አቶ አብነት ገብረመስቀል፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር ቦርድ ሊቀመንበር
ቅዱስ ጊዮርጊስ በ80 ዓመት የምሥረታ ታሪክ ዘንድሮ ያስመዘገበው ውጤት ተጠቃሽ ነው፡፡ ክለቡ በአገሪቱ በዓይነቱም ሆነ በይዘቱ የመጀመሪያ የሆነውን ‹‹የአፍሪካ እግር ኳስ አባት›› ተብለው በሚታወቁት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ስም የእግር ኳስ አካዴሚ አስገንብቶ ለአገልግሎት አብቅቷል፡፡ የአካዴሚው ብስራት ዕውን በሆነበት ማግሥት ደግሞ አንጋፋው ቅዱስ ጊዮርጊስ ለአገሪቱ ክለቦች የዓመታት ህልም ሆኖ በቆየው የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ምድብ ድልድል ውስጥ መግባት ችሏል፡፡ ይሁንና የክለቡ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ አብነት ገብረመስቀል ቡድኑ ባሳካው ውጤት ቢደሰቱም፣ ገና ብዙ እንደሚቀረው ያምናሉ፡፡ ችግሩም የቅዱስ ጊዮርጊስ ብቻ ሳይሆን የአገሪቱ ክለቦች ጭምር መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡ መፍትሔ የሚሉት ደግሞ ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ መድረኮችን ፈጥሮ ስፖርቱን በሚመለከተው ከአገሪቱ ሕግ ጀምሮ የእግር ኳሱን አደረጃጀት መፈተሽን ይጠይቃል፡፡ በአገሪቱ እግር ኳስ መሠረታዊ የሕግ ክፍተቶችም እንዳሉ አቶ አብነት ያምናሉ፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ እግር ኳስ መሥራች መሆኗ ካልሆነ በአህጉራዊው ተቋም በተለይም በአሁኑ ወቅት ይህ ነው የሚባል ድርሻ እንደሌላትም ይናገራሉ፡፡ መፍትሔ የሚሉትንም ያስረዳሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ከቅዱስ ጊዮርጊስ አልፎ በካፍ የክለቦች ጉዳይ ኮሚቴ በቋሚ አባልነት እያገለገሉ የሚገኙት አቶ አብነት፣ በእነዚህና በሌሎች የአገሪቱ እግር ኳስና ተያያዥ በሆኑ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ደረጀ ጠገናው አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ ለአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ምድብ ድልድል ገብቷል፡፡ ይኼ ለቡድኑም ሆነ ለአገሪቱ ክለቦች የመጀመሪያ ያደርገዋል፡፡ ቀጣይነቱ ላይ ምን ታስቧል?
አቶ አብነት፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ እዚህ ደረጃ ለመድረስ መንቀሳቀስ ከጀመረ ቆይቷል፡፡ ውጤቱም የክለቡ ዕቅዱ አንዱ አካል ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የአመራሩ፣ የተጨዋቾቹ ጥረትና ደጋፊዎቹ ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ያደረጉለት የድጋፍ ውጤት ነው፡፡ አሁንም ገና ብዙ ይቀረናል፡፡ ምክንያቱም ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ምድብ ድልድል መግባት አለበት፤ ብለን ስንነሳ ዕቅዳችን የቅርብ ጊዜ አይደለም፣ የቆየ ነው፡፡ ለዚህ ማረጋገጫ የሚሆነን እ.ኤ.አ. በ2013 ቅዱስ ጊዮርጊስ አሁን ለደረሰበት ደረጃ የቀረበበት ዓመት እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ በወቅቱ የግብፁ ዛማሌክን በሜዳው 1 ለ1 ተለያይቶ በመልሱ ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ ደግሞ 2 ለ1 ሲመራ ቆይቶ በ87ኛው ደቂቃ ተቆጥሮበት ነው፣ ከሜዳው ውጪ ብዙ ባገባ በሚለው ሕግ ከምድብ ድልድሉ ውጭ የሆነው፡፡ ከዚያ በኋላ ትልቁ ውጤታችን በሻምፒዮንስ ሊጉ የዘንድሮው ነው፡፡ እውነት ለመናገር ይህ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱም አዲስ ምዕራፍ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ምድብ ድልድል መግባት ለቅዱስ ጊዮርጊስ ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱ እግር ኳስ አንድ ዕርምጃ ወደ ፊት መሆኑ እንደተጠበቀ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ በምድብ ድልድሉ የሚያደርገው ተሳትፎ ወሳኝነት አለው፡፡ ከዚህ አኳያ ምን ዓይነት ዝግጅት እያደረጋችሁ ነው?
አቶ አብነት፡- የምድብ ድልድሉ ዕጣ በቅርቡ እንደሚታወቅ ይጠበቃል፡፡ አዲስ መጪ በመሆናችን በምድብ አራት ውስጥ እንደምንካተት እንጠብቃለን፡፡ እንደተባለው ቅዱስ ጊዮርጊስ በምድብ ድልድሉ የሚያደርገው ተሳትፎ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡ ይህንኑ ስለምናውቅ ማድረግ የሚጠበቅብንን ሁሉ ዝግጅት እያደረግን እንገኛለን፡፡ እርግጥ ነው በአሁኑ ደረጃ አዳዲስ ተጨዋቾችን ወደ ቡድናችን ማምጣት አንችልም፡፡ ስምንቱ ውስጥ የምንገባ ከሆነ ግን ዕድሉ ይኖረናል፡፡ ያም ሆነ ይህ አንዴ ገብተናል፤ ወደ ኋላ የምንልበት ምንም ምክንያት ስለማይኖር፣ በያዝናቸው ተጨዋቾች ተገቢውን ዝግጅት እያደረግን እንገኛለን፡፡ ራሳችንን ማሻሻል ይጠበቅብናል፡፡ ጠንካራና ደካማ ጎኖቻችንን በሚገባ ፈትሸናል፡፡ የቡድናችን የመሀል ክፍል ክፍተት እንዳለበት ተመልክተናል፡፡ ፊት ላይ ሳላዲን ሰይድ ብቻውን ነው፡፡ ራኬም ሎክ በጉዳት እስካሁን አልነበረም፣ አልደረሰልንም፡፡ በቀጣይ ከአንድ ጨዋታ በኋላ ወደ ቦታው ይመለሳል፡፡ ሌሎችም እንደነ ምንያህል ተሾመ የመሳሰሉት በጉዳት ከቡድኑ ጋር አልነበሩም፡፡ በቅርቡ ወደ ሙሉ ጤንነታቸው እንደሚመለሱ እንጠብቃለን፡፡ ጠንካራ ተፎካካሪ እንደምሆን አልጠራጠርም፡፡
ሪፖርተር፡- የአንድ ቡድን ጥንካሬ ተብሎ ከሚወሰደው አንዱ የተጋጣሚ ቡድኖችን አጠቃላይ ገጽታ መከታተልና ማወቅ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ቅዱስ ጊዮርጊስ ምን አድርጓል? ወደፊትም ምን ለማድረግ አቅዷል?
አቶ አብነት፡- የኮንጎው ሊዮፓርደስ፣ ከእኛ በፊት ካደረጋቸው ጨዋታዎች ካሜሩን ላይ ያደረገውን ጨዋታ ባለሙያ ልከን ጨዋታውን በሙሉ አስቀርፀን ተመልክተናል፡፡ ውጤትም አግኝተንበታል፡፡ እንቀጥልበታለን፣ የተጋጣሚ ቡድንን አቅም ቀድሞ ማወቅ ለታክቲካል ዲሲፕሊን ትልቅ ጥቅም አለው፡፡ ሊዮፓርድስ በቅዱስ ጊዮርጊስ መሸነፉ መታየት የለበትም፡፡ እጅግ በጣም ጠንካራ ቡድን እንደነበር መካድ አይገባንም፡፡ ለሽንፈታቸው ትልቁ ተጠያቂው በረኛው ነው፡፡ እንደዚያም ሆኖ ቡድኑ ከነተቀያሪዎቹ ያለውን ብቃት ተመልክተናል፡፡ በአዲስ አበባ ስታዲየም 90 ደቂቃ ሙሉ ተጭኖ የተጫወተ ቡድን ዓይተን አናውቅም፡፡ ያሸነፍናቸው በታክቲካል ዲሲፕሊን ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት በምድብ ድልድሉ ህልማችን ስምንቱ ውስጥ ለመግባት ነው፡፡ አስፈላጊውን ዝግጅት ካደረግን ህልማችንን ዕውን የማናደርግበት ምክንያትም አይኖርም፡፡
ሪፖርተር፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ በዚህ ዓመት ካሳካቸው ድሎች ትልቅም እንደሆነ የሚታመንበት በቢሾፍቱ (ደብረዘይት) በአቶ ይድነቃቸው ተሰማ ስም ያስገነባው የወጣቶች እግር ኳስ አካዴሚ ይጠቀሳል፡፡ አካዴሚው ተመርቆ ለአገልግሎትም ክፍት እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ነገር ግን አካዴሚ ገንብቶ ማስመረቅ ብቻውን ግብ ይሆናል ብሎ መጠበቅ ስለማይቻል፣ በቀጣይ የሚሰጠው አገልግሎት ነው ትልቁ ግብ ተብሎ ሊወሰድ የሚገባው፡፡ በዚህ ረገድ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው? የአካዴሚው የቅብብሎሽ ሒደትስ እንዴት ይገለጻል?
አቶ አብነት፡- በግሌ አካዴሚ መክፈት ብቻውን በቂ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ እንደተባለው የአካዴሚው የወደፊት እንቅስቃሴ ነው ለእኔ ትልቁ ነገር፡፡ ቀጣይነቱ እንዴት ነው? አካዴሚው መቀጠል የሚኖርበት በምን መልኩ ነው? ምን ዓይነት የአሠራር ሥርዓት ነው የሚከተለው? የሚያቅፋቸው ታዳጊዎችና ሙያተኞችስ? የሚለው ዋናው መሠረታዊ ነገር ነው፡፡ የአካዴሚውን ውበት ብቻ ተመልክተን እጃችንን አጣጥፈን የምንቀመጥበት ጊዜ አልፏል፡፡ በእያንዳንዱ የአካዴሚው ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ላይ አስበንበትና ተጨንቀንበት ነው የገነባነው፡፡ ከዚህ በኋላም አንድ አካዴሚ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊያሟላ የሚገባውን ሁሉ አሟልተን እንደምናስቀጥለው ይሰማኛል፡፡ አካዴሚው የሚመራው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መስፈርት ወጥቶ ያንን በሚያሟሉ ሙያተኞች ካልሆነ፣ በዘመድ አዝማድና በቅርበት የሚሆን ነገር እንደ ሌለ ከወዲሁ መተማመኛ መስጠት እፈልጋለሁ፡፡ ለዚህ ማረጋገጫ ካስፈለገ አካዴሚው ማክሰኞ መጋቢት 5 ቀን 2009 ዓ.ም. ተመርቆ መጋቢት 6 ቀን ከአውሮፓ ስፔን የመጡ ከፍተኛ ባለሙያዎች ጋር በአካዴሚ እንቅስቃሴ ላይ ተነጋግረናል፡፡ እነዚህ ሙያተኞች እንዳቀረቡት ፕሮፖዛል ከሆነ ቻይና ውስጥ ስድስት የታዳጊ ወጣቶች አካዴሚ ከፍተዋል፡፡ እንግሊዝ ሦስት፣ ስፔን ውስጥ ደግሞ አሥር አካዴሚዎች አሏቸው፡፡ ከዚህ በመነሳት አካዴሚው ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የምሥራቅ አፍሪካና የሌሎችም የአፍሪካ አገሮች ታዳጊዎችን እንደሚያካትት እንጠብቃለን፡፡ ጥያቄዎችን እያቀረቡልን ነው፡፡ አካዴሚው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አቅሙና ብቃቱ ያላቸው መልማዮች (ስካውት) ይኖሩታል፡፡ ወደ አካዴሚው የሚመጡ ታዳጊዎች ከእግር ኳስ ክህሎታቸው በተጨማሪ የአካዴሚክ ደረጃቸውም ግምት ውስጥ የሚገባ ይሆናል፡፡ ከፍተኛ ወጪ እንደሚጠይቅ እናውቃለን፡፡ ነገር ግን ይህን በተመለከተ በቢጂአይና ከሚድሮክ ግሩፕ ኩባንያዎች ሞሐ ለስላሳ መጠጦች፣ ደርባ ሲሚንቶ፣ አግሪ ሴፍት፣ ሆራይዘንና ሌሎችም ኩባንያዎች እንደሚደገፉ መተማመኛ ተገኝቷል፡፡ ለዚህም ነው ከታላላቅ ዓለም አቀፍ ሙያተኞች ጋር የማኔጅመንቱ ጉዳይ እርግጠኞች ሆነን ለመነጋገር የበቃነው፡፡ ሙያተኞቹ ዳይሬክተር ከመቅጠር ጀምሮ ሙሉ ኃላፊነት የሚወስዱ ናቸው፡፡ ተጠያቂነትም አለባቸው፡፡ የሚገርመው የአካዴሚውን ጉዳይ በተመለከተ ሌሎችም የአውሮፓ አገሮች ጣሊያንና ሆላንድ የመሳሰሉ አገሮች ሳይቀር ጥያቄ ያቀረቡልን አሉ፡፡
ሪፖርተር፡- የዕድሜ ጣሪያስ እንዴት ነው?
አቶ አብነት፡- ለጊዜው ዕቅዳችን ከ12 ዓመት ለመጀመር ነው፡፡ ምክንያቱም እንደ አውሮፓውያኑ ከስምንት ዓመት እንጀምር ብንል የአገራችን ማኅበረሰብ አስተሳሰብ ይገድበናል፡፡ ማንም ኢትዮጵያዊ የስምንት ዓመት ልጁን አሳልፎ አይሰጥም፡፡ በመሆኑም ለጊዜው ከ12 እስከ 15 ያሉትን ይዘን፣ ከዚያም ከ15 እስከ 17 ለመቀጠል ነው ዕቅዳችን፡፡ ይህ ማለት አካዴሚው በ12 ዓመቱ የተረከበውን ታዳጊ በ17 ዓመቱ ለብሔራዊ ቡድን ተስፋ የማይሆን ከሆነ፣ ዕቅዱ ያልተሳካ መሆኑ እንዲያዝልኝ እፈልጋለሁ፡፡ ለዚህም ነው የአካዴሚውን ኃላፊነት የሚወስደው አካል ተጠያቂነትም ይኖርበታል ያልኩት፡፡ ዝም ብለን ሰጥተን የምንተወው ነገር እንዳልሆነም ሊታወቅ ይገባል፡፡ በሕይወት የምቆይበትን መናገር ባልችም፣ እስካለሁ ድረስ ግን እንደነ ኤቶና ማሕሬዝን የመሰሉ ኢትዮጵያውያን እግር ኳሰኞች የመመልከት ምኞት አለኝ፡፡ ይድነቃቸው የበለጠ የሚያብቡት ያኔ ነው፡፡ ይኼ የእኔ ብቻ ሳይሆን የብዙ ኢትዮጵያውያን ምኞት ስለመሆኑ ለሰከንድ አልጠራጠርም፡፡
ሪፖርተር፡- የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች እንደ አካዴሚው ሁሉ ክለቡ የራሱ ስታዲየም እንዲኖረው እንደሚፈልጉ በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚናገሩት እውነታ ነው፡፡ እርስዎስ እዚህ ላይ አስተያየትዎ ምንድነው?
አቶ አብነት፡- አካዴሚውን ስናስገነባ ከዚያ የሚወጡ ልጆች የሚጫወቱበት ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም ያስፈልጋል፡፡ ይኼ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ የራሱ ስታዲየም እንዲኖረው የቅርብ ጊዜ ብቻ ሳይሆን የዓመታት ህልምና ምኞቴ ነው፡፡ ቀጣይ ዕቅዳችንም ይህንኑ ዕውን ማድረግ ነው፡፡ ቃል በተገባው መሠረትም ተጀምሯል፡፡ በመሀል በተለያዩ ምክንያቶች ተቋርጧል፡፡ ቀጣይ ፕሮጀክታችን ስታዲየሙ ነው፡፡ አሁን ላይ እንዲህ ነው ማለት አልችልም፤ ነገር ግን በቅርቡ ዕውን የምናደርገው አንድ ዕቅድ አለን፡፡ በመሆኑም ፕሮጀክቱ በሚቀጥሉት ሦስትና አራት ዓመት ውስጥ እንደምናጠናቅቅ እምነቴ ነው፡፡ አዲስ ነገር ለደጋፊዎቻችን እንደምናበስር እምነቱ አለኝ፡፡ በቅርቡ ከስፖንሰሮቻችን ጋር አንድ መድረክ ይኖረናል፡፡ ፕሮፖዛሉም ተጠናቋል፡፡ ይኼ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም የአገሪቱ ክለቦች ወደ ልማቱ መግባት የውዴታ ግዴታ ስለመሆኑ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም፡፡ ሕዝባችን 100 ሚሊዮንና ከዚህም በላይ ሆኗል፡፡ በአሁኑ ይዘታችን እግር ኳሱ ሊቀጥል እንደማይችል ሒደቱ ራሱ ያስገድደናል፡፡
ሪፖርተር፡- ሒደት የሚሉትን ሊገልጹልን ይችላሉ?
አቶ አብነት፡- ምክንያቶቹ የአደባባይ ምስጢር ናቸው፡፡ ስለ ኢትዮጵያ እግር ኳስ መናገር የጀመርኩት አሁን አይደለም፡፡ ከኢትዮጵያ ውጪ በነበርኩባቸው ዓመታት ጀምሮ ነው፡፡ እግር ኳስ ያለ ገንዘብ በስሜት ብቻ የትም አይደርስም፡፡ ሁሉም እንዲያውቀው የምፈልገው የአንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዓለም ላይ ተወዳጅ የሆነው እግር ኳሱና ገንዘቡ ስለተጣጣሙ ነው፡፡ እግር ኳሱ ከሌለ ገንዘቡ አይኖርም፣ ገንዘቡ ከሌለ እግር ኳሱ አይኖርም፡፡ ይኼ ለአገራችን እግር ኳስ ትልቅ ምሳሌ ሊሆን ይችላል፡፡ በእግር ኳስ ታሪክ ግብፅና ኢትዮጵያ ተመሳሳይ የአጀማመር ዕድሜ ያላቸው ናቸው፡፡ አሁን ያላቸው ልዩነት ግልጽ ነው፡፡ ይህንኑ ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ አፍሪካ ኅብረት አዳራሽ በተከናወነው 39ኛው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ጉባኤ ላይ ተናግሬዋለሁ፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ መንግሥታት ብዙ ኃላፊነቶች አሏቸው፡፡ ከነዚህ ውስጥ ትምህርት፣ ጤናና ሌሎችም ለአንድ አገር ሕዝብ መሠረታዊ የሚባሉ መሠረተ ልማቶች የመንግሥት ኃላፊነቶች ናቸው፡፡ ስፖርቱ ሲጨመር ደግሞ የኃላፊነቱ መጠን በዚያው ይሰፋል፡፡ እግር ኳስ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ምንም እንኳ ትልቅ የኢንቨስትመንት አማራጭ እየሆነ መምጣቱ እሙን ቢሆንም፣ በአብዛኛው ግን በመዝናኛነት የሚወሰድ (የሚታይ) ነው፡፡ ከስፖርቱ በተጓዳኝ የተጠቀሱት ግን ለመንግሥት አስገዳጅ ናቸው፡፡ የአገሪቱን ቀጣይ ትውልድ መማርና ጤናው መጠበቅ አለበት፡፡ ከነዚህ ነገሮች በተጓዳኝ ወደ ስፖርቱ ስንመጣ መንግሥት የስፖርቱን 99 በመቶ በጀት እየሸፈነ ይገኛል፡፡ መቀጠል ያለበት አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ክለቦቻችን ወደ ሕዝባዊ አደረጃጀት እየተለወጡ በስፖርቱ ልማት ላይ መሳተፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በአሁኑ አደረጃጀት ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና ሕዝባዊ ክለቦች ናቸው ተብሎ ይታሰባል፡፡ ወደ ልማቱ እንግባ ቢሉ ግን አይችሉም፡፡ በእግር ኳሱ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት የማያሠሩ ሕጎችንና የመንግሥት ድጎማን መመልከት ያስፈልጋል፡፡
ሪፖርተር፡- ለምን?
አቶ አብነት፡- ያለው ሕግ አይፈቅድላቸውም፤ ሕጉ ቅዱስ ጊዮርጊስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ልሁን ቢል አይፈቅድለትም፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም ሆኑ ኢትዮጵያ ቡና ሕዝባዊ ክለቦች ነን ብለን ነው የምናስበው፤ ውሸት ነው፡፡ ምክንያቱም ልማት ውስጥ ገብተው እንደ ሕዝባዊ ክለብ እንቀሳቀስ ቢሉ ከሕጉ ጋር ይጋጫሉ፡፡ ለምን ሕጉ ስለሚያግዳቸው፡፡
ሪፖርተር፡- በ1990ዎቹ መጀመርያ በአገር አቀፍ ደረጃ የወጣው የስፖርት ፖሊሲ ክለቦች ቀስ በቀስ ሕዝባዊ አደረጃጀት እንዲኖራቸው ይደግፋል፡፡ እርሶ የሚሉት ከዚህ ፖሊሲ አንፃር እንዴት ይታያል?
አቶ አብነት፡- መናገርና ማድረግ የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ቀላል ምሳሌ ማንሳት ይቻላል፡፡ በአገሪቱ በሁሉም ክልሎች የከነማ ቡድኖች ናቸው ያሉት፡፡ የሁሉም በጀታቸው ከመንግሥት ቋት ነው፡፡ መቼ ነው እነዚህ ክለቦች ሕዝባዊ አደረጃጀት እንዲኖራቸው የሚታሰበው? ስለሕዝባዊ አደረጃጀት ሲወራ የባለቤትነት ጉይም አብሮ መታየት ይኖርበታል፡፡ ሌላው የስፖርቱ መተዳደሪያ ደንብ ሕዝባዊ አደረጃጀት ስለሚባለው ነገር የሚያወራው አንዳችም የለም፡፡ መፍትሔ ከተባሉ ደግሞ እነዚህና ሌሎችም አሳሪና ገዳቢ ሕጎች የግድ መሻሻል ይኖርባቸዋል፡፡ ሊጋችንን መቀየርና መለወጥ ይኖርብናል፡፡ የሌሎች አገሮች እግር ኳስ እንዴትና በምን ሁኔታ ሊያድግ እንደቻለ ኮርጀን ለእኛ በሚጣጣም መልኩ መተግበር ይኖርብናል፡፡ ከማንኛውም አካል ነፃ የሆነና ቢዝነስ ተኮር የሊግ አደረጃጀት መፍጠር ይኖርብናል፡፡ የሊጉ አደረጃጀት ከክለቦች ጋር ምንም ንክኪ የሌለው ፕሮፌሽናሎች የሚመሩት መሆን ይኖርበታል፡፡ ሊጉ የቴሌቪዥን መብቶችን የሚጠብቅ፣ የክለቦችን የንግድ ምልክት የሚያስጠብቅና ራሱ ሊጉን የሚያንቀሳቅሰው የበጀት ባለቤት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ክለቦችን ከታች ጀምሮ የሚደጉም ሊግ ሊኖረን ይገባል፡፡ የሚገርመው በአሁኑ ወቅት የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ የሚሆን ክለብ ከፌዴሬሽኑ የሚያገኘው ሽልማት ክለቡ ለአንድ ተጨዋች የሚከፍለው የአንድ ወይም የሁለት ወር ደመወዝ ነው፡፡ ሁሉም ክለቦች በአካፋ አውጥተው በማንኪያ እንኳን አያገኙም፡፡ እዚህ እውነታ ላይ ሆነን ነው፣ ስለ እግር ኳስ ዕድገት የምናወራው፡፡ ሁሉ ነገራችን ስሜት ብቻ ነው፡፡ ይህንን እንዴት ብለን ነው ሊግ ብለን የምንጠራው፡፡ የሁላችንም እምነት ዕድገት ክሆነ የሊጉን አደረጃጀት መቀየር ይኖርብናል፡፡ ከልባችን ከሆነ ደግሞ መቀየር እንችላለን፡፡ ወረቀት ላይ ሳይሆን ሰዎች ላይ ኢንቨስት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በአገሪቱ ለማመን በሚያዳግት ሁኔታ ወጣቶች አሉ፡፡ የዕውቀት ችግር ካለብንም የተወሰኑ ሙያተኞችን ወደ አደጉ አገሮች ልከን ማሠልጠን ካለብም እናሠልጥን፡፡ የመንግሥት ድጎማ ሲቀር አብሮ የሚቀር የክለብ አደረጃጀት፣ በአገሪቱ እግር ኳስ ላይ እያሳደረ ያለውን ተፅዕኖ በዓይናችን እያየን ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ አመራርነቴና እንደ ክለብም ቅዱስ ጊዮርጊስ እስካሁን ዓይነት የመቀጠል ፍላጎት የለውም፡፡ በዚህ ሁለት ዓመት ውስጥ በተግባር የሚሠራቸው ይኖራሉ፡፡ ምክንያቱም አሁን ከምንገኝበት ደረጃ እንደገና ወደ መመለስ የለብንም፡፡ በዕድሜ ብቻ ምሳሌ መሆን አንፈልግም፡፡ በሥራና በተግባር ምሳሌ መሆንም ይጠበቅብናል፡፡
ሪፖርተር፡- እርስዎ ቀደም ሲል እንደ ሥጋት ያነሱት የሌሎች ክለቦች አደረጃጀትና ራሱ የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አደረጃጀት ብዙ ክፍተት ያለበት መሆኑ እሙን ነው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ብቻውን ይህን ክፍተት ተቋቁሞ መለወጥ ይችላል?
አቶ አብነት፡- ምንም ጥርጥር የለውም እንቸገራለን፡፡ ነገር ግን እጅና እግራችንን አጣጥፈን መቀመጥ ደግሞ አንፈልግም፡፡ ምክንያቱ ለዓመታት ይዘን የቀጠልነው አሠራር አላዋጣንም፡፡ ይህን ደግሞ ሌሎች ክለቦችም ያጡታል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ሁላችንም የችግሩ ተጠቂዎች ሆነናል፡፡ ይኼ ከሆነ አብረን ለመታገል ዳተኛ የምንሆንበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ብሔራዊ ቡድናችን እኮ የክለቦችና የአደረጃጀታቸው ውጤት ነው፡፡ ሐቁ ይህ ከሆነ ደግሞ እውነትን መዋጥ ይኖርብናል፡፡ ራሳችንን ካልሆነ ማንንም እያታለልን እንዳልሆነ ቆም ብለን ማሰብ ይኖርብናል፡፡ የእግር ኳሳችን መድኃኒት እውነትን መዋጥ ብቻ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ከክለብ አመራሮች ጀምሮ እስከ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ያለው አመራር ይህንን መሸከም የሚችል አቅም ያለው ይኖራል ብለው ያምናሉ?
አቶ አብነት፡- እስካሁን ባለው አለ ብሎ አፉን ሞልቶ ለመናገር ይቸግረኛል፡፡ ምክንያቱም አቅሙ ካለን ከስህተታችን ለመማር አንቸገርም ነበር ብየ አስባለሁ፡፡ የሚገርመው እንዲህ ዓይነቱን መድረክ ያገኘሁት ባለፈው ሳምንት በተካሄደው 39ኛው የካፍ ጉባኤ ላይ ነው፡፡ የልቤንም ተናግሬያለሁ፡፡ ብዙዎቹ አፍሪካውያንም ይሁንታ ሰጥተውታል፡፡ በቅርቡ በእንግሊዝ የግብፁ አልሃሊ፣ ከኢትዮጵያው ቅዱስ ጊዮርጊስ እኔ፣ የደቡብ አፍሪካው ሳንዳውስን ክለብ ፕሬዚዳንትና የወቅቱ የካፍ ፕሬዚዳንት አህመድና ሌሎችም በሚገኙበት ስብሰባ እናደርጋለን፡፡ አጀንዳችን በዋናነት አደረጃጀትን የተመለከተ ነው፡፡ በእርግጥ የት ድረስ እንደምንዘልቅ ባላውቅም ፍላጎቴ ግን ይኼ ነው፡፡ በአገራችን የዚህ ዓይነት መድረክ ያስፈልገናል፡፡ በኳሳችን እስከ ጥግ ሄደን ልንከራከር ይገባል፡፡ መለመድም ይኖርበታል፡፡ እርግጥ ነው እንዲህ ዓይነት ነገር ስለምን ታነሳለህ? የሚሉ እንደማይጠፉ አውቃለሁ፡፡ ጥሩ ነገር አንድ ቀን አንድ ቦታ እንደሚጀምር ግን ሙሉ እምነቱ አለኝ፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ እንዲለወጥ ከተፈለገ መድረክ የግድ ነው፡፡ በመድረኩ አብነት ያነሳው ሐሳብ ትክክል አይደለም ብሎ የሚያሳምነኝ ከመጣ የተሻለውን ሐሳብ ጎንበስ ብዬ ለመቀበል ዝግጁ ነኝ፡፡ በእግር ኳስ አትችልም፣ እችላለሁ ተባብለን የግድ ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ መሄድ ይኖርብናል፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ፣ በተለይም አሁን አሁን በስፖርቱ ምንም ዕውቀት የሌለው መሪና አስተዳዳሪ መሆን የሚገባኝ እኔ ብቻ ነኝ ብሎ የሚመጣ በዝቷል፡፡ በግሌ ይኼ ስሜታዊነት ካልሆነ ለስፖርቱ አንዳች ነገር እንደማይፈይድ ግልጽ ነው፡፡ የማይሆን ነገር ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ሐኪም መሐንዲስ ሊሆን እንደማይችል ሁሉ፣ ስፖርታችንም በዚሁ አግባብ ሊቃኝ ይገባል፡፡ ቀደም ብሎ ተቋሙን አስተዳድረው የሄዱ ጭምር አንድ የእግር ኳስ ሜዳ ስንት በስንት ነው? ተብለው ቢጠየቁ የሚያውቁት አንዳች እንደማይኖር እርግጠኛ ሆኜ ነው የምናገረው፡፡ የኳሷን ኪሎ ቢጠየቅ እህል በረንዳ ሄዶ ካልሆነ መልስ የሌለው ብዙ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ሜዳ ቁጭ ብለን ጨዋታ እየተከታተልን ባለበት ሰዓት፣ አሠልጣኙ ተጨማሪ ተጨዋቾችን የማያስገባው ለምንድነው? ሲል ያዳመጥኩት አመራር አውቃለሁ፡፡ እግር ኳሳችን እየተመራ ያለው እነዚህን በመሰሉ ሰዎች ነው፡፡ እጅግ በጣም የሚያስተዛዝብ ነገር እያስተዋልን ነው፡፡ በግሌ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ አዝናለሁ፡፡ ቀጣይነቱ እንዴት ነው? የሚለውም ያሳስበኛል፡፡ መድረክ ተፈጥሮ እንነጋገርበት፣ እንከራከርበት የምለውም ለዚህ ነው፡፡ ማሸነፍ መሸነፍ ሜዳ ላይ ብቻ ሳይሆን መድረክም ላይ መለመድ ይኖርበታል፡፡
ሪፖርተር፡- መድረኩ እንደሚፈጠር ማስተማመኛ ይኖርዎታል?
አቶ አብነት፡- የለኝም፡፡
ሪፖርተር፡- እንዲህ ከሆነ እግር ኳሱ ገና ብዙ ፈተና ይጠብቀዋል ማለት እንችላለን እንበል?
አቶ አብነት፡- እያልኩ ያለሁት ፈተናውን ፈርተን እጃችንን አጣጥፈን መቀመጥ የለብንም ነው፡፡ የአንድ ጆንያ ክብደትና ቅለት የሚታወቀው ተሸክመን ስናየው ነው፡፡ ስለሆነም የእግር ኳሳችን ፈተና ሸክም ነው፡፡ ተሸክመን ችግሩን ልንጋፈጠው ይገባል፡፡ ሸክሙ ጥጥ ወይም ጤፍ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርብናል፡፡ አብነት ሸክሙን ተሸክሞ ራሱን ለማየትና ለመፈተሽ ዝግጁ ነው፡፡ ከወደቀም አጋጣሚው ጥሩ ይሆንለታል፡፡ ያለን ብቸኛው አማራጭም ይኼው ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በአዲስ አበባ በተካሄደው የካፍ ጉባኤ ብዙ ነገር ታይቷል፡፡ ኢትዮጵያ የመሥራችነቷን ታሪክ ካልሆነ፣ በቀጣይ የአጃቢነት ሚና ካልሆነ ወደ ቀደመው ታሪኳ እንደማይታሰብ ታዝብናል፡፡ በእግር ኳሱ ብቻ ሳይሆን ከአመራር ሰጪነትም እየወጣን ነው፡፡ ምን ይላሉ?
አቶ አብነት፡- እየወጣን ነው ሳይሆን ወጥተናል በሚለው ነው የምስማማው፡፡ ወደ ቀደመው ለመምጣት ለመግባት ከፈለግን ደግሞ መንግሥት በግማሽ ሳይሆን መቶ በመቶ መግባትና መደገፍ ይኖርበታል፡፡ የዘንድሮ የካፍ ምርጫ ባልታሰበ መልኩ እንዲለወጥ የግብፅ ሚና ቀላል እንዳልነበረ ተመልክተናል፡፡ መንግሥት ስፖርቱ ውስጥ አያገባውም የሚባለው ውሸት ነው፡፡ እንደሚያገባው በአውሮፓም ሆነ በሌሎች አገሮች በፊፋ የታየውን እውነታ መመልከት በቂ ነው፡፡ የአገርን ጉዳይና የመጠበቅና የመከታተል ትልቁ ኃላፊነት የመንግሥት ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት ለዚህ ኃላፊነት የሚያቀርባቸው ሰዎች ላይ ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ አንዱ ኃላፊነቱ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በካፍ ውስጥ ከእኔ ውጭ ተወካይ የለም፡፡ ግን መሥራች ነን እያልን ነው የምናወራው፡፡ እኛ ከጀመርነው ቤት እየወጣን ነው፡፡ ምንድነው ድክመታችን? መጠያየቅና መተማመን ያስፈልጋል፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ አይደለም፣ ክለብ የሌላቸው ወደ ካፍ አመራርነት መጥተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለሌሎች እያመቻቸች የራሷን ችላ ማለት አይገባትም፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ በአሁኑ ወቅት በራሷ ኃይልና አቅም የምትንቀሳቀስ አፍሪካ አይደለችም፡፡ ሁሉም ነገር እየሄደ ያለው በአውሮፓውያን ፍላጎት ነው፡፡ ከአዲሱ የካፍ ፕሬዚዳንት ጋር ስለዚህ ጉዳይ ተገናኝተን ተነጋግረናል፡፡ ይህን ስል ኢሳ ሐያቱ ለምን ወረዱ? አይደለም፡፡ የእሳቸው የመውረጃ ጊዜ አሁን ሳይሆን ቀደም ብሎ እንደነበር አምናለሁ፡፡ ለዚህም ነው መንግሥት ካሁኑ ትምህርት እንዲወስድ የምጠይቀው፡፡ ለጊዜውና ለስፖርቱ ተመጣጣኝ አቅምና ዕውቀት ያላቸው ያስፈልጉናል፡፡ በየአራት ዓመቱ መቀያየር ብቻውን መፍትሔ አይሆንም፡፡ ይኼ በራሱ ትልቅ ችግር መሆኑ ሊገባን ይገባል፡፡ ለስፖርቱ የሚጠቅሙ ሰዎችን ለምንድነው የምንቀያይረው?
ሪፖርተር፡- ለዚህ የሚመጥኑ ሰዎችስ በተገቢው ቦታ አሉን ብለን መውሰድ እንችላለን?
አቶ አብነት፡- በሚገባ ካሰብንበት አሉን፡፡ የሚመጡበትን መንገድና የሚመጡት ሰዎች ምርጫ ላይ ግን መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡ ይኼ ደግሞ የእኛ ብቻ ሳይሆን የመንግሥትም ኃላፊነት ነው፡፡ በስፖርቱ አልፈው ነገር ግን ወደ ስፖርቱ ለመምጣት ያለውን ሽኩቻና ውጣ ውረድ በመፍራት ብቻ ሙያውን የጠሉ በርካቶች ለመኖራቸው፣ መጫወቻ ሜዳውን ክፍት አድርጎ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡