው ብለው በአንድ ድምፅ ወስነው ፓርላማ ላይ የቀረብነው የማንም ፖለቲካ ፓርቲ አባል አይደለንም፡፡ ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ መሆን እንዳለብን አዋጁ ያሰምርበታል፡፡ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ወገንተኝነት ነፃ ነን፡፡ ሦስተኛ ደግሞ የሙያ ብቃት ያላቸውና በመልካም ሥነ ምግባራቸው የሚታወቁ መሆን አለባቸው ይላል፡፡ በእነዚህ አራት መሥፈርቶች ዘጠኛችን ቀርበን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ልንሾም ችለናል ማለት ነው፡፡ ይህ የሕጉ መርህና አካሄድ ነው፡፡ በተግባር ስንመጣ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲደራጁ በወጣው አዋጅ መሠረት ነው ለሁሉም ፓርቲዎች ዕውቅና የምንሰጠው፡፡ ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዳንዱን በተለየ ሕግ ሌላውን በተለየ መሥፈርት አሟልተው እንዲመጡ የምንጠይቅበት ሁኔታ የለም፡፡ ዕውቅና ስንሰጣቸው በአንድና አንድ አዋጅ ነው፡፡ ስለዚህ ይኼ አንዱ ሥራችን ነው፡፡ ዕውቅና ስንሰጣቸው የሚጠየቀው ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በአንድ መሥፈርት ነው፡፡ ሁለተኛ በምርጫ ሲወዳደሩ ይፋዊ መግለጫ ሰጥተን ነው፡፡ ፓርቲዎች መጥተው ዕጩዎቻቸውን ሲያስመዘግቡ ሁሉ በእኩልነት ነው የሚስተናግዱት፡፡ በእኩልነት ተስተናግደውና ዕጩዎቻቸውን አስመዝግበው፣ ችግር ያለባቸው ደግሞ ቅሬታ አቅርበው ቅሬታቸውን ፈተን እንዴት አመስግነውን እንደሚሄዱ እኛ እናውቀዋለን፡፡
ሥልጠና ስንጠራ በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት ነው፡፡ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የስም ዝርዝራቸው አለ፡፡ ማኔጅመንት ማሠልጠኛ ተቋም ገብተው ሥልጠና ወስደው አመስግነው እንዴት እንደሄዱ ይታወቃል፡፡ የፋይናንስ ድጋፍ ስናደርግ በፍትሐዊነትና በእኩልነት መሥፈርት ለሁሉም በትክክል የሚሠራጭበት አሠራር ነው ያለው፡፡ ወደ አየር ሰዓት ስንመጣ እንዲያውም በ2002 ዓ.ም. ምርጫ ኢሕአዴግን ጨምሮ የተሰጣቸውን የአየር ሰዓት መጠቀም አልቻሉም፡፡ መቶ በመቶ የተጠቀመ አንድም የፖለቲካ ፓርቲ የለም፡፡ ለፖለቲካ ፓርቲዎች የተሰጠው የአየር ሰዓት ከመብዛቱ የተነሳ ሊጠቀሙበት አልቻሉም፡፡ ቅሬታቸውን ስንፈታ ከእነርሱ ጋር ታች ወረዳና ቀበሌ ድረስ በመሄድ ነው፡፡ ቅሬታቸውን በመፍታትና ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ በማድረግ አኳያ ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ያስተናገድንበት ሥራ ይኼ ነው፡፡ ይህንን በቃላት አይደለም እየተናገርኩ ያለሁት፡፡ ይህንን ተግባሩ መናገር አለበት፡፡ ከቃላት ይልቅ ተግባሮቻችን በይበልጥ ይናገራሉ፡፡ ሌላው የሥነ ምግባር አዋጅ ከመውጣቱ በፊት ስናወያያቸው ቦርዱ ገለልተኛ ነውና ቦርዱ ያወያየን ብለው ሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች አዳራሽ ውስጥ የተናገሩት፡፡ ይህም በመገናኛ ብዙኃን የተገለጸ ነው፡፡
ስለዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቦርዱ ገለልተኛ አይደለም ሲሉ መገለጫውንስ ምነው አብረው ቢያቀርቡ፡፡ አንድ ነገር እኮ መገለጫ አለው፡፡ ገለልተኛ አይደለም ሲባል ምክንያቱም በዚህ በዚህ ተብሎ ይቀርባል፡፡ ገለልተኛ ማለት እኮ እንዲሁ ቃላት ብቻ አይደለም፡፡ በደምሳሳው ገልጸህ የምታልፈው ጉዳይ አይደለም፡፡ ገለልተኛ ያልሆነበት ምክንያት አንድ እዚህ ላይ፣ ሁለት እዚህ ላይ፣ ሦስት እዚህ ላይ ተብሎ በዝርዝር ይቀርባል፡፡ እንግዲህ በጽሕፈት ቤታችን ላይ መዓት ቅሬታ ያቀርባሉ፡፡ ምነው ይህንንስ አብረው ቢያቀርቡ ነው እኮ የእኛ ጥያቄያችን፡፡ እኛም እንማርበታለን ነው በግልጽ የምንለው፡፡ ሁላችንም ተማምረን ወደሚቀጥለው ምዕራፍ እንሸጋገራለን፡፡ ስለዚህ ገለልተኛ አይደለም የሚለውን ቋንቋ እኛም መማር እንድንችል ለፖለቲካ ፓርቲዎች ሁልጊዜ የምናስተላልፈው መልዕክት ምኑ ጋ ነው ገለልተኛ ሳንሆን ሥራችንን የሠራነው? አሁን እኛ በጣም የሚገርመው በዚህ ቋንቋ ላይ ተንተርሰን መፈላሰፍ አንችልም፡፡ ምን ሊሆን ይችላል ብለን ራሳችንም እናያለን፣ እንፈትሻለን፡፡ አሁን በቅርቡ ለምሳሌ ይፋ በሆነው የፋይናንስ ድጋፍ ቀመር መሠረት ከዚህ በፊት መጀመሪያ የፋይናንስ ድጋፍ ስንጀምር በ2002 ምርጫ 55 በመቶ ለወንበር፣ 25 በመቶ ዕጩ ላቀረበ፣ አሥር በመቶ ሴት ዕጩዎችን ላቀረበና አሥር በመቶ ደግሞ በእኩልነት መሥፈርት ነበር፡፡
በሌሎች አገሮች ለምሳሌ በደቡብ አፍሪካ 90 በመቶ ለወንበር፣ አሥር በመቶ ደግሞ በእኩልነት ነው የሚከፋፈሉት፡፡ ይህን ተግባራዊ እናድርግ ብንል ፖለቲካ ፓርቲዎች ተጠቃሚዎች ይሆናሉ? አይሆኑም፡፡ ስለዚህ ምንድን ነው ያደረግነው 55 በመቶ የነበውን አወረድነው፡፡ ዘንድሮስ ምንድነው ያደረግነው? ዘንድሮ የወንበር 35 በመቶ አደረግነው፣ ለዕጩ 40 በመቶ አደረግነው፣ ለሴት ዕጩ 15 በመቶ አደረግነው፣ በእኩልነት አሥር በመቶ አደረግነው፡፡ ይህ ማንን ለመጥቀም ነው? እንግዲህ ለወንበር ቢሆን ማን ነው የሚጠቀመው የሚለው ነው፡፡ ስለዚህ አሳታፊነትን ለማበረታታት በተግባር ፓርቲዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ በተግባር ገለልተኝነታችን ይገለጻል፡፡ ስለዚህ ገለልተኛ አይደለም ሲባል የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በአንዳንዶቹ ከፖለቲካ ፓርቲዎችም ግለሰቦች አሉ፡፡ ሁሉም ፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ያለ ሁሉ ማለት አይደለም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ያሉ ግለሰቦች ናቸው ቦርዱ ገለልተኛ አይደለም የሚሉት፡፡
ሪፖርተር፡- በተደጋጋሚ ወደ ቦርዱ የሚቀርቡ አቤቱታዎች አሉ፡፡ ዘንድሮ እንኳን ብንመለከት የሕዝብ ታዛቢዎች ምርጫ ይደገም ከሚለው ጀምሮ ሌሎች በርካታ ጥያቄዎች ይቀርባሉ፡፡ ከዚህ አንፃር እነዚህን ጥያቄዎች በበቂ ሁኔታ ከማስተናገድና ከመመለስ አንፃር ቦርዱ በቂ ሥራ ሠርቷል ብላችሁ ታምናላችሁ?
ዶ/ር አዲሱ፡- ለፖለቲካ ፓርቲዎች አጽንኦት ሰጥተን ለቀናት ሥልጠና የሠጠነው በምርጫ ሒደት ስለሚነሱ አቤቱታዎችና ክርክሮች ቅሬታ አፈታት ላይ ነው፡፡ ለምን ምርጫ ሲቃረብ ስሞታዎች ይበዛሉና፡፡ ቅሬታዎች የሚበዙት ቅሬታዎች ስላሉ አይደለም፡፡ ግን ቅሬታ የሚያቀርቡ ፓርቲዎች ከዚህም ከዚያም ስለሚመጡ የእነርሱን ጥያቄ ለማስተናገድ የቅሬታ አፈታት ደረጃ አለው፡፡ በሕጋችን መሠረት ምዕራፍ ስምንት ላይ በመራጮች ምዝገባ ሒደት ስለሚነሱ ክርክሮች፣ በዕጩዎች ምዝገባ ሒደት ስለሚነሱ ክርክሮች፣ በምርጫ ውጤት ስለሚነሱ ክርክሮች፣ በድምፅ አሰጣጥ ሒደት ስለሚነሱ ክርክሮች፣ በቆጠራ ሒደት ስለሚነሱ ክርክሮች፣ በምርጫ ውጤት ስለሚነሱ ክርክሮች ሁሉም ደረጃ አለው ዓይነትም አለው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች እነዚህ ቅሬታዎች ሲያጋጥሟቸው ለምን ያነሳሉ አይደለም እየተባለ ያለው፡፡ ሲያነሱ ግን ሕጉን መሠረት አድርገው በየደረጃው ማቅረብ አለባቸው፡፡ ሁለተኛ ማስረጃ አያይዘው ያቅርቡልን ነው፡፡ ስሞታ ወይም ቅሬታ በማስረጃ ተደግፎ ካልመጣ ሕጉን መሠረት አድርገን ውሳኔ የምንሰጥ አካል ነን፡፡ ውሳኔ ለመስጠት ማስረጃ ያስፈልጋል፡፡ በሕግ ቋንቋ ስሞታ ስለመጣ እርሱን መሠረት አድርገህ ውሳኔ አትሰጥም፡፡ ለምሳሌ የሕዝብ ታዛቢዎች ምርጫ አንዳንዶቹ ፓርቲዎች በጠቅላላ ለአገሪቱ ያለው የሕዝብ ታዛቢዎች አመራረጥ ሕጉን መሠረት ያደረገ ስላልሆነ በድጋሚ ምርጫ ይካሄድ ነው ያሉት፡፡ ወደ 250,000 የሚሆኑ የሕዝብ ታዛቢዎች እንደገና ይመረጡ ነው እያሉ ያሉት፡፡ 250,000 ገለልተኛ ስላልሆኑ ነው? ወይስ የተወሰነ ቦታ ላይ ቅሬታ አላቸው? ማስረጃ ያላቸው ጉዳይ አለ? ወይም ለሁሉም ማስረጃ አላቸው? እንዲህ ዓይነት ክስ ሲመጣ ምንድነው የሚደረገው? በአገሪቱ ያለውን የሕዝብ ታዛቢዎች ምርጫ በድጋሚ አድርጉት ነው እኮ ያሉት፡፡
የወጣ የጊዜ ሰሌዳ አለ፡፡ ይኼ ቀልድ አይደለም፡፡ በቦርዱ የተወሰነ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ አለ፡፡ ከፓርቲዎች ጋር ባደረግነው ውይይት የፀደቀ ነው፡፡ ቦርዱ ያፀደቀውን የጊዜ ሰሌዳ አንድ የሆነ የፖለቲካ ፓርቲ ተነስቶ ሊሰርዘው ይችላል? እንደዚህ ዓይነት አካሄድ አለ? ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ነው? ጥያቄያቸውን ያቅርቡ፡፡ ግን በአገሪቱ ያሉት የሕዝብ ታዛቢዎች ምርጫ እንደገና ካልተመረጠ የሚል አካሄድ አነጋገሩ በመሠረቱ የሕግም ፍሬ ነገር የለውም፡፡ እዚህ እዚህ ቦታ ላይ ጥያቄ አለን ብለው ማስረጃ አያይዘው ቢመጡ ከዚህ በፊትም እኮ ዕርምጃ ወስደናል፡፡ ዕርምጃ የምንወስድበት ሁኔታ እኮ አለ፡፡ ቦርዱ ዕርምጃ መውሰድ የሚችለው ግን ማስረጃ ይዘው ሲቀርቡ ነው፡፡ ስለዚህም ምርጫ ሲደርስ እንደዚህ ዓይነት ወከባዎች ምንድን ናቸው ሲባል፣ እኔ ከአንዳንዶቹ ቅን ህሊና ከማጣት የተነሳ ነው እላለሁ፡፡ የምርጫውንም ሒደት ለማበላሸት ከመፈለግ ካልሆነ በስተቀር እዚህ ጋ ማስረጃ አለኝ፡፡ እናም እስቲ ዕርምጃ ውሰዱልኝ፡፡ እስቲ እዩልኝ ብሎ የመጣ የፖለቲካ ፓርቲ የለም፡፡ ሕዝብ ራሱ ጆሮዬና ዓይኔ ይሆንልኛል ብሎ የሚመርጠውን የሕዝብ ታዛቢ መጥታችሁ ታዘቡ ብለን በመገናኛ ብዙኃን ነው መግለጫ የሰጠነው፡፡ የጊዜ ሰሌዳ በእጃቸው አለ፡፡ መቼ ቀን የሕዝብ ታዛቢዎች እንደሚመረጡ ያውቃሉ፡፡ ያን የጊዜ ሰሌዳ መሠረት አድርገው በሚወዳደሩበት ጣቢያ ላይ በመገኘት የሕዝብ ታዛቢዎች እንዴት እንደሚመረጡ ክትትል ማድረጉ ደግሞ የእነሱ ድርሻ ነው፡፡ በመገናኛ ብዙኃን ጥሪ አድርገናል፡፡ በተጨማሪ ደግሞ እጃቸው ላይ የጊዜ ሰሌዳው አለ፡፡ አንዱ ጥሪ አልተደረገልንም ያሉት ይህ እኮ ድብቅ አይደለም፡፡ በመገናኛ ብዙኃን ጥሪ አድርገናል፡፡ ሁሌ እንደምናደርገው በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የጊዜ ሰሌዳው አለና እንዲህ ዓይነት ክሶች የምርጫውን ሒደት ለማበላሸት ካልሆነ በስተቀር፣ ተጨባጭነት ያለው ወደ ቢሮአችን የገባ ማስረጃ ያለው ጉዳይ የለም፡፡
ሪፖርተር፡- በተደጋጋሚ እንደገለጹልኝና እንዳብራሩት ፓርቲዎቹ የሚተዳደሩት በአዋጁ መሠረት ነው ብለዋል፡፡ ነገር ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተደጋጋሚ ውሳኔና መግለጫ ስትሰጡበት የነበረው የመኢአድና የአንድነት ጉዳይ አለ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ወቀሳ እያቀረቡ ያሉት ግለሰቦች ናቸው፡፡ አንድነትም ሆነ መኢአድ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ የተወሰኑ ግለሰቦች መጥተው ተቃውሞ ስላቀረቡ አሁን ፓርቲዎቹ ጠቅላላ ጉባዔ እንዲጠሩ አዛችኋልና ይህንንስ እንዴት ማስታረቅ ይቻላል?
ዶ/ር አዲሱ፡- የሚተዳደሩበትን ደንብ አርቅቀውና አፅድቀው ለቦርዱ የሚሰጡት ፓርቲዎቹ ናቸው፡፡ የምርጫ አዋጁ እኛ ዘንድ አለ፡፡ ፓርቲዎች ግን ሕገ ደንብ በማውጣት ረገድ ግን የራሳቸው ሥራ ነው፡፡ ፓርቲዎች ራሳቸው ያፀደቁትን ሕገ ደንብ ማክበር ያለባቸው ራሳቸው ናቸው፡፡ እኛም ደግሞ ሕጉ በቦርዱ ፀድቆ ሥራ ላይ ከዋለ ጀምሮ የምንከታተላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ራሳቸው ባፀደቁት የውስጥ ሕገ ደንብ ነው፡፡ በፓርቲዎች የውስጥ መተዳደሪያ ደንብ፡፡ ይህን ሕገ ደንባቸውን መሠረት እናደርጋለን፡፡ ለምንሰጣቸው ውሳኔዎች አንደኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅን፣ ሁለተኛ የራሳቸው መተዳደሪያ ደንብን መሠረት አድርገን ነው ሥራዎቻችንን የምንሠራው፡፡ አሁን ወዳነሳኸው ጥያቄ ልምጣ፡፡ ይህን መሠረታዊ መርህ ላስቀምጥና አንድነት ፓርቲ በሕጉ መሠረት ፕሬዚዳንት መምረጥ ያለበት በጠቅላላ ጉባዔው ነው ይላል፡፡ የራሳቸው መተዳደሪያ ደንብ የሚለው ነው፡፡ እነርሱ ጠቅላላ ጉባዔን ወደ ጐን ትተው ብሔራዊ ምክር ቤት ተነሳና ፕሬዚዳንት መርጫለሁ አለ፡፡ አፅድቀው ወደ እኛ ሲመጡ ብሔራዊ ምክር ቤት የመረጠው ፕሬዚዳንት ነው፡፡ ቦርዱ እንዲህ ዓይነት ነገር አይቀበልም፡፡ የራሳችሁ መተዳደሪያ ደንብ የሚለው ጠቅላላ ጉባዔ ፕሬዚዳንት ይመርጣል ነው፡፡ ብሔራዊ ምክር ቤት አሁን መርጦ የላከልንን ፕሬዚዳንት ዕውቅና ልንሰጥ አንችልም፡፡ ነገ ደግሞ አንዱ ተነስቶ እኔ ፕሬዚዳንት ነኝ ሲል ቦርዱ ሊቀበለው ነው ማለት ነው፡፡ ሕግን በጣሰ መንገድ የሚሻርም ሆነ የሚመረጥ ተቀባይነት የለውም፡፡ ለዚያ ነው አስቀድመን የምንጠይቃቸው፡፡ ማን በማን እንደሚመረጥና እንዴት እንደሚመረጥ በሕገ ደንባቸው አስፍረው ሲያመጡልን እርሷ ፋይላችን ነች፡፡ እርሷን መሠረት አድርገን ነው እያንዳንዱን እንቅስቃሴያቸውን የምንከታተለው፡፡ በዚህ መሠረት ነው፡፡ እነርሱም የሚጓዙት በዚያው ነው፡፡ ስለዚህ ቦርዱ ገለልተኛ አይደለም እንዲህ ነው እንዲያ ነው ይላሉ፡፡ የራሳችሁ ሕገ ደንብ ይከበር ስላልን እኛ ምሥጋና ይገባን እንደሆነ እንጂ፣ እንዴት አድርጐ ነው እኛን ማጥላላት የሚቻለው? የራሳቸውን ሕገ ደንብ በማክበራችን ቦርዱ ገለልተኛ አይደለም ይላሉ፡፡ ቀድሞውኑ ቦርዱ ነው እንዴ ያወጣው? የእነሱን ሕገ ደንብ ቀድሞውኑ ያወጡት እኮ ራሳቸው የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ናቸው፡፡ ቀድመው ያወጡትን ሕግ ደግሞ እነርሱ ባያከብሩ ቦርዱ ያከብረዋል፡፡ ሁለት ሌላ አርቅቀናል ብለው ያረቀቁትን ሕገ ደንብ መጥቀስ ጀመሩ፡፡ ማን ዕውቅና ሰጥቶት? ያለው ሳይሻር ሌላ ሕገ ደንብ ማውጣት ይቻላል እንዴ? ያልተሻረውን ሕግ በራሳቸው ሽረው በቦርዱ ያልፀደቀውን ሕገ ደንብ መጥቀስ ጀመሩ፡፡ ይህ እንዴት ይሆናል? ሕግ በሌላ ሕግ ካልተሻለ በስተቀር ተፈጻሚ እንደሆነ ይቆያል፡፡ ስለዚህ በዚህ መንገድ ችግሮቻችሁን በውስጥ ፈታችሁ ወደ ቦርዱ ቅረቡ የሚል ነው፡፡ ውስጣቸውም አልገባንም፡፡
በዚያ በኩል ደግሞ እንዳልከው ከፓርቲዎች እስከ ቀጣና ዞን አስተባባሪዎች ያሉበት ይህንን በመቃወም ለጽሕፈት ቤቱ አቅርበዋል፡፡ እነርሱም በራሳቸው ጥያቄያቸውን እያቀረቡ ነው፡፡ ግለሰቦች ናቸው የሚለውን ጉዳይ የግለሰቦች የሕግ ጥያቄ መሰማት የለበትም የሚል አካሄድ የለም፡፡ ፓርቲው ነው እንዳይባል የትኞቹ ናቸው የፓርቲው አባላት? ዕውቅና ያለውን ፓርቲ ዕውቅና አልጠየቅንም፡፡ ቦርዱ በተደጋጋሚ ይህን ጉዳይ እያሰመረበት ነው የሄደው፡፡ ፓርቲው እንደ ፓርቲ የሕግ ሰውነት አለው፡፡ ዕውቅና ያገኘ ፓርቲ ነው፡፡ እኛ እያልን ያለነው አመራሩን ነው፡፡ ለአመራሩ የተሰጠው የሕግ ዕውቅናና ለፓርቲው የተሰጠውን የሕግ ዕውቅና ለያይተን ማየቱ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ፓርቲው ውስጥ የመጡት አመራሮች በየትኛው የሕግ አካሄድ ነው የመጡት ነው ጥያቄያችን፡፡ እነዚህም እኮ የፓርቲው አባላት ናቸው፡፡ አመራር ላይ የነበሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ሕጉ ተጥሷል ሕጉ ይከበር ብለው ነው ጥያቄ ያቀረቡት፡፡ እነዚያ ደግሞ ፕሬዚዳንት መርጠናልና ዕወቁልን አሉ፡፡ ሕገ ደንባችሁን መሠረት ያደረገ አይደለም ተባሉ፡፡ ቦርዱ ጣልቃ ገባብን አሉ፡፡ በየትኛው ነው ጣልቃ የገባነው? ጣልቃ መግባት ማለት እንዲህ አይደለም፡፡ ሕገ ደንባቸው እንዲከበር ማድረግ የቦርዱ ሥራ ነው፡፡ ኃላፊነታችን ነው፡፡ ስለዚህ ለራሳቸው ሕገ ደንብ እነርሱ ካልተገዙ እኛ እንደ እነርሱ መሆን አንችልም፡፡ ሕገ ደንባቸውን እናከብራለን፡፡ ደግሞም እናስከብራለን፡፡ በመኢአድም ቢሆን ተመሳሳይ ጉዳይ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ቦርዱ ታህሳስ 10 እና 28 ቀን 2007 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ አንድነትና መኢአድ የውስጥ ችግሮቻቸውን ፈተው ይቅረቡ የሚል ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡ እንዲሁም ጥር 5 ቀን 2007 ዓ.ም. የቦርዱ ትዕዛዝ አልተከበረም በሚል ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. ሁለቱ ፓርቲዎች ባደረጉት ጠቅላላ ጉባዔ የተመረጡትን ፕሬዚዳንቶች ቦርዱ እንደማይቀበልና ተጨማሪ የሁለት ሳምንት የመጨረሻ የጊዜ ገደብ ሰጥቷል፡፡ የፓርቲዎች ዕጩዎች ምዝገባ ደግሞ የሚጠናቀቀው ጥር 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ነው ከዚህ አንፃር ሁለቱ ፓርቲዎች ዝግጅታቸውን አጠናቀው እንዴት ሊወዳደሩ ይችላሉ?
ዶ/ር አዲሱ፡- እኛን የሚገዛን ሕጉ ነው፡፡ በስሜታችን፣ በራሳችን አስተሳሰብና ፍላጐት የምንሄድበት አንድም ኢንች አይኖርም፡፡ ምክንያቱም በፍላጐት፣ በስሜትና በአስተያየት የሚሆን ነገር የለም፡፡ ዋናው ትልቁ ገዥው ሕግ ነው፡፡ ከፓርቲዎች ጋር ስንገናኝ ለሁለቱም ያነሳነው ጥያቄ የሕግ ጉዳይ ነው፡፡ እስከ መጨረሻው የሕግ ጉዳይ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ የመጨረሻ ዕድል የተሰጣቸው ባለፈው መግለጫ የሁለት ሳምንት ጊዜ ለምንድን ነው እነዚህ ተጨማሪ ቀናት እየተሰጡ ያሉት የሚለውን ማሳወቁ አስፈላጊ ነው፡፡ ቦርዱ በዚህም ይሁን በሌላ ጉዳይ በጣም ይወያያል፡፡ ትልልቅ ውይይቶችና ፍጭቶች አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ክርክሮች ዞሮ ዞሮ ወደ መቋጫው ሲመጡ የፓርቲዎችን በምርጫ ላይ ተሳታፊነትን የሚያበረታቱ ናቸው፡፡ ፓርቲዎች የዲሞክራሲውን ሒደት ከማጐልበትም አኳያ፣ እንዲሁም ከጀርባ ያለውን ሕዝብ በማየት ሆደ ሰፊነትን መርጧል፡፡ ዝም ብሎ እንዲሁ የተዘለለ ጉዳይ አይደለም፡፡ እነዚህን ሁሉ ከግምት ውስጥ አስገብተን ተጨማሪ ጊዜ መስጠት በመርህ ደረጃ ክፋት ያለው ሆኖ አናየውም፡፡ ሕዝብንና የዴሞክራሲውን ዕድገት ዓይተን፣ የፓርቲዎችንም የውስጥ ጉዳይ በማየት ዕድል በመስጠት ችግሮቻቸውን ይፈታሉ በሚል እምነት ነው፡፡ እነዚህን ሁሉ ከግምት ውስጥ አስገብተን ነው አሁንም ሁለት ሳምንት የሰጠነው፡፡ ስለዚህ ለግንቦት ምርጫ አሁን ጥር ላይ ነው ያለነው፡፡ ወራት አሉ፡፡ ዕጩ የማስመዝገቢያ ጊዜ ደግሞ የቀሩት ቀናት አለ፡፡ ስለዚህ ፓርቲዎች በዚህ ጊዜ ነገራቸውን አስተካክለው የቦርዱን ትዕዛዝ ብቻም ሳይሆን የራሳቸውን ሕገ ደንብ አክብረው ከመጡ ቦርዱ የሚወያይበት ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ቦርዱ የበላይ አስተዳዳሪ ነው፡፡ ስለዚህ በሰጠው ትዕዛዝ ላይ ውይይት አድርጐ ውሳኔ ማሳለፍ የቦርዱ ሥልጣን ነው፡፡ ስለዚህ ለፓርቲዎቹ ያለን ምክር ምንድነው? በዚች ሁለት ሳምንት ጊዜ ወስደው ጠቅላላ ጉባዔያቸውን በተናጠል ከሚሆን በጋራ ጠርተው ችግሮቻቸውን ፈተው ለእኛ ካቀረቡልን እሰየው ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በቅርብ ጊዜ ቦርዱ በሚሰጣቸው መግለጫዎች ላይ የምትጠቀስ አባባል አለች፡፡ ‹‹ሆደ ሰፊነት›› የምትባል፡፡ እርስዎ ደግሞ በተደጋጋሚ እንደገለጹት የመጫወቻ ሜዳው የሚዳኘው በሕግ ነው ይላሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ‹‹ሆደ ሰፊነት›› ማለት ምን ማለት ነው?
ዶ/ር አዲሱ፡- የሕጉን መርህ ማንም የሚጥስ የለም፡፡ ሕጉን እናከብራለን፡፡ ሕጉን በማክበር ጉዳይ ሁለት ሦስት ቋንቋዎችም የሉም፡፡ አንድ ቋንቋ ነው ያለው፡፡ ሕጉን የማክበርና የማስከበር ብቻ፡፡ ከሕጉ ጀርባ ሕዝብ አለ፡፡ ሕጉ ላይ አንድም ጥሰት እያደረግን አይደለም ያለ ነው፡፡ ሕጉን እያስከበርን ነው ያለነው፡፡ ሕጉን እንዲያከብሩ ነው ተጨማሪ ጊዜ እየሰጠን ያለነው፡፡ ሊስማሙ ስላልቻሉ ነው ቦርዱ ተጨማሪ ጊዜ እየሰጣቸው ያለው፡፡ መልሰው መላልሰው ሕጉን ማክበር እንዲችሉ ነው፡፡ አሁን ጊዜያት እየጨመርን ፓርቲዎቹ በመሀላቸው የተፈጠረው ቅራኔ ምናልባት በአንድ ጊዜ አይፈታም በሁለት ጊዜ አይፈታም፡፡ እኛም ሁለቱን ፓርቲዎች ለማስማማት ሞክረናል፡፡ በተለይ በአንድነት ፓርቲ በኩል አንደኛው ወገን ቁጭ ብለን አንወያይም ብሎ ረግጦ ወጥቷል፡፡ እኛ ይህን ሁሉ እያደረግን ያለነው ከመስመር ወጥተን ነው፡፡ በመካከላቸው ያለውን ቅራኔ ፈትተው እንዲመጡ ለማድረግ ነበር ከመስመር ወጥተን እያመቻቸን የነበረው፡፡ እነዚህ ሁሉ ‹‹ሆደ ሰፊነት›› የምንላቸው ከመስመር ወጥተን የምናስተናግዳቸው ያለነው፣ ሁለቱም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕጉን ተመልሰው ዓይተው አክብረው እንዲመጡ ለማስቻል ነው፡፡ ሁለተኛ ለፖለቲካ ፓርቲዎች 23 ዓመታት የሞላው የዲሞክራሲ ዕድገት ነው ያለው፡፡ ፍፁም ዴሞክራሲያዊ የሆነ አስተሳሰብ ነው ይኼ ‹‹ሆደ ሰፊነት›› የምንለው፡፡ አንድን ነገር ከመስመር ወጣ ብሎ ማስተናገድ ለዴሞክራሲው ሲባል ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ምርጫ ሲደርስ በርካታ ስሞታዎችና ቅሬታዎች ወደ ቦርዱ ይመጣሉና እንዲህ ዓይነት ተቃውሞዎች፣ ክሶችና ቅሬታዎች ምርጫው ሲደርስ ከመፈጠራቸው በፊት እንዳይከሰቱ ከፓርቲዎች ጋር ውይይት ይካሄዳል? ተካሂዶ ያውቃል? ተካሂዶስ ከሆነ ውጤቱ ምን ነበር?
ዶ/ር አዲሱ፡- በአዋጁ መሠረት ቦርዱ የሚያዘጋጀው የፓርቲዎች የጋራ መድረክ የሚባል አለ፡፡ የጋራ ምክር ቤት ሌላ ነው፡፡ እኛ የምናዘጋጀው ግን የጋራ መድረክ የሚባል ነው፡፡ በጋራ መድረክ ላይ የፓርቲዎቹን ጉዳይ ነው የምናየው፡፡ ከፓርቲዎች ጋር ሰፋፊ የሆኑ መድረኮች አሉን፡፡ በዚህም ብቻ ሳይሆን በምናካሂዳቸው ሥልጠናዎች ላይ ሰፋፊ ውይይቶች ነው የምናደርገው፡፡ ባለፈው ዓመት በርካታ ጉዳዮች አንሰተን ነው ስንወያይ የነበረው፡፡ አስቀድመን እነዚህን መድረኮች የምናዘጋጃቸው አንደኛው ፓርቲዎች በምርጫ ወቅት የሚሠሩትን፣ የሚያደራጁትን፣ የሚያዘጋጁዋቸውን ነገሮች ሁሉ ምርጫ ተኮር እንዲሆኑ ከማድረግ አኳያ ነው፡፡ ሁለትም ችግሮችም ካሏቸው አስቀድመው መፍታት የሚችሉበት በየደረጃው ያለውን የቅሬታ አፈታትን አውቀው እንዳመጡ ከማስቻል አኳያ ነበር፡፡ ይገርማል አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች እኮ ችግር ውስጥ የሉም፡፡ ሥራዎቻቸውን እየሠሩ እኮ ነው፡፡ ከ75 የፖለቲካ ፓርቲዎች 60ዎቹ ምልክት ወስደዋል፡፡ ከ60ዎቹ ከሁለቱ ጋር ብቻ ነው እየተነጋገርን ያለነው፡፡ ሌሎቹ ሥራቸውን እየሠሩ ነው ያሉት፡፡ ይህ ማለት ምን ማለት ነው? ቦርዱ ያዘጋጀው ሥልጠና ጠቅሟቸዋል ማለት ነው ብዬ ነው የምወስደው፡፡ ጥያቄ ያነሳ ሁሉ ክስ ነው ማለት አይደለም፡፡ ይህ ተቋም የሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊያስተናግድ የተቋቋመ ነው፡፡ ምርጫ ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን፣ ሕዝብ ተሳታፊ እንዲሆን፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑና የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ደግሞ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት እንዲቋቋም የማድረግ ዓላማ ያለው ተቋም ነው፡፡ ስለዚህ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጥያቄዎች መምጣታቸው ጤናማ ነው፡፡ ጥያቄው ላይ አይደለም ችግሩ፡፡ እዚህ እሰጥ አገባ ውስጥ የምንገባው ሕግ አክብሩ በሚል ጉዳይ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ተመልከታቸው ሥራቸውን እየሠሩ ዕጩዎቻቸውን እያስመዘገቡ ነው ያሉት፡፡ ጥያቄ እያቀረቡ ያሉት ወይም ቦርዱን እየከሰሱ ያሉት በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡
ሪፖርተር፡- ቦርዱ ታህሳስ 28 ቀን 2007 ዓ.ም. ለሰማያዊ ፓርቲ በጻፈው ደብዳቤ ፓርቲው የቦርዱን የተለያዩ ስብሰባዎች ረግጦ በመውጣቱና ከዘጠኝ ፓርቲዎች ጋር ትብብር በመመሥረቱ፣ እንዲህ ዓይነት የሕግ አሠራር የለም በሚል ቦርዱን በጽሑፍ ይቅርታ እንዲጠይቅ አዞ ነበር፡፡ ነገር ግን ቦርዱ አንድን ፓርቲ ይቅርታ ይጠይቀኝ የሚልበት የሕግ መሠረት ምንድነው?
ዶ/ር አዲሱ፡- በሥልጡን ማኅበረሰብ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አዳብራለሁ የሚል የፖለቲካ ፓርቲ፣ የሕዝብን ይሁንታ አግኝቼ ሥልጣን ይዤ መንግሥት እመሠርታለሁ የሚል የፖለቲካ ፓርቲ ይቅርታ መጠየቅ ባህሪው ሊሆን ይገባል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ከምሥረታው ወቅት ጀምሮ የተለያዩ ነገሮችን ሲያደርግም እያስተዋልን፣ ነገር ግን ከትናንት ዛሬ ከዛሬ ደግሞ ነገ ይሻላል በሚል ብዙ ነገሮችን ታግሰናል፡፡ ባለፈው የተካሄዱ ስብሰባዎች ግን ረግጦ መውጣቱ ብቻ አይደለም፡፡ ሌሎቹም ረግጠው እንዲወጡ የማስተባበር ሥራ ነው ሲሠራ የነበረው፡፡ ይኼ ደግሞ በሥነ ምግባሩም ሆነ በፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ መሠረት አንቀጽ ተጠቅሶ ሕግን መሠረት አድርጐ ነው የተጻፈለት፡፡ በተለይ ፓርቲው ከምሥረታው ወቅት ጀምሮ በቦርዱ ተመዝግቦ ዕውቅና ሳይሰጠው እንደተቋቋመ በማስመሰል መግለጫዎችን ሲያወጣና ሕዝቡን ግራ ሲያጋባ እንደነበር ማስታወስ ይቻላል፡፡ ከተቋቋመ በኋላም ፓርቲው የተለያዩ አፍራሽ ተግባሮች ውስጥ እየተሳተፈ መሆኑ ቢታወቅም፣ ቦርዱ በሆደ ሰፊነት አሁንም ከዕለት ተዕለት እያሻሻለ ይሄዳል በሚል ቢመለከትም በዚህ ተግባሩ በቀጣይም ገፍቶበታል፡፡ እነዚህ ተደምረው ቦርዱ ተወያየ፡፡ ሲወያይ ደህና በሕጉ መሠረት ጥፋቱን ለፈጸመ ሰው ወይም የፖለቲካ ፓርቲ ይፋ ማስጠንቀቂያ መስጠት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው ዕርምጃ እያለ እስከ መጨረሻው ቢኬድ የፖለቲካ ፓርቲው በምርጫ እንዳይሳተፍ እስከማገድ የሚያደርስ የሕግ ድንጋጌ አለ፡፡ ይኼንን የሕግ ድንጋጌ ተግባራዊ ማድረግ ቀላል ነው፡፡ ግን ለፓርቲው የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ አንጽፍም፡፡ ፓርቲው ይቅርታ ይጠይቅ ሲባል ለፓርቲውና ከፓርቲው ጀርባ ላለው ሕዝብ ታስቦ ነው፡፡ ይቅርታ አልጠይቅም አለ የፖለቲካ ፓርቲው፡፡ ይቅርታ የማይጠይቅ ከሆነ የሚቀጥለውን አካሄድ መተግበር ነው፡፡ እርሱም ይፋ ማስጠንቀቂያ መስጠት ነው፡፡ እርሱም ተደርጓል፡፡ በዚያ ከገፋበት ደግሞ የሚቀጥሉ ዕርምጃዎች አሉ፡፡ ግን የእኛ እምነት ይህ የፖለቲካ ፓርቲ ሕግ ተጠቅሶ ከተጻፈለት ይታረማል የሚል እምነት አለን፡፡
ሪፖርተር፡- ፓርቲው የሚያነሳው የመከራከሪያ ነጥብ አለ፡፡ ይህም የፓርቲው ጥያቄ ለቦርዱ በቀረበ በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ምላሽ ካላገኘ ተቀባይነት እንዳገኘ ይቆጠራል የሚል የሕግ አንቀጽ በመጥቀስ ያስረዳል፡፡ ይህስ እንዴት ይታያል?
ዶ/ር አዲሱ፡- ይህ እውነታ የሌለው አካሄድ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ነገር ግን የአዋጁን አንቀጽ እየጠቀሱ ነው የሚያስረዱት?
ዶ/ር አዲሱ፡- ገባኝ፡፡ አንቀጹን የፖለቲካ ፓርቲው ለክሱና ለአካሄዱ እንዲመቸው የጠቀሰው እንጂ፣ እኛ የፖለቲካ ፓርቲውን ስናስተናግድ አሟልቶ እንዲገኝ የጠየቅነው ጥያቄ አለ፡፡ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ዕውቅና ለማግኘት ሲንቀሳቀስ በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ መሠረት አሟልቶ እንዲገኝ የሚጠየቅ ነው፡፡ የመመሥረቻ ጽሑፍ፣ ሕገ ደንብ፣ የጠቅላላ ጉባዔ አባላት እነማን እንደሆኑ፣ የፓርቲው ስያሜና ዝርዝር ጉዳዮች አሉ፡፡ እነዚህን አሟልቶ እንዲገኝ፡፡ ምክንያቱም ሳያሟላ የሚቀርብባቸው ሁኔታ ነበር፡፡ ሳያሟላ የሚቀርብ የፖለቲካ ፓርቲ አሟልቶ እንዲቀርብ ጊዜ ይሰጠዋል፡፡ ፓርቲው ያንን ደምሮ ነው ሦስት ወራት አልፎታልና በራሴ ዕውቅና አውጃለሁ ቢል ሕጋዊ አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- የእናንተ ቦርድ ቆይታ ከሁለት ዓመት በኋላ ይጠናቀቃል፡፡ ዘንድሮ የሚካሄደው ምርጫ የመጨረሻችሁ ነው የሚሆነው፡፡ በነበራችሁ ጊዜ ምን አሳካን? ምን ጐደለን ትላላችሁ? እናንተን ለሚተኩ ግለሰቦች ከተቋማዊ አሠራር አንፃር ምን አቅዳችኋል? በዚህ መሥሪያ ቤት ትታችሁት የምታልፉት ነገር ምን ይሆናል?
ዶ/ር አዲሱ፡- አሁን በሥራ ላይ ያለነው የቦርድ አባላት ወደዚህ ቤት ስንመጣ ያየናቸውና ያገኘናቸው ስኬቶች አሉ፡፡ በተለይ እኛ እስክንመጣ ድረስ ሦስት ጠቅላላ ምርጫ የተካሄደበት ጊዜ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ የ2000 የአካባቢ ምርጫ ጀመርን፡፡ በ2002 ዓ.ም. ጠቅላላ ምርጫ አካሄድን፡፡ በ2005 ዓ.ም. ደግሞ የአካባቢ ምርጫ አደረግን፡፡ አሁን ደግሞ ዘንድሮ የ2007 ጠቅላላ ምርጫ ለማካሄድ ዕድሉን አገኘን ማለት ነው፡፡ አንዱ እዚህ ቤት ያገኘነው እነዚህን ሦስት ጠቅላላ ምርጫዎች በሚገባ አካሂዶ ያስረከበን ቦርድ ጠንካራ የቁሳቁስ ማንቀሳቀስ ሥራ ሲያከናውን እንደነበርና ያንን ደግሞ ወስደን ያየናቸው ክፍተቶች እየሞላን ቀጠልን ማለት ነው፡፡ እስካሁን ድረስ በነበረን ቆይታ ያሳካነው አንዱ ነገር ተቋማዊ ለውጥ ማምጣት ነው፡፡ ተቋማዊ ለውጥ መገለጫ አለው፡፡ አንደኛ የሰው ኃይሉ ነው፡፡ የሠለጠነ፣ የተማረ፣ በትክክል ገለልተኛ ሆኖ ምርጫን ለማስፈጸም የሚችል ተቋም ከማድረግ አኳያ የውስጡ ጥንካሬ በሚገባ መርምረንና ፈትሸን ያንን ወደተሻለ ደረጃ አድርሰናል፡፡ ሌላው የሕግ ማዕቀፎች ናቸው፡፡ ሦስት አዋጆች፣ 16 ደንቦችና መመርያዎች፣ የዚህ አዋጅ ዝርዝር፣ የደንቦቹ ዝርዝር መመርያዎችና በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ አንድም ጉዳይ ሳይቀር በሚገባ የሠራንበት ሁኔታ አለ፡፡ ዝርዝር የምርጫ ሕጉን ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ያከፋፈልንበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ይህ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ አንድ ተቋም ተቋማዊ ለውጥ አመጣ የሚባለው በአደረጃጀት ብቻ አይደለም፡፡ በአሠራርም ነው፡፡ ሌላው የሥነ ዜጋና የመራጮች ትምህርት የሥራ መመርያ ሠርተናል፡፡ አሁን በስሜት አይደለም ሰው ሥነ ዜጋና የመራጮች ትምህርት የሚያስተምረው፡፡ አሁን ወጥ የሆነ የመራጮችና የሥነ ዜጋ ትምህርት የሥራ መመርያ አለን፡፡ ያ ደግሞ ከአሠራር አኳያ ተቋማዊ ለውጥ ለማምጣት እጅግ ትልቅ ሚና ያለው ነው፡፡