Wednesday, December 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየቡድን ውጤት ያንሰራራበት የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና

የቡድን ውጤት ያንሰራራበት የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና

ቀን:

  • ፌዴሬሽኑ የማበረታቻ የገቢ ሽልማት አበርክቷል

   በምሥራቅ አፍሪካዊቷ ኡጋንዳ አስተናጋጅነት፣ ባለፈው እሑድ መጋቢት 17 ቀን 2009 ዓ.ም.  በተካሄደው 42ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና፣ ኢትዮጵያ ከዓለምም ሆነ ከአፍሪካ የሁለተኝነትን ደረጃ በመያዝ አጠናቃለች፡፡ የምንጊዜም ተቃናቃኟ ኬንያ በዘርፉ ያላትን የበላይነት አስጠብቃ ውድድሩን በበላይነት መፈጸሟም ታውቋል፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ለዓመታት በክፍተትነት ሲያነጋግር የቆየው የቡድን ሥራና ውጤት በአዲሱ አመራር ከታቀደው ጊዜ ቀድሞ መታየቱ የሚያረካ መሆኑ ተነግሯል፡፡

በ42ኛው የዓለም አገር አቋራጭ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ አራት የወርቅ፣ አራት የብርና አንድ የነሐስ በድምሩ ዘጠኝ ሜዳሊያዎችን አስመዝግባ ከዓለምም ሆነ ከአፍሪካ የሁለተኛነትን ደረጃ ይዛ ሻምፒዮናውን አጠናቃለች፡፡ ኬንያ አራት የወርቅ፣ አምስት የብርና ሦስት የነሐስ በድምሩ 12 ሜዳሊያዎችን ሰብስባ በአትሌቲክሱ ያላትን ጥንካሬ ማስጠበቅ ችላለች፡፡

በዚሁ የዓለም አገር አቋራጭ ውድድር ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ለተሰንበት ግደይ የወርቅ፣ ሃዊ ፈይሳ የብር ሜዳሊያ ማስገኘት ለኢትዮጵያ የቻሉ ሲሆኑ፣ በተመሳሳይ የዕድሜ ምድብ ወንዶች ዐምደወርቅ ዋለልኝ የብር ሜዳሊያ አስመዝግቧል፡፡ በአዋቂ ወንዶች አባዲ ሐዲስ የነሐስ ሜዳሊያ ሲያስመዘግብ፣ በድብልቅ ሪሌ ደግሞ በቡድን የብር ሜዳሊያ ተገኝቷል፡፡

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ቀደም ባሉት ዓመታት የሚታወቁበት የቡድን ሥራና ውጤት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መጥፋቱ ሲያነጋግር መቆየቱ የሚታወቅ ነው፡፡ ችግሩም ካሁን ቀደም ለነበሩበት የፌዴሬሽኑ አመራሮችና ሙያተኞች እጅግ አስቸጋሪ ሆኖ መቆየቱ አልቀረም ነበር፡፡ የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ በሆነው መስከረም ወር ላይ የብሔራዊ ፌዴሬሽኑን አመራርነት በአዲስ መልክ የተረከበው የሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ካቢኔ የጠፋውን የቡድን ሥራና ውጤት ወደ ነበረበት መመለስ የዕቅዱ አንዱ አካል አድርጎ ሲንቀሳስ መቆየቱም ይታወቃል፡፡

በዘንድሮው የዓለም አገር አቋራጭ የተገኘው ሜዳሊያ በአብዛኛው የቡድን ውጤት ሲሆን፣ ይኼውም በአዋቂ ወንዶች፣ ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች በሁሉም ጾታ በቡድን የወርቅ ሜዳሊያ ሲመዘገብ፣ በአዋቂ ሴቶችም እንደዚሁ የተመዘገበው የብር ሜዳሊያ በቡድን መሆኑ ማሳያ ይሆናል፡፡

ባለፈው ሰኞ መጋቢት 18 ቀን 2009 ዓ.ም. የልዑካን ቡድኑ አዲስ አበባ ሲገባ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ኃይሌ ገብረሥላሴ ‹‹በእንኳን ደህና መጣችሁ›› ንግግራቸው ይህንኑ አስረግጠው ሲናገሩ ተደምጧል፡፡ በሻምፒዮናው ቡድኑ በከፍተኛ ደረጃ ካሳካቸው ተልዕኮዎች መካከል የቡድን መንፈስ የሚለውን እንደ አመራር ብቻ ሳይሆን እንደ ዜጋ የረኩበት ስለመሆኑ ጭምር ሲናገሩ ተደምጧል፡፡ ሌላው በአቀባበል ሥርዓቱ የተገኙት የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ይግዙ የተገኘውን ውጤት አድንቀው፣ ነገር ግን በቀጣይ ከዚህ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የተቀናጀ ጠንካራ ሥራ እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ትናንት መጋቢት 19 ቀን ዓ.ም. በአራራት ሆቴል ባዘጋጀው መድረክ ለአትሌቶችና ለተሳታፊ ልዑካን ሸልሟል፡፡ የማበረታቻ የገንዘብ ሽልማቱ መጠን ለቡድን ወርቅ ብር 20,625፣ ለብር – 13,125፣ ለነሐስ ብር 9,375፣ ለዲፕሎማ ብር 5,625 እና ለተሳታፊዎች 2,500 ብር መሸለሙ ታውቋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...