የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) አዲሱ አሠልጣኝ አሸናፊ በቀለ ለመጪዎቹ ሁለት ዓመታት የሚያቆያቸውን የሥራ ውል ተቀበሉ፡፡ 100 ሺሕ ብር ያልተጣራ ወርኃዊ ክፍያ ያገኛሉ፡፡ ኮንትራቱ የቡድኑን ውጤት መሠረት እንደሚያደርግም በፌዴሬሽኑ የብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ መናገራቸው ታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2019 ለሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጋና፣ ኬንያና ሴራሊዮን በሚገኙበት ምድብ መደልደሏ ይታወቃል፡፡ አዲሱ አሠልጣኝ አሸናፊ በቀለ የብሔራዊ ቡድኑን ኃላፊነት በተረከቡ ማግስት ለተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ሲናገሩ እንደተደመጡት ከሆነ፣ የሁሉም ድጋፍና ክትትል ከታከለበት የተሳካ ውጤት ማምጣት ይቻላል፡፡ ትናንት መጋቢት 19 ቀን 2009 ዓ.ም. በኢንተርኮንትኔታል ሆቴል የሁለት ዓመት ኮንትራት መቀበላቸውን ይፋ ባደረጉበት ወቅት ይህንኑ የ‹‹አብረን እንሥራ›› ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
ዋና አሠልጣኙ ለሁለት ዓመት የሥራ ቆይታቸው ብሔራዊ ቡድኑ የሚያስመዘግበው ውጤት ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው በፌዴሬሽኑ በኩል ተነግሯል፡፡ ፌዴሬሽኑ በበኩሉ፣ ለአቶ አሸናፊ በቀለ ከሚከፍለው ወርኃዊ ክፍያ በተጨማሪ የመኪና፣ የጤና መድን ሽፋንና ሌሎችንም የቁሳቁስ አቅርቦት የማሟላት ግዴታ እንደሚኖርበት በኮንትራቱ ተካቷል፡፡