ከተገኙት ቅሪተ አካላት መካከል አሥራ አንዱ የሰው ልዩ ልዩ አካል ክፍል ሲሆኑ፣ ዝርያቸው የጠፋና አሁንም ያሉ እንስሳትም ይገኙበታል፡፡ የአፍሪካ የፈረስ ዝርያ፣ ቀጭኔ፣ አውራሪስ፣ ዝሆን፣ አሳማና የዝንጀሮ ቅሪቶችና የድንጋይ መሣሪያም ይገኙበታል፡፡ ዶ/ር ብርሃኔ እንደተናገሩት፣ ግኝቶቹ በወቅቱ የነበሩትን ሰው፣ እንስሳትና መሣሪያዎች በጥልቀት ለማጥናት ይረዳሉ፡፡ ዶክተር ብርሃኔ፣ ‹‹በሰው ልጅ አመጣጥ ታሪክ እጅግ አስፈላጊ የሆነውን ክፍተት ሞልተናል፤›› ብለዋል፡፡ ግኝቱ የሰው ልጅ አመጣጥን ታሪክ ለመረዳት እንደሚያግዝና ለዘርፉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም አክለዋል፡፡ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሩ አቶ አሚን አብዱልቃድር በበኩላቸው፣ ግኝቱ ለቀጣይ ጥናትና ምርምር ከሚኖረው አስተዋጽኦ በተጨማሪ አገሪቷን የበለጠ ያስተዋውቃል ብለዋል፡፡