ብሔራዊ ፌዴሬሽኖችን የሚወክለው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ቅዳሜ መጋቢት 23 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዳማ በሚያከናውነው ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴውን ለመጪዎቹ አራት ዓመታት የሚያስተዳድሩትን የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አመራር ምርጫ ያደርጋል፡፡
ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫው የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ብቸኛ ዕጩ ሆነዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይኦሲ) ቻርተር መሠረት በ1960 ዓ.ም. ዳግም የተደራጀው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ቀጥሎ ጠንካራ አቅም ፈጥሮ ጉልህ እንቅስቃሴ ከሚያደርጉ የስፖርት ተቋማት መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው የራሱን ቢሮ ከማደራጀቱም በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት በዓይነቱም ሆነ በይዘቱ የተለየ የሆነውን የኦሊምፒክ አካዴሚ በነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በማስገንባት ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ቅዳሜ በአዳማ በሚያደርገው ዓመታዊ ጉባኤ ለመጪዎቹ አራት ዓመታት ተቋሙን የሚያስተዳድሩ የሥራ አስፈጻሚ ምርጫ እንደሚያደርግ ኦሊምፒክ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡ ከተለያዩ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች አትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣ እጅ ኳስ፣ ቅርጫት ኳስ፣ ወርልድ ቴኳንዶ፣ ጅምናስቲክ፣ ውኃ ዋና፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ቦውሊንግ፣ ካራቴ፣ ውሹ፣ ክብደት ማንሳት፣ ባድሜንተንና መረብ ኳስ ፌዴሬሽኖች ከእያንዳንዱ እንደ አንድ በአጠቃላይ 15 ዕጩ ተወዳዳሪዎች ለሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ብሔራዊ መወከላቸው ኦሊምፒክ ኮሚቴው ቀደም ብሎ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
ላለፉት ስምንት ዓመታት የፕሬዚዳንትነቱን ኃላፊነትን ይዞ የቆየው የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ሲሆን፣ አሁንም ለሦስተኛ ጊዜ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑን የወከሉት ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ብቸኛ ዕጩ ሆነው ቀርበዋል፡፡
ለሥራ አስፈጻሚነት ምርጫ ከቀረቡት 14 ተወካዮች ውስጥ አብላጫ ድምፅ የሚያገኙት ሰባቱ የመጪዎቹ አራት ዓመት በብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴነት ይካተታሉ፡፡ አነስተኛ ድምፅ የሚያገኙት ደግሞ በብሔራዊ ፌዴሬሽኖቻቸው ይቆያሉ፡፡ የዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይኦሲ) አባሏ ወ/ሮ ዳግማዊት ግርማይ፣ በቀጥታ የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አባል ሲሆኑ፣ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ተወካይና የኦሊምፒያኖች ተወካይ ያለ ድምፅ እንደሚካተቱ በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታምራት አበበ አስረድተዋል፡፡