Wednesday, October 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሐበሻ ሲሚንቶ በቅርቡ ወደ ገበያ እንደሚቀላቀል አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሐበሻ ሲሚንቶ አክሲዮን ማኅበር ሲሚንቶ ለማምረት የሚያስፈልገውን የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር በማግኘቱ፣ በሦስት ሳምንት ውስጥ ምርቱን ለገበያ እንደሚያቀርብ አስታወቀ፡፡

ቀደም ሲል ፋብሪካው ባለፈው ዓመት ሥራ እንደሚጀምር በግንባታ ዕቅዱ ላይ ቢሰፍርም፣ በተለያዩ ምክንያች ዘግይቶ አሁን ግን ለመጀመር መዘጋጀቱን ኃላፊዎቹ ገልጸዋል፡፡

የሐበሻ ሲሚንቶ አክስዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን አቢ (ኢንጂነር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በመጪዎቹ 20 ቀናት ውስጥ የፋብሪካው ምርቶች በአዲስ አበባና በሌሎች የአገሪቱ ከተሞች መሠራጨት ይጀምራሉ፡፡

ግንባታው በቅርቡ የተጠናቀቀው የሐበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካ ምርቱን ከወራት በፊት ለማቅረብ የሚያስችለው ደረጃ ላይ ቢደርስም፣ የኤሌክትሪክ ኃይል እስኪለቀቅለት ድረስ በመጠባበቅ እንደቆየ አቶ መስፍን ገልጸዋል፡፡

ከአዲስ አበባ በ35 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሆለታ ከተማ አካባቢ በ33 ሔክታር መሬት ላይ የተገነባው ፋብሪካው፣ 3.4 ቢሊዮን ብር ገደማ የግንባታ ወጪ እንደጠየቀ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ዓመታዊ የማምረት አቅሙ 1.4 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ እንደሆነና ወደ ውጭ ገበያ የመድረስ ዕቅድ እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡

በገበያ ረገድም ቢሆን ምርቱን ይዞ መቅረቡ ለአገሪቱ አማራጭ እንደማያደርገው የሚገልጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ በአገሪቱ ውስጥ ሰፊ የገበያ ዕድል በመኖሩ ከነባሮቹ ፋብሪካዎች የተለየ የገበያ ችግር እንደማይገጥመው አስረድተዋል፡፡

ሐበሻ ሲሚንቶ አክሲዮን ማኅበር በ2000 ዓ.ም. ሲመሠረት ከ16,000 በላይ ባለድርሻዎችን በመያዝ ነበር፡፡ ይሁንና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የደቡብ አፍሪካዎቹ ግዙፍ የሲሚንቶ አምራቾች የሆኑት ፒፒሲና አይዲሲ የተባሉ ኩባንያዎች የ50 በመቶውን ድርሻ በመግዛት መቀላቀላቸው ይታወሳል፡፡

አክሲዮን ማኅበሩ ከማዕድን፣ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር በሆለታ አካባቢ የጥሬ ዕቃ ማምረቻ ቦታ ተሰጥቶት ለሲሚንቶ ዋንኛ ግብዓት የሆኑትን ቀይ አፈር፣ የኖራ ድንጋይ፣ ጂፕሰምና መሰል ግብዓቶች በማውጣት ለ60 ዓመታት መጠቀም የሚያስችለውን ስምምነት ማድረጉ አይዘነጋም፡፡

ከአራት ዓመታት በፊት ከአፍሪካ ንግድና ልማት ባንክ (የቀድሞው ፒቲኤ ባንክ) 50.4 ሚሊዮን ዶላር ብድር ማግኘቱም ይታወሳል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች