Tuesday, April 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከዘጠኝ ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ለኦሞ ኩራዝ ስኳር ፕሮጀክቶች የመስኖ ግንባታ ሊካሄድ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ንግድ ባንክ ለፕሮጀክቱ አሥር ቢሊዮን ብር አበድሯል

በደቡብ ክልል በመስኖ ልማት ዘርፍ ትልልቅ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ እንደሆነ የተጠቀሰውና 185 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው የኦሞ ኩራዝ መስኖ ልማት ፕሮጀክት ዋና የቦይ፣ የመስኖ ካናሎችንና ተያያዥ ግንባታዎችን ለማከናወን ከዘጠኝ ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያለው ስምምነት ተፈረመ፡፡

በግዙፉ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ባለቤትነት ይህንን ሜጋ ፕሮጀክት እንዲገነቡ ከተመረጡት ውስጥ ሦስቱ በኮርፖሬሽኑ ሥር የሚተዳደሩት የግድብና መስኖ አውታር ልማት ዘርፍ፣ የውኃ መሠረተ ልማት ኮንስትራክሽን ዘርፍና የትራንስፖርት ኮንስትራክሽን መሠረተ ልማት ዘርፍ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ሦስቱ ባሻገር የግንባታ ሥራው የተሰጣቸው ሌሎች ሁለት ተቋማት ደግሞ የደቡብ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራከሽን ኢንተርፕራይዝና የቻይናው ጂያንግዚ ኃይድሮፓወር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል መሆናቸው ታውቋል፡፡

ግንባታውን እንዲያካሂዱ የተመረጡት እነዚህ ተቋማት 185 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን የኦሞ ኩራዝ የቦይ፣ የመስኖ እንዲሁም የመዋቅር ግንባታ ፕሮጀክቱን ተከፋፍለው የሚሠሩ ሲሆን፣ አጠቃላይ የግንባታ ሥራዎቹን በአሥር ወራት አጠናቀው ለማስረከብ በመስማማት ቅዳሜ፣ የካቲት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. ከኮርፖሬሽኑ ጋር የግንባታ ውል ተፈራርመዋል፡፡  

ከፕሮጀክት ውስጥ የቻይናው ጂያንግዚ ኃይድሮፓወር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር 4.1 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚጠይቀውን የቦይ ግንባታ፣ የፕሮጀክቱን የውኃ መቆጣጠሪያና መሰል መዋቅራዊ ግንባታዎች ያከናውናል፡፡

 የኦሞ ኩራዝ መስኖ ልማት ፕሮጀክት አካል የሆኑትን ሁለት የመስኖ ቦይ መስመሮች ግንባታዎችን በኮርፖሬሽኑ ሥር እንደ እህት ኩባንያ የሚታየው የውኃ መሠረተ ልማት ኮንስትራክሽን ዘርፍ ከ1.49 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ለመገንባት ፊርማውን አኑሯል፡፡ የዚሁ ፕሮጀክት አካል የሆነውን ሦስተኛውን የመስኖ ቦይ መስመር ግንባታም ይኸው የውኃ መሠረተ ልማት ኮንስትራክሽን ዘርፍ በ485 ሚሊዮን ብር እንደሚገነባ ስምምነቱ በተደረገበት ወቅት ተገልጿል፡፡

የፕሮጀክቱን አራተኛና አምስተኛ የሥራ ክፍሎች ደግሞ የደቡብ ውኃ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ኢንተርፕራይዝ በ1.97 ቢሊዮን ብርና በ394 ሚሊዮን ብር እንደሚገነባ ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት ተነግሯል፡፡

ስድስተኛው የፕሮጀክቱ ክፍል የሆነውን የመስኖ ቦይ ግንባታ እንዲሠራ የተመረጠውና ቅዳሜ ስምምነት የፈጸመው የትራንስፖርት መሠረተ ልማት ዘርፍ የተባለው ሌላኛው በኮርፖሬሽኑ ሥር የሚገኝ የግንባታ ዘርፍ ተቋም ነው፡፡ ይህ ተቋም የተረከበው ሥራ በጠቅላላው 584 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚጠይቅ ታውቋል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኃይለ መስቀል ተፈራ (ኢንጂነር) እንደገለጹት፣ ከተለመደው የኮንትራት አሰጣጥ በተለየ መልኩ በ‹‹እደላ›› ሥርዓት ለግንባታ የተላለፉት ሥራዎች ላይ ከተሳተፉትና የኮንትራት ውል ከፈጸሙት ውስጥ ሦስቱ በኮርፖሬሽኑ ሥር የሚተዳደሩ፣ ነገር ግን ለየብቻቸው ራሳቸውን ችለው በተቋምነት የተዋቀሩ የተቋራጭ ሥራዎችን የሚያከናውኑ አካላት ናቸው፡፡

ያለጨረታ በእደላ ሥርዓት የግንባታ ሥራዎቹ የተሰጣቸው እነዚህ ተቋማት ከዚህ ቀደም የነበራቸው የሥራ አፈጻጸም ተገምግሞ በነበራቸው ጥሩ አፈጻጸም እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በአገር በቀል ኮንትራክተሮች ሊሠሩ የማይችሉና በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ክፍተት ይኖርባቸዋል የተባሉትን ሥራዎች እንዲያከናውን  የቻይናው ኩባንያ እንዲሳተፍ መደረጉ በዕለቱ ከተሰጠው ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በበጀት ዓመቱ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሠራ የተፈለገው የኦሞ ኩራዝ የመስኖ ቦይ እንዲሁም የውኃ መስመር ግንባታ ዋናው ዓላማ በአካባቢው የተገነቡት የስኳር ፋብሪካዎች ለአገዳ ልማት የሚያስፈልጋቸውን የውኃ አቅርቦት ለማድረስ ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት ከስኳር ልማት ባሻገር በአቅራቢያው የሚካሄዱ ሌሎች ሥራዎችንም ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ በአገሪቱ የግብርና ሥራዎች በተለይም ለሰፋፊ እርሻዎች ልማት አዲስ ሞዴል አሠራር ሊሆን እንደሚችል የኮርፖሬሽኑ የግንባታና መስኖ ልማት አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙላቱ ታፈሰ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ የቦይና የውኃ መስመሮች ግንባታውን ከማካሄድ ባሻገር ከአሥር ወራት በኋላ እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቀውን ፕሮጀክት ተረክቦ በማስተዳደር ለስኳር ፋብሪካዎቹ ውኃውን በሽያጭ ያቀርባል ተብሏል፡፡ ስኳር ልማቱ የሚፈልገው የውኃ መጠን ምን ያህል እንደሆነ፣ ውኃ መቼ እንደሚፈልግ እንዲሁም ለስኳር ልማቱ የሚቀርበው ውኃ በምን ያህል ዋጋ እንደሆነና ሌሎችም ዝርዝር ጉዳዮች ተጠንተው ከስኳር ኮርፖሬሽን ጋር የውኃ ሽያጭ ስምምነት የተፈረመበት ፕሮጀክት እንደሆነም አቶ ኃይለ መስቀል ተናግረዋል፡፡ ሥራ አስፈጻሚው፣ የስኳር ፋብሪካዎቹ ለሚቀርብላቸው ውኃ ተገቢውን የአገልግሎት ዋጋ እንዲከፍሉ ይደረጋል ይበሉ እንጂ በሽያጭ ለሚቀርበው ውኃ ምን ያህል ዋጋ እንደተተመነለት ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡

የመስኖ ፕሮጀክቱ 125 ሺሕ ሔክታር መሬት ውኃ ገብ እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችል ውኃ የመሸከም አቅምና አስተማማኝ ፍሰት እንዲፈጠር የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡ ከዚህ ውስጥ በመጀመርያው ምዕራፍ 25 ሺሕ ሔክታር በማልማት ለኦሞ ኩራዝ ስኳር አንድ፣ ሁለትና ሦስት ፋብሪካዎች የሸንኮራ አገዳ ለማቅረብ ያስችላል፡፡  ከዚያም 93 ኪሎ ሜትር ተጉዞ 50 ሺሕ ሔክታር የመስኖ መሬት በማልማት ለስኳር ፋብሪካ ቁጥር አምስት ሸንኮራ አገዳ ማቅረብ የሚያስችል አቅም ይኖረዋል፡፡ ለዚህ ፕሮጀክት የሚያስፈልገውን ገንዘብ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሚገኝ ብድር የሚሸፈን ይሆናል፡፡ እንደ አቶ ኃይለ መስቀል ገለጻ፣ ለዚህ ፕሮጀክት ባንኩ አሥር ቢሊዮን ብር ብድር መፍቀዱ ታውቋል፡፡

ፕሮጀክቱ ከተጠናቀቀ በኋላ የኦፕሬሽንና ጥገና ሥራዎችን በማከናወን የኮርፖሬሽን ግድብና መስኖ አውታሮች አስተዳደር ዘርፍ ባለቤት ሆኖ ከሚሸጠው ውኃ ብድሩ ተመላሽ ያደርጋል ተብሏል፡፡ ባንኩ ብድሩን የፈቀደውም በኢትዮጵያ የሚተገበረው የመስኖ የውኃ ሽያጭ ብድሩን ለማስመለስ የሚያስችል ገቢ እንደሚያገኝ በማመኑ እንደሆነም ተነግሯል፡፡

ፕሮጀክቱ ከአሥር ሺሕ በላይ ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድሎች በመፍጠር የአካባቢውን አርብቶ አደር ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የገለጹት ሥራ አስፈጻሚው፣ የመስኖ ውኃው ለአካባቢው አርብቶ አደሮችና አርሶ አደሮች ጥቅም እንደሚሰጥ ጠቅሰዋል፡፡

ይህንን ፕሮጀክት ልዩ ከሚያደርገው አንዱ የመስኖ ግንባታው በሚከናወንበት ክልል የሚገኙ ፓርኮች ተፈጥሮአዊ ይዞታቸው ተጠብቆ እንዲቆይ፣ የውኃ ማስተላለፊያ መስመሩ ከ50 ኪሎ ሜትር በላይ በልዩ ግንባታ ተሸፍኖ እንዲሠራ ዲዛይን መደረጉ ነው ተብሏል፡፡ የዲዛይኑም ሆነ የግንባታው ሒደት ተፈጥሮን ለመጠበቅና ለመንከባከብ ከፍተኛ ጥንቃቄ የተደረገበት ምሳሌያዊ ፕሮጀክት መሆኑን ኃላፊዎቹ አስታውቀዋል፡፡ የማማከር ሥራውን የፌዴራል የኮንስትራክሽን ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ሥራዎች ኮርፖሬሽንና የደቡብ ዲዛይንና ኮንስትራክሽን ቁጥጥር ኢንተርፕራይዝ ተረክበዋል፡፡

የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከአንድ ዓመት በፊት ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ካፒታል መቋቋሙ ይታወቃል፡፡ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ግዙፍ መንግሥታዊ ኩባንያ ለመፍጠር ታስቦ ሲቋቋም፣ ቀደም ብለው በተናጠል ሲንቀሳቀሱ የነበሩትን የኢትዮጵያ መንገድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ የውኃ ሥራዎች ኮርፖሬሽንና የኢትዮጵያ የትራንስፖርት ዲዛይንና ቁጥጥር ሥራዎች ድርጅትን በማዋሃድ ነው፡፡

በአገሪቱ ከሚገኙ ግዙፍ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች አንዱ ሆኖ የመጣው ይህ ኮርፖሬሽን፣ በዚህ ዓመት መጀመርያ የኢትዮጵያ የተገጣጣሚ ሕንፃ አካላት ማምረቻ ድርጅትንም መጠቅለሉ አይዘነጋም፡፡

ኮርፖሬሽኑ ከ15 ሺሕ በላይ ሠራተኞችንና በተመሳሳይ ሥራ ዘርፍ ውስጥ የነበሩ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን አዋህዶ እንዲይዝ ከተደረ በኋላ የትራንስፖርት፣ የውኃ፣ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎችና መሣሪያዎች አስተዳደርና አቅርቦት ሥራዎችን ማከናወን ጀምሯል፡፡ የሕንፃ ቴክኖሎጂና መሰል የሲቪል ግንባታዎችን እንዲያናውን ኃላፊነት የተሰጠው ይህ ተቋም፣ አሁን ደግሞ ግዙፍ የመስኖ ግድብ ሥራዎችን የመገንባትና የማስተዳደር ሥራም ተረክቧል፡፡

በተለይም የመስኖ ውኃ ሽያጭ ሥራ የሚሠራ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ሥር የነበሩ አሥር የመስኖ ግድቦችን ተረክቦ በማስተዳደር ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህ ኮርፖሬሽን ከኢትዮጵያ ውጭም በግንባታና በመሳሰሉት መሠረተ ልማት ሥራዎች ላይ ተወዳዳሪ መሆን እንደሚጠበቅበት ከተሰጠው ተልዕኮ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ባለፈው ቅዳሜ የተካሄደውን የግንባታ ስምምነት በኮርፖሬሽኑ በኩል ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ሙላቱ፣ ግንባታዎቹን ለማከናወን የትራንስፖርት መሠረተ ልማት ኮንስትራክሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዓለማየሁ አስፋው፣ የውኃ መስኖ ልማት ኮንስትራክሽን ዘርፍ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አታክልቲ ተካ፣ የጂያንግዚ ሃይድሮፓወር ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚ/ር ዋንግ ዩፒንግና የደቡብ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤልያስ ኪሮ ተፈራርመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች