Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርየስምረት አበሳ

የስምረት አበሳ

ቀን:

በሚካኤል መድኅን

በምዕራብ ትግራይ የሚገኙ ማይ ዓይኒ፣ ዓዲ ሐሪሽ፣ ሕንፃፅና ሽመልባ የሚባሉት የመጠለያ ጣቢያዎች የኤርትራ ስደተኞችን ያስተናግዳሉ፡፡ በየወሩ በአማካይ 3,000 ሰዎች ድንበር አቋርጠው ይገባሉ፡፡ ከዚያች አገር ፈልሰው በኢትዮጵያ የሚኖሩት ስደተኞች በአሁኑ ጊዜ በድምሩ 161 ሺሕ መድረሳቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ ያሳያል፡፡

የመጀመሪያ ጉብኝቴን ያደረኩት በማይ ዓይኒ ነበር፡፡ ከሽሬ ወደ ሑመራ በሚወስደው መንገድ በስተቀኝ በኩል የተቋቋመ ካምፕ ነው፡፡ ቀኑ እሑድ ስለነበር ብዙ ሰዎች በአብያተ ክርስቲያናት ይፀልያሉ፣ በርከት ያሉ ወጣቶች ደግሞ ለተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች ዝግጅት ያደርጋሉ፡፡ ጊዜያቸውን ሙሉ ተቀምጠው የሚያሳልፉት ስደተኞቹ እንዲህ ዓይነት አጋጣሚዎች ሲገኙ በብዛት ይሳተፋሉ፡፡ በጋራ ጉዳያቸው ላይም ይወያዩባቸዋል፡፡ በዕለቱ ከተከናወኑት ሥነ ሥርዓቶች አንዱ የብስክሌት ውድድር ነበር፡፡ በትግራይና በኤርትራ ወጣቶች ዘንድ በእጅጉ የሚወደድ ስፖርት ነው፡፡ ብቸኛው የጊዜ ማሳለፍያ ግን አይደለም፡፡ እግር ኳስና ቴኒስን የመሳሰሉ ጨዋታዎችም ይዘወተራሉ፡፡

- Advertisement -

የብስክሌት ውድድሩን በተመልካች ለማድመቅ ቅስቀሳ ተደረገ፡፡ በዚህ የተካኑ የማስታወቂያ ነጋሪዎችና የመድረክ መሪዎች አሏቸው፡፡ በጥሪ ማስታወቂያው ተነሳስተው በርካታ ተመልካቾች ከያሉበት ወጥተው ውድድሩን በድጋፍ ለማድመቅ ወደ አስፋልት መንገድ ተመሙ፡፡ የሚበዙት ወጣቶች ናቸው፡፡ የተቀሩት ደግሞ ሕፃናት፡፡ የኤርትራ ስደተኞች የከተሜ ወጣቶችና ሕፃናት ይበዙባቸዋል፡፡ ከጠቅላላው 15 በመቶ የሚሆኑት ሕፃናት ናቸው፡፡  

ይህንን ያየ ሰው “በቃ ያች አገር ቀጣይ ትውልድ ላይኖራት ነው?” ብሎ መደምደሙ አይቀርም፡፡ በቀጣይ አገሪቱን ማን ይሆን የሚረከባት? በተፈጠሩበት ምድር ተስፋ የራቃቸው ወጣቶች፣ ሕፃናትና አዛውንት በአገራቸው ሁኔታ ተማርረው ድንበር አቋርጠው ይሰደዳሉ፡፡ የተወሰኑት በለስ ቀንቷቸው በአጎራባች አገሮች ይጠለላሉ፡፡ ጥቂቶቹ በሕጋዊ መንገድ ወደ ሦስተኛ አገር ይሄዳሉ፡፡ አብዛኞቹ በሱዳንና በግብፅ በረሃዎች አበሳቸውን አይተው፣ አካላቸውንና ሕይወታቸውን ገብረው የበረሃ ሲሳይ ሆነው ይቀራሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ የአውሮፓን ምድር ለመርገጥ በሚያደርጉት ትግል በሜዲትራኒያን ባህር ሰምጠው የዓሳ ነባሪ ቀለብ ይሆናሉ፡፡

የብስክሌት ውድድሩን ለማስጀመር ተወዳዳሪዎች ቦታ ቦታቸውን እንዲይዙ፣ ተመልካቾችም በሞራል እንዲያበረታቷቸው በመድረክ መሪው ተነገረ፡፡ ሙዚቃ ከፍ ብሎ ተለቋል፡፡ ለጆሮ የሚጥም ለስለስ ያለ የናፍቆት ዜማ ነው፡፡ አብዛኞቹን ተመልካቾች ቀልባቸውን አስቶ በትዝታ ማዕበል እንደሚወስዳቸው እርግጠኛ ነኝ፡፡ ስሜታቸውን፣ ምሬታቸውንና ናፍቆታቸውን በእነዚህ ዜማዎች ነው የሚገልጹት፡፡ ይህን የናፍቆት ዜማ የሚቀምሩ በርካታ ከያንያን አሏቸው፡፡ ከዜማው ውጪ ሁሉም ነገር ይናፍቃቸዋል፡፡ በሚወዷት አገራቸው ያሳለፉት ሕይወት፣ የልጅነት ዓለም፣ የወጣትነት ጊዜ፣ ቤተሰቦቻቸው፣ የትውልድ ቀያቸው፣ አፈር ምድሩ፡፡ በተለይ ሕፃናቱ ኢትዮጵያ ከደረሱ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ በቤተሰብ ናፍቆት እንደሚሰቃዩ የካምፑ አስተባባሪዎች ነግረውኛል፡፡  

 

ውድድሩ ብስክሌተኞቹ በከፍተኛ ፍቅር የከወኑት፣ ታዳሚዎቹም በጋለ ሞራል የደገፉት አዝናኝ ጨዋታ ነበር፡፡ በደመቀ ሁኔታ ተጀምሮ ሁሉንም አዝናንቶ በድል ተጠናቀቀ፡፡ ከአንድ እስከ ሦስት የወጡ አሸናፊዎች ሽልማት ተበረከተላቸው፡፡ ሽልማቱ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ምርትና አገልግሎታቸውን ካስተዋወቁ የንግድ ተቋማት የተገኘ ነበር፡፡

የኤርትራ ወጣቶች በመጠለያ ጣቢያዎቹ ጊዜያቸውን በዚህ መልኩ ያሳልፉታል፡፡ ይህ አምራች ኃይል ትኩስ ጉልበቱን ሳይጠቀምበት፣ ለስደት የዳረገውን ምክንያት እያሰበ፣ ለዚህ አበሳ ያበቃውን ሥርዓት እየረገመ፣ የዛሬውን እያሰላሰለ፣ የወደፊቱን እያማተረ፣ የሚወዳት አገሩን እየናፈቀ የስደት ኑሮውን ይገፋል፡፡ ተስፋቸው መቼ እውን እንደሚሆን ግን አይታወቅም፡፡ ከዛሬ ነገ የተሻለ ይሆናል እያሉ እስከ ዘጠኝ ዓመት ድረስ የኖሩ ስደተኞች አሉ፡፡

የውድድር ሥነ ሥርዓቱ እንዳበቃ ከካምፑ አስተባባሪዎች ጋር ተገናኘሁ፡፡ ሰላምታ ተለዋወጥን፡፡ ስለስደተኞች ሕይወትና አኗኗር፣ ስለገጠመኞቻቸውና በኤርትራ ስለሚደርስባቸው ግፍ መጫወት ጀመርን፡፡ የዓለማችን ትልቋ እስር ቤት ተብላ በተፈረጀችው ኤርትራ ውስጥ ስላለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ለስደት ስለዳረጓቸው ምክንያቶች፣ እንዲሁም በጉዞዋቸው ስለአጋጠሟቸው ችግሮች አንድ በአንድ ሊያጫውቱኝ ተዘጋጁ፡፡ ሲበዛ ግልጽ ናቸው፡፡ በራሳቸው የደረሰባቸውንና በሌላውም ላይ የደረሰውን የግፍ ታሪክ በግልጽ አጫወቱኝ፡፡ ታሪኮቹ እንኳንስ ለመናገር ለመስማትም የሚዘገንኑ ቢሆኑም እነሱ ግን ቀለል አድርገው ይተርኳቸዋል፡፡

“የትኛውን አንስተን የትኛውን እንደምንተወው አስቸጋሪ ነው፤” አለኝ አንደኛው፡፡ “ለማንኛውም በጣም አሳዛኝ ከምላቸው ታሪኮች ልጀምርልህ፡፡ እንትና እስር ቤት ውስጥ በደረሰበት ድብደባ ምክንያት ብልቱ ፈሳሽ መቆጣጠር ስለማይችል አሁንም ድረስ በቀን እስከ 20 ኮንዶም ይቀይራል፡፡ እንትና በ70 ዓመቱ እጆቹ በሰንሰለት እንደ ታሰሩ ከእስር ቤት አምልጦ ኢትዮጵያ ደረሰ፡፡ እንትና ለረዥም ጊዜ በጨለማ ውስጥ በመታሰሩ ዓይኖቹ ጠፍተው በሰው እየተመራ ወደዚህ መጥቷል፡፡ እከሌ አካል ጉዳተኛ ልጇን ይዛ በሱዳን በኩል ወደዚህ ተሰዳለች፡፡ 15 ወጣቶች የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግረው ወደዚህ ሊመጡ ሲሉ በኤርትራ ወታደሮች ተይዘው እዚያው ለሕዝብ ማስተማሪያነት ተብሎ በአደባባይ ተረሽነዋል….” እያለ ቀጠለ፡፡

አንዳንዶቹን ታሪኮች ከባለቤቶቹ አንደበት መስማት እችል እንደሆነ ጠየቅኳቸው፡፡ ከተወሰኑት ጋር አስተዋወቁኝ፡፡ ስምረት አንዷ ነች፡፡ ታሪኳን ልታጋራኝ ፈቀደች፡፡ ጥቁር ሱሪ አድርጋለች፡፡ ከላይ ነጭ ከነቲራ ለብሳለች፡፡ ዓይኖቿ እንደ ኮከብ የሚያበሩ፣ መካከለኛ ቁመት ያላት፣ የተስተካከለ ተክለ ሰውነት የተቸረች፣ የጠይም ቆንጆ፣ ለግላጋ፣ በተስፋ የተሞላ፣ በወኔ የጋለ፣ በጽናት የበረታ ሕይወት የምትመራ ትመስላለች፡፡ ፊቷ በፈገግታ ያበራል፡፡ ሰውነቷም የድሎት ነፀብራቅ ሆኗል፡፡ ውስጧ ግን ሌላ ነው፡፡

ነጭ ከነቲራዋ ላይ “ሓውኻ አበይ ኣሎ” (ወንድምህ ከወዴት አለ) የሚል የመጽሐፍ ቅዱስ አባባል ተጽፏል፡፡ የወጣቶች ፍልሰትና መከራ ያሳሰባቸው የካቶሊክ ቄሶች በዚህ ሃይማኖታዊ ጥቅስ አስደግፈው ያወጡት መረር ያለ መግለጫ በኤርትራ ምድር ለተወሰነ ጊዜ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡ ወንድሞቻቸው፣ ልጆቻቸውና ወላጆቻቸው የት እንዳሉ የማያውቁ በርካቶች ይህን ጥያቄ ዘወትር ያነሱታል፡፡ ስምረትም እንዲሁ፡፡ በለበሰችው ከነቲራ ላይ የታተመው ጽሑፍ፣ ላለፉት ስድስት ዓመታት በልቧ ውስጥ ታትሞ የሚኖረውን ህያው ስሜት ያንፀባርቃል፡፡ እናቷና ታናሽ ወንድሟ እሷን ተከትለው ወደ ኢትዮጵያ ሲሰደዱ ድንበር ላይ ተይዘው በኤርትራ እስር ቤት ውስጥ ይማቅቃሉ፡፡ አሁን በሕይወት ይኑሩ አይኑሩ አታውቅም፡፡ እናም “ወንድምህ ከወዴት አለ” የሚለው ጥያቄ 24 ሰዓት ሙሉ ከምናቧ የሚጠፋ አይደለም፡፡ በአንዱ ቀን አንዳች ምላሽ እስክታገኝለት ድረስ፡፡

ስምረት ቃለ መጠይቁን በፈገግታ ጀመረችው፡፡ ለአቅመ ሔዋን አልደረሰችም፡፡ በዚህ ዓመት 18 ይሞላታል፡፡ ሆኖም ከሚጠበቀው በላይ የተረጋጋች፣ አንደበተ ርቱዕ፣ በሳልና አስተዋይ ልጅ ነች፡፡ ዕድሜ ከቁጥር የዘለለ ትርጉም እንደሌለው እሷ ምስክር ነች፡፡ ገና ትንሽ እንደ ተጫወትን ንግግሯ በእንባ መታጀብ ጀመረ፡፡ ከውብ ዓይኖቿ የሚፈልቀው እንባ በጠይም መልከ መልካም ፊቷ ላይ ጎረፈ፡፡ ድንቡሽቡሽ ጉንጮቿ በእንባ ታጠቡ፡፡ “እንባ አንድ በመቶ ውኃ ሲሆን ዘጠና ዘጠኙ ግን ስሜት ነው፤” ይባላል፡፡ አዎ! በደስታም ሆነ በሐዘን የሚያጅበን እንባ ከውስጣችን ፈንቅሎ የሚወጣ ስሜት ነው፡፡ የስምረት ደግሞ በድርብርብ ሐዘን የመሰበር ስሜት፡፡

በስሜት የታጀበ አነጋገሯ ተሰምቶ አይጠገብም፡፡ ታሪኳን ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻው ያለማዛነፍ ተረከችልኝ፡፡ “እናቴ በወታደሮች ካምፕ ውስጥ የምግብ አዘጋጅ ነበረች፡፡ በሒደት ከአንድ ወታደር ጋር ተዋውቃ ግንኙነት ጀመሩ፡፡ ከዚያም እኔ ተወለድኩ፡፡ እሱ ግን አባትነቱን ካደ፡፡ እናም ያለ አባት አሳደገችኝ፡፡ የምትሠራበት ካምፕ ከምንኖርበት ከተማ ትንሽ ይርቅ ስለነበር ተመላልሳ መሥራት አልቻለችም ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ብቻዬን ማደርና መዋል ስለሚከብደኝ ብዙውን ጊዜ ከአያቴ ጋር ነበር የምኖረው፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን እናቴ በአንድ ወታደር ከሰል ላከችልኝ፡፡ እኔም ከሰሉን ተቀብዬ ወታደሩን በባህላችን መሠረት ቡና አፍልቼ፣ ምሳ አቅርቤ አስተናገድኩት፡፡ ያኔ ገና የአሥር ዓመት ልጅ ነበርኩ፡፡ ሰውዬው ከተስተናገደ በኋላ ግን አስገድዶ ደፈረኝ….”፡፡ ይህን ተናግራ ሳትጨርስ በውስጧ ታምቆ የነበረው ስሜት ገንፍሎ ወጣ፡፡ ፈቷ ከመቅፅበት በእንባ ታጠበ፡፡  

በመደፈሯ የደረሰባትን ጉዳትና ተከትሎ የመጣውን የሕይወት ዘመን መዘዝ ለመግለጽ ቃላት አቅም ያንሳቸዋል፡፡ ስምረት በውስጧ ያለውን ጉዳት እያሰበች በሳግ ብዛት አንደበቷ ቃላት ሲያጥረው፣ እነዚያ ውብ ዓይኖቿ ውስጣዊ ስሜቷን በእንባ ይናገሩታል፡፡ መልሳ እስክትረጋጋ ድረስ በድንጋጤ ፈዝዤ አያታለሁ፡፡ ምንስ ብዬ ላረጋጋት? ውስጡ የዓመታት መከራ ተሸክሞ በስሜት ያለማቋረጥ የሚያነባን ሰው እንደ ቀላል “አይዞህ በቃ” ማለት እንዴት ይቻላል? ሕመሟን የሚያስታግስ፣ ስሜቷን የሚያበርድ ቃላት ከዬት ላመጣ እችላለሁ? በመሀላችን ፀጥታ ሰፈነ፡፡ ትንሽ ቆይቼ ዝምታውን ለመስበር ያህል፣ ጨዋታውንም ለመቀጠል ብዬ፣ “በቃ ቻል አድርጊው ስምረት” ብዬ ተነፈስኩ፡፡ “የሰው ልጅ የማይችለው ነገር የለም” የሚለውን አባባል እያስታወስኩ፡፡  

በለጋ ዕድሜዋ የወረደባት ዱብ ዕዳ ከሥነ ልቦና ቀውስ አልፎ የሕይወት ዘመን ጠባሳ አስከትሎባታል፡፡ ስምረት ለጊዜው ስሜቷን ዋጥ አድርጋ የሰቆቃ ታሪኳን መተረክ ቀጠለች፡፡ “ወታደሩ እንደ ደፈረኝ ለማንም አልተናገርኩም፡፡ በነገታው ከትምህርት ቤት ቀረሁ፡፡ በቀጣዮቹ ቀናትም አልሄድኩም፡፡ ጓደኞቼ መጥተው ለምን እንደቀረሁ ጠየቁኝ፡፡ ምላሼ ‘አሞኛል’ የሚል ነበር፡፡ ከዘመዶቼ ተመሳሳይ ግፊት ሲበዛብኝ ለአያቴ አንድ ወታደር እንደደፈረኝ ነገርኳት፡፡ እሷም ለእናቴ ነገረቻት፡፡ እጅጉን ደነገጠች፡፡ እኔን ለማሳደግ ቤት ንብረቷን ትታ ኑሮዋን በረሃ አድርጋለች፡፡ አሁን በእኔ ላይ ይህ ችግር መድረሱን ስትሰማ ማመን አልቻለችም፡፡ ሳትውል ሳታድር መጣች፡፡ በነገታው ወደ ካምፑ ተመልሳ ወታደሩን ለመክሰስ ሞከረች፡፡ ‘የት እንዳለ አጣነው’ አሏት፡፡ ትንሽ ቆይተው ደግሞ ‘አርፈሽ ተቀመጪ’ ብለው አስጠነቀቋት፡፡ በዚህ ጊዜ እናቴ ሁሉንም ነገር ትታ ወደኔ መጣች፡፡”

እናቷ ሁሉንም ነገር ትታ የተደፈረችውን ልጇን ለመንከባከብ ወደ ቤቷ ተመለሰች፡፡ ስምረትም እንደ ምንም ትምህርቷን ቀጠለች፡፡ በዚህ መሀል የጤና እክል ገጠማት፡፡ በቀላሉ የጀመራት ሕመም እየጠናባት ሄደ፡፡ እናቷ በየጠበሉ ይዛት ትዞር ጀመር፡፡ ሕመሟ በቀላሉ ፈውስ የሚገኝለት አልሆነም፡፡ የስምረት የልጅነት ሰውነት እየመነመነ፣ ወዘናዋ እየነጠፈ፣ ልምላሜዋ እየጠወለገ፣ ሁለመናዋ እየገረጣ ሄደ፡፡ ወዳጅ ዘመድ ሁሉ ወደ ዘመናዊ ሕክምና እንድትወስዳት እናቷን መከራት፡፡ በምክራቸው ተስማምታም ወደ ሆስፒታል ወስዳ አስመረመረቻት፡፡ ሕመሟ ተደረሰበት፡፡ መድኃኒት መውሰድም ጀመረች፡፡ ልጅቱ ይህን ስትነግረኝ እንደ አዲስ ትደነግጥ ነበር፡፡ የምርመራው ውጤት ለእናቷ ሲነገራት ስምረት ልጅ ስለነበረች ምን ዓይነት በሽታ እንደያዛት አላወቀችም፡፡ ለረዥም ጊዜ የማያቋርጥ መድኃኒት የመውሰዷ ነገር ግን ያስገርማት ነበር፡፡  

መቼም ችግር ሲመጣ ጓዙን ጠቅልሎ ነው፡፡ ስምረት በመደፈሯ የደረሰባት የሥነ ልቦና ችግር ሳያንስ፣ የዕድሜ ልክ ታማሚ ሆናለች፡፡ ይባስ ብሎ መገለሉ ሊያሳብዳት ተቃረበ፡፡ የመታመሟ ወሬ በፍጥነት ተዛመተ፡፡ መጀመሪያ በጎረቤት፣ ከዚያም በመንደር፣ አልፎም በትምህርት ቤት ተዳረሰ፡፡ የምትናፍቃቸውና የሚናፍቋት የሠፈርና የትምህርት ቤት ጓደኞቿ በአንዴ ይሸሹዋት ጀመር፡፡ ይህን መገለል በጨቅላ ዕድሜዋ፣ በሕፃን አዕምሮዋ የምትቋቋመው አልሆነም፡፡ እናም እናቷን ጠየቀቻት፡፡ “ምንድነው የሆንኩት?”፣ ሰዎች ለምን እንደሚጠቋቆሙባት፣ ለምን እንደሚሸሹዋት፣ ለምን እንደሚያገሏት እንድትነግራት ተማፀነቻት፡፡ እሷም የማይቀረውን ዜና እንዲህ በማለት ተነፈሰችው፡፡ “በቫይረሱ ተይዘሻል፣ እንግዲህ ቻይው፣ እስከ ዛሬ ድረስ ዕድሜሽ ስለማይፈቅድ ነበር ያልነገርኩሽ፡፡”

ስምረት ቀጠለች፡፡ “በዚህ ጊዜ ድንጋጤ መላ አካላቴን ወረረኝ፣ አዕምሮዬ ተረበሸ፣ ተረጋግቼ መማር አቃተኝ፡፡ ‘ከዛሬ ነገ ልጄ ለቁም ነገር ትበቃለች’ ብላ ስትመኝ የነበረችው እናቴ፣ መታመሜን ከሚያውቁ ሰዎች ለመሸሽ ይዛኝ ከቦታ ቦታ መንከራተት ጀመረች፡፡ ከምንኖርበት ከተማ ለቀን ሌላ ቦታ መኖር ጀመርን፡፡ እዚያ ትምህርት ጀመርኩ፡፡ ብዙም ሳልቆይ ወሬው ተሰማ፡፡ አድልዎና መገለሉ ቀጠለ፡፡ ትምህርቴን አቋረጥኩ፡፡ በምግብ ቤት ሥራ ጀመርኩ፡፡ እዚያም አልሆነም፡፡ ሁኔታው እየተባባሰ መጣ፡፡ ችግሬ እየከፋ ሄደ፡፡ አማራጭ ሳጣ፣ በአገሬ መኖር ሲያቅተኝ፣ በመጨረሻ ከአንዲት ጓደኛዬ ጋር ወደዚህ ተሰደድን፡፡ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላም ኢትዮጵያ ደረስን፡፡”

ስምረት በማይ ዓይኒ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ አዲስ ሕይወት ጀመረች፡፡ የተለያዩ አገልግሎቶች እየተሰጣት፣ መድኃኒቷንም በአግባቡ እየተጠቀመች ሰውነቷ መሻሻል አሳየ፡፡ በኤርትራ የነበረው የመገለል ችግር ግን ተከትሏት መጥቷል፡፡ በመጠለያ ጣቢያው ስደተኞቹ እየተበራከቱ ሲመጡ የሚያውቋት ሰዎች እየበዙ ሄዱ፡፡ በበሽታው የመያዟ ወሬም መናፈስ ጀመረ፡፡ መገለሉም አገረሸ፡፡ በዚህ ምክንያት ብቻዋን ቤት ውስጥ መዋል ጀመረች፡፡ እንቅስቃሴዋ ተገደበ፡፡ ዓለሟ ጠበበ፡፡ ከሰዎች ዕይታ ለመሸሽ ብላ ቤት በምትውልበት ጊዜ ዋናው ሥራዋ በሽታዋን ማዳመጥ፣ ጭንቀቷን ማሰብ ሆነ፡፡ በዚህ ላይ የቤተሰብ ናፍቆትና ሐሳብ ተጨምሮበት ነገሩ ሁሉ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆነባት፡፡ ዓለም ፊቷን አዞረችባት፡፡

 

ይህን ሁሉ ታሪክ ስትነግረኝ ከዓይኖቿ የሚጎርፈው እንባ አላቋረጠም፡፡ “የሚቻል ቢሆን ከዚህ የመጠለያ ጣቢያ ወጥቼ የከተማ ስደተኛ ሆኜ ሰፋ ባለ ከተማ ውስጥ ከሰው ጋር ተመሳስዬ መኖር ነው፡፡ የሆነ ሙያ ተምሬ ሕይወቴን መምራት ብችል ደስ ይለኛል፡፡” ይህ ቀላል እንዳልሆነ ልቧ ያውቀዋል፡፡ በእርግጥ የኢትዮጵያ መንግሥት ለኤርትራ ስደተኞች የሰጠው አንድ ዕድል አለ፡፡ በከተማ የመኖር፡፡ ይህን ለማድረግ ግን የመተዳደሪያ ገቢ ያስፈልጋል፡፡ የከተማ ስደተኛ ሆኖ የመኖር እንጂ የመሥራት ፈቃድ አልተሰጣቸውም፡፡ ስለሆነም ደጋፊ ያላቸው ስደተኞች ናቸው በዚህ ዕድል የሚጠቀሙት፡፡ ይህን ማድረግ የማትችለዋ ስምረት ያላት አማራጭ ሌላ ነው፡፡ እግዚአብሔር ብሎ ለወደፊት ወደ ሦስተኛ አገር የመሄድ ዕድል እስኪገጥማት ድረስ ባለችበት የመጠለያ ጣቢያ ሆና በመገለል የታጀበ የስደት ሕይወቷን መምራት፡፡

ከስምረት ጋር በፈገግታ የተጀመረው ቃለ መጠይቅ በእንባ ሊቋጭ ተቃርቧል፡፡ “አሁን የወደፊት ተስፋሽ ምንድነው?” ብዬ ብሶቷን ያባባሰ ጥያቄ ሰነዘርኩ፡፡ በቁስሏ ላይ እንጨት ሰደድኩበት፡፡ የሰጠችኝ ምላሽ ልብ የሚሰብር ነበር፡፡ “እኔ ምን ተስፋ አለኝ? ራዕዬ ጨልሟል፣ ተስፋዬ ከስሟል፣ ህልሜ መክኗል፡፡ የሰው ልጅ ተስፋው የሚጀምረው ከእናቱ እቅፍ ወርዶ ትምህርት ቤት በሚገባበት ቀን ነው፡፡ እንደ ሰው ይህን ሒደት ጀምሬዋለሁ፡፡ ከዚያም ተስፋህ ከዕድሜህና ከትምህርት ደረጃህ ጋር እያደገ ይሄዳል፡፡ የእኔ ግን ገና በአሥር ዓመቴ ነው ሳይታሰብ የተቀጨው” ብላ መቼም የማልረሳውን መራራ ዓረፍተ ነገር ሰንዝራ በእንባ ተሰናበተችኝ፡፡

 ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡      

                                                 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...