Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቱርክ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር የንግድ ድርድር እንደሚያካሂድ አስታወቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ከዚህ ቀደም ጥያቄ የቀረበባቸው ጉዳዮች ለድርድር እንደሚቀርቡ ይጠበቃል

በመጪው ሳምንት በቱርክ ርዕሰ ከተማ አንካራ በንግድና በኢንቨስትመንት ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ድርድር ለማካሄድ ቀነ ቀጠሮ መያዙን የቱርክ ዲፕሎማት አስታወቁ፡፡

በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ፋቲህ ኡልሶይ ለሪፖርተር እንደገለጹት በሁለቱ አገሮች ባለሥልጣናት መካከል በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በኢኮኖሚ መስኮች ድርድር እንደሚካሄድ ይጠበቃል፡፡ ለዚህም ከአዲስ አበባ በርካታ ልዑካን የሚሳተፉበት ቡድን ወደ ቱርክ እንደሚያቀና አምባሳደሩ አስረድተዋል፡፡

በታኅሳስ ወር የቱርክ ንግድ ልዑካንን በመምራት በአዲስ አበባ ቆይታ ያደረጉት የኢኮኖሚ ሚኒስትሩ ኒሃት ዜይቤች፣ ኢትዮጵያ የነፃ ገበያ ስምምነትን ከቱርክ ጋር ከመፈረም በተጨማሪ የቱርክ አየር መንገድ የሚያስተዳድራቸውን ትልልቅ የመንገደኛና የካርጎ አውሮፕላኖች እንድታስተናግድ ያቀረቧቸው ጥያቄዎች ይታወሳሉ፡፡ ‹‹የቱርክ አየር መንገድ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር እንዲፎካከር አንፈቅድም፡፡ ሆኖም አየር መንገዳችን ትልልቅ አውሮፕላኖቹን የሚያስተናግድበት አሠራር እንዲፈቀድለት እንጠይቃለን፤›› በማለት ሚኒስትሩ መናገራቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ከእነዚህ ጥያቄዎች በተጓዳኝ በቱርክ የንግድ ማኅበረሰብ  አባላት ተከታትለው ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከልም የቱርክ ባለሀብቶችን የፋይናንስ ጥያቄዎችን ለማስተናገድ ይቻል ዘንድ፣ የወኪል ባንክና የቅርንጫፍ ባንክ አገልግሎት ይፈቀድልን የሚለው ይገኝበታል፡፡

እነኚህን ጥያቄዎች በሚመለከት የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም ምን እንደሆነ በወቅቱ ያብራሩት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተው፣ መንግሥታቸው ነፃ የገበያ ዕድልም ሆነ የቱርክ ባንኮች በኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ይክፈቱ ለሚለው ጥያቄ ምላሹ አይሆንም እንደሆነ መግለጻቸውም ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያ በነፃ ገበያ ስምምነት ለቱርክ ባለሀብቶች በሯን የምትከፍትበት ጊዜ ገና መሆኑን፣ የአገር ውስጥ አምራቾች አቅም ከቱርኮች ጋር ለመወዳደር የሚችልበት ደረጃ ላይ አለመድረሱን በመግለጽ፣ የነፃ ገበያ ስምምነት ይደረግ የሚለው ጥያቄ ተቀባይነት እንዳላገኘ አስታውቀዋል፡፡

ይልቁንም በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያደረጉ ባለሀብቶችና ኩባንያዎቻቸው ያመረቷቸው ምርቶች ከቀረጥና ከታክስ ነፃ ሆነው መላክ እንዲችሉ ለቱርክ ባለሥልጣናት ጥያቄ መቅረቡን ያብራሩት አቶ አህመድ፣ ምንም እንኳ ቱርክ እንደ አሜሪካ ያሉ አገሮች የሰጡትን ዓይነት የነፃ ገበያ ዕድል ለኢትዮጵያ ለመስጠት ስትል በሯን ለሌሎችም ለመክፈት እንዳትገደድ ካስፈለጋትም፣ ከኢትዮጵያ ጋር ብቻ በሚደረግ የሁለትዮሽ ስምምነት መሠረት ጥያቄውን ማስተናገድ እንደምትችል ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር የቱርክ ባንኮች በኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ይክፈቱ ለሚለው ጥያቄ የአገሪቱ ባንኮች በተለይም የግሎቹ ከቱርኮች ጋር የመወዳደር አቅም ስለሌላቸው፣ ይህ ጥያቄም በአጭር ጊዜ ውስጥ መስተናገድ ከማይችሉት ጋር ተመድቧል፡፡፡ ይሁንና እንደ ሌሎች አገሮች ቱርኮችም የላይዘን ጽሕፈት ቤት በመክፈት፣ ከብድር፣ ከቁጠባና ከወለድ መሰብሰብ፣ በጠቅላላው ከፋይናንስ በስተቀር ያለውን ሥራ እንዲሠሩ እንደሚፈቀድላቸው አቶ አህመድ ጠቁመዋል፡፡  

ቱርኮች ላቀረቡት የትልልቅ አውሮፕላኖች ማስተናገጃ ጥያቄም አቶ አህመድ የኢትዮጵያ መንግሥት ምላሽ ምን እንደሆነ ከሪፖርተር ተጠይቀው አብራርተዋል፡፡ የቱርክ አየር መንገድ በሳምንት ሰባት ቀን በአዲስ አበባና በኢስታምቡል ከተሞች መካከል መብረር እንዲችል መፈቀደኑ ጠቅሰው፣ ይሁንና የኢትዮጵያ አየር መንገድ እየተካሄዱለት ከሚገኙ የኤርፖርትና የሌሎች አገልግሎቶች ማሻሻያዎች አኳያ የውጭ ትልልቅ አውሮፕላኖችን ለማስተናገድ የሚችልበት አቅም ላይ ሲደርስ እንደሚፈቀድ፣ ከዚህ ባሻገር ግን ኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁንም ድረስ የመንግሥት ድጋፍና ከለላ የሚያስፈልገው በመሆኑ የቱርኮች ጥያቄ ወደፊት እንደሚታይ አስረድተዋል፡፡  

ቱርኮችም ሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥት ያነሷቸው ጥያቄዎች ወደፊት በሚካሄዱ የዲፕሎሲና የኢኮኖሚ ትብብር የቴክኒክ ስብሰባዎች በድርድር እንደሚታዩ በተገለጸው መሠረት፣ የመጀመሪያው የድርድር መድረክ በቱርክ ሊካሄድ ጥቂት ቀናት ቀርተውታል፡፡

ለድርድር ወደ ቱርክ ከሚያቀናው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በተጨማሪም በግብርናው መስክ ለመነጋገር የሚጓዝ ልዑክ እንደሚኖርም አምባሳደር ኡልሶይ ገልጸዋል፡፡ በአንፃሩ ከቱርክ የሚመጡ ልዑካን እንደሚኖሩ፣ በተለይም በኢነርጂ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ያሳየ ትልቅ ኩባንያም ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ አምባሳደሩ ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ 148 ያህል ኩባንያዎች ከ2.5 ቢሊዮን ዶላር ያላነሰ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እንዳስዘመገቡ ከሁለቱ ወገኖች የተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ቱርክ በአፍሪካ ያስመዘገበችው ጠቅላላ የኢንቨስትመንት መጠን ከስድስት ቢሊዮን ዶላር በላይ መሆኑን አስታውቃለች፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች