Wednesday, October 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለመሬት ሊዝ ጨረታ 305 ሺሕ ብር ያቀረበው ኩባንያ ውል ሳይፈጸም ቀረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአዲስ አበባ ከተማ ለሊዝ ጨረታ ለቀረበ መሬት በካሬ ሜትር 305 ሺሕ ብር ያቀረበው ዝዋይ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ ኩባንያ ውል ሳይፈጽም ቀረ፡፡ ኩባንያው ቅድመ ክፍያ ፈጽሞ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር ውል መግባት የነበረበት በአሥር ቀናት ውስጥ ቢሆንም፣ ተፈጻሚ ሳያደርግ ቀርቷል፡፡ አስተዳደሩ አሥሩ ቀናት ቢጠናቀቁም በተጨማሪ የሦስት ቀናት የሰጠው ጊዜ ባለፈው ሰኞ ተጠናቋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ በ11ኛው ሊዝ ጨረታ በተለይ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ መርካቶ አካባቢ ላቀረበው 449 ካሬ ሜትር ቦታ፣ 136.9 ሚሊዮን ብር ካቀረበው ዝዋይ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ ጋር ውል ለመፈጸም ዝግጁ ነበር፡፡ ነገር ግን ኩባንያው መቅረብ ባለመቻሉ ሁለተኛ ለወጣው ኤስኤፍ ትሬዲንግ ቦታውን ለመስጠት ጥሪ አቅርቦለታል፡፡ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የሊዝ ጨረታ ኬዝ ቲም ምንጮች፣ ኤስኤፍ ትሬዲንግ ቦታውን ለመረከብ ፍላጎት አሳይቷል ሲሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ኤስኤፍ ትሬዲንግ ለዚህ መሬት ከዝዋይ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ ጋር ተወዳድሮ ሁለተኛ መውጣቱ ይታወሳል፡፡ ዝዋይ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ ለዚህ መሬት በካሬ መሬት 305 ሺሕ ብር ሲያቀርብ፣ ኤስኤፍ ትሬዲንግ ደግሞ በካሬ ሜትር 268 ሺሕ ብር አቅርቧል፡፡ ዝዋይ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ ተወዳዳሪውን ማሸነፍ የቻለው ባቀረበው ገንዘብ መጠን ብቻ አይደለም፡፡ ከገንዘብ በተጨማሪ ከተለመደው ውጪ 25 በመቶ ቅድመ ክፍያ እከፍላለሁ በማለቱ ጭምር ነው፡፡ ኤስኤፍ ትሬዲንግ 20 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ እንደሚፈጽም በወቅቱ በጨረታ ሰነዱ ላይ አመልክቷል፡፡ የአስተዳደሩ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ባስተላለፈው ጥሪ ሁለተኛ የወጣው ኤስኤፍ፣ ዝዋይ ትሬዲንግ ያቀረበውን ገንዘብ ከከፈለ ቦታውን እንደሚያስረክበው ይጠበቃል፡፡ በእስካሁኑ ሒደት ኤስኤፍ ትሬዲንግ አስተዳደሩ ላቀረበለት ጥያቄ ይፋዊ ምላሽ አለመስጠቱ ታውቋል፡፡ ዝዋይ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ ባሸነፈው መሠረት ውል መግባት ባለመቻሉ፣ ለጨረታ ማስከበሪያ በሲፒኦ ያስያዘው የጨረታ መነሻ ዋጋ 20 በመቶ ገንዘብ ለመንግሥት ገቢ ተደርጓል፡፡ ዝዋይ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ ለጨረታው ያቀረበው ዋጋ ከፍተኛ የመነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ኩባንያው በተፈጠረበት ጫና ምክንያት ውል መፈጸም አለመቻሉን የሚገልጹት ምንጮች፣ ኩባንያው ከውጭ ብቻ ሳይሆን ከራሱ ባለአክሲዮኖችም ጭምር ተቃውሞ እንደገጠመው ይናገራሉ፡፡ ቅሬታ አቅራቢ ባለአክሲዮኖች ኩባንያቸው ያቀረበው ዋጋ እነሱን እደማይመለከታቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ማሳወቃቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ዝዋይ ኢንተርናሽናልና ሁለተኛ የወጣው ኤስኤፍ ትሬዲንግ ያቀረቡት ገንዘብ በከተማው ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ አዲስ አበባን ከዓለም ውድ ከተሞች ተርታ አስፍሯታል፡፡ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ይህ ዋጋ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ይዞታ አመላካች አይደለም በማለት መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች