Saturday, January 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየማዳበሪያ ንግድ አዋጅና አጠቃላይ የሕግ ማዕቀፍ በመዘጋጀት ላይ ነው

የማዳበሪያ ንግድ አዋጅና አጠቃላይ የሕግ ማዕቀፍ በመዘጋጀት ላይ ነው

ቀን:

ለኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ትልቅ የግብዓት ወጪ የሆነውን ኬሚካል ማዳበሪያ በአገር ውስጥ ለማምረት፣ የምርትና የገበያ ሥርዓቱን ለመምራት የሕግ ማዕቀፍ በመዘጋጀት ላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በአሁኑ ወቅት የተረቀቁት የሕግ ማዕቀፎች ሦስት መሆናቸውን የገለጹት አንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን፣ የሕግ ማዕቀፎቹን አስመልክቶ የባለድርሻ አካላት ውይይት በቅርቡ እንደሚጠራም ታውቋል፡፡

በዋናነት የተዘጋጀው የሕግ ማዕቀፍ የማዳበሪያ ፖሊሲና ስትራቴጂ ነው፡፡ ይህም ዘርፉ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ሊጫወት የሚገባውን ሚና በመለየት አቅጣጫ የሚያስቀምጥ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ማዳበሪያ አገር ውስጥ እንዲመረት በማድረግ በኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ላይ ማምጣት የሚቻለውን ትርጉም ያለው ለውጥ እንደሚያስቀምጥ፣ ከኢትዮጵያ ውጭ ኤክስፖርት በማድረግ ሊገኝ የሚችለውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አስመልክቶ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የተረቀቀው የሕግ ማዕቀፍ የማዳበሪያ ምርትና ንግድ አዋጅ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በአሁኑ ወቅት ማዳበሪያ በቀጥታ ከውጭ በከፍተኛ ወጪ የሚገባ ሲሆን፣ በአገሪቱ ውስጥ የማዳበሪያ የውጭ ግዥን የሚያስተዳድር ራሱን የቻለ ግልጽ ሕግ አለመኖሩን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም በመዘጋጀት ላይ የሚገኘው የማዳበሪያ ማምረትና ንግድ አዋጅ አጠቃላይ ለኢትዮጵያ ተስማሚ የሆነውን የማዳበሪያ ዓይነት በመለየት ስለአመራረቱ ሕጋዊ መሥፈርቶችን የሚያስቀምጥ ሲሆን፣ ለውጭ ገበያ ተፈላጊ የሆኑ የማዳበሪያ ዓይነቶች አመራረትን በተመለከተም በሕጉ እንደሚካተት አስረድተዋል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የማዳበሪያ ኢንዱስትሪ ኤጀንሲ ማቋቋሚያ አዋጅ በዝግጅት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ኤጀንሲው ማዳበሪያ ማምረት ላይ ለሚሰማሩ ኩባንያዎች ፈቃድ መስጠትና የቁጥጥር ሥራዎችን የማከናወን ኃላፊነት እንደሚኖረው ታውቋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የማዳበሪያ ማምረት ላይ ለተሰማሩ ኩባንያዎች ፈቃድ የሚሰጠው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሲሆን፣ በማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ላይ የተሰማራው ደግሞ መንግሥት ነው፡፡ ኤጀንሲው እንዲቋቋም የተፈለገው መንግሥት ከዚህ ዘርፍ እንዲወጣና የግል ኩባንያዎች ተሳትፎ እንዲጎለብት ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት የሞሮኮ ኩባንያ ኦሲፒ በአራት ቢሊዮን ዶላር የማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል፡፡ ይህ ኩባንያ የማዳበሪያ ፋብሪካውን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ለመገንባት ስምምነት መፈረሙ አይዘነጋም፡፡ ከአንድ ወር በፊት ከሞሮኮ የመጡ የኩባንያው ልዑካን ከመንግሥት ልማት ድርጅት ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች ጋር በኢትዮጵያ መንግሥት ድርሻ ላይ ውይይት ማድረጋቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ሌላው የማዳበሪያ ፋብሪካ ፕሮጀክት ከአምስት ዓመታት በፊት የተጀመረውና እስካሁን ድረስ መጠናቀቅ ያልቻለው የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ ነው፡፡

የዚህ ፋብሪካ ግንባታ የተጀመረው እ.ኤ.አ. በ2011 ነው፡፡ ግንባታውን በማከናወን ልምድ እንዲያካብት የተመረጠው የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ ግንባታውንና የሙከራ ሥራውን አጠናቆ ለኢትዮጵያ ኬሚካል ኮርፖሬሽን በ11 ቢሊዮን ብር ወጪ ለማስረከብ ስምምነት ፈጽሟል፡፡ ይሁን እንጂ ግንባታው ከአምስት ዓመታት በኋላም 41 በመቶ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት የዚህ ማዳበሪያ ፋብሪካ አጠቃላይ ወጪ 19 ቢሊዮን ብር መድረሱን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቅዱስ ሲኖዶስ ሦስቱን ጳጳሳት ስልጣነ ክህነታቸውን አንስቶ አወገዘ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ሰሞኑን ጥር 14...

አቶ እየሱስወርቅ ዛፉ ከህብረት ባንክ ቦርድ አባልነት ለቀቁ

አንጋፋው የፋይናንስ ባለሙያ አቶ እየሱስወርቅ ዛፉ ከህብረት ባንክ ቦርድ...

አቶ በረከት ስምኦን ከእስር ተፈቱ

ከአራት ዓመታት በፊት በተከሰሱበት በከባድሙስና ወንጀል ስድስት ዓመታት ተፈርዶባቸው...

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ ቢሯቸው እንደገቡ የፖለቲካ አማካሪያቸው ስለ ሰሜኑ ግጭት የሰላም ስምምነት አተገባበር ማብራሪያ ለመጠየቅ ገባ]

ክቡር ሚኒስትር ጥሰውታል? እንዴ? እስኪ ተረጋጋ ምንድነው? መጀመርያ ሰላምታ አይቀድምም? ይቅርታ...