Sunday, May 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዓለምየአሜሪካና የሩሲያ ጥልፍልፎሽ በትራምፕ የመጀመሪያዎቹ የሥልጣን ወራት

የአሜሪካና የሩሲያ ጥልፍልፎሽ በትራምፕ የመጀመሪያዎቹ የሥልጣን ወራት

ቀን:

አሜሪካ በሩሲያ ላይ ያላት ጨለምተኝነት በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዘመን ወደ ወጋገንነት ይለወጣል የሚል መላምት ሲሰነዘር የነበረው፣ ትራምፕ ለአሜሪካ ፕሬዚዳንትነት የምረጡኝ ቅስቀሳ ከጀመሩበት እ.ኤ.አ. ከ2016 አጋማሽ ወዲህ ነው፡፡ በቀዝቃዛው ጦርነት ውስጥ ለዓመታት የከረሙት አሜሪካና ሩሲያ የቃላት ጦርነታቸውን ቢያለዝቡም አብሮ ከመሥራት ይልቅ በዓይነ ቁራኛ መተያየትን፣ አንዱ ለአንዱ ኃያልነቱን ለማሳየት መጠላለፍን መርጠው ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡

አሜሪካ ከጦር በስተቀር ያላትን አቅም ተጠቅማ ሩሲያን ለማንኮታኮት ያልሄደችበት መስመር ባይኖርም፣ ሩሲያን ማንበርከክ አልሆነላትም፡፡ የቀድሞዋን ሶቪየት ኅብረት ብትፈራርስም፣ አንድነትን የሚያቀነቅኑት የሩሲያ ባለሥልጣናት ክራይሚያን ከዩክሬን ቀምተው ቀላቅለዋል፡፡

ሩሲያ ከዩክሬን ጋር በነበራት ግጭት ሳቢያ በኋላም ክራይሚያን ወደራሷ በመቀላቀሏ፣ በአሜሪካና በሌሎች የአውሮፓ አገሮች የተለያዩ ማዕቀቦችም ተጥሎባታል፡፡ የማዕቀቡ አቀንቃኝም አሜሪካ ነበረች፡፡

- Advertisement -

ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ለሩሲያ የነበራቸው አቋም፣ ከዚህ ቀደም አሜሪካ በሩሲያ ላይ ያላትን አቋም ገሸሽ ያደረገ ነበር፡፡ ገና ከጅምሩ አሜሪካ በሩሲያ ላይ የጣለቻቸውን ማዕቀቦች እንደሚያነሱ፣ ከሩሲያ ጋር በጋራ ለመሥራትም ፍላጐት እንዳላቸው ሲናገሩ የነበሩት ትራምፕ፣ አሁንም የፕሬዚዳንትነቱን መንበር ይዘው በዙሪያቸው ያሉ ባለሥልጣናት ከሩሲያ ጋር ግንኙነት እየፈጠሩ ስለመሆኑ ተነግሯል፡፡

ትራምፕና በዙሪያቸው ያሉ ባለሥልጣናት ለሩሲያ ያላቸው ፖለቲካዊ አቋም ከዚህ ቀደም አሜሪካ ለሩሲያ ያለበሰቻትን ጥቁር ካባ የሚያወልቅ ዓይነት ነው የሚሉም አሉ፡፡ በተለይ ሩሲያ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ የሳይበር ጥቃት በመፈጸም ተባብራለች መባሉ፣ የትራምፕና የሩሲያውን ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ግንኙነትን ያመለክታል የሚሉ አሉ፡፡ ትራምፕ ፕሬዚዳንት ከመሆናቸው በፊት ነው ቢባልም፣ የትራምፕ ሴት ልጅ ባለቤትና የትራምፕ ከፍተኛ አማካሪ ጄርድ ኩሽነር ከሩሲያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ቢያንስ ለሁለት ጊዜ ተገናኝቷልም ተብሏል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2017 መግቢያ ላይ በአሜሪካ ምርጫ ወቅት ትራምፕ እንዲያሸንፉ የሩሲያ መንግሥት ጣልቃ ገብቷል በማለት የአሜሪካ ደኅንነት ኤጀንሲ ያሳወቀ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ ኩሽነር ከሩሲያ ባለሥልጣናት ጋር ግንኙነት መፍጠሩና መወያየታቸው ተነግሯል፡፡ በአሜሪካ ከፍተኛው የሥልጣን እርከን ላይ ባሉ ሰዎች በሚኖር ግንኙነት ሩሲያን ስታጠለሽ ለኖረችው አሜሪካ አስደንጋጭ ቢሆንም፣ በትራምፕ የሥልጣን ዘመን ግን ከሩሲያ ጋር ለመሥራት አመላካች ሁኔታዎች እየታዩ ነውም አስብሏል፡፡

ይህ መሆኑ ግን ለአሜሪካ ሴኔት ደኅንነት ኮሚቴ ተጨማሪ ሥራ ፈጥሮለታል፡፡ ኒውዮርክ ታይምስ ሰሞኑን እንደዘገበው፣ የትራምፕ ልጅ ኢቫንካ ትራምፕ ባለቤት  ኩሽነር እ.ኤ.አ. በ2016 የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሰሞን ከሩሲያ ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝቶ ነበር በሚለው ላይ የሴኔቱ ደኅንነት ኮሚቴ ሊያነጋግረው ነው፡፡

የትራምፕ አስተዳደርና ሩሲያ ግንኙነት አላቸው ተብሎ በዋይት ሐውስ ባለሥልጣናት እርከን ከቀዳሚና ከዋና ከሚመደቡት አንዱ ኩሽነር፣ በሴኔቱ የደህንነት ኮሚቴ ሲጠየቅም ይህ የመጀመሪያው ይሆናል፡፡

የዋይት ሐውስና የኮንግረሱ ባለሥልጣናት ኩሽነር በአሜሪካ የሩሲያ አምባሳደር ሰርጌይ ኪስሊያን ጨምሮ ከሩሲያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር መቼ እንደተገናኘም ይጠይቃሉ ተብሏል፡፡  እ.ኤ.አ. በ2016 ማብቂያ የአሜሪካ የቀድሞው ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ማይክል ፍሊንና ኩሽነር ከሩሲያው አምባሳደር ኪስሊያ ጋር በትራምፕ ታወር ተገናኝተዋል ተብሎ ሪፖርት የቀረበ ቢሆንም፣ ዋይት ሐውስ ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች ውይይቶች እንደነበሩ አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡

ትራምፕ ሥልጣን ለመረከብ ዝግጅት ላይ በነበሩበት ጊዜ የትራምፕ የቅርብ ሰዎች ከሩሲያ ባለሥልጣናት ጋር ይወያዩ ነበር ከሚለው በተጨማሪ፣ ኩሽነር ከሩሲያ መንግሥት የባንክ ኃላፊ ጋር ተወያይቷል ተብሏል፡፡ ባንኩ ደግሞ ሩሲያ ክራይሚያን ወደ ራሷ ከመቀላቀሏ ጋር ተያይዞ በኦባማ የሥልጣን ዘመን ማዕቀብ የተጣለበት ነው፡፡

በዋይት ሐውስ ከፍተኛ ሥልጣን ያለው ኩሽነር ለትራምፕ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አማካሪ ነው፡፡ በዋይት ሐውስ አዲስ በተከፈተውና የፖሊሲ አቅጣጫዎችንና ስትራቴጂዎችን ቀጥታ ለትራምፕ ሪፖርት የሚያደርገውን ቢሮም ይመራል፡፡

የፖሊሲና የስትራቴጂ ጉዳዮችን የሚመራ የአሜሪካ ባለሥልጣን ከሩሲያ ጋር መገናኘቱ ሥጋት የገባው የአሜሪካ ሴኔት ደኅንነት ኮሚቴ ለሚያደርገው ምርመራ፣ ኩሽነር ፈቃደኛ መሆኑንና ራሱንም እንደሚከላከል የዋይት ሐውስ ፕሬስ ሴክሬተሪ ሾን ስፓይሰር ሲናገሩ፣ ቃል አቀባይዋ ሆፕ ሂክስ ደግሞ የኩሽነርና የሩሲያ ባለሥልጣናት ግንኙነት የተለመደ ነበር፡፡ የፕሬዚዳንቱ አማካሪ እንደ መሆኑ ከሰዎች ጋር መወያየት የሥራው አንድ አካል ነው ብለዋል፡፡

‹‹ለቁጥር ከሚያዳግቱ ግለሰቦች ጋር ተወያይቷል፡፡ ይህ ደግሞ የሥራው አካል ነው፤›› ሲሉም ስፓይሰር አክለዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2016 የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የሩሲያ ጣልቃ ገብነት ነበር በሚል ምርመራ እያደረገ የሚገኘው የሴኔቱ ደኅንነት ኮሚቴ የኩሽነርንም ጉዳይ የሚያይ ሲሆን፣ ጉዳዩም ኩሽነር ከሩሲያ ባለሥልጣናት ጋር ከአንድ ጊዜ በላይ ተገናኝቷልና በምን አጀንዳ ላይ ተወያዩ የሚል ነው፡፡

ኩሽነር ማንኛውንም ነገር ከመርማሪ ኮሚቴው ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ ነው፡፡ ለመደበቅ የሚፈልገው አጀንዳም የለውም፡፡ ከባንክ ኃላፊው ጋርም ሆነ ከአምባሳደሩ ጋር ስለነበረው ውይይት ለመናገር ፈቃደኛ ነው ተብሏል፡፡ ከሩሲያ ባንክ ኃላፊ ጋር የተወያየውም የትራምፕ አማካሪ ከመሆኑ በፊት ሲሆን፣ የባንኩ አማካሪ በተለያዩ አገሮች የሚገኙ ኩባንያዎችን ባነጋገሩበት ወቅትም ነው፡፡  

ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር የቅርብ ግንኙነት አለው ከሚባለው የሩሲያ መንግሥት ባንክ ዋና ኃላፊና በአሜሪካ ከሩሲያ አምባሳደር ጋር ግንኙነት ፈጥሯል የተባለው የትራምፕ አማካሪ፣ አሜሪካን አደጋ ውስጥ ጥሏታል ያሉም አሉ፡፡

ሆኖም ይህ ትራምፕን አላስደነገጣቸውም፡፡ ይልቁንም የጣሊያን ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ተጫዋችና እ.ኤ.አ. በ2011 ለማንቸስተር ሲቲ ሲጫወት ማንቸስተር ዩናይትድ ላይ ያስቆጠረው ማሪዮ ባሌቶሊ “why always me?” [ለምን ሁሌም እኔ?] የሚል ጽሑፍ የሰፈረበትን ካናቴራ ማሊያውን ገልጦ እንዳሳየው፣ በኋላም ለምን እንዲህ አልክ ሲባል ‹‹እኔን ተውኝ ለማለት ፈልጌ ነው›› እንዳለው፣ ትራምፕም ለምን የእኔ የተለየ ሆነ በሚል በትዊተራቸው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

‹‹የሴኔቱ ደኅንነት ኮሚቴ ቢልና ሒላሪ [የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተንና የቀድሞዋ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባለቤታቸው ሒላሪ ክሊንተን] ከፍተኛ መጠን ያለው ዩራኒየም ወደ ሩሲያ እንዲሄድ ያደረጉትን ስምምነት አይመረምርም?›› ሲሉ ትራምፕ ትዊት አድርገዋል፡፡

ሲኤንኤን ትራምፕ ቀልብ ለመሳብ ብሎ የሚታወቅ ታሪክ ደግሞ አንስቷል ሲል፣ ትራምፕ ደግሞ የትራምፕና የሩሲያ ጉዳይ ጥልፍልፎሽ የበዛበት ነው ብለዋል፡፡  

በትራምፕ ሥልጣን የመጀመሪያው ወር፣ አንድ ወር ሳያገለግሉ ከሥልጣን የለቀቁት የአገሪቱ ብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ማይክል ፍሊን ከሥልጣን ለመልቀቃቸው ምክንያቱ፣ ትራምፕ የፕሬዚዳንትነቱን በዓለ ሲመት ከማድረጋቸው ሳምንት አስቀድሞ በአሜሪካ ከሩሲያ አምባሳደር ጋር በነበራቸው የስልክ ንግግር ነው፡፡

የፍሊን የስልክ ንግግር አሜሪካ በሩሲያ ላይ ስለጣለችው ማዕቀብ ቢሆንም፣ ለአሜሪካው ምክትል ፕሬዚዳንት ማይክ ፔንስ የተናገሩት ግን ሸራርፈው ነበር፡፡ የተሟላ መረጃ ካለመስጠታቸው አስቀድሞም ስለነበራቸው ውይይት ሲጠየቁ ክደው እንደነበርም ይታወሳል፡፡      

ዶናልድ ትራምፕ የቀድሞው ፕሬዚዳንት በራክ ኦባማ በምርጫ ቅስቀሳው ወቅት ስልኬን አስጠልፈውብኝ ነበር በማለት ያቀረቡት መሠረተ ቢስ የተባለ ወሬ የዓለም መነጋገሪያ ከመሆን አልፎ፣ የመገናኛ ብዙኃኑ መቀለጃ ሆኖ መሰንበቱ አይዘነጋም፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...