Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የሜትር ታክሲዎች ፈተና

የአዲስ አበባ ከተማን የትራንስፖርት አገልግሎት ለማዘመን ታስበው ከተወሰዱ ዕርምጃዎች መካከል አንዱ የሜትር ታክሲ አገልግሎትን ወደ ሥራ የማስገባት ተግባር ነው፡፡

አገልግሎቱ ተጀመረ ይባል እንጂ ከጀምሩ አንስቶ ብዥታዎችን ፈጥሯል፡፡ እርግጥ ነው በመላምት ከሚደረግ የኮንትራት ታክሲ የዋጋ ትመና ይልቅ፣ አገልጋዩንም ሆነ ተገልጋዩን በሚያስማማ እንዲሁም ሕግ በሚያውቀው ዋጋ እንድንገለገል ማስቻሉ ትልቅ እመርታ ነው፡፡ ያለክርክርና ጭቅጭቅ በተጓዝነው ርቀት ልክ እንዲሁም በተተመነው ዋጋ መሠረት ለመገልገል የሚያስችል መሆኑ የትራንስፖርት ዘርፉን ለማዘመን አንድ ዕርምጃ ወደፊት የሚባል ጅምር እንደሆነ አይጠረጠርም፡፡

ይሁን እንጂ ለአገልግሎቱ የተተመነው ዋጋ በተማኙና አገልግሎቱን ለመስጠት ተሽከርካሪዎቹን በገዙት ባለንብረቶች መካከል ያለመግባባት ተፈጥሯል፡፡ በዚህ ምክንያትም የሜትር ታክሲ አገልግሎት ጠዓምን በቅጡ ልናውቀው አልቻልንም፡፡ የሜትር ታክሲ አገልግሎት መላው ግራ ቢያጋባም እንዲጀመር ለማድረግ የተኬደበት መንገድ ይደነቃል፡፡ ያለመግባባቱ ዕልባት አግኝቶ የሜትር ታክሲዎች በተገቢው መንገድ አገልግሎት መስጠት መቻላቸው ግን ዋናው ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ማድረግ ካልተቻለ ግን አሁንም የኮንትራት ታክሲ አገልግሎት እንደቀድሞመው በዘፈቀደ ዋጋ የሚጠየቅበት ሆኖ ይቀጥላል ማለት ነው፡፡ የሜትር ታክሲዎች ሊያስገኙ ይችላሉ ተብለው የታመነባቸውን ዘመናዊ ትራንስፖርት አሰጣጥ ሥርዓት ሊያደናቅፍ ይችላል፡፡ ይህ እንደማይሆን ግን ተስፋ እናደርጋለን፡፡

በአሁኑ ወቅት ሜትር ታክሲዎች መስጠት የሚገባቸውንና የሚጠበቅባቸውን ትክክለኛ አገልግሎት እየሰጡ ባይሆንም፣ ከባለንብረቶቹ የሚነሱ ቅሬታዎችን በአግባቡ መፈተሽ፣ መተማመንና አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ግድ የሚባልባቸው ነጥቦች አሉ፡፡

ተደጋግሞ እንደተገለጸው፣ ሜትር ታክሲዎች በባንክ ብድር የተገዙ ናቸው፡፡ ዕዳቸውም እስከነወለዱ መከፈል አለበት፡፡ ይህንን ዕዳ ለመክፈልም ጠንክረው መሥራት ይጠቅባቸዋል፡፡ በአግባቡ ለመሥራት ደግሞ መስማማትና መግባባት ያሻል፡፡ ባለንብረቶቹ ከዘፈቀደ የአገልግሎት አሰጣጥ ወጥተው ዘመናዊውን መንገድ ሊከተሉ ይገባቸዋል፡፡ ይህንን ይቀበሉታል፡፡ መንግሥት እየሠሩ ጥያቄያቸውን እንዲያቀርቡ እየተወተወተ ይገኛል፡፡ ያወጣሁትን ታሪፍ ሞክሩት እያየሁ አስተካክላለሁ የሚለው መንግሥት፣ የታክሲ ባለንብረቶቹንም ጥያቄ በጥሞና ተመልክቶ ወደ መግባባቱ ለመምጣት የሚያበቃ መትፍሔ እንዲሰጥ ይመከራል፡፡ በመሆኑም በሁለቱ ወገን የሚታየው ፍጥጫ ከአጀማመሩ በተገልጋዩም በታክሲ ባለንብረቶችም ዘንድ ጉጉት አሳድሮ የነበረውን አገልግሎት ውኃ የቸለሰበትን አካሄድ ማጣኔንም ይገባል፡፡  

ከታሪፍ ጋር በተገናኘ ሜትር ታክሲዎቹ እያነሷቸው ካሉት ጥያቄዎች ይበልጥ ግን ለብዙዎች ትልቅ ትኩረት የሚሻ ሌላ አንኳር ጉዳይም አለ፡፡ የሜትር ታክሲ ባለንብረቶች የገዟቸውን ተሽከርካሪዎች ለማስጠገን፣ ሌላው ቀርቶ የሞተር ዘይት  ለመቀየር ቢፈልጉ እንኳ አማራጭ አልባ መሆናቸው እየታየ ነው፡፡ መኪኖቹን ወደ አቀረበው ብቸኛ ኩባንያ ሔዳችሁ ተገልገሉ መባላቸው ነገሩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎባቸዋል፡፡

ከሰሞኑ እንደሰማነው ተሽከርካሪዎቻቸው ቢጎዱ ወይም የቴክኒክ ችግር ገጥሟቸው፣ ጥገና ቢያሻቸው መሄድ የሚችሉት አሁንም በብቸኝነት ኃላፊነት ተሰጥቷል ወደተባለው ሊፋን ኩባንያ መሆኑ ግራ ያጋባል፡፡ በአንድ የአገልግሎት ዘርፍ ያለተወዳዳሪ እንዲሠራ መፍቀድ ብዙ ነገር ይበላሻል፡፡ ሥራውን በሞኖፖል የያዘው አካል ያሻውን ዋጋ ተክሎ፣ እንዳሻው ከተገልጋዩ ፍላጎት ውጭ በመሆን የሚሠራበትን ዕድል የሚፈጥር፣ የአገልገሎት አሰጣጡን የሚያንሻፍፍ ክስተት ይፈጥራል፡፡

በዘመነ ነፃ ገበያ ለእነዚህ ተሽከርካሪዎች ጥገና አንድ ተቋም ብቻ ውክልና ማግኘቱና መደምደሙ፣ ይህንንም አሠራር ተግባራዊ እንዲሆን መንግሥት ተቀብሎ ማፅደቁ ከምን የመነጨ እንደሆነ ግልጽ ባይሆንም፣ አሠራሩ መተግበሩ ግን ግርታን ብቻም ሳይሆን ሥጋትንም ያጭራል፡፡ ባለንብረቶቹም ይህ አሠራር ተገቢነት እንደሌለው ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አኳያ የባለንብረቶቹ መማረር ሲመዘን ትክክለኛ ሆኖ ይገኛል፡፡ በሞኖፖል  እየተያዘ የሚሰጥ አገልግሎት፣ ያውም ሌሎች ብቁ ተወዳዳሪዎች ባሉበት አግባብ መደረጉ የፀረ ነፃ ገበያ ተግባር ብቻም ሳይሆን መጥፎ ምሳሌ የሚሆን ብልሹ አሠራርን ያሰፍናል፡፡ ያልተገባ የዋጋ ንረትን ያስከትላል፡፡ በአንድ ኩባንያ ብቻ እንዲገለገሉ መወሰን የሚያስከትለውን ጉዳት በብዙ መንገድ መተንተን ቢቻልም፣ የዚህ ዓይነት አሠራር በአማራጭና በተሻለ ዋጋ እንዳይጠቀሙ ዕድሉን የሚነፍግ ውጤትን ያስከትላል፡፡

እንዲህ ያለው ውሳኔ ሲወሰን የቱንም ያህል ምክንያታዊ ጉዳዮች ቢኖሩም ዕርምጃቸው ግን አሳማኝ ሊሆን አይችልም፡፡ ተሽከርካሪዎቹ በባንክ ብድር መገዛታቸው እውነት ሲሆን፣ ንብረትነታቸውም የገዢዎቹ ነው፡፡ የብድር ስምምነቶች ግን አገልግሎት ስትፈልግ መገልገል ያለብህ እኛ ከመረጥንልህ ኩባንያ ብቻ ነው የሚል ግዳጅ አያስቀምጡም፡፡ ተሽከርካሪውን የሸጠው ኩባንያም ቢሆን ክፍያው እስከተፈጸለት ድረስ ባስተላለፈው ንብረት ላይ አዛዥ መሆን አይችልም፡፡ በቂ መለዋወጫ ማቅረብ አለበት፡፡ ሌሎችም እንዲያመጡ ዕድል የማይሰጥ ከሆነ ችግሩ ይበረታል፡፡ የእነዚህን ተሽከርካሪዎች  አጠቃላይ የቴክኒክ ፍተሻ፣ የሚያስፈልጋቸውን የመለዋወጫ አቅርቦትና የጥገና አገልግሎት እኔ ብቻ ነኝ ማቅረብ ያለብኝ ብሎ ከቀጠለ አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ጉዳይ አሳሳቢ ሆኖ ይቀጥላል፡፡

ለዚህ ክፍተት መፍትሔ ካልተሰጠ ችግሩ ባለንብረቶቹን ብቻ ሳይሆን ዘመናዊ አገልግሎት አሰጣጡንም ይጎዳል፡፡ የነፃ ገበያ መርሆዎችንም ይቃረናል፡፡ በሌሎች ተሽከርካሪ አምራች ኩባንያዎች ዘንድ ያልተተገበረን አሠራር ሜትር ታክሲዎች ላይ ብቻ እንዲተገበር የተፈለገበት ምክንያት ግልፅ መውጣት አለበት፡፡ ዜጎች የገዛ ንብረታቸውን በአግባቡ ያሠሩ እንጂ በሚስማማቸው የትኛውም ቦታ የማሠራት መብታቸው መነፈግ የለበትም፡፡ መለዋወጫዎቹም ቢሆኑ በነፃ ገበያ መርህ ገብተው ሊሸጡ ይገባል፡፡ የተለያዩ ተሽከርካሪዎችን በመጠገን፣ ቴክኒካዊ ፍተሻ በማድረግ እየሠሩ ያሉት ጋራዦችስ ለምን የሥራ ዕድል ይነፈጋሉ? 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት