ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተሰበሰበው 9.6 ቢሊዮን ብር ውስጥ፣ አምስት ቢሊዮን ብር የተዋጣው ከመንግሥትና ከግል ሠራተኞች መሆኑ ተገለጸ፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሮማን ገብረ ሥላሴ እንደገለጹት አርሶና አርብቶ አደሮች፣ የመንግሥትና የግል ሠራተኞች፣ ባለሀብቶች፣ ነጋዴዎች፣ ዳያስፖራውና ሌሎች ዜጎች ለህዳሴ ግድቡ ግንባታ በገንዘብ፣ በቁሳቁስ፣ በዕውቀትና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ቃል ከተገባው 12.4 ቢሊዮን ብር ውስጥም 9.6 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ውስጥ የመንግሥትና የግል ሠራተኞች አምስት ቢሊዮን ብር በማዋጣት ከፍተኛውን ድርሻ እንደያዙ አስታውቀዋል፡፡
በአርሶና በአርብቶ አደሮች አማካይነት በመላ አገሪቱ ከአራት ቢሊዮን በላይ የሚሆኑ ዛፎች እንደተተከሉ የገለጹት ዳይሬክተሯ፣ በአሁኑ ወቅትም 70 በመቶ የሚሆኑ ዛፎች እንደፀደቁ አክለዋል፡፡ ይኼ ደግሞ የህዳሴ ግድቡ በደለል ተሞልቶ ችግር እንዳይፈጥር የራሱ የሆነ ሚና ይጫወታል ሲሉ አብራርተዋል፡፡ በገንዘብ ሲተመንም ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
ከነጋዴዎች ሁለት ቢሊዮን ብር እንደተሰበሰበ የተናገሩት ወ/ሮ ሮማን፣ ዳያስፖራው በበኩሉ እስካሁን ድረስ 888 ሚሊዮን ብር ማሰባሰቡን ገልጸዋል፡፡
የታላቁ የህዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ የተጣለበትን ስድስተኛ ዓመት በማስመልከት ‹‹ታላቁ የህዳሴ ግድባችን የአገራችን ኅብረ ዜማ፣ የህዳሴያችን ማማ!›› በሚል መሪ ቃል ለስድስተኛ ጊዜ ከየካቲት 26 እስከ መጋቢት 24 ቀን 2009 ዓ.ም. እየተከበረ ነው፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የፕሮጀክት ማኔጅመንት፣ የአካባቢ ጥበቃና የሥነ ጥበብ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ተካ፣ ሐሙስ መጋቢት 14 ቀን 2009 ዓ.ም. የታላቁ የህዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ የተጣለበትን ዕለት በማስመልከት ለአንድ ወር ያህል በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው ብለዋል፡፡
በክብረ በዓሉም ‹ግድባችንን በቁርጠኝነት አጋምሰናል›፣ ‹ለፍጻሜውም ተነስተናል›፣ ‹የታላቁ ህዳሴ ግድባችን የቁርጠኝነት ሐውልት ነው›፣ ‹ያገባደድነው ግድባችን ለጀመርነው ህዳሴያችን ፋና ነው› የሚሉና ሌሎች መልዕክቶች የሚተላለፉ መሆኑን ከአቶ ሰለሞን ለመረዳት ተችሏል፡፡ ከዝግጅቶቹ መካከልም ሩጫ፣ የቦንድ ሳምንት፣ የእግር ኳስ ውድድር፣ የሕፃናት ሥዕል ውድድር፣ የጥያቄና መልስ ውድድርና ሌሎች ፕሮግራሞች እንደሚካሄዱ አስረድተዋል፡፡
ይኼ ለአንድ ወር ያህል የሚቆየው የህዳሴ ግድብ ግንባታ ክብረ በዓል መጋቢት 24 ቀን 2009 ዓ.ም. ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና ሌሎች ባለሙያዎች በተገኙበትና ታላቁ የህዳሴ ግድብ በሚገነባበት በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባ ወረዳ እንደሚጠናቀቅ ለማወቅ ተችሏል፡፡