– አቤቱታቸውን በጽሑፍ እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ተሰጠ
ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፈራረስ፣ ከግንቦት 7 እና ዲምሕት (ትሕዲን) ከሚባሉ ቡድኖች አመራሮች ጋር በህቡዕ በመገናኘት ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል በሚል ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችና ግለሰቦች፣ በእስር ላይ በሚገኙበት ማረሚያ ቤት ስርቆት እንደተፈጸመባቸው ለፍርድ ቤት ያቀረቡት አቤቱታ በዕለቱ እየተቀረፁ ያስመዘገቡ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ እንዳልተቀረፁ ወይም የተቀረፀበት ካሴት ባዶ መሆኑ እንደተነገረው ጥር 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ገለጸ፡፡ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በአንድነት፣ በዓረናና በሰማያዊ ፓርቲ አራት አመራሮችና ስድስት ግለሰቦች ላይ የመሠረተውን ክስ እየመረመረ የሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት መዝገቡን ቀጥሮ የነበረው፣ ተጠርጣሪዎቹ በማረሚያ ቤት ተሰርቀናል ብለው ያቀረቡትን አቤቱታ፣ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ከመቅረፀ ድምፅ ተገልብጦ እንዲሰጠውና ምላሹን ይዞ እንዲቀርብ ነበር፡፡ የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር በትዕዛዙ መሠረት ለመፈጸም አቤቱታውን ለመውሰድ ጥረት ያደረገ ቢሆንም፣ አቤቱታው ባለመቀረፁ ምላሽ መስጠት አለመቻሉን እንዳስታወቀም ፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡ በመሆኑም ተጠርጣሪዎቹ በጽሑፍ ማቅረብ የሚችሉ ከሆነ ተጠይቀው ጠበቃቸው አቶ ተማም አባቡልጉ ጥር 14 ቀን 2007 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤት በኩል እንደሚያስገቡ አሳውቀዋል፡፡ የማረሚያ ቤት አስተዳደርም ከጽሕፈት ቤት ወስዶ ምላሹን እንዲያቀርብ ለጥር 26 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀደም ብለው ካደረጉት የክስ መቃወሚያ ክርክር ጋር ለብይን ተቀጥሯል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ በእስር ላይ በሚገኙበት የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ታህሳስ 12 ቀን 2007 ዓ.ም. ከሌሊቱ 8፡00 ሰዓት እስከ ታህሳስ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀኑ 5፡00 ሰዓት ድረስ፣ የማረሚያ ቤቱ ባልደረቦች ባልሆኑ ነገር ግን እነሱ ማዕከላዊ ማረፊያ ቤት በነሩበት ጊዜ ይመረምሯቸው በነበሩ የደኅንነትና የፌዴራል ፖሊስ አባላት ተፈትሸው ስርቆት እንደተፈጸመባቸው ለፍርድ ቤቱ ማመልከታቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡