ትዕግሥት በተፈታተነ የረዥም ሰዓት ጥበቃ አንዲት ታክሲ ዞራ መጣች። እነሆ ከካዛንቺስ ፒያሳ ልንጓዝ መሆኑ ነው። ዛሬም እንደ ትናንቱ፣ እንደ ሳምንቱ፣ እንደ አምናው ለመጓዝ. . . የሕይወት ዋናው ቀመር በእንቅስቃሴ የተነደፈ መሆኑን ማንም ሳያስረዳን የተረዳነው የኑሮ ፊዚክስ ነው። ‹በእንቅስቃሴ ውስጥ ትግል፣ በትግል ውስጥ ለውጥ› በሚል ርዕስ መጽሐፍ ሳይጻፉ በፊት ይህን እውነት የሁሉም ሰው ነፍስ ደርሰችበት። እናም ያለአስገዳጅ እየተጓዘች፣ እየሮጠች፣ እየታገለች ነፍሳችን በሥጋ አድራ ትኖረዋለች። ኑሮ የዕለት ጉርስን ለማግኘት በመላወስ ውስጥ አቻና ተቀናቃኝ ዓላማ ሳይኖረው ዘልቋል።
የሰው ልጅ ከእምነቱ፣ ከፍልስፍናው፣ ከፍላጎቱና ከምኞቱ ለአፍታ ገለል ሲል የሚታየው ሲጓዝ ብቻ ነው። ሒደት ዋና የለውጥ መካኒክ ነውና። ታክሲዋ በሚተራመሰውና በሚጋፋው ሰው እየተወዛወዘች የቻለችውን ያህል አስገብታን ስታበቃ ሞላች። “ይኼው ነው እኮ! ቦታ እስኪይዙ ትግል ግድ ነው፤” አለና አንድ ጎልማሳ ተሳፋሪ ደግሞ ወዲያው መልሶ፣ “ሕይወትን ማለቴ ነው ጎበዝ። ደግሞ አደራችሁን ስውር ፖለቲካ የለውም። ኑሮ እግር ተሰቅሎ አይሆንም ለማለት ነው፤” እያለ አጠገቡ ላለው ወጣት ያብራራ ጀመር። ውስጡ ሌላ ስምና ቅጥያ እንደፈራ ንግግሩ ይመሰክራል። ወያላው ገብቶ በሩን እየዘጋ “ሳበው!” ይለዋል ሾፌሩን። ሁላችንም ሳይታወቀን ከቦታ ቦታ እንጎተታለን!
ከጎልማሳው አጠገብ የተቀመጠው ወጣት፣ “አይዞህ ገብቶናል። ምን ይህን ያህል አጨናነቀህ?” ብሎ ሊያረጋጋው እየሞከረ ጠየቀው። “ወዳጄ ሥልጣን ለማግኘት ብቃት ሳይሆን አቋራጭ እንደ አማራጭ በሚያዝበት አገር እንዲያ ብዬ መናገር እንዴት አያደናብረኝ?” አለው ቀስ ብሎ አሁንም ሌላው ሰው እንዳይሰማው። “አገራችን እኮ የዴሞክራሲ ባህል እንደ ልቡ የሚንሸራሸርበትን መስመር እየዘረጋች ነው፤” ሲለው ወጣቱ ጎልማሳው ሳቅ እያለ “እ? . . . ምነው ግድቡን ረሳኸው?” አለው። ተግባቡና ተሳሳቁ። ከሳቃቸው ኋላ የምሬት ወዮታ ስንሰማ ጆራችን እዚያ ተሰደደ። “በሞቀበት መሰደድ ግን በደም ነው እንዴ የወረስነው?” ስትለኝ አጠገቤ የተቀመጠችው ልጅ ቁንጅናዋን አስተዋልኩ። “ቆንጆ አለማየት ከብዶን፣ ኑሮ ከብዶን እንዴት ይሆን የምንኖር?” ይላል ሌላው እያንሾካሾከ።
የሚሊኒየሙ ዓብይ ጥያቄ አትሉም? “ውይ ውይ ውይ! ኧረ ምን አባታችን ይሻለን ይሆን?” ወደሚለው አውቆ አበድ መሳይ ወጣት እንደ ዞርን ነን። ለራሱ በፈጠረው ነፃነት ውስጥ ሌላ የሚያይም የሚሰማም አይመስልም። “ምነው?” አሉት ‹አንዳንድ› አጠገቡ የተቀመጡ ተሳፋሪዎች። “ታክሲ ነዋ። እዚህ ቆሜ ስጠብቅ ሰዓቱ አልፎኛል። ብደርስም አልገባም እኮ፤” አለ ጨንቆትና ከፍቶት። “የት ነው የማትገባው?” አሉት አንድ አዛውንት። “ክፍል ነዋ። አስተማሪው ከጀመረ በቃ አያስገባም፤” ብሎ ሳይጨርስ፣ “አይዞህ ማርፈድ ራሱ አንዱ የትምህርቱ አካል ነው። ጎበዝ! ስም ጠሪ የለብንም እንጂ ለአንዳንዶቻችን እኮ ውሏችን ትምህርትና ፈተና ሆኗል፤” ብለው አዛውንቱ ፈገግ አሰኙን። ‘ተጨዋች ሽማግሌ አንቱ ሳይባል ያረጃል’ ማለት እሳቸው ይመስሉ ነበር!
ወያላው ሒሳቡን እየተቀበለ፣ “ሳንቲም ካላችሁ ተባበሩኝ!” ሲል ያስተጋባል። ሾፌሩ “ትርፍ ጭነሃል እንዴ?” ብሎ ድንገት በርግጎ ጠየቀው። “አዎ! ሁለት ሰው አለኝ ምነው?” ከማለቱ ሾፌሩ በብስጭት፣ “ስንቴ ትርፍ አትጫን ብዬ ላስጠንቅቅህ ግን? ያው ሁለት ናቸው፤” ብሎ ትራፊኮቹን እየጠቆመ የታክሲዋን ፍጥነት አቀዘቀዘ። ወያላው “አንተ ደግሞ? ሀቀኝነት ማንን ሲያነሳውና ሲያከብረው አይተህ ነው ትርፍ አልጭንም የምትለው? እየተበላንም ቢሆን መሥራት አለብን ፍሬንድ፤” ብሎ ያደፋፍረው ጀመር። ትራፊኮቹ አፍ ለአፍ ገጥመው እያወሩ ሳያዩን አለፍናቸው። “አቤት ሥራና ወሬ! በዚህ ዓይነት ስንቱ አገር አጥፊ ይሆን ተዝናንቶ የሚኖረው? ኧረ አቋራጩና ተቆራራጩ በዛ?” አለች መጨረሻ የተቀመጠች ወጣት። “ምናልባት ይኼ መከረኛ ኮምፒዩተር ከ’ዴስክቶፕ’ በ’ሾርትከት’ ‘ፕሮግራም’ እየከፈተ ማቋረጥን ክፉኛ አለማምዶን ይሆን?” ብሎ ፈገግ አሰኘን አንዱ። እውነቱን እኮ ነው! ሰው ከአየውና ከሰማው ውጪ መች ይኖርና!
“አበስኩ ገበርኩ!” ይላሉ መጨረሻ ወንበር የተቀመጡ አዛውንት። ግርማ ሞገሳቸው ልዩ ነው። ፀገሩራቸው ሪዛቸውን ጨምሮ ቡፍ ብሎ ቆሟል። “ምነው አባት? ምን ሆኑ?” አጠገባቸው የተቀመጠች አጭር ቀይ ኮረዳ ታጫውታቸዋለች። “የምሆነው እየጨነቀኝ እንጂ ምንም አልሆንኩ እስካሁን!” መለሱላት በእርጋታ። “ማን የሚሆነውን ያውቃል ብለው ነው?” ለማወጣጣት ነው ነገሩ። “እሱን ብዬ እኮ ነው ልጄ ነጋ ጠባ አሟሟቴን አሳምረው የምለው። ሳይሰለቸው ቀረ ብለሽ ነው?” ፍስስ ይላሉ ደርሰው በተመስጦ። “ምነው ካልጠፋ ነገር አሟሟትዎ ያስጨንቀዎታል? ልጆች የሉዎትም? ባለቤትዎስ?” የምትለቃቸው አትመስልም ወጣቷ።
“ኧረ ሁሉም አሉ። የሁሉም አጠገቤ መኖር ነው አንድም የሚያሳስበኝ። በዚያ ላይ አንዳንዱ በአሟሟቱ ይበደልና በአቀባበሩ ይካሳል። ለምሳሌ ይኼው እንደምትሰሚው በአሸባሪዎች ሴራ የሞቱ ሰዎች ምንም እንኳ እንደወጡ በዚያው አፈር ቢለብሱም፣ ይኼው ዓለም በየሰዓቱ በየደቂቃው እያሰባቸው ይውላል። ዓለም ይኼው በባንዲራቸው ምሥሉን እስከ መሸፈን ደርሶ የሐዘናቸው ተካፋይ ሆኗል። ሲኖሩ ተረስቶ ሲሞቱ መታወስ እጅግ የሚገርመኝ የዓለም ጠባይ ነው ልጄ። አየሽ ብዙ ብዙ አለ የሚያሳስበኝ፡፡ ወዲያ ደግሞ ወደ ጋዛ ወደ ፓለስቲንና ወደ አፍጋኒስታን ብትሄጂ በቦምብ ተገደልሽ፣ ታመሽ ሞትሽ፣ ሮኬት አገኘሽ፣ ፍንጣሪው ዓይንሽን አጠፋው ከአበቃልሽ አበቃልሽ ነው። በበኩሌ ታዲያ በሕይወት ስኖር ለመኖሬ ዕውቅና ባይሰጠኝም ስሞት ቀባሪ ካላሳጣኝ አሟሟቴ ‘ክላሲ’ ባይሆንም እንኳ አስታዋሾቼ ‘ክላሲ’ በሆነ መንገድ ካስታወሱኝ ምን እፈልጋለሁ?” ብለው ፈገግ አሉ። ወይ ሰው! መፈለግም አለመፈለግም በማይችልበት ሁናቴ ውስጥ የሚገኝበት ቀን እንደሚመጣ እያሰበም፣ የሚፈልገውና የማይፈልገውን ሲመርጥ ይኖራል? ‹‹ታዲያ ከሞት በኋላም ምርጫ አማረህ?›› ሲል የሰማነው ወያላ ስንት ቢያጆ ሸቅሎ ይሆን ከነጋ?
ጉዞ እየቆየ ነውና የሚያስተያየው አንድ እርጉዝ ተሳፋሪ በረዥሙ ስትተነፍስ አየናት፡፡ ብዙም ሳትቆይ፣ “እኔስ ምን አማረኝ መሰላችሁ?” ብላ ዓይናችን አስፈጠጠችው። በዚህ የኑሮ ውድነት እርጉዝ እናቶች እንዳማራቸው ሳይበሉ እንደሚወልዱ ድንገት ብናስብ ዘመኑን ክፉኛ ረገምነው። “ምን የእኔ ልጅ?” አሉዋት አዛውንቱ በትዝታ ወደ ኋላ እያጠነጠኑ ያሉ መስለው። “ኮምፒዩተር . . .” ብላ ቀጣዩን ቃል ሳትናገር፣ “ጉድ ሆንን ሾፌር! የዘንድሮ እርግዝና ደግሞ ምነው ምግብና መጠጡን ትቶ ቴክኖሎጂ ላይ ሆነሳ? የእኔዋ ባለፈው ‘አይፎን’ አማረኝ ብላ በአለ በሌለ አቅሜ አስገዛችኝ፤” ብሎ ወደ ጎልማሳነት ዕድሜ እየተጠጋ ያለ ወጣት አወራ።
“ኧረ እኔ አልጨረስኩም። እኔ ለማለት አስቤ የነበረው አገሬ ኮምፒዩተር የሚመረትባት፣ ስልክ፣ መኪናና ባቡር የሚመረትባት ሆና ማየት አማረኝ ነበር፤” ስትል ውጥረቱ ጋብ አለ። “ምናለበት የእኔዋም እንዳንቺ የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መሳካት ቢያምራት? ችግሩ ሁላችሁም ቢያምራችሁ ኮብልስቶኑ ተነጥፎ ሳያልቅ ምርምር የሚኖር አይመስለኝም፤” አላት። “ውይ ሴቶች? ቆይ ግን እንዲህ ሁሉም ‘ብራንድ’ እየለበሱ፣ በዝነኛ ሽቶ እየታጠቡ፣ ሽቅርቅር ብለው በከተማው የምናያቸው የኑሮ ውድነቱን በምን ቢቆጣጠሩት ነው?” ብሎ ከኋላችን ካሉት ወጣት ተሳፋሪዎች አንደኛው አንደኛውን ቢጠይቀው እንዳልሰማ ሆኖ ሌላ ወግ አስጀመረው። ‘ሰምተሃል!’ የሚሉዋት ደግሞ ፋሽን ሆናለች ዘንድሮ!
“ወይ ዘንድሮ! ለመሆኑ አሠሪዎቻችን፣ አስተማሪዎቻችን በታክሲ ጥበቃ የምናጠፋውን ጊዜ እያሰቡ የማርክና የደመወዝ ጭማሪ ቢያደርጉልን ምናለበት?” አለ የማይሰማ መስሎት አንድ ወጣት እየተንሾካሾከ። “ታክሲ የምንሠለፍበትንና የምንጠበቅበት ይታሰብልን ማለትህ ነው?” ይለዋል ጓደኛው። “ታዲያስ! እንዲህ ተሰባብረን እንዳንሆን ሆነን እየሠራንና እየተማርን የማርፈድ ቅጣት፣ በ’አቴንዳንስ’ ሰበብ ‘ኤፍ’ ሰለቸን አቦ!” እያለ ምሬቱን ከቀልድ ወደ ምር ሲያሸጋግረው፣ “እርፍ ይኼ ነበር የቀረን። መቼ ይሆን ሰበብ እየፈለግን ከዚህች ደሃ አገር ጉሮሮ ቀምቶ ለመጉረስ ማሰብ የምናቆመው?” ትላለች አጠገቤ የተቀመጠችው ቆንጆ። “አሄሄ አንተ ጉርሻውን ትላለህ የደላህ። ምናለበት መዋጮው ባበቃ አትልም?” አሉ አዛውንቱ። ሁሉም ከራሱ ሕመም እየተነሳ አስተያየቱን ሲዘነዝር ቆየና ድንገት፣ “ለመሆኑ አገራችን በየዓመቱ በስንት አኃዝ ነበር እያደገች ነው የተባለው?” ብሎ ጎልማሳው ሲጠይቅ ‘በሁለት’ ብለው ሁለት ወጣቶች እኩል መለሱለት። “እሺ! እኛና ኑሯችን በስንት አኃዝ ነበር ቁልቁል የምንወርደው?” ባለ ጊዜ ግን እንኳን የሚመልስ የሚተነፍስ ጠፋ። ‘ምርጥ ምርጡን ለእኛ አለ መንግሥት!’ የምትል ደፋር ጥቅስ ታክሲያችን ውስጥ ተለጥፋ ብናይ ያየነውን ማመን አቃተን። ቆይ የሚታመን እንዲህ ይጥፋ? እንዲህ እያውካካን ፒያሳ መድረሳችን ሳይታወቀን ወያላው ‹‹መጨረሻ›› ሲለን ዱብ ዱብ እያልን ወረድን፡፡ ጉዞአችን በአጭሩ ባይቋጭ ኖሮ ትንፋሽ ከሚያጥረን ባልሰማ ብናልፈው አይሻለንም? መልካም ጉዞ!