ከፍቅር ጥያቄ ጋር በተገናኘ የካቲት 21 ቀን 2009 ዓ.ም. ከቀኑ 10፡00 ሰዓት በጠራራ ፀሐይ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ የ17 ዓመት ታዳጊ አንገቷንና ጀርባዋን በስለት ወግቶ ገድሏል የተባለ የ21 ዓመት ወጣት፣ ማክሰኞ መጋቢት 19 ቀን 2009 ዓ.ም. ክስ ተመሠረተበት፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበው ክስ እንደሚያስረዳው፣ ተከሳሹ የ21 ዓመት ወጣትና የኮሌጅ ተማሪ ነብዩ ዮናስ ነው፡፡
ተከሳሹ ኑሀሚ ጥላሁን የተባለችውን የ17 ዓመት ታዳጊና የአሥረኛ ክፍል ተማሪ፣ ‹‹ከእኔ ጋር የነበረሽን የፍቅር ጓደኝነት ትተሽ ከሌላ ሰው ጋር ጀምረሻል፤›› በሚል ሰበብ ቂም ይዞ እንደነበር ክሱ ያስረዳል፡፡ የካቲት 21 ቀን 2009 ዓ.ም. ከካዛንቺስ እስከ ሜክሲኮ አደባባይ ድረስ አብረው ለመምጣት ታክሲ ሲጠብቁ፣ የጥርስ መፋቂያ ከሚሸጥ ግለሰብ ላይ ቢላዋ ገዝቶ እንደያዘም በክሱ ተጠቅሷል፡፡ በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ልዩ ቦታው አረቄ ፋብሪካ አካባቢ ሲደርሱ፣ ‹‹አትወጂኝም ወይ? የሚል ጥያቄ ሳቀርብላት አሉታዊ መልስ ሰጠችኝ፤›› በማለት፣ አንገቷ ላይ አንድ ጊዜና ጀርባዋ ላይ አንድ ጊዜ በመውጋት መሬት ላይ ጥሏት እንደሄደ ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ ወጣቱ ለማምለጥ ሲሮጥ በአካባቢው በነበሩ ሰዎች እጅ ከፍንጅ ሊያዝ መቻሉንም ክሱ አክሏል፡፡
ታዳጊዋ ሟች ኑሀሚ በፈሰሳት ደም ምክንያት በተፈጠረ የአተነፋፈስ መታወክ ሕይወቷ ሊያልፍ በመቻሉ፣ ወጣቱ በ1996 ዓ.ም. የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 539 (1ሀ) ላይ የተደነገገውን በመተላለፉ በከባድ ሰው መግደል ወንጀል ክስ እንደመሠረተበት የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡
ፍርድ ቤቱ ለተከሳሹ ክሱን አንብቦለት ግልጽ ስለመሆኑ ሲጠይቀው፣ ‹‹ግልጽ ነው፤›› ብሏል፡፡ የተመሠረተበት ክስና የተጠቀሰበት የሕግ አንቀጽ ወደፊት ጥፋተኛ ከሆነ የሚያስከትልበት ቅጣት ከባድ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ገልጾለት፣ አቅም ካለው በራሱ ጠበቃ እንዲያቆም ወይም መንግሥት ጠበቃ እንዲያቆምለት ጠይቆት ‹‹አቅም የለኝም፤›› ብሏል፡፡ በመሆኑም የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለተከሳሹ ተከላካይ ጠበቃ እንዲያቀርብለት ካዘዘ በኋላ፣ ለመጋቢት 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡