Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሐኒከን ቢራ በኢትዮጵያ ሊመረት ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

ዋሊያ የተባለውን ቢራ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ያስተዋወቀው ሐኒከን፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆነውን ሔኒከን ቢራ ለማምረት በዝግጅት ላይ መሆኑን ይፋ አደረገ፡፡ ኩባንያው ይህንን ይፋ ያደረገው ባለፈው ሐሙስ በአዲስ አበባ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በቂሊንጦ አካባቢ ያስገነባውን ቢራ ፋብሪካ ሲያስመርቅ ነው፡፡ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና የሐኒከን ግሩፕ የቦርድ ሊቀመንበርና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጂያን ፍራንቻይስ ቫን ቦዝሚር ተገኝተዋል፡፡ ኩባንያው በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆነውን ሐኒከን ቢራ በዚሁ ፋብሪካ በሚቀጥለው ዓመት ማምረት እንደሚጀምር የገለጹት፣ የኩባንያው የአፍሪካና የመካከለኛው ምሥራቅ ፕሬዚዳንት ሴፕ ሒምስትራ ናቸው፡፡ የሐንኪን ቢራ በአፍሪካ በተለይም በምዕራብ አፍሪካ ተወዳጅ መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ የአዲስ አበባው ፋብሪካ የሐኒከን ቢራን ለኢትዮጵያ ከማቅረብ ባሻገር ለምዕራብ አፍሪካ አገሮች ለማቅረብም ዕድሉን እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡ ሐኒከን ወደ ኢትዮጵያ የገባው እ.ኤ.አ. በ2011 ሐረርና በደሌ የተባሉትን የመንግሥት ቢራ ፋብሪካዎች በ200 ሚሊዮን ዶላር በመግዛት ነበር፡፡ ኩባንያው ሁለቱን ኩባንያዎች በገዛበት ወቅት የነበራቸው የማምረት አቅም 600,000 ሔክቶ ሊትር እንደነበር የገለጹት የሐኒከን ኢትዮጵያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጆዋን ዶየር ናቸው፡፡ ሁለቱ ቢራ ፋብሪካዎች በአሁኑ ወቅት የማምረት አቅማቸው 900 ሺሕ ሔክቶ ሊትር መድረሱን ተናግረዋል፡፡ በቂሊንጦ የሚገኘውን የከርሰ ምድር ውኃ በመጠቀም ዋሊያ ቢራን ማምረት የጀመረው አዲሱ ፋብሪካ፣ በዓመት 1.5 ሚሊዮን ሔክቶ ሊትር የማምረት አቅም አለው፡፡ ዋሊያን ለማምረት የሚያስፈልገውን የገብስ ምርት ከአካባቢው ገበያ ለመግዛትም ከስድስት ሺሕ ገበሬዎች ጋር ኩባንያው በጋራ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ምርጥ ዘሮችን ያለመጠቀምና ኋላቀር የግብርና ዘዴ በገብስ ጥራት ላይ ተፅዕኖ ያሳደረ ቢሆንም፣ ይህንን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችለውን ፕሮጀክት ነድፏል፡፡ እ.ኤ.አ. 2017 ድረስ እስከ 20,000 ቶን የገብስ ምርት ከገበያው ዋጋ በላይ ለመረከብና ከ20,000 ገበሬዎች ጋር ለመሥራት ዕቅድ መያዙ ታውቋል፡፡ የተመረቀው ቢራ ፋብሪካ 280 የአገር ውስጥ ሠራተኞችን የቀጠረ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ዘጠና በመቶ የሚሆኑት በቢራ ኢንዱስትሪ ውስጥ ምንም ዓይነት ልምድ የሌላቸው ናቸው፡፡ በመሆኑም ናይጄሪያ በመላክና ባለሙያዎችን ከውጭ በመጥራት ሥልጠና እንዲያገኙ ማድረጉ ተገልጿል፡፡ በሁኔታው የተደሰቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የሁለትዮሽ ጥቅምን ያረጋገጠ ኢንቨስትመንት መሆኑን ጠቅሰው፣ ቢሮአቸው ምንጊዜም ለኩባንያው ክፍት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች