Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምትራምፕ በመጀመሪያዎቹ 50 ቀናት

ትራምፕ በመጀመሪያዎቹ 50 ቀናት

ቀን:

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካን ወደነበረችበት ታላቅነት እመልሳለሁ ብለው ሥልጣን ከያዙ 50 ቀናትን ያስቆጠሩት ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ነው፡፡

በአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሥራ በጀመረ በመጀመሪያዎቹ 100 ቀናት ውስጥ በሕዝቡና በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የሚመዘንበት፣ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ለሕዝቡ ቃል የገባውን ለመተግበር ዕርምጃ የሚጀምርበት፣ ታላላቅ የሚባሉ ፕሬዚዳንታዊ ውሳኔዎችን የሚወስንበት፣ ለአሜሪካ ሕዝብ ጠቃሚ የሆኑ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን የሚያሳውቅበትና በአጠቃላይም ለሕዝቡ ማንነቱን የሚያሳይበት ነው፡፡

ፕሬዚዳንት ትራምፕም 100ዎቹን የመጀመሪያ የሥልጣን ቀናት አጋምሰዋልና በሠሩዋቸው ሥራዎችና በንግግራቸው ተመዝነዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ትራምፕ ሥልጣን ከመያዛቸው አስቀድሞ በነበሩዋቸው የምረጡኝ ዘመቻዎች ቃል የገቧቸውና አወዛጋቢ የተባሉት የስደተኞች ጉዳይ፣ የአሜሪካውያን የጤና ኢንሹራንስ ፖሊሲ (ኦባማኬር)፣ አሜሪካን ከነፃ ታሪፍ ንግድ ስምምነት መነጠልና ሌሎችም ዋይት ሐውስን ሲረግጡ ተግባራዊ ላይሆኑ ይችላሉ ተብሎ ተገምቶ ነበር፡፡

የትራምፕ ሁኔታ ጥርጣሬ አጭሮ የነበረ ቢሆንም ዋይት ሐውስ ይቀይራቸዋል፣ እንደ ቃላቸውም አያደርጉም ተብሎም ሲነገር ከርሟል፡፡ እውነታው ግን ይህ አይደለም፡፡ ዋይት ሐውስ መቀየር የቻለው የዶናልድ ትራምፕን አቅጣጫ ሳይሆን ፕሬዚዳንታዊ ወንበሩን ብቻ ነው፡፡

በየደቂቃ ትዊት በማድረግ ለነቀፏቸው አፀፋ የሚመልሱት ትራምፕ፣ ለዋይት ሐውስ ልማድና ባህል ተገዢ አልሆኑም፡፡ ለሚገምቷቸውም ሆነ ለሚሰነዘሩባቸው ቃላዊ ጥቃቶች፣ መደበኛ ጋዜጣዊ መግለጫ በራሳቸው ወይም በዋይት ሐውስ በኩል ከመስጠት ይልቅ፣ ትዊት ማድረግን ይመርጣሉ፡፡ ከውጭ ጉዳይ እስከ አገር ውስጥ ያሉ አጀንዳዎችን ዋይት ሐውስ ሲጠቀምበት ከነበረው አሠራር ውጪ በራሳቸው አካሄድ ከመናገርም ሆነ ትዊት ከማድረግም አልተቆጠቡም፡፡ በዋይት ሐውስ የተለመደውን ፕሮቶኮል የበዛበት አሠራር ለመልመድም ተቸግረዋል፡፡

ተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ሥልጣን በያዙ በመጀመሪያዎቹ 50ዎቹ ቀናት ብዙ ሕጐችን ከጫፍ ማድረስ ችለዋል፡፡ የትራምፕ አጀንዳዎች ግን እንዲሁ ሁሉን የሚያስማሙና በቀላሉ ከጫፍ የሚደርሱ አይደሉም፡፡

የጤና ኢንሹራንስ መግባት የማይችሉ አሜሪካውያንን ታድጓል የተባለውን ኦባማኬር መተካት፣ የመሠረተ ልማትና የታክስ ሥርዓት መልሶ ማዋቀር የሚሉት የትራምፕ አጀንዳዎች የካቢኔያቸውን ይሁኝታ የሚጠይቁ ናቸው፡፡ ሆኖም ትራምፕ በመጀመሪያዎቹ 50 ቀናት ያነሷቸው አጀንዳዎች በሁሉም ደረጃ ያሉ የመንግሥት አሠራሮችን አወዛግቧል፡፡ የአሠራርና የአመራር ለውጥም ተደርጓል፡፡

ኃላፊነት በሚሰማው መንገድ አይናገሩም ሲል ታይም የሚገልጻቸው ትራምፕ፣ ለካቢኔያቸውም ሆነ ለመከላከያ የፖሊሲ አጀንዳ ሲያነሱ ኃላፊነት በተሞላው ሁኔታ አይደለም ተብለውም ተተችተዋል፡፡

ትራምፕ ለአሜሪካ ለውጥና ዕድገት ወሳኝ ናቸው ያሏቸውን አጀንዳዎች በማንሳት ለሕዝባቸው አሳውቀዋል፡፡ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ቃል ከገቧቸው ውስጥ አከራካሪና ተግባራዊ ሊሆኑ አይችሉም ተብለው የሚገመቱትንም አንቀሳቅሰዋል፡፡ በስደተኞች ላይ አደርገዋለሁ ያሉትን ዕገዳ ሥልጣን በያዙ በሳምንት ጊዜ ውስጥ በሰባት አገሮች ዜጎች ላይ ተግባራዊ እንዲሆን ያሳለፉት ውሳኔ ለአንድ ቀን ያህል ተግባራዊ ከሆነ በኋላ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተፈጻሚ እንዳይሆን ተደርጐ ነበር፡፡ በኢራን፣ በኢራቅ፣ በሶሪያ፣ በሶማሊያ፣ በሱዳን፣ በየመንና በሊቢያ ዜጐች ላይ ያሳለፉት የጉዞ ዕገዳ ለጊዜው ቢስተጓጐልም፣ በሁለተኛው ዙር ባሳለፉት ውሳኔ ከኢራቅ ዜጐች በስተቀር በሁሉም ላይ ከረቡዕ ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል፡፡

በአዲሱ የሪፐብሊካን የጤና ሽፋን ፖሊሲ መሠረም 14 ሚሊዮን የሚሆኑ አሜሪካውያን እ.ኤ.አ. በ2018 የጤና መድን ሽፋን ያጣሉ፡፡  

ትራምፕ የመንግሥት በጀት ቅነሳ እንደሚያደርጉ ያሳወቁትም በዚሁ ጊዜ ነው፡፡ ከስቴት ዲፓርትመንት የ37 በመቶ በጀት ቅነሳ፣ እንዲሁም ከቤቶችና ከተማ ልማት ዲፓርትመንት፣ ከአካባቢ ጥበቃ ኤጀንሲና ከሌሎች የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችም በቢሊዮን የሚቆጠር በጀት እንደሚቀንሱ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የመከላከያ ኃይሉን በጀት እንደሚያሳድጉና እንደሚያጠናክሩ በዚሁ ጊዜ አሳውቀዋል፡፡

በኦባማ የሥልጣን ዘመን የነበሩ 90 የቁጥጥር ሕጐች ሙሉ ለሙሉ እንዳይተገበሩ ወይም ለተወሰነ ጊዜ እንዲዘገዩም ተደርጓል፡፡ ቁጥጥሮቹ የነበሩት በገንዘብና በቴሌኮሙኒኬሽን ተቋማት፣ በመሣሪያ ሽያጭና በአካባቢ ጥበቃ ላይ ነው፡፡

ኦባማ በዘመናቸው ሦስት ሚሊዮኖችን ወደ አገራቸው በመጠረዝ ሪከርድ ይዘው የነበረ ቢሆንም፣ የፕራምፕ ስደተኞች ፖሊሲ እስከ ስምንት ሚሊዮን የሚደርሱ የሌሎች አገር ዜጐችን ወደመጡበት እንዲመለሱ የሚያደርግ ነው፡፡

ትራምፕ ከምረጡኝ ቅስቀሳ ወቅት ጀምሮ ከሚዲያው ጋር ፀብ ነበራቸው፡፡ ባለፉት 50 ቀናትም ትራምፕ ለሚዲያው ያላቸው ምልከታ ‹‹አድርባዮች›› ናቸው ከሚል የዘለለ አልሆነም፡፡

ትራምፕ ባለፉት 50 ቀናት 16 ትዕዛዞችን ያሳለፉ ሲሆን፣ ኦባማ በተመሳሳይ ጊዜ ያሳለፉት 17 እንደነበር ዘ ሂል አስፍሯል፡፡

አሜሪካን ጨምሮ 12 የፓስፊክ ውቅያኖስን የሚጋሩ አገሮች የንግድ ትስስራቸውን ለማጠናከርና ነፃ የንግድ ዕድል ለመፍጠር እ.ኤ.አ. በ2016 ከስምምነት ቢደርሱም፣ ሁሉም አገሮች በአገራቸው መንግሥት ስምምነቱን ማፀደቅ ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ ትራምፕ ከቅስቀሳቸው ወቅት ጀምሮ የትራንስ ፓስፊክ ፓርትነርሺፕ ለአሜሪካ አስፈላጊ እንዳልነበርና እንደማይስማሙበት ሲገልጹ የከረሙ ሲሆን፣ ሥልጣን በያዙ ሰሞን የስምምነቱ አካል እንደማይሆኑ በፊርማቸው አረጋግጠዋል፡፡

አርባ በመቶ የሚሆነው የዓለም ኢኮኖሚ በሚንቀሳቀስባቸው አገሮች በእያንዳንዳቸው መፅደቅ ብቻ የቀረውን ስምምነት ትራምፕ አለመደገፋቸው፣ ለተቀሩት 11 አገሮችም አሥጊ ነው፡፡ ምክንያቱም የኢኮኖሚው መዘውር አሜሪካ ናትና፡፡

ትራምፕ ከምርጫ ቅስቀሳቸው ጀምሮ አከራካሪ አጀንዳዎችን ያነሱ የነበረ ቢሆንም፣ የሕዝቡን ይሁኝታ አግኝተው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነዋል፡፡ በምርጫ ሲያሸንፉ በኋላም ሥልጣን ይዘው በሚያነሷቸው አጀንዳዎችና በሚያሳልፏቸው ውሳኔዎች ተቃውሞ ገጥሟቸዋል፡፡ ትራምፕ ግን አሜሪካን ዳግም ታላቅ የማድረግ ዓላማ አንግበው በአሜሪካ ከሚገኙ ትልልቅ ኢንዱስትሪዎችና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ጋር በመምከር ለአሜሪካ ይበጃል የሚሉትን እያደረጉ ነው፡፡ በመጀመሪያዎቹ 50 የሥልጣን ቀናትም ቃል የገቡዋቸውን ከምድር ለማድረስ ሲማስኑ ተደምጠዋል፣ ተስተውለዋል፡፡ የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንገላ መርከል የአሜሪካ ጉብኝት በመጨረሻ ሰዓት እንዲራዘም ወይም እንዲሰረዝ ትራምፕ ጠይቀው ነበር ተብሏል፡፡ ነገር ግን በኤንቢሲ ዘገባ መሠረት አንገላ መርከል የፊታችን ዓርብ ከትራምፕ ጋር ይገናኛሉ ተብሏል፡፡ የትራምፕ አካሄድ ለአሜሪካ ምን ይዞ ይመጣ ይሆን?

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...