– ለስምንት ርዕሰ ጉዳዮች ኮሚቴ ተዋቅሯል
የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረገውን ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በማዘጋጀት ላይ ናቸው፡፡ በስምንት መሠረታዊ ርዕሰ ጉዳዮች ተከፍሎ እየተዘጋጀ የሚገኘው የአምስት ዓመቱ ዕቅድ በዚህ ዓመት ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በመጪው ዓመት መጀመሪያ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ለቀጣዩ ዕቅድ ዘመን መሠረታዊ የተባሉ ስምንት ርዕሰ ጉዳዮች ተለይተዋል፡፡ በርዕሰ ጉዳዮቹ ላይ እንዲመጣ የሚፈለገው መዋቅራዊ ለውጥ በኮሚቴዎቹ ከተነደፈ በኋላ፣ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ መፅደቅ ይኖርበታል፡፡ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ሐጂ ኢብሳ ገንዶ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት መዋቅራዊ ፕላኑን ካፀደቀ በኋላ ሁሉም መሥሪያ ቤቶች በየካቲት ወር በሚሰጣቸው ምክረ ሐሳብ ላይ ተመርኩዘው ዕቅዳቸውን ያዘጋጃሉ፡፡ ለስምንቱም ርዕሰ ጉዳዮች የኮሚቴ አባላትና ኮሚቴዎቹን የሚሰበስቡ ባለሥልጣናት ተደልድለው ዕቅዱን በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኙም ታውቋል፡፡ በመጀመርያ የተቀመጠው ነጥብ የማክሮ ኢኮኖሚ ጉዳዮች፣ የዕቃዎችና የአገልግሎቶች ኤክስፖርት ላይ አነጣጥሯል፡፡ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ዘጠኝ አባላት ያሉት ኮሚቴ የተቋቋም ሲሆን፣ ኮሚቴውን የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ አቶ ሱፊያን አህመድ ይመሩታል፡፡ ከአቶ ሱፊያን ጋር ይህንን ዕቅድ ከሚያመነጩት መካከል የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ አማካሪ አቶ ንዋይ ገብረአብና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ ይገኙበታል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠው የግብርናና የገጠር ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ነው፡፡ ኮሚቴው አምስት አባላት አሉት፡፡ ይህንን የአምስት ዓመት ዕቅድ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ በረከት ስምኦን ይመሩታል፡፡ ከአቶ በረከት ጋር ዶ/ር ካሱ ኢላላ፣ የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ ደርበውና የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ካሊድ ቦምባ ተሠልፈዋል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የተቀመጠው የኢንዱስትሪ ልማትና የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያመጣ የተሰየመው ኮሚቴ ነው፡፡ ኮሚቴው በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ የሚመራ ነው፡፡ ኮሚቴው ስድስት አባላት ሲኖሩት፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ዓባይ ፀሐዬና የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተው በኮሚቴው ውስጥ ተካተዋል፡፡ የሰው ሀብት ካፒታል ማሳደግና የቴክኖሎጂ አቅም ግንባታን በተመለከተ የተቋቋመው ኮሚቴ ዘጠኝ አባላት አሉት፡፡ ኮሚቴውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ይመራሉ፡፡ በኮሚቴው ውስጥ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የመልካም አስተዳደር ክላስተር አስተባባሪና የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትሯ ወ/ሮ አስቴር ማሞ፣ ልዩ ድጋፍ የሚሹ ክልሎች አስተባባሪ አቶ አዲሱ ለገሠና የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ተካተዋል፡፡ ዘመናዊ የከተማ ልማትና የኮንስትራክሽን ዘርፍ አቅም ግንባታን በተመለከተ የተቋቋመው ኮሚቴ አራት አባላት አሉት፡፡ ኮሚቴውን አቶ ዓባይ ፀሐዬ የሚመሩት ሲሆን፣ በኮሚቴ ውስጥ የከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ኃይሌና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ ተካተዋል፡፡ ወሳኝ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችና የማስፈጸም አቅም ግንባታን በተመለከተ የተቋቋመው ኮሚቴ ሰባት አባላት አሉት፡፡ ኮሚቴውን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ይመሩታል፡፡ በኮሚቴ ውስጥ የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ወርቅነህ ገበየሁና የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ አቶ ዓለማየሁ ተገኑ ተካተዋል፡፡ በሰባተኛ ደረጃ የተቀመጠው ርዕሰ ጉዳይ ልማታዊ መልካም አስተዳደር፣ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ከምንጩ በማድረቅ ተወዳዳሪነትን ማጎልበት የሚለው ነው፡፡ ኮሚቴው ስምንት አባላት ሲኖሩት፣ ይህን ኮሚቴ ወ/ሮ አስቴር ማሞ ይመሩታል፡፡ በኮሚቴው አቶ መኩሪያ ኃይሌ፣ የንግድ ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔና የፍትሕ ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው አምባዬ ተካተዋል፡፡ በስምንተኛ ደረጃ የተቀመጠው ዴሞክራሲን ማስፈን፣ ብሔራዊ መግባባት መፍጠርና የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ሥራን የመተለከተ ነው፡፡ ይህ ኮሚቴ ስምንት አባላት አሉት፡፡ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ የአምስት ዓመት ዕቅድ የሚነድፈውን ኮሚቴ አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ ይመሩታል፡፡ በኮሚቴ ውስጥም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ካሳ ተክለብርሃንና የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን ተካተዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የኮሚቴዎቹ የሥራ እንቅስቃሴ ድጋፍና ክትትል የሚያደርገው በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና ብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ነው፡፡ በእነዚህ ኮሚቴዎች የታቀደው አገራዊ ዕቅድ ውይይት ከተደረገበት በኋላ አገሪቱ ለአምስት ዓመታት የምትመራበት ብሔራዊ ሰነድ እንደሚሆን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡