Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊዘጠና ተቋማት ሠራተኞቻቸው በማኅበር እንዲደራጁ ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ተገለጸ

ዘጠና ተቋማት ሠራተኞቻቸው በማኅበር እንዲደራጁ ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ተገለጸ

ቀን:

በዳዊት እንደሻው

የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ወደ ዘጠና የሚሆኑ ተቋማት ሠራተኞቻቸው በማኅበር እንዳይደራጁ ፈቃደኛ እንዳልሆኑና በዚህም ምክንያት ሠራተኞቹ ለመብት ረጋጣ እንደተጋለጡ አስታወቀ፡፡

ከእነዚህም ውስጥ በአዲስ አበባ የሚገኙ ትልልቅ ባለ ኮኮብ የግል ሆቴሎች፣ የግል ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች፣ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ ታዋቂ ድርጅቶች እንደሚገኙበት ኮንፌዴሬሽኑ ገልጿል፡፡

- Advertisement -

ከባንክና ከኢንሹራንስ ኩባንያዎች ጋር በተያያዘ ከአቢሲኒያ ባንክ አክሲዮን ማኅበር፣ እንዲሁም በመንግሥት ሥር ከሚተዳደሩ የባንክና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውጪ ያሉት ኩባንያዎች ማኅበራት እንደሌላቸው የኮንፌዴሬሽኑ መረጃ ያሳያል፡፡

በተጨማሪም እንደ ምድር ባቡር ያሉ በሥራቸው በርካታ ሠራተኞች የሚያስተዳድሩ የመንግሥት ተቋማትን በተመለከተ ኮንፌዴሬሽኑ ተደጋጋሚ ሙከራዎች ቢያደርግም፣ እስካሁን ማኅበራት ማቋቋም እንዳልተቻለ የኮንፌዴሬሽኑ የኢንዱስትሪ ግንኙነትና ማደራጀት ክፍል ኃላፊ አቶ ሙሉነህ ደሳለኝ ገልጸዋል፡፡

በዚህም ምክንያት ሠራተኞች መብታቸው ሲረገጥ የሚከላከልላቸው አካል እንደሌለና ከዕድገትና ከደመወዝ ጋር የተያያዙ ቅሬታዎች በአብዛኛው እያስተናገድን ነው ሲሉ አቶ ሙሉነህ ይናገራሉ፡፡ እስካሁን ከኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በኩል ለምን ማኅበር መመሥረት እንዳልተቻለ ግልጽ መልስ አልተሰጠም ብለዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ የተሰማሩ ፋብሪካዎች በተመሳሳይ ማኅበራት እንደሌሉዋቸውና ብዙዎቹም ይኼንን ለማድረግ እንቢተኛ እንደሆኑ አቶ ሙሉነህ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የተለያዩ የጨርቃ ጨርቅ አምራቾች ተመሳሳይ እንቢተኝነት በማሳየት ተጠቃሽ ናቸው ተብለዋል፡፡

ከአሁን ቀደም ሠራተኞችን ከተፈቀደው የሥራ ሰዓት ውጪ በማሠራት፣ ለአካላቸው ደኅንነት መከላከያ አስፈላጊ የሆኑ ዕቃዎችን የማያቀርቡና በሠራተኞቻቸው ላይ የአካልና የአዕምሮ ጫና የሚያደርሱ እንዳሉ ተገልጿል፡፡

ይኼ ችግር ሞጆ አካባቢ በሚገኙ አንዳንድ ፋብሪካዎች ተባብሶ መቀጠሉና በወረዳው ያለው የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ችግሩን መፍታት እንዳልቻለ አቶ ሙሉነህ አስረድተዋል፡፡

ከዚህም ጋር በተያያዘ መብታቸውን የሚያስጠብቅ ማኅበር ባለመኖሩ፣ በቻይናውያን ባለሀብቶች የሚተዳደር የቆዳ አምራች ኩባንያ ውስጥ ከሥራ ብዛት እጃቸውን እስከማጣት የሚያደርስ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው እንዳሉ ተገልጿል፡፡

ድርጅቱ እስከ አንድ ሺሕ የሚጠጉ ሠራተኞች ቀጥሮ 75 በመቶ የሚሆኑት ሠራተኞች ከድርጅቱ ጋር ውል እንደሌላቸውና ቋሚ ደመወዝ ያላቸው ሠራተኞች ጥቂት እንደሆኑ አቶ ሙሉነህ ይገልጻሉ፡፡ ቀሪዎቹ ሠራተኞች ደመወዛቸው ባመረቱት ልክ እንደሚከፈላቸው ገልጸዋል፡፡

ይኼ ደግሞ ሠራተኛው ከአቅሙ በላይ ለረዥም ጊዜ እንዲሠራና ለአደጋ እንዲጋለጥ እያደረገ እንዳለ አቶ ሙሉነህ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ያለውን ችግር እንዲያስተካክል ለድርጅቱ የአንድ ወር ጊዜ ሰጥተነዋል፤›› ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የፆታዊ ትንኮሳዎች ጥቆማ እንደደረሳቸው ይገልጻሉ፡፡

በዚህ የበጀት ዓመት የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን 180 ማኅበራትን ለማደራጀት ያቀደ ሲሆን፣ እስካሁን ወደ ስልሳ የሚሆኑት ብቻ ናቸው የተሳኩት፡፡ ከሆቴሎች ጋር በተያያዘ የአዲስ አበባ ሆቴል ባለቤቶች ማኅበር፣ ሆቴሎች ሠራተኞቻቸውን እንዳያደራጁ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር አቶ ሙሉነህ ይናገራሉ፡፡ የአገልግሎት ክፍያ የሚከለክሉና ያላግባብ ከሕግ ውጪ ከሥራ የሚያሰናብቱ ሆቴሎች እንዳሉ አቶ ሙሉነህ ተናግረዋል፡፡

ሪፖርተር የማኅበሩን ሰብሳቢ አቶ ቢኒያም ብሥራትን አግኝቶ ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡ አቶ ቢኒያም በሞባይል አጭር ጹሑፍ ለቀረበላቸው ማብራሪያ መልስ ሳይሰጡ ቀርተዋል፡፡

በቀጣይ ተቋማቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ አማካይነት ለመወያየት እንደሚሞከር፣ ነገር ግን ተቋማቱ አሻፈረኝ ካሉ ኮንፌዴሬሽኑ ጉዳዩን ወደ ሠራተኞችና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር እንደሚወስደው አቶ ሙሉነህ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ከዚህ ባለፈ የተቋማቱን ማንነት በግልጽ ለሕዝብ ማሳወቅ ያልተፈለገ ተፅዕኖ ይፈጥራል፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...