Tuesday, February 20, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ለምርጫው ዴሞክራሲያዊነት ገዢው ፓርቲ ለሰላማዊነቱ ደግሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቁርጠኛ ይሁኑ!

የዘንድሮው ምርጫ ‹‹ዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ፣ ነፃና ተዓማኒነት›› ያለው እንደሚሆን አገር በሚያስተዳድረው መንግሥትና ምርጫውን በሚያስፈጽመው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተደጋጋሚ እየተነገረ ነው፡፡ ዋናው ጥያቄ ግን እርግጠኛ ናችሁ ወይ የሚለው ነው፡፡ አንድ ጉዳይ በእርግጠኝነት ከተነገረ ተግባራዊነቱ ይጠበቃል፡፡ ነገር ግን የይስሙላ ከሆነ የሚባለው ሁሉ ዋጋ የለውም፡፡ ሆኖም ምርጫው ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከተፈለገ የገዢው ፓርቲና የተቃዋሚ ፓርቲዎች ቁርጠኝነት ከምንም ነገር በላይ ወሳኝ ነው፡፡ በዘመናችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እየተገነባባቸው ባሉ በርካታ አገሮች ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በተወሰነ ወቅት ውስጥ ማካሄድ የዴሞክራታይዜሽን ሒደት ዝቅተኛው መሥፈርት እየሆነ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያለውን ምርጫ ለማከናወን ደግሞ መሪ ተዋንያኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ ተቀባይነታቸው ተመዝኖ ውሳኔ የሚሰጣቸውም በሕዝቡ ወሳኝ ድምፅ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ዴሞክራሲያዊ ሒደት እንዲቀላጠፍ ሲፈለግ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ብቻ መከተል አለባቸው፡፡ ከዚያ ውጪ ያለው አካሄድ ኢዴሞክራሲያዊ ከመሆኑም በላይ፣ የአገርን ገጽታ ያበላሻል፡፡ የሕዝቡን ሞራልና ሥነ ልቦና ያላሽቃል፡፡ አሁንም ደግመን ደጋግመን የምንለው ገዢው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚዎች ሕዝቡን አክብረው ምርጫው ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ እንዲሆን ከልባቸው እንዲሠሩ ነው፡፡ ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ሁሌም በተቃዋሚ ፓርቲዎች እየተወቀሰ ያለው የፖለቲካ ምኅዳሩን በማጥበብ ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንቅፋት መሆኑ ነው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በሚከተሉት ርዕዮተ ዓለምና በሚያራምዱት አቋም ምክንያት በጠላትነት ፈርጆ ለአገሪቱ ምንም ዓይነት ፋይዳ እንደሌላቸው ነው ዕርግማኑን የሚያወርድባቸው፡፡ በመድበለ ፓርቲ ፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ማንም የመሰለውን አቋም በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ የማራመድ መብት አለው፡፡ ይህ መብትም ፈጽሞ የማይገሰስ ነው፡፡ ዳኝነቱ ያለው የሥልጣን ምንጭ ባለቤት የሆነው ሕዝብ ዘንድ እስከሆነ ድረስ፣ ገዢው ፓርቲ ተቃዋሚዎችን ማንገላታት አይችልም፡፡ ሕገወጥ ነው፡፡ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ መሆን የሚችለው ሁሉም ፓርቲዎች የመወዳደሪያ ሜዳው እኩል ሲመቻችላቸው ነው፡፡ ከዚያ ውጪ በተጣበበ ምኅዳር ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ መጠበቅ አይቻልም፡፡ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የአንድ አገር ሕዝብን ነፃነትና የተለያዩ መብቶች ለማስከበር ከመርዳቱም በላይ፣ በሒደቱ ውስጥ ተሳታፊ የሚሆኑ ፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያዩ አማራጮችን በማቅረብ ሕዝቡ በዳበረ ግንዛቤ የሚሻለውን እንዲመርጥ ዕድሉን ያመቻቻሉ፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ የሆኑ አስተሳሰቦችና አመለካከቶች እንዲንሸራሸሩ ያስችላሉ፡፡ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ለአገር ጠቃሚ የሚሆኑ ሁሉን አቀፍ ዕውቀቶች ይገኛሉ፡፡ ዜጎች በነፃነት አንገታቸውን ቀና አድርገው አገራቸውን ለማገልገል ይነሳሳሉ፡፡ ሌሎች በጣም በርካታ ጥቅሞችም ይገኛሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ አገርን በመምራት ላይ ያለው ገዢ ፓርቲ ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ ከብጥብጥና ከሁከት የፀዳ ማኅበረሰብ የሚፈጠረው ምርጫ በዴሞክራሲያዊ አግባብ ብቻ ሲከናወን ነው፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ የተቀሰቀሰው የዓረቦች የፀደይ አብዮት ለዘመናት የታመቀ የሕዝብ ብሶትን አስተጋብቶ ቢጀመርም፣ ሒደቱ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ባለመሆኑ ምክንያት በርካታ አገሮች አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የአብዮቱ መነሻ ከሆነችው ቱኒዝያ በስተቀር ሊቢያና ሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ገብተዋል፡፡ ግብፅ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠው ፕሬዚዳንትና ፓርላማ ተባረው ሌላ ምርጫ ቢካሄድም አሁንም ውጥረት ውስጥ ነች ያለችው፡፡ በየቀኑ የቦምብ ፍንዳታና ግድያዎች ይሰማሉ፡፡ ሶሪያ እየወደመች ነው፡፡ ወይም አብቅቶላታል ማለት ይቻላል፡፡ ሊቢያ ከጋዳፊ መንግሥት ውድቀት በኋላ ጠንካራ መንግሥት ባለመኖሩ ምክንያት በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጠቅላላ ጦርነት ውስጥ ገብታለች፡፡ ሕዝቡም ሰላሙን አጥቷል፡፡ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ በሌለበት ሁሌም የሚከተለው እልቂትና ውድመት ነው፡፡ ሕዝባችን ይህንን በፍፁም አይፈልገውም፡፡ ላለፉት ሃያ ዓመታት የተካሄዱት አራት ምርጫዎች በውዝግብ ነው የተቋጩት፡፡ ሌላው ቀርቶ በ1997 ዓ.ም. የተከናወነው ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ጎልተው የታዩበት ቢሆንም፣ ከውጤት ጋር በተነሳ አለመግባባት 200 ያህል ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተውበታል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ለእስር ተዳርገዋል፡፡ በርካቶች አገር ጥለው ሸሽተዋል፡፡ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሒደቱ በአግባቡ ሊቀጥል ባለመቻሉ ምክንያት በአገሪቱ ላይ ጥቁር ነጥብ ጥሎ አልፏል፡፡ ለዚህ ዓይነቱ አሳዛኝ ክስተት ገዢው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚዎች የራሳቸው ድርሻ ነበራቸው፡፡ የዚያ ድኅረ ምርጫ ጦስ ለ2002 ምርጫ ያተረፈው ቢኖር ዴሞክራሲን እንዲቀለበስ ማድረግ ነበር፡፡ ይህንንም ማንም አይክደውም፡፡ እንደዚያ ዓይነቱ ክስተት እንዲደገም ማንም አይፈልግም፡፡ ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ይህንን ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ ከማንም የበለጠ ኃላፊነት ስላለበት በአንክሮ ሊያስብበት ይገባል፡፡ ሥልጣንን ከማጠናከር በላይ የሕዝብ ፍላጎት መጠበቅ አለበት፡፡ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ሲፈለግ ከልብ ቁርጠኛ ሆኖ ማሳየት ተገቢ ነው፡፡ ዴሞክራሲ የሚያብበው የተለያዩ ሐሳቦች በነፃነት እንዲንሸራሸሩ ሲያደርግ ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉ ሚዲያዎች ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በፍትሐዊነት የአየር ሰዓትና ገጾችን እንዲሰጡ መደረግ አለበት፡፡ ለምርጫ የሚያገለግሉ ሕጎች በሙሉ በነፃነት ሁሉንም ወገን ማገልገል አለባቸው፡፡ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ መራጮችን እንዲቀሰቅሱ ድጋፍ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ አባላቶቻቸውና ደጋፊዎቻቸው ሕግ አክብረው እስከተንቀሳቀሱ ድረስ መዋከብ የለባቸውም፡፡ የምርጫ አስፈጻሚዎችና የሕዝብ ታዛቢዎች ከማንኛውም ፖለቲካ ፓርቲ ተፅዕኖ ነፃ መሆን አለባቸው፡፡ ለምርጫ የሚመደበው በጀት ድልድሉ ፍትሐዊና ሁሉን አሳታፊ መሆን ይኖርበታል፡፡ ሁሉም ዓይነት እንቅስቃሴ በግልጽነት እንዲከናወን መደረግ አለበት፡፡ የፀጥታ ኃይሎች ከምንም ነገር ገለልተኛ መሆን አለባቸው፡፡ በዚህ ሁኔታ የሚካሄድ ምርጫ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ይሆናል፡፡ ገዢው ፓርቲ በቁርጠኝነት ፈቃደኛ ከሆነ ለአመፅና ለብጥብጥ ክፍተት አይኖርም፡፡ ምርጫውም በሰላም ይካሄዳል፡፡ በሌላ በኩል ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተግተው መሥራት ያለባቸው እንቅስቃሴያቸው በሙሉ ሰላማዊ እንዲሆን ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲኖር ሲፈልጉ ያጋጥሙናል በሚሉዋቸው ችግሮች ምክንያት ወደ አመፅና ሕገወጥ ጎዳና ውስጥ ከመግባት መታቀብ ይኖርባቸዋል፡፡ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ውስጥ ሁሌም ቅድሚያ መሰጠት ያለበት ለሕጋዊነት ነው፡፡ የምርጫ ሒደቱ ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ሲፈለግ ችግር ቢያጋጥም እንኳ፣ በተቻለ መጠን ወደ ብጥብጥና ያልተገባ ድርጊት ውስጥ ከመግባት በሰላማዊ መንገድ የመፍትሔ አካል መሆን አለባቸው፡፡ ከገዢው ፓርቲም ሆነ ሁሌም ከሚከሱት ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር አለመስማማት ሲኖር ሕጋዊውን መንገድ እስከ መጨረሻው ድረስ መጠቀም አለባቸው፡፡ በጋዜጣዊ መግለጫዎቻቸውም ሆነ በቅስቀሳዎቻቸው ከጥላቻ አነጋገሮች መቆጠብ፣ ዓላማቸውን ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ማስረዳትና ከስሜታዊነት መፅዳት ይኖርባቸዋል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሒደት የሚኖረው ሰላም ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ሰላም በሌለበት ምንም ዓይነት ምርጫ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ይሆናል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡ እልህ በመጋባት ደጋፊዎችን ተገቢ ላልሆነ ድርጊት ማንቀሳቀስ የዴሞክራቶች መገለጫ አይደለም፡፡ ስለዚህ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በትዕግሥት ሕጋዊውን መንገድ ብቻ ተከትለው እጅግ አስቸጋሪ የሆነውን ትግል በሰላማዊ መንገድ መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡ ለሕዝቡም ዓላማቸው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መሆኑን ያረጋግጡለት፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው ጎዳና ለማንም አይጠቅምም፡፡ ምርጫውን በበላይነት የሚያስፈጽመው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ ምርጫ በመጣ ቁጥር ገለልተኝነቱ በጥያቄ ውስጥ ያለው ምርጫ ቦርድ፣ የአሠራሩን ግልጽነትና ገለልተኝነት ማሳየት ከተሳነው ችግር አለ፡፡ የምርጫ ቁሳቁሶችንና የሎጂስቲክስ አቅርቦቶችን በብቃት ማቅረብ መቻሉ ሁሌም ቢወሳ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች ቅሬታና አቤቱታ መስተንግዶ ላይ ሁሌም እንደተተቸ ነው፡፡ አንድ ምርጫ የሚያስፈጽም አካል የሚቀርቡበት ትችቶች ሁሉ ትክክል ናቸው አይባልም፡፡ ነገር ግን በተለይ ዋነኛ ከሚባሉት የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ያለው ግንኙነት የተበላሸ በመሆኑ ሁሌም ቅሬታዎች ይቀርባሉ፡፡ በዚህ ዓይነቱ ድባብ ውስጥ ምርጫ ሲካሄድ ሁሌም ውዝግብ አለ፡፡ ችግሮችን ለመፍታት ከፓርቲዎቹ ጋር ተቀምጦ መነጋገር ተገቢ ነው፡፡ ምርጫው ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ይሆናል ሲባል ለዓመታት ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችም ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ በቅርቡ እንኳ ከአንድነት፣ ከመኢአድና ከሰማያዊ ፓርቲዎች ጋር የገባበት እስጥ አገባ አንድ ቦታ ላይ መቆም አለበት፡፡ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ሕጎችን ያለምንም አድልኦ ተግባራዊ ማድረግ ሳይቻለው ሲቀር ችግር ይፈጠራል፡፡ ስለዚህ ምርጫ ቦርድ እንደ አንድ ዴሞክራሲያዊ ተቋም ለግልጽነትና ለተጠያቂነት ራሱን ያዘጋጅ፡፡ ምርጫውን በዴሞክራሲያዊና በሰላማዊ መንገድ ይምራ፡፡ ለሚነሱበት ቅሬታዎች በዴሞክራሲያዊ አግባብ መልስ ይስጥ፡፡ ሁሉንም ወገን ያሳምን፡፡ ሁሌም እንደምንለው ወሳኙ ሕዝብ ነው፡፡ የአገሪቱም ሆነ የምርጫው ባለቤት ሕዝብ ነው፡፡ ሕዝባችን በእጅጉ የሚታወቀው በጨዋነቱና በመልካም ሥነ ምግባር እሴቶቹ ነው፡፡ ይህንን የመሰለ አገር ወዳድና አኩሪ ታሪክ ያለውን ሕዝብ ለማገልገል ለፖለቲካ ሥልጣን የምትወዳደሩ ፓርቲዎች በሙሉ ሕግ አክብሩ፡፡ ለሰላም ዘብ ቁሙ፡፡ ጉልበተኝነት፣ አሻጥረኝነት፣ ሸፍጠኝነት፣ ጥላቻና አላስፈላጊ ግብግቦችን አቁሙ፡፡ ምርጫውን የሕዝብ ሉዓላዊነት መገለጫ አድርጉት እንጂ፣ ሕዝብ አንገቱን የሚደፋበትና የሚያፍርበት አታድርጉት፡፡ ከሁሉም ነገር በላይ ይህች ታሪካዊት አገር ትከበር፡፡ ስለዚህ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ራሳችሁን አሳልፋችሁ ስጡ፡፡ ከታሪክ ተጠያቂነት ይልቅ ታሪክ ሠሪነት ይበልጣል! ያስከብራል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የካቲት አብዮት – ጥያቄዎችሽ ዛሬም እየወዘወዙን ነው!

በበቀለ ሹሜ አጭር መግቢያ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ከ1960ዎች ወጣቶች ርዝራዦች አንዱ...

የሰሞኑ የ“መኖሪያ ቤቶች” የጨረታ ሽያጭ ምን ዓይነት ሕጋዊ መሠረት አለው?   

በዳዊት ዮሐንስ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ አየር ላይ ከሚንሸረሸሩ ዜናዎች...

ሁለቱ ወጎች፡ ከሰማየ ሰማያት አድርሶ መላሹ ቋንቋ! እስከ በዓሉ ቤርሙዳ

በተክለ ጻድቅ በላቸው ሰማየ ሰማያት አድርሶ መላሹ ቋንቋ! ከሁለት ሦስት ዓመት...

ለትግራይ ክልል ድርቅ ተፈናቃዮች አፋጣኝና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንዲደረግ ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዩች ቋሚ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

አፍሪካውያን እንዳይታዘቡን ጥንቃቄ ይደረግ!

የአፍሪካ ኅብረት 37ኛው የመሪዎች ጉባዔ በኅብረቱ መቀመጫ አዲስ አበባ እየተካሄደ ባለበት በዚህ ጊዜ፣ ከዛሬ 61 ዓመት በፊት ከጥንስሱ እስከ ምሥረታው ወሳኝ ሚና የነበራት ኢትዮጵያ...

ታሪክን ከመዘከር ባሻገር የመግባቢያ መንገዱም ይፈለግ!

እሑድ የካቲት 3 ቀን 2016 ዓ.ም. በይፋ የተመረቀው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ከታላላቅ አገራዊ ክንውኖች ተርታ የሚመደብ ነው፡፡ ይህንን መሰል የታሪክ ማስታወሻ በታላቅ ክብር...

ባንኮቻችን ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር ያስፈልጋቸዋል!

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከሚመሰገንባቸው ተግባራት መካከል አንደኛው፣ በውስጣዊ ትርምስ ለመፍረስ ይንገዳገዱ የነበሩ ባንኮችን በጠንካራ ቁጥጥር መታደግ መቻሉ ነው:: ከዚህ ቀደም በተለያዩ ነባር የግል ባንኮች...