Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለኢትዮጵያዊው ሕልፈት ምክንያት ኢቦላ አለመሆኑን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ማረጋገጫ ሰጠ

ለኢትዮጵያዊው ሕልፈት ምክንያት ኢቦላ አለመሆኑን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ማረጋገጫ ሰጠ

ቀን:

በኢቦላ ቫይረስ ተጠርጥሮ የነበረው ኢትዮጵያዊ ሕልፈት ምክንያት ኢቦላ አለመሆኑን፣ ከአገር ውስጥ በተጨማሪ በውጭ አገር ላብራቶሪ ምርመራ ውጤት መረጋገጡን፣ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጥር 8 ቀን 2007 ዓ.ም. አስታወቀ፡፡ የኢቦላ ወረርሽኝ በምዕራብ አፍሪካ በመከሰቱ ምክንያት በግል ኢንተርናሽናል ሪስኪው ኮሚቴ (IRC) በተሰኘ ዓለም አቀፍ ድርጅት ከሦስት ወራት በፊት ወደ ሴራሊዮን ያመራው የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያው አቶ አንበሳው በላይ፣ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰው ከ19 ቀናት በፊት እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ ባለሙያው ወደ አገር ውስጥ ሲገባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ምርመራ እንደተደረገለትና ምንም ዓይነት ትኩሳት እንዳልነበረው፣ ከዚያም ለተከታዮቹ አሥራ አምስት ቀናት የጤና ባለሙያዎች እያገኙት ትኩሳቱን ሲከታተሉ ጤናማ የነበረ ቢሆንም፣ በአሥራ ስድስተኛው ቀን ላይ በድንገት ራሱን መሳቱን የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶ/ር ከተሰብርሃን አድማሱ ጥር 6 ቀን 2007 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች ገልጸው ነበር፡፡ ባለሙያው ራሱን በመሳቱ ምክንያት ምናልባት ኢቦላ ይሆናል የሚል ጥርጣሬ በመፈጠሩ፣ ወዲያው ለኢቦላ ሕክምና ወደተዘጋጀ ማግለያ ማዕከል ተወስዶ ምርመራ እንደተደረገለት ታውቋል፡፡ ቤተሰቦቹ፣ ያገኛቸው የነበሩ የቅርብ ጓደኞቹና ፍቅረኛው ኢቦላ መሆን አለመሆኑ እስኪረጋገጥ ድረስ ከሰው ጋር እንዳይገናኙና በቤት ውስጥ ተጠብቀው እንዲቆዩ መደረጉን ሚኒስትሩ ተናግረው ነበር፡፡ በወቅቱ በአገር ውስጥ ላብራቶሪ በተደረገ ምርመራ ውጤት ሙሉ በሙሉ ኢቦላ ሳይሆን፣ የጭንቅላት ወባ (Cerebral Malaria) እንደሆነ እርግጠኛ መሆን ቢቻልም፣ ይበልጥ እርግጠኛ ለመሆን አሜሪካ ወደሚገኘው ሲዲሲ (Center for Diseases Control) የሕመምተኛው ደም መላኩም ተገልጾ ነበር፡፡ ሕመምተኛው ባለፈው ረቡዕ ማለዳ ሕይወቱ ያለፈ ሲሆን፣ የሲዲሲ ውጤት በ48 ወይም በ72 ሰዓታት ውስጥ እስኪደርስ በሚል አስከሬኑ ለቤተሰብ ሳይሰጥ መቆየቱን፣ የተገለሉት ቤተሰቦቹና ጓደኞቹም በሕክምና ባለሙያዎች በየሰዓቱ የሰውነት ሙቀታቸው እየተለካ፣ መኖሪያቸውም በፀጥታ አስከባሪዎች እየተጠበቀ እንደነበር ሚኒስትሩ ለጋዜጠኞች አስረድተው ነበር፡፡ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባለፈው ዓርብ ማለዳ በሰጠው መግለጫ ለሕመምተኛው ሕልፈት ምክንያት ኢቦላ አለመሆኑን በውጭ አገር ላብራቶሪ መረጋገጡን አስታውቋል፡፡ ሚኒስቴሩ ባለፈው ረቡዕ በሰጠው መግለጫ የሲዲሲው ውጤት በፍጥነት መምጣትን እንደሚጠባበቅ አስታውቆ የነበረ ቢሆንም፣ ከበረራ ጋር በተያያዘ በሲዲሲ የሚደረገው ምርመራ ውጤት በሳምንት ሊዘገይ እንደሚችል በመታወቁ ምርመራው በዓለም አቀፍ የጤና ድርጅት ተቀባይነት ካለውና በደቡብ አፍሪካ በሚገነው “National Institute for Communicable Discasess” (NICD) በተባለ ድርጅት ተሠርቶ ውጤቱ በቶሎ እንዲደርስ መደረጉን፣ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች አማካሪ ዶ/ር መርዓዊ አራጋው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በምዕራብ አፍሪካ የኢቦላ ወረርሽኝ መቀስቀሱን ተከትሎ ከጥቂት ሳምንታት በፊት መንግሥት ከአፍሪካ ኅብረት ጋር በመተባበር 189 የጤና ባለሙያዎችን ወደ ላይቤሪያ፣ ሴራሊዮንና ጊኒ ከመላኩ ቀደም ሲል አርባ አምስት ያህል የጤና ባለሙያዎች በግላቸው በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤጀንሲዎች አማካይነት ወደ አገሮቹ ሄደው እንደነበር ዶ/ር ከሰተብርሃን አስታውቀው ነበር፡፡ ይህ በኢቦላ የተጠረጠረው ባለሙያም በኢንተርናሽናል ሪስኪው ኮሚቴ ሴራሊዮን ውስጥ ከኢቦላ ጋር በተያያዘ ከተሰማሩ የጤና ባለሙያዎች አንዱ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ ምንም እንኳ የባለሙያው ሕመም ኢቦላ እንዳልሆነና ይልቁንም የጭንቅላት ወባ መሆኑ በአገር ውስጥ በተደረገ የላብራቶሪ ምርመራ ቢረጋገጥም፣ ወደ ውጭ መላክ ያስፈለገው ያለምንም ጥርጣሬ ይበልጥ እርግጠኛ ለመሆን እንደሆነ ዶ/ር ከሰተብርሃን አስረድተዋል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የኢቦላ ቫረይስ ምልክት የታየባቸው ሰዎች ስለመገኘታቸው የተለያዩ መረጃዎች በማኅበራዊ ድረ ገጾች ሲለቀቁ እንደነበር በመጥቀስ፣ እስከዛሬ አጠራጣሪ ኬዝ ተገኝቶ ከነበረና የደም ናሙና ወደ ውጭ አገር ላብራቶሪ የተላከበት አጋጣሚም ካለ የሚል ጥያቄ ከሪፖርተር የቀረበላቸው ዶ/ር ከሰተብርሃን፣ ሁለቱም አጋጣሚዎች እንዳልነበሩ አረጋግጠዋል፡፡ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፣ ከእነዚህ አገሮች የመጡ መንገደኞች ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሲመረመሩ፣ ትኩሳት ካለባቸው ወደ ኢቦላ ማግለያ ማዕከል ሲወሰዱ ትኩሳት የሌለባቸው ግን ቫይረሱን ያስተላልፋሉ ተብሎ ስለማይታመን አድራሻቸው ተመዝግቦ በቀጣይ ቀናት በባለሙያ ክትትል ይደረግባቸዋል፡፡ አቶ አንበሳው ደግሞ አሥራ አምስት ቀናት ምንም ዓይነት ትኩሳት ሳይታይበት በመጣ በአሥራ ስድስተኛው ቀን ላይ አቅሉን በመሳት ኮማ ውስጥ ሊገባ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ ግለሰቡ ለቀናት ሙሉ በሙሉ ጤነኛ እንደነበርና በመጨረሻው ቀን አቅሉን ስቶ ‹‹ዲፕ ኮማ›› (Deep Coma) መግባቱን ለገለጹት ዶ/ር ከሰተብርሃን የጭንቅላት ወባ እንዲህ የማድረግ ባህሪ አለው? የሚል ጥያቄ ከሪፖርተር ቀርቦላቸው ሲመልሱ፣ ‹‹እንደ ባለሙያ ስመለከተው ምንም ጥርጣሬ የለኝም፡፡ ዲፕ ኮማ ውስጥ መግባቱ አንድ ማሳያ ነው፡፡ ኢቦላ እዚህ ደረጃ ላይ የሚያደርሰው ቫይረሱ ‘አድቫንስድ’ ደረጃ ላይ ደርሶ መድማትና ሌሎችም ምልክቶች ከታዩ በኋላ ነው፡፡ ዓይኑ ላይ የሚታየው ነገርም ወባ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነበር፡፡ ብዙ የጭንቅላት ወባ ኬዞችን አይቻለሁ፡፡ የዚህ ሰውም ተመሳሳይ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት መንግሥት 189 ኢትዮጵያዊያን የጤና ባለሙያዎችን በኢቦላ ወረርሽኝ ወደተጠቁ የምዕራብ አፍሪካ አገሮች ሲልክ ባለሙያዎቹ ተልዕኳቸውን ጨርሰው ሲመለሱ ለ21 ቀናት ተገልለው እንዲቆዩ እንደሚደረግ ዶ/ር ከሰተብርሃን ማረጋገጣቸው ይታወሳል፡፡ ይህ የበሽታውን ከባድነትና የባለሙያዎቹን ለቫይረሱ የመጋለጥ ዕድል ታሳቢ ያደረገ አካሄድ፣ በግላቸው በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ከኢቦላ ጋር በተያያዘ ወደተጠቀሱት አገሮች ሄደው ለሚመለሱ ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎችስ ለምን ተግባራዊ አልሆነም? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ዶ/ር መርዓዊ፣ ከዚህ በኋላ ይህን ማድረግ ግድ እንደሆነና ከዚህ አጋጣሚ መማራቸውን በቀጣይ ለተመሳሳይ ተልዕኮ ሄደው የሚመለሱ ሁሉ ለ21 ቀናት ተገልለው እንዲቆዩ እንደሚደረግ ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡ የግለሰቡን የደም ናሙና ወደ ውጭ አገር መላክ ያስፈለገው ከፍተኛ ጥንቃቄ ለማድረግ ሲሆን፣ ሁኔታውን ለሕዝብ ማሳወቅ የተፈለገውም ነገሮችን ግልጽ ለማድረግ እንደሆነ ያስታወቁት ዶ/ር ከሰተብርሃን፣ የኢቦላ ሽፋን በምዕራብ አገሮች ሚዲያ ከተቀዛቀዘ በኋላ በሕዝቡ ዘንድም መዘናጋት መኖሩንም ጠቁመዋል፡፡ የግለሰቡን ጉዳይ በሚመለከት ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መግለጫ የሰጠው በአጋጣሚው ሕዝቡን ዳግም ለማሳሰብም ጭምር እንደሆነ የገለጹት ዶ/ር ከሰተብርሃን፣ ‹‹አፍሪካና ዓለም ነፃ እስኪሆኑ ኢቦላ አሁንም ለእኛ ሥጋት ነው፤›› ብለዋል፡፡ በደቡብ አፍሪካው ላብራቶሪ የሟቹ ሕመም ኢቦላ አለመሆኑ መረጋገጡ ይፋ ከተደረገ በኋላ፣ በክትትልና በጥበቃ ሥር የነበሩ ቤተሰቦቹና ጓደኞቹ ነፃ ተደርገው አስከሬን እንዲወስዱም ተደርጓል፡፡ ሪፖርተር ማተሚያ ቤት እስከገባበት ዓርብ እኩለ ሌሊት ድረስ በነበረው መረጃ፣ የአቶ አንበሳው ቀብር ቅዳሜ ታኅሳስ 9 ቀን 2007 ዓ.ም. እኩለ ቀን ላይ በሳህሊተምሕረት ቤተ ክርስቲያን እንደሚፈጸም ይጠበቅ ነበር፡፡ ሟቹ በኢንተርናሽናል ሪስኪው ኮሚቴ በሴራሊዮን የቆየው ለሦስት ወራት ሲሆን፣ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰው ኮንትራቱን ጨርሶ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ ባለፈው ረቡዕ ጠዋት ሕይወቱ ከማለፉ በፊት ሰኞ ዕለት በሌላ ኮንትራት ተመልሶ ለመሄድ የሕክምና ምርመራ ሲያደርግ እንደነበር ማወቅ ተችሏል፡፡ ቀድሞም በድርጅቱ ይሠራ እንደነበርና በመሀል ወጥቶ ሌላ ድርጅት ይሠራ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

በዚያን ሰሞን የሹክሹክታ ወሬ ደርቶ ነው የሰነበተው፡፡ የአገራችን ልጆች...

በፓሪስ ኦሊምፒክ ዝግጅት ዙሪያ

‹‹ድንጋይ ላይ ሠርተን እንዴት ነው ውጤት እንድናመጣ የሚጠበቀው?›› የኦሊምፒክ አትሌቶች በደረጀ...

በአዲስ አበባ የታቀደ ጥቃት ማክሸፉን መንግሥት አስታወቀ

በኦነግ የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ኡርጌሳ ግድያ የተጠረጠሩ መያዛቸው...