Wednesday, February 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የተረጂዎች ቁጥር እጥፍ ቢሆን እንኳን የመቋቋም አቅም አለን››

አቶ አይድሩስ ሐሰን፣ የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር

ኮሚሽን የአቅርቦትና የሎጂስቲክስ ዋና ዳይሬክተር

ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ ሰፊ ቦታ የሚሸፍን የድርቅ አደጋ ደርሶባታል፡፡ በዚህም ድርቅ 10.2 ሚሊዮን ወገኖች ለምግብ ዋስትና ዕጦት የተዳረጉ ሲሆን፣ መንግሥት 15 ቢሊዮን ብር ወጪ በማድረግ አደጋውን ተጋፍጧል፡፡ በተያዘው ዓመትም እንዲሁ 5.6 ሚሊዮን ዜጎች ለአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ የተዳረጉ ሲሆን፣ ችግሩን ለመቋቋም 948 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል፡፡ በሁለቱም ተከታታይ የድርቅ አደጋዎች ይህ ነው በሚባል ደረጃ የውጭ ዕርዳታ ባይገኝም፣ መንግሥት ከራሱ ግምጃ ቤት በጀት በመመደብ ችግሩን ለመቀልበስ እየሞከረ ነው፡፡ በዚህ ሒደት የመሠረተ ልማትና የውኃ እጥረት ችግሩን ከማባባሳቸው በተጨማሪ፣ ሕገወጦች ለተጎዱ ወገኖች የሚላከውን ዕርዳታ ለራሳቸው ለማዋል የሚሞክሩበት አጋጣሚም እየተፈጠረ እንደሚገኝ ታይቷል፡፡ በወቅታዊው የድርቅ ሁኔታ፣ አዲስ አበባ በገጠማት የቆሻሻ መደርመስ አደጋና የተለያዩ ችግሮችን በተመለከተ ውድነህ ዘነበ የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የአቅርቦትና የሎጂስቲክስ ዋና ዳይሬክተር አቶ አይድሩስ ሐሰንን አነጋግሯል፡፡  

ሪፖርተር፡- ባለፈው ዓመት 10.2 ሚሊዮን ዜጎች፣ በዚህ ዓመት ደግሞ 5.6 ሚሊዮን ዜጎች ያጋጠማቸውን የምግብ እጥረት ለመቅረፍ እየተሞከረ ነው፡፡ ነገር ግን የእርስዎ መሥሪያ ቤት እነዚህ ወገኖች ያሉበት አካባቢ ለመድረስ በአቅርቦትና በሎጂስቲክስ ብቁ ነው ማለት ይቻላል?

አቶ አይድሩስ፡- እኛ ቀድመን ተዘጋጅተን ነበር፡፡ የኤልኒኖ ክስተቶች ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛ ላኒና ነው፡፡ ላኒና በውኃ ብዛት ጉዳት የሚያደርስ ክስተት ነው፡፡ እኛ በድርቁ አንድም ሰው ሳይሞትብን በውኃ ሙላትና በመሬት መንሸራተት የሰው ሕይወት አልፏል፡፡ ይህ ማለት ክስተቱ ከእኛ ቁጥጥር ውጭ ስለሆነ ነው፡፡ ጥሩ ጥያቄ ነው ያነሳኸው፡፡ እኛ በቂ ዝግጅት አድርገን ነበር፡፡ አንደኛ የመጠባበቂያ እህል ክምችት ነበረን፡፡ በቂ እህል አስገብተን ነበር፡፡ ሁለተኛ ባለፈው ዓመት ድርቁ ሲከሰት የድርቁ አወጣጥም ስለማይታወቅና ሊያስከትል የሚቻለው ጉዳት ስለማይተነበይ መንግሥት የራሱን ዝግጅት አድርጎ ነበር፡፡ እንደ ኮሚሽንም የራሳችንን ዝግጅት አድርገን ነበር፡፡

ከአምና የተሻገሩ ምርቶች በትክክል መጠናቸው እንዲታወቁ ተደርጓል፡፡ ሁለተኛ በአምናው ግዥ አገር ውስጥ ያልገቡ ምርቶች በወቅቱ ባለመግባታቸው ያልተቸገርንባቸው ምርቶች እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ከስትራቴጂካዊ መጠባበቂያ ምግብ ክምችት እንድንወስድ መንግሥት አቅጣጫ ሰጥቷል፡፡ ይህን አድርገናል፡፡ አሁን ደግሞ እጅግ የባሰ ሁኔታ ይመጣል የሚል ሥጋት ስላለን፣ የብሔራዊ ሚቲዮሮሎጂ ትንበያንም ስንመለከት የበልግ ዝናብ እጥረት ስለሚታይ ድርቁ ሊጨምር ይችላል፡፡ መንግሥት 5.6 ሚሊዮን ተረጂዎች አሉ ብሎ ይፋ ያደረገው የመኸር ግምገማ ውጤት ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡ የበልግ ግምገማ ቀጥሎ ይካሄዳል፡፡ በዚህ ግምገማ የተረጂዎች ቁጥር ወይ ሊቀንስ ወይ ሊጨምር ይችላል፡፡ እኛ ለዚህ የአስቸኳይ ጊዜ የምንይዘው ተጨማሪ መጠባበቂያ የምግብ ክምችት ነው፡፡ የአደጋ ጊዜ ፋይናንስ እንይዛለን፡፡

ስለዚህ በእነዚህ ስትራቴጂካዊ ዕርምጃዎች ነው ችግሮችን የምንወጣው፡፡ አሁን ያጋጠመን ችግር ከአምና የሚለይባቸው ባህርያት አሉት፡፡ በአሁኑ ጊዜ የምግብ ዋስትና ችግር ያጋጠመው በአርብቶ አደር አካባቢዎች ነው፡፡ አካባቢዎቹ ቆላማና ጠረፋማ ናቸው፡፡ የተደራሽነት ችግሮች አሉ፡፡ ለዚህ መፍትሔ አበጅተናል፡፡ በከባድ ተሽከርካሪዎች (400 ኩንታል የሚጭኑ) እስከ አደጋ ቀጣናው የተወሰነ ቦታ ድረስ የዕርዳታ ምግቦችን እናደርሳለን፡፡ ከዚያ በኋላ በመለስተኛ የጭነት ተሽከርካሪዎችና በጋማ ከብቶች በማጓጓዝ ተደራሽ እያደረግን ነው፡፡ እያንዳንዱ ክልል፣ ዞንና ወረዳ ኮማንድ ፖስት አለው፡፡ እነዚህ መዋቅሮች ትልቅ ሥራ እየሠሩ ነው፡፡ ዝግጅቱ በበቂ ሁኔታ ስላለ ሥራዎች በዕቅዳችን መሠረት እየሄዱ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የተረጂዎች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለውን የመጠባበቂያ እህል ክምችት ሊያዝ ከሚገባው ደረጃ (ስታንዳርድ) ጋር ቢያነፃፅሩልኝ?

አቶ አይድሩስ፡- አሁን ባለው ስታንዳርድ በወር 47 ሺሕ ሜትሪክ ቶን (470 ሺሕ ኩንታል) እህልና አልሚ ምግቦች አሉ፡፡ ለ5.6 ሚሊዮን ተረጂዎች 35 በመቶ ክምችት አለን፡፡ አልሚ ምግቦች ለእናቶችና ለሕፃናት የሚውሉ ናቸው፡፡ ስለዚህ ሙሉ ክምችት አለን፡፡ ሁለተኛ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ በክምችት ላይ ያለ እህል እንዳይበላሽ እየተጠቀምን ከሥር ከሥር እንተካለን፡፡ ስለዚህ በኮሚሽናችን አስተማማኝ ክምችት አለን፡፡ የተረጂዎች ቁጥር እጥፍ ቢሆን እንኳ የመቋቋም አቅም አለን፡፡

ሪፖርተር፡- ለተረጂዎች ያስፈልጋል የተባለው 948 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ በመንግሥትና በግብረ ሰናይ ተቋማት የሚሸፈነው ምን ያህል ነው?

አቶ አይድሩስ፡- እስካሁን በአብዛኛው እየተሸፈነ ያለው በመንግሥት ነው፡፡ ሁለት መሠረታዊ አጋሮች አሉን፡፡ አንደኛ የሶማሌ ክልልን በአብዛኛው የያዘልን የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) ነው፡፡ ሁለተኛ በካቶሊክ ሪሊፍ አስተባባሪነት በጥምረት የሚሠሩ ግብረሰናይ ድርጅቶች አሉ፡፡ ኪስ ወረዳዎችን ይዘው እየሠሩ ነው፡፡ አምና የያዙትን ኪስ ቦታዎች ይዘው ቀጥለዋል፡፡ ከዚያ ውጪ መንግሥት እየሸፈነ ይገኛል፡፡ በአጠቃላይ ለተረጂዎች 919,179 ሜትሪክ ቶን ምግብ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ውስጥ 744,275 ሜትሪክ ቶን እህል፣ 74,428 ሜትሪክ ቶን ጥራጥሬ፣ 22,328 ሜትሪክ ቶን ዘይት፣ 78,148 ሜትሪክ ቶን አልሚ ምግብ ያስፈልጋል፡፡ በገንዘብ ደግሞ 948 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለተረጂዎች ከሚያስፈልጉት እነዚህ የምግብ ዓይነቶች 35 በመቶ የሚሆነው በመጠባበቂያ እህል ክምችት ውስጥ አለ ማለት ነው?

አቶ አይድሩስ፡- እሱ ምን ማለት ነው? አልሚ ምግብ የሚሰጠው ለሕፃናትና ለሚያጠቡ እናቶች ነው፡፡ በደረጃ አስቀምጠናል፡፡ ለአብነት ትኩረት የሚሹ አካባቢዎች ተለይተዋል፡፡ ሦስት የትኩረት ቦታዎች ለይተናል፡፡ በትኩረት አንድ 192 ወረዳዎች አሉ፡፡ በትኩረት ሁለት 174 ወረዳዎች አሉ፡፡ በትኩረት ሦስት 88 ወረዳዎች አሉ፡፡ ጠቅላላ 454 የትኩረት ወረዳዎች አሉ፡፡ ለእነዚህ በተለይ ለትኩረት አንድና ለትኩረት ሁለት ነው አብዛኛውን አልሚ ምግብ የምንሰጠው፡፡ አልሚ ምግብ የምንሰጠው ፅኑ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ላለባቸው አካባቢዎች ነው፡፡ በዚህም የተጠቃሚዎችን 35 በመቶ የሚሆነው አለን ማለት ነው፡፡ በተረጂዎች ቁጥር ላይ የተመሠረተ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የሎጂስቲክስ አቅርቦት ምን ይመስላል? ከጂቡቲ ወደብ የዕርዳታ እህል የማንሳት አቅምስ? ለተረጂው ወገን በወቅቱ የማድረስ አቅማችሁ ምን ይመስላል? ምክንያቱ በአንዳንድ ቦታዎች በወቅቱ ዕርዳታ እየደረሰ አይደለም የሚል ቅሬታ ይሰማልና፡፡

አቶ አይድሩስ፡- አቅም ተፈጥሯል፡፡ ከጂቡቲ የሚነሳው ለግል የትራንስፖርት ኩባንያዎች በጨረታ እየተሰጠ ነው፡፡ በርካታ አቅም ያላቸው የትራንስፖርት ድርጅቶች ተፈጥረዋል፡፡ እኛ አንድ ሚሊዮን ኩንታል የማከማቸት አቅም ያለው መጋዘን አዳማ ከተማ ውስጥ አለን፡፡ እያንዳንዳቸው 300 ሺሕ ኩንታል የመያዝ አቅም ያላቸው መጋዘኖች በኮምቦልቻና በድሬዳዋ ከተሞች አሉን፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከክልሎች እንከራያለን፡፡ ስለዚህ እህሉን ከወደብ አንስተን ወደ እነዚህ መጋዘኖች እናስገባለን፡፡ ወደ ተጠቃሚው ሕዝብ ለማድረስ እኛ 20 ከባድ ተሽከርካሪዎች (400 ኩንታል የሚጭኑ)፣ እንዲሁም 200 ኩንታል የሚጭኑ 20 ተሽከርካሪዎች አሉን፡፡ እነዚህን ከባድ ተሽከርካሪዎች የምንጠቀመው በጣም አስቸኳይ ለሆኑ ጉዳዮች ነው፡፡ ለጨረታ ዕድል ለማይሰጡ ለአብነት በአዲስ አበባ ከተማ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ረጲ አካባቢ በቆሻሻ ክምር ናዳ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ሐሙስ ትዕዛዝ ተሰጥቶ ዓርብ [መጋቢት 8 ቀን 2009 ዓ.ም.] በአስቸኳይ ለተጎጂዎች ተከፋፍሏል፡፡ ወዲያውኑ ማለት ነው፡፡ ድንገት ከግምገማ በኋላ የደረሰ አደጋ ካለ በፍጥነት ለመድረስ እንጠቀምባቸዋለን፡፡ ከዚያ ውጪ የኢትዮጵያ ትራንስፖርት ባለሥልጣን የሰጠን ዝርዝር አለ፡፡ እነዚያ የትራንስፖርት ባለንብረቶች ይጋበዙና በጨረታ አወዳድረን እናሠራለን፡፡

ሪፖርተር፡- ድርቅ በሚያጋጥምበት ወቅት መንግሥትም፣ ኅብረተሰቡም የተቻላቸውን በማድረግ ለችግር የተዳረጉ ወገኖችን ለመታደግ ይሞክራሉ፡፡ ድርቅ ረሃብን የሚፈጥር በመሆኑም ክስተቱ አስፈሪ ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ ውስጥ ተዋናይ ከሚሆኑ አካላት መካከል የተወሰኑት በዘረፋ መሳተፋቸው፣ በሕገወጥ መንገድ ጥራት የሌለው ምርት እንዲዳረስ ማድረጋቸው፣ በተለይም የሻገተ የከብት መኖ ማቅረባቸው ይነገራል፡፡ ይህንን ክስተት ኮሚሽኑ እንዴት ይቀበዋል? በዚህ በኩል ቅሬታዎችና ጥቆማዎች ይቀርባሉና በእናንተ በኩል ያለው አቋም ምንድነው?

አቶ አይድሩስ፡- ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ ከማዕከላዊ መጋዘኖች የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ይላካል፡፡ ቦታው ከደረሰ በኋላ የክልሎች ድርሻ ነው፡፡ እኛ አሠራር አለን፡፡ ቦታው ከደረሰ በኋላ ሰነድ እስካልመጣ ድረስ ለትራንስፖርት ድርጅቶች ክፍያ አይወራረድላቸውም፡፡ ይኼ አንደኛው መቆጣጠሪያችን ነው፡፡ ሁለተኛው ክልሎች ትኩረት ሰጥተው መቆጣጠር አለባቸው፡፡ ትክክል ነው እንዲህ ዓይነት ነገሮች አልፎ አልፎ ይከሰታሉ፡፡ በድርጊቱ የተሳተፉ ተይዘው ለቅጣት የተዳረጉም አሉ፡፡ ትልቅ ሀብት በሚንቀሳቅስበት ወቅት እንዲህ ያለ ክስተት ያጋጥማል፡፡ እኛ ሁለት ነገሮችን እናደርጋለን፡፡ አንደኛ በኮሞዲቲ ማኔጅመንት አሠራራችን እንቆጣጠራለን፡፡ ሰነዶች ይቀርቡልናል፡፡ እዚያ ዕርዳታው ከደረሰ በኋላ ሥርጭቱ የክልሎች ፋንታ ነው፡፡ ምክንያቱም እህሉ ከተራገፈ በኋላ ለተጠቃሚዎች ስለመድረሱ ከክልሎች የአጠቃቀም ሪፖርት ይቀርብልናል፡፡ በዚህ መሠረት ደግመን እናጣራለን፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ተንቀሳቃሽ ተቆጣጣሪ ቡድኖችን አቋቁመናል፡፡ ሌላው ከመጠን ጋር ተያይዞ የተቀመጠ አለ፡፡ ለአንድ ሰው 15 ኪሎ ግራም ታስቦ ይሰጣል፡፡ ጥራጥሬ 4.5 ኪሎ ግራም፣ ዘይት አምስት ሊትር ይሰጣል፡፡ አቅሙ የሚኖር ከሆነ ክልሎችም ይረዳሉ፡፡ በቂ ነው የሚል ድምዳሜ ባይኖርም አገሪቱ ማስተናገድ በምትችለው መጠን እየተዳረሰ ነው፡፡ ተጎጂዎች በትክክል ከደረሳቸው ለአንድ ወር ይበቃቸዋል በሚል ታሳቢ ነው እየታደለ ያለው፡፡

የከብት መኖን በሚመለከት እኛ በባለሙያ ዶክተር ነው ጥራትን እየተቆጣጠርን ቀለብ የምንቆርጠው፡፡ እኛ ችግር አልገጠመንም፡፡ ነገር ግን የተለያዩ ድርጅቶች መኖ ይገዛሉ፡፡ የተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችና የክልል መንግሥታት ይገዛሉ፡፡ በተለያየ የእርስ በርስ መደጋገፍ ሙያ ይለካል፡፡ የመኖ ጥራት ሲጓደል መኖ አጠረ ይባላል፡፡ እኛ የራሳችን የቁጥጥር አሠራር አለን፡፡ በዚህ መሠረት ሳይጫን እየተቆጣጠርን ነው፡፡ ባለፈው ሶማሌ ክልል 20 ሺሕ ኩንታል የሚጠጋ የተበላሸ መኖ ደርሷል ተብሎ ሪፖርት እንደቀረበልን ወዲያውኑ እንዲመለስ አድርገናል፡፡ አልፎ አልፎ መኖው ውስጥ እሾህ ሊኖረው፣ የበሰበሰም ሊኖር ይችላል፡፡ ይህን ሁሉ ሳይጫን እየተቆጣጠርን ነው፡፡ ነገር ግን ይኼ ችግር ይነሳል፣ እኔም እሰማለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ለዕርዳታ የሚቀርብ ምግብ ቢኖርም የመሠረተ ልማት አለመሟላትና የውኃ እጥረት እንደ ችግር ይነሳል፡፡ እነዚህ ችግሮች እየፈተኑዋችሁ ነው?

አቶ አይድሩስ፡- የመሠረተ ልማት ችግሮች አሉ፡፡ ጠረፍ አካባቢዎች ቶሎ ለመድረስ መንገድ በትክክል ባለመኖሩ እንቸገራለን፡፡ እኛ መድረስ አለብን፡፡ ነገር ግን መንገድ ተግዳሮት ነው፡፡ ለምሳሌ አፋር ክልል አሸዋው ከባድ ተሽከርካሪዎችን እያሰመጠ ለ15 ቀናት ቆመው ይቆያሉ፡፡ ሁለተኛው አልፎ አልፎ የተቆርቋሪነት ስሜት አነስተኛ ይሆንና ዕርዳታ በማድረስ በኩል ችግር ይፈጠራል፡፡ ሌላው የውኃ እጥረት አለ፡፡ የዝናብ እጥረት ባጋጠማቸው አካባቢዎች የውኃ ችግር አለ፡፡ ብዙ ዋጋ ያስከፍለናል፡፡ የውኃ ቦቴዎችን ተጠቅመን ውኃ እናቀርባለን፡፡ የመኖ ሳርን በተመለከተ ለምሳሌ እኛ አንድ ጊዜ የምንልከው ሳር ላሉት ከብቶች በቂ ሆኖ አይደለም፡፡ ግን በበቂ ሁኔታ እንኳ አቀርባለሁ ቢባል ከብቶቹ ተሸጠው የማያወጡትን ዋጋ ነው እያወጣን ያለነው፡፡ የአርብቶ አደሩን ሞራል ከመጠበቅ አንፃር መንግሥት ትልቅ ዋጋ ከፍሎ መኖ እያቀረበ ይገኛል፡፡ እነዚህ ተግዳሮቶች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የዕርዳታ ሰጪዎች አሠላለፍ ምን ይመስላል? ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ በሚከሰቱ የድርቅ አደጋዎች የዕርዳታ ሰጪዎች ምላሽ ፈጣን ነበር፡፡ አሁን ግን ይህ ሁኔታ እየታየ አይደለም፡፡ የአሠላለፍ ለውጥ አለና እናንተ ለጉዳዩ ቅርብ እንደ መሆናችሁ የምትከተሉት መንገድ ምንድን የሚሆነው?

አቶ አይድሩስ፡- ፖለቲካውን ስትመለከተው ዓለም እየተቸገረ ነው፡፡ ትኩረቱ የተሳበው በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ብጥብጥ የመን፣ ሶሪያ፣ እንዲሁም ሊቢያ ነው፡፡ ምሥራቅ አፍሪካን ብትወስድ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳንና ኬንያም የድርቅ ችግር ገጥሞአቸዋል፡፡ ዓለም አቀፍ ለጋሾች ቅድሚያ የሚሰጡት አለ፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን የተሻልን እንደሆንን አስተውለውናል፡፡ እኛን እንደ ቀድሞው አያዩንም፡፡ ለምሳሌ አምና ግሎባል ሎጂስቲክ ክላስተር የሚባል ግብረ ሰናይ ድርጅት የተወሰነ ረድቶናል፡፡ መጋዘን ማጠናከር፣ የሎጂስቲክስ ሠራተኞች አቅም ግንባታና የምግብ ማሠራጫ ጣቢያ አስተዳደር ላይ ድጋፍ አድርጎልናል፡፡ ከዚያ ውጪ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ረድቶናል፡፡ በዚህ ዓመትም የያዙትን ይዘው ቀጥለዋል፡፡ እጅ የሚሞላ ዕርዳታ ግን አልተገኘም፡፡

ሪፖርተር፡- አገሪቱን ባለፈው ዓመትም በዚህ ዓመትም ድርቅ አጋጥሟታል፡፡ በሚቀጥለው ዓመት ምን ሊያጋጥም ይችላል? የእናንተስ ዝግጅት ምን ይመስላል?

አቶ አይድሩስ፡- በጥናት ላይ ነው የሚመሠረተው፡፡ በዓመት ሁለት ጊዜ ጥናት ይካሄዳል፡፡ በጥናቱ ላይ ተመሥርተን ነው የምናውቀው፡፡ የብሔራዊ ሚቲዮሮሎጂ ኤጀንሲ የበልግ ትንበያ ገና ነው፡፡ መንግሥት በኤጀንሲው ትንበያ ላይ ነው የሚያተኩረው፡፡ ዝናብ ይከሰታል ወይ? የሚለው በኋላ የሚታወቅ ነው፡፡ አደጋው ይጨምራል? ወይ ይቀንሳል? የሚለውን ዛሬ መናገር አንችልም፡፡

ሪፖርተር፡- ለለጋሽ አገሮችና ተቋማት የድጋፍ ጥሪ አድርጋችኋል፡፡ ነገር ግን እስካሁን ምላሽ የለም፡፡ መንግሥት ጥሪ አድርጎ ምላሽ ባያገኝም በራሱ አቅም ለተጎጂዎች ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡ ጥሪ አድርጋችሁ ምላሽ ካላገኛችሁ ጥሪውን ማቆም አዋጭ የፖለቲካ መንገድ ይሆናል? የመንግሥት አቋምስ ምንድነው? ጉዳዩ ለውይይት ቀርቦ ይሆን?

አቶ አይድሩስ፡- ይኼ ጉዳይ በአገር ደረጃ በከፍተኛ አመራሩ የሚታይ ነው፡፡ እኛ እንደ ተቋም የምናየው ጉዳይ አይደለም፡፡ ሊታይ የሚችለው በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ነው፡፡ ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ነው፡፡ የራሱ ብሔራዊ ምክር ቤትም አለው፡፡ በዚህ ደረጃ የሚታይ ነው፡፡ አምና አሳይተናል፡፡ 15 ቢሊዮን ብር ተመድቦ የጎላ ዕርዳታ ሳናገኝ የአንድም ሰው ሕይወት ሳያልፍ ችግሩን ተቋቁመናል፡፡ ይህ ጉዳይ ግን በከፍተኛ አመራሩ የሚታይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሰሞኑን አዲስ አበባ ከተማ በርካታ ነዋሪዎቿን በቆሻሻ ክምር ናዳ አጥታለች፡፡ ከተማው በእናንተ ቅርፅ የተቋቋመ ተቋም የሌለው በመሆኑ የእናንተ አስተዋጽኦ ምንድነው? የሥጋት ቀጣናዎችን በመለየት ተመሳሳይ ቅርፅ ያለው ተቋም እንዲቋቋም ለማድረግ ምን እየሠራችሁ ነው?

አቶ አይድሩስ፡- እኛ በፌዴራል ደረጃ ነው የተቋቋምነው፡፡ ለሁሉም ክልሎች ድጋፍ እናደርጋለን፡፡ ነገር ግን ክልሎች የራሳቸው ሕገ መንግሥት አላቸው፡፡ የራሳቸውን መዋቅር ራሳቸው የመፍጠር መብት አላቸው፡፡ እኛ ጣልቃ አንገባም፡፡ ነገር ግን እናማክራለን፡፡ ኦሮሚያ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በእኛ ቅርፅ አቋቁሟል፡፡ በአዲስ አበባ የተከሰተው አደጋ በጣም አሳዛኝ ነው፡፡ ከተማው የራሱ መዋቅር አለው፡፡ የከተማው የእሳት አደጋ ብርጌድ በበቂ ሁኔታ የተደራጀ ነው፡፡ የተሟሉ መሣሪያዎች አሉት፡፡ የአደጉ አገሮችን ያህል የተሟሉና የተለያዩ መሣሪያዎች አሉት፡፡ የከተማው አስተዳደር ኮማንድ ፖስት አቋቁሟል፡፡ ኮማንድ ፖስቱ በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሥር የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ አማካይነት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ደርሶአል፡፡

እኛ አደጋው ከተከሰተበት ቀን ጀምሮ የበኩላችንን እያደረግን ነው፡፡ የከተማው አስተዳደር አደጋን በመቆጣጠር ስታንዳርድ እየሠራ መሆኑን ታዝበናል፡፡ ሕይወቱ ያለፈ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ይፈጸማል፡፡ የጠፋ ከሆነ ፈልጎ የማዳን ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ ከአደጋው የተረፉትንም የሕክምና ተቋማትና መጠለያ ጣቢያዎች በማስገባት ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል፡፡ የእኛ ተቋም አደጋ ለደረሰባቸው ወገኖች ዘለቄታዊ ማቋቋሚያና ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማቅረብ ወስኖ እየሠራን ነው፡፡ ዓርብ [መጋቢት 8 ቀን 2009 ዓ.ም.] ጉዳት ለደረሰባቸው 400 ያህል ወገኖች ዱቄት፣ አልሚ ምግብ፣ ወተትና የተለያዩ ቁሳቁሶች አድለናል፡፡ 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹በአመራሮቻችን የተነሳ የፓርቲያችን ህልውና ጥያቄ ውስጥ ገብቷል›› አቶ አበባው ደሳለው፣ የአብን አባልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ከተመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአመዛኙ የተሻለ ሕዝባዊ ድጋፍ ያገኘ፣ ከሦስት ዓመታት በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ተወዳዳሪ...

‹‹የግሉን ዘርፍ በመዋቅር መለያየት የነበሩ ችግሮችን ከማባባስ ውጪ መፍትሔ አያመጣም›› አቶ ሺበሺ ቤተማርያም፣ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ

አቶ ሺበሺ ቤተማርያም በኢኮኖሚክስ፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲና ዕቅድ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በማግኘት ለ36 ዓመታት የዘለቀ የሥራ ልምድ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ በዕቅድና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ በዓለም አቀፍ...

‹‹የኢትዮጵያን የውስጥ ችግሮች ሁሌም የሚያባብሰው ከውጭ የሚመጣ አስተሳሰብ ነው›› ሳሙኤል ነጋሽ (ዶ/ር)፣ በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር

በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር የሆኑት ሳሙኤል ነጋሽ (ዶ/ር) የታሪክ ባለሙያዎች ማኅበር የውጭ ግንኙነት ኃላፊም ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለሁለት አሥርት ዓመታት ታሪክ አስተምረዋል፡፡...