Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበአክሲዮን ማኅበራት ተደራጅተው መሬት የጠየቁ ከ10 ሺሕ በላይ ነጋዴዎች መንግሥትን አማረሩ

በአክሲዮን ማኅበራት ተደራጅተው መሬት የጠየቁ ከ10 ሺሕ በላይ ነጋዴዎች መንግሥትን አማረሩ

ቀን:

በአሥሩም ክፍላተ ከተሞች የገበያ ማዕከላት ለመገንባት የሚያስችል መሬት እንደሚሰጣቸው ተነግሯቸውና 583 ሚሊዮን ብር በዝግ ሒሳብ አስቀምጠው ከአሥር ዓመት በላይ ቢጠባበቁም፣ መሬቱ እንዳልተሰጣቸውና የሚያስተናግዳቸው አካል እንዳጡ ነጋዴዎች አማረሩ፡፡

ከአሥር ዓመት በላይ የቆየው ጥያቄ በመንግሥት ችላ መባሉ አማሮናል ያሉት የአዲስ አበባ ነጋዴዎች፣ በ110 አክሲዮን ማኅበራት የተደራጁና 583 ሚሊዮን ብር በባንክ ዝግ ሒሳብ ለአሥር ዓመታት አጠራቅመው መሬት ለማግኘት ሲጠባባቁ የቆዩ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡

ከ1994 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ በአሥሩም ክፍላተ ከተሞች የገበያ ማዕከላት ለመገንባት በርካታ አክሲዮን ማኅበራት ተመሥርተዋል፡፡ ከተመሠረቱት አክሲዮን ማኅበራት መካከል የተወሰኑት በድርድር መሬት ተሰጥቷቸው ወደ ግንባታ የገቡ፣ ግንባታ አጠናቀው ሥራ የጀመሩም አሉ፡፡ ነገር ግን በዚያኑ ወቅት ተደራጅተው በዝግ ሒሳብ ገንዘብ አስቀምጠው በተለያዩ ምክንያቶች ቦታ ያላገኙ አክሲዮን ማኅበራትም በርካታ ናቸው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በአሁኑ ወቅት ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቅሬታ በማቅረብ ላይ የሚገኙት 110 አክሲዮን ማኅበራት በሥራቸው 10,700 አባላት ያሉዋቸው መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ የሚገባቸውን አገልግሎት ማግኘት ባለመቻላቸው ለከፍተኛ ችግርና መጉላላት መዳረጋቸውን፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በመሰላቸታቸው ማኅበራቱን ለማፍረስ መቃረባቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አቶ ዘውዱ ግዛውና አቶ ደሳለኝ ክፍሌ መስተናገድ ያልቻሉ 110 አክሲዮን ማኅበራት ያቋቋሙት ‹‹የአክሲዮን ማኅበራት ኅብረት›› መፍትሔ ፈላጊ ኮሚቴ አስተባባሪዎች ናቸው፡፡

አቶ ዘውዱ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ሲነሳ፣ ሲንከባለል የቆየውን የአክሲዮን ማኅበራት የቦታ ጥያቄ ይመልሳል ብለው ተስፋ አድርገው ነበር፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ ግዮን ሆቴል ተካሂዶ በነበረው የመልካም አስተዳደር ጉባዔ ላይ ይህ ጉዳይ ጎልቶ የተነሳ በመሆኑ፣ ጉዳዩን የሚያጠናና የውሳኔ ሐሳብ የሚያቀርብ ኮሚቴ ይቋቋማል ብለው ነበር ብለዋል፡፡ ነገር ግን እስካሁን አንድ ውሳኔ ላይ መድረስ ባለመቻሉ ገንዘባቸውን በዝግ ሒሳብ አስቀምጠው የሚገኙ የከተማው ነጋዴዎች ተስፋ እንደቆረጡ፣ ለከፍተኛ ችግርም እየተዳረጉ መሆኑን አቶ ዘውዱ አስረድተዋል፡፡

አቶ ደሳለኝ በበኩላቸው፣ ምናልባት አስተዳደሩን ለውሳኔ ከረዳ በሚል  የአክሲዮን ማኅበራቱ ኅብረት የቴክኒክ ኮሚቴ አቋቁሞ ጥናት እንዳካሄደ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹የጥናቱንም ግኝት ለአስተዳደሩ አቅርበናል፡፡ ነገር ግን እስካሁን የተሰጠ ምላሽ የለም፤›› ሲሉ አቶ ደሳለኝ ቅሬታቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለይ በዶ/ር አርከበ ዕቁባይ በሚመራው የከተማው ጊዜያዊ አስተዳደር የሥልጣን ዘመን፣ በርካታ ነጋዴዎች በአክሲዮን እየተደራጁ ይነግዱ የነበሩበትን ቦታ በማፍረስ ግዙፍ የገበያ ማዕከላትን ሲገነቡ ቆይተዋል፡፡

አብዛኞቹ አክሲዮን ማኅበራት ግን በዚያው ዘመን የተቋቋሙ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ሊያለሙ የፈለጉትን ቦታ ሳያገኙ ቆይተዋል፡፡ በኅዳር 2004 ዓ.ም. የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ የወጣው አዋጅ ቁጥር 721 ጭራሹኑ ቦታ በድርድር የመስጠትን ጉዳይ በመዝጋቱ ባለአክሲዮኖቹ ሊስተናገዱ እንዳልቻሉ ተገልጿል፡፡

አቶ ዘውዱ እንደሚሉት፣ አብዛኞቹ አክሲዮን ማኅበራት የተቋቋሙት የሊዝ አዋጅ ከመውጣቱ በፊት እንደመሆኑ ሊስተናገዱ ይገባል፡፡ የሊዝ አዋጅም ቢሆን ልዩ አገራዊ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶች የሚስተናገዱበትን መንገድ ክፍት ስላደረገው ጉዳዩ ሊታይ እንደሚገባው ያብራራሉ፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ለዓለም ተሠራ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የከተማ ቦታ በሊዝ ስለመያዝ በወጣው አዋጅ ቁጥር 721/2004 መሠረት መሬት በድርድር መሰጠት ቆሟል፡፡ መሬት ለአልሚዎች እየቀረበ የሚገኘው በመደበኛና በልዩ ጨረታ ብቻ ነው፡፡

‹‹ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የሊዝ አዋጅ እንዲሻሻል የተወሰነ በመሆኑ፣ በአክሲዮን ማኅበር ተደራጅተው ቦታ የጠየቁ ነጋዴዎች ጉዳይ የሚካተት ከሆነ በሊዝ አዋጅ ማሻሻያ ከተደረገ በኋላ የሚታይ ነው፤›› ሲሉ አቶ ለዓለም ገልጸዋል፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...