Monday, October 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

እንዴት ነው ነገሩ? ያለ ድጋፍ ከአምስተኛ ፎቅ ላይ ጥገና ማድረግ

ትኩስ ፅሁፎች

ከጨረቃ ጋራ
እንደተቃጠረ – ምሽቱን ጠብቆ – ኮቴ እንደሚያሰማ
‹‹መጣሁ›› ላለማለት – ‹‹ሄድኩኝ›› እንደማይል – የወንዝ ዳር ሳማ
እኔም እንደዚያ ነኝ
ቀን አለሁ እንዳልል – ቀን ያጣሁ፣ የነጣሁ
ጊዜ አለኝ እንዳልል – በጊዜ የተቀጣሁ
ከሁሉ የተጣጣሁ
ሹልክ ብዬ ሄጄ – ሹልክ ብዬ መጣሁ
ያው እንደልማዴ – ፊታችሁ ተሰጣሁ፡፡

  •  ደመቀ ከበደ

* * *

የ76 ዓመቱ ምክር ስለታሪክ ድርሰት

በዚህ በዘመናችን በጣም ከሚያስፈልጉት መጻሕፍት አንዳንዱ ታሪክ ነውና የታሪክ ድርሰት ያለው ሰው እንዳለ በደስታ እንቀበላለን። ታሪክ ትልቅ ነገር ነውና ከፍ ባለ ሐሳብ መጻፍ ያስፈልጋል። ታሪኩን የሚጽፉ ሰዎች ሁሉ በእውነተኛነትና በትክክለኛነት፣ አድልኦ ሳያደርጉ መጻፍ ያስፈልጋቸዋል። በሐቅ ካልተጻፈ ግን የታሪክ ድርሰት ዋጋውን ያጣና ታሪክ መሆኑ ይቀራል። ስለዚህ ታሪክ ጸሐፊዎች ሁሉ ትክክለኛውን መንገድ እየተመለከቱ እውነቱን ብቻ የሚገልጸውን ትርጉም ሊሰጡት ይገባቸዋል።

በእውነት ላይ መጨመር፣ ወይም ከእውነቱ ማጉደል፣ አድልኦም ማድረግ ለታሪክ ጸሐፊዎች የተገባ ነገር አለመሆኑን ባለማወቅ አንድ አንድ ታሪክ ጸሐፊዎች በጠባብ ሐሳብ የአንዱን ሕዝብ አኗኗርና አስተያየት ብቻ ተከትለው የጻፉ አሉ። ሌሎች ግን የዓለምን ሕዝብ ሁሉ ሐሳብና አኗኗር ተመልክተው ትርጉሙን አስፋፍተው ይጽፋሉ።

ዛሬ የዓለምን የፖለቲካ የኢኮኖሚክና የሕዝብ አኗኗርን ስንመለከት ጸሐፊዎችን በጠባብ አስተያየት ታሪክ እንዲጽፉ አንመክራቸውም። ለሕዝብ ከሌላው ዓለም ሁሉ ተለይታችሁ ለብቻችሁ የምትኖሩ ናችሁ ብሎ መስበክ ስህተት ያመጣል። የዓለም ሕዝብ ሁሉ ዛሬ በሥራቸውም በትዳራቸውም እየተጋገዙና እየተባበሩ ነው የሚኖሩት።

  • (ይልማ ዼሬሳ – ሰኔ 1933)

* * *

ቡኒዎቹ የገጠር ቤቶች

በገጠሪቱ ስዊድን የሚታዩ የገበሬ ቤቶች ሙሉ በሙሉ ለማለት በሚያስችል መልኩ ቡኒ ቀለም የተቀቡ ናቸው፡፡ ቡኒው ቀለም የቤታቸውን ግድግዳ ብቻ ሳይሆን የጣራ ክዳኑንም  ይጨምራል፡፡

ግለሰቦች ለምን የተለያየ የቀለም ምርጫ እንደማይኖራቸውና የቤቶቹ ቀለም መመሳሰል ከምን የመጣ እንደሆነ አንዱን ስዊድናዊ ጠየቅሁት፤ ምላሹም ወደ ድሮው ቀደምት ታሪክ የሚወስድ ነበር፡፡

በጥንታዊት ስዊድን መሳፍንት፣ መኳንንትና ሀብታሞች ቤቶቻቸውን የሚያስገነቡት በሸክላ ጡብ እንደነበር አጫወተኝ፡፡ መኖሪያ ቤት በሸክላ ጡብ መገንባት ደግሞ አቅም ይጠይቅ ስለነበር፣ ብዙኃን ሕዝብ ያንን ማድረግ አይችልም፡፡ አቅሙ የማይፈቅደው ብዙኃኑ ሕዝብ ከመሳፍንቱ፣ ከመኳንንቱና ከሀብታሞቹ ለመመሳሰል ፈለገ፡፡ ስለዚህ የመኖሪያ ቤቶቹን ከጣውላም ሥራው ከሌሎች የእንጨት ዓይነቶች ቀለም አቀባቡ ላይ ቡኒ ቀለም መጠቀም ጀመረ፡፡ ግድግዳውን ብቻ ሳይሆን ጣራ ክዳኑንም ጭምር ቡኒ ቀለም መቀባት ተለመደ፡፡ ከሸክላ ጡብ የተገነቡ ቤቶች ቡናማ ቀለም እንዳላቸው ሁሉ የብዙኃኑ ቤቶችም ቡኒ ቀለም እየተቀቡ መመሳሰል ጀመሩ፡፡

የዛሬ የስዊድን ገጠር ቤቶች ታሪክም ከዚህ ጋር የተያያዘና ለብዙ ዓመታት እንደ ባህላዊ የቤት አሠራር ሆኖ የዘለቀ መሆኑን ስዊድናዊው አጫወተኝ፡፡ ካጤኑትና ከጠየቁ እንደ ቀላል አይተን የምናልፋቸው ነገሮች በአብዛኛው የራሳቸው ምክንያቶች ሊኖራቸው እንደሚችል ተገነዘብኩ፡፡

ቡናማዎቹ የስዊድን ገጠር ቤቶች ያምራሉ፣ ታሪካቸውም ይገርማል፡፡

– (ከሮቤል ባልቻ)

* * *

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች