Sunday, April 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት በባለአደራ ቦርድ እንዲመራ ተወሰነ

ተዛማጅ ፅሁፎች

– ባለአደራ ቦርዱ አዲስ ምርጫ እስኪደረግ በጊዜያዊነት ይሠራል

 የንግድ ሚኒስቴር የሚመራው ባለአደራ ቦርድ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቱን እንዲረከብ ተወሰነ፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ ባለፈው ዓመት አካሂዶት የነበረውን ዘጠነኛ መደበኛ ጉባዔ ድጋሚ እንዲጠራና እንደ አዲስ የፕሬዚዳንት፣ የምክትል ፕሬዚዳንትና የቦርድ አባላት ምርጫ እንዲካሄድ ውሳኔ ተላልፏል፡፡ ይህንን ውሳኔ የሰጠው የኅብረት ኢንሹራንስ ኩባንያንና የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን ጉዳይ ሲመለከት የቆየው የፌዴራል መጀመርያ ፍርድ ቤት ነው፡፡ በሁለቱ ወገኖች መካከል በነበረው ክርክር ፍርድ ቤቱ ቀደም ብሎ ግንቦት 11 ቀን 2006 ዓ.ም. በዋለው ችሎት፣ ንግድ ምክር ቤቱ ባለፈው ዓመት ያካሄደው ዘጠነኛ ጠቅላላ ጉባዔና በጉባዔው የተላለፉት ውሳኔዎች መሻራቸውን ውሳኔ በመስጠቱ፣ በዚህ ውሳኔ መሠረት የፍርድ አፈጻጸሙ ተግባራዊ እንዲሆን በመጠየቁ ነው፡፡ በዚሁ ጉዳይ ሁለቱም ወገኖች ያላቸውን ሐሳብ በማቅረብ ተከራክረዋል፡፡ ኅብረት ኢንሹራንስ ዘጠነኛው ጠቅላላ ጉባዔ በድጋሚ እንዲጠራና አዲስ የቦርድ አባላት፣ የፕሬዚዳንትና የምክትል ፕሬዚዳንት ምርጫ እንዲደረግ፣ ጠቅላላ ጉባዔውም የንግድ ምክር ቤቱ መሥራች ጉባዔ ባፀደቀው ቀመርና የውክልና ሥርዓት እንዲከናወን ጠይቆ ነበር፡፡ አሁን ያለውም ቦርድ ሥልጣን የሌለው በመሆኑ ድጋሚ የሚጠራው ጉባዔ እስኪካሄድ ድረስ፣ የንግድ ምክር ቤቱ የዕለት ተዕለት ተግባር የውጭ ኦዲተርን ያካተተ ባለአደራ ቦርድ እንዲቋቋም ጠይቆ ነበር፡፡ ንግድ ምክር ቤቱም ኅብረት ኢንሹራንስ ያቀረበውን ሐሳብ በመቃወም የአዲስ አበባ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ባለአደራ ቦርድ ሆኖ እንዲሠራ የሚያስችለው የሕግ አግባብ የሌለው በመሆኑ፣ አሁን ያሉት የቦርድ አባላት እንደ ባላደራ ቦርድ ሆነው እንዲሠሩና አዲስ ቦርድ ማቋቋሙ አስፈላጊ አለመሆኑን ጠቅሶ ተከራክሯል፡፡ ኅብረት ኢንሹራንስ በድጋሚ ባቀረበው አቤቱታ ተጠባባቂ ባለአደራ ቦርድ እንዲሾም ሥልጠኑ የፍርድ ቤቱ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ባለአደራ ቦርድ ሆኖ እንዲሾም ለንግድ ሚኒስቴርና ለኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ትዕዛዝ ይሰጥልኝም ብሎ ነበር፡፡ ይህንንም ሐሳብ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ተቃውሞ፣ ነገር ግን በአዲስ አበባ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ በኩል ተፈጻሚ እንዲሆን ጠይቋል፡፡ እንዲህ ያሉ ሰፋ ያሉ ክርክሮችን በማስተናገድ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ውሳኔ ዘጠነኛው ጠቅላላ ጉባዔ በድጋሚ እንዲጠራና ይህንንም ለማድረግ የንግድ ሚኒስቴር የሚመራው ባለአደራ ቦርድ እንዲቋቋም አዟል፡፡ በንግድ ሚኒስቴር የሚመራው ባለአደራ ቦርድም ከአዲስ አበባ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮና ከኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት የተውጣጡ አባላትን ያካተተ ሊሆን እንደሚገባ ፍርድ ቤቱ አዟል፡፡ ታኅሳስ 10 ቀን 2006 ዓ.ም. የተደረገው ዘጠነኛው መደበኛ ጉባዔ በፍርድ ቤት ውሳኔ የተሻረ በመሆኑና በዚህ ጉባዔ የተላለፉ ውሳኔዎች በመሻራቸው፣ ንግድ ምክር ቤቱን በጊዜያዊነት የሚያስተዳድርና በድጋሚ ዘጠነኛ ጉባዔውን የሚጠራ ባለአደራ ቦርድ ሊቋቋም ይገባልም ብሏል፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ በድጋሚ ዘጠነኛው መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ እንዲጠራ ተደርጎ ሕጋዊ ሥርዓትን በተከተለ መልኩ በአባላቱ ቦርዱ ሊመረጥ ይገባል ተብሏል፡፡ ጉባዔው ተደርጎ ንግድ ምክር ቤቱን የሚያስተዳድሩ የቦርድ አባላት ተመርጠው ተረክበው ማስተዳደር እስኪጀምሩ ድረስ፣ ንግድ ምክር ቤቱን የሚያስተዳድር የባለአደራ ቦርድ ሊመረጥ የሚገባ መሆኑን ችሎቱ አስታውቋል፡፡ የባለአደራ ቦርድ ሊቋቋም የሚገባው ደግሞ የንግድ ምክር ቤትን ዓላማ እንዲያሳካ፣ ተግባሩንም በአባላቱ መብትና እምነት ላይ ጉዳት ሊያደርስ በማያስችል ሁኔታ ሊሆን እንደሚገባም መዝገቡ ያሳያል፡፡ የሚቋቋመው ቦርድ የተቋቋመበትን ዓላማ ተረድቶ ተግባሩን ማከናወን ይችል ዘንድ ደግሞ፣ ገለልተኛ የንግድ ምክር ቤቱን ተግባርና ዓላማ የሚያውቅና የሚረዳ ሊሆን እንደሚገባ ያመለከተው ፍርድ ቤቱ፣ የሚቋቋመው ቦርድ በሕግ ሥልጣን በተሰጠው የበላይ ሆኖ የንግድ ሥራውን በሚቆጣጠረው የመንግሥት አካል በኢፌዲሪ የንግድ ሚኒስቴር በኩል ሊመረጥና ሊመራ የሚገባ ሆኖ እንዳገኘውም ይገልጻል፡፡ በዚህ የባለአደራ ቦርድ በአዋጅ ቁጥር 341/95 ፈቃድ የሚሰጠውና ውሳኔውን የሚመዘግበው የአዲስ አበባ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ፣ እንዲሁም ንግድ ምክር ቤቱ አባል የሆነበት የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ተካተው የባለአደራ ቦርዱ ሊቋቋም የሚገባ በመሆኑ፣ በዚህ መንገድ የባለአደራ ቦርድ እንዲቋቋምም ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ የባለአደራ ቦርዱ በዚህ ትዕዛዝ መሠረት ለመፈጸም፣ ተጨማሪ ትዕዛዝ ከፈለገም ለችሎቱ እንዲያሳውቅ፣ እንዲሁም ፍርድ ቤቱ ግንቦት 11 ቀን 2006 ዓ.ም. ባዋለው ችሎት የሰጠው ፍርድ አብሮ እንዲላክለት አዟል፡፡ ፍርድ ቤቱ እንዲሻር ውሳኔ ያሳለፈበት ንግድ ምክር ቤቱ ታኅሳስ 10 ቀን 2006 ዓ.ም. ያደረገው ዘጠነኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔና በዚሁ ጉባዔ የተላለፉት ውሳኔዎች ተመዝግበው ከሆነ ሊሰረዙ የሚገባ በመሆናቸው፣ የጉባዔውን ውሳኔ የመዘገቡት አካላት እንዲሰርዙት ጭምር ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች