የማሪታይም ጉዳይ ባለሥልጣን ማክሰኞ መጋቢት 19 ቀን 2009 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሆቴል በተካሄደው የምረቃ ሥነ ሥርዓት፣ ላለፉት አራት ወራት ያሠለጠናቸውን በሌሎች አገሮች የሚሠሩ ኢትዮጵያዊ መርከበኞችን አስመረቀ፡፡ የማሪታይም ጉዳይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን አበራ እንደተናገሩት፣ ዓለም አቀፉ የማሪታይም ድርጅት ባህረተኞች በሚመደቡበት የሥራ መደብ ሠልጥነው የብቃት ማረጋገጫ ሠርቲፊኬት መያዝ እንደሚገባቸው ያምናል፡፡
በዚህ መሠረት የማሪታይም ጉዳይ ባለሥልጣን ከስድስት ዓመት በፊት የፊሊፒንስ መዲና በሆነችው ማኒላ ከተማ በተካሄደው ጉባዔ እንዲሻሻል በተደረገው የብቃት ማረጋገጫ ሠርቲፊኬት አሰጣጥ መሥፈርትን ለሚያሟሉ፣ በባህር ጠረፍ አካባቢ ለተሰማሩ ኢትዮጵያውያን ባህረተኞች በሦስት ዙር ሥልጠና በአጠቃላይ ለ224 ባለሙያዎች የብቃት ማረጋገጫ ሠርቲፊኬት ሰጥቷል፡፡
ነገር ግን እነዚህ ባህረተኞች የተሰጣቸው የምስክር ወረቀት እንደማያሠራቸው በመግለጽ እስከ ‹‹ቺፍ ኢንጂነር›› ደረጃ ድረስ የብቃት ማረጋገጫ ሠርቲፊኬት እንዲሰጣቸው በድጋሚ ጥያቄ ማቅረባቸው ተመልክቷል፡፡ ሥልጠናውን የመስጠት ጉዳይ ውዝግብ ፈጥሮ እንደነበር ተጠቁሟል፡፡
የማሪታይም ጉዳይ ባለሥልጣን ይህንን የባህረተኞች ጥያቄ ከገመገመ በኋላ ጥያቄያቸውን የተቀበለ ሲሆን፣ ጥያቄያቸውን ተግባራዊ ለማድረግ ከኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ኢንተርፕራይዝ፣ ከባህረተኞች ማኅበርና ከአማካሪ ድርጅቶች የተወጣጣ ኮሚቴ አቋቁሟል፡፡ በዚህ መሠረትም በመጀመሪያ ዙር ፓይለት ፕሮግራም 83 ባህረተኞችን ማስመረቁን አቶ መኮንን አስታውቀዋል፡፡
‹‹ሥልጠና የሚፈልጉ ሌሎች ባህረተኞችን ጥያቄ ለማስተናገድ በፓይለት ፕሮግራም መቀጠል ስለማይቻል፣ ባለሥልጣኑ ቋሚ በሆነ ትምህርት ቤት ሥልጠና ለመስጠት ከዋነኛ ተዋናዩ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ኢንተርፕራይዝ ጋር ውይይት እያደረገ ነው፤›› ሲሉ አቶ መኮንን ገልጸዋል፡፡
በማሪታይም ጉዳይ ባለሥልጣን ባለቤትነት የሚሰጠው ሥልጠና ግዙፍ መርከቦችን የሚመሩ ኦፊሰሮችን የሚያበቃ ነው፡፡ አቶ መኮንን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከዚህ ቀደም ሥልጠና የሚሰጠው በህንድ፣ በእንግሊዝ በኋላም በጋና ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ለኢትዮጵያም ሆነ ለውጭ አቻ ተቋማት አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች በኢትዮጵያ ይሠለጥናሉ፡፡
‹‹በኢትዮጵያ የማሪታይም ኢንስቲትዩት ይቋቋማል፡፡ የሎጂስቲክስ ኢንተርፕራይዝ የባቦ ጋያ ባህርተኞች ማሠልጠኛ ተቋምን ማዕከል በማድረግ ሥልጠና ይሰጣል፤›› ሲሉ አቶ መኮንን ተናግረዋል፡፡
የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ደሳለኝ አምባው በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው ለተመራቂዎች ሠርቲፊኬት ሰጥተዋል፡፡