ፖሊሲ አውጪዎች ስለ አርብቶአደሩ ያላቸው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆን፣ ለዘርፉ አዋጭ ፖሊሲና የልማት ድጋፍ እንዳይኖር ማድረጉን ‹‹የአርብቶ አደርነት የወደፊት ዕጣ ፈንታ በኢትዮጵያና የፖሊሲ አማራጮች›› በሚል ማኅበራዊ ጥናት መድረክ ያስጠናው ጥናት አመልክቷል፡፡ ዘርፉ ከግብርና እኩል ድጋፍ እንደማይደረግለትና ይህም አርብቷደሮችን ለተለያዩ ችግሮች እንዳጋለጣቸውም ተገልጿል፡፡
በአገሪቱ ያለው የአርብቷደርነት ሥርዓት ተለዋዋጭና ውስብስብ እንዲሁም ከማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አካባቢያዊ ለውጦች ጋር ተስማምቶ የመቆየት ባህሪ አለው፡፡ ይሁንና ፖሊሲ አውጪዎችና ሌሎች የልማት ተዋናዮች ይህንን ባለመረዳታቸው አርብቷደርነትን ኋላቀር አድርገው እንደሚያስቡት ጥናቱ አሳይቷል፡፡
የአርብቷደሩ ቁጥር መጨመር፣ ድርቅና ለአየር ንብረት ለውጥ በቀላሉ ተጋላጭ መሆን፣ ዘርፉ የሚጠበቅበትን ያህል እንዳያድግ እንቅፋት ቢሆንበትም ለችግሩ ምላሽ የሚሰጥ ተገቢ ትኩረትም አልተቸረውም፡፡
ከ60 እስከ 65 በመቶ የሚሆኑት የአገሪቱ ክፍሎች ደረቃማና ከፊል ደረቃማ ሲሆኑ፣ ለከብት እርባታም የተመቹ ናቸው፡፡ ጥናቱን ያቀረቡት የኢትዮጵያ የወተት አቀናባሪዎች ኢንዱስትሪ ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅና የፓስቶራሊስት ፎረም ኢትዮጵያ ምክትል የቦርድ ሊቀመንበሩ ዶ/ር ታፈሰ መስፍን እንደሚሉት፣ አርብቷደርነት ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ አገሪቱ ለውጭ ገበያ ከምታቀርበው ምርት 10 በመቶ የሚገኘውም ከአርብቶ አደሩ ነው፡፡ በየዓመቱም 15 ቢሊዮን ብር ይገኝበታል፡፡ 16 በመቶ ለሚሆነው የአገሪቱ ጠቅላላ ዓመታዊ ምርት ምንጭም ነው፡፡ 12 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጐችም የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡
ይሁንና ተገቢው ትኩረት ስለተነፈገው የተለያዩ ፈተናዎች ተጋርጠውበታል፡፡ የሕዝብ ቁጥር መጨመርና ድርቅ ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ እነዚህም አርብቷደርነት መልኩን እንዲቀይር እያስገደዱት ይገኛሉ፡፡ የከብት እርባታውን ወደጎን ብለው ወደ እርሻ የሚገቡ እንዲሁም አንፃራዊ ድርቅ የመቋቋም አቅም ያላቸውን ከብቶች ብቻ ማርባት የጀመሩም አሉ፡፡
ጥናቱ እንደሚያሳየው፣ በአገሪቱ የከብት እርባታ በስፋት በሚከናወኑባቸው አፋርና ሶማሌ ክልሎች የሕዝብ ቁጥር በተከታታይ በ33 በመቶ እና በ39 በመቶ አድጓል፡፡ የአብዛኛው ሕዝብ ኑሮም ከብት ማርባት ላይ ስለተመሠረተ የግጦሽ መሬት እጥረትና ሌሎችም ተያያዥ ችግሮች እየገጠመው ይገኛል፡፡
‹‹ለከብቶቹ ደህንነት፣ ለሕክምናና ለውኃ ብዙ ገንዘብ ከወጣና ብዙ ከተለፋ በኋላ ተፈጥሮ እንዲወስደው እናደርጋለን፡፡ ተለፍቶም ከብቶች በድርቅ ያልቃሉ፡፡ ከ70 በመቶ እስከ 80 በመቶ የሚሆኑት ከብቶች በድርቅ ይሞታሉ›› ያሉት ዶክተር መስፍን፣ ድርቅ ከመከሰቱና በከብቶች ላይ ጉዳት ከማድረሱ አስቀድሞ የመከላከል ሥራ ሊሠራ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
‹‹ከብቶቹ አንዴ ካለቁ በኋላ ለሚቀጥሉት ዓመታት የሚሠሩት ሥራዎች የመተካት እንጂ ምርታማነትን የማሳደግ አይደለም›› ያሉት ዶ/ር ታፈሰ፣ ከብቶች በድርቅ ሞተው ከሚያልቁ ለምግብነት የሚውሉበትን ባህል ማዳበር እንደሚያስፈልግም አክለዋል፡፡
ግብርናና የእንስሳት እርባታ አብረው ማደግ አለባቸው፡፡ ሆኖም የአርሶ አደሩ ምርታማነት የሚለካባቸው ደረጃዎች ቢኖሩም፣ ለአርብቶ አደሩ ተብሎ የተቀመጠ አለመኖሩን አስመልክቶ ዓርብ መጋቢት 15 ቀን 2009 ዓ.ም. በግዮን ሆቴል ጥናቱ ይፋ በተደረገበት ወቅተ ተሳታፊዎች ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡
የትኛው የአገሪቱ ክፍል ለእርሻ፣ የትኛው ለከብት እርባታ መዋል እንዳለበት ከውጤታማነቱ አንጻር ተገምግሞ ሊወሰን እንደሚገባ ‹‹ቦረና ላይ ስንዴ መዝራት ነው ወይስ ከብት ማርባት ነው የሚያዋጣው›› ሲሉ፣ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራበት እንደሚገባም ከተሳታፊዎቹ አንዱ ገልጸዋል፡፡